"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Tuesday, 2 July 2013

‹‹ሥልጣን ልቀቁ?››


ዳንኤል ክብረት 

click here for pdf
ኢትዮጵያ ከቦትስዋና ጋር ስትጫወት ተገቢ ያልሆነ ተጨዋች አሰልፋችኋልና ሦስት ነጥብ ታጣላችሁ ብሎ ፊፋ የሚባል ቡዳ አገሩን ቀወጠው፡፡ እንደ አውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ነገር ማድረግ የሌለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ፊፋ ከአድኅሮት ኃይሎች ጋር ካልተሰለፈ በቀር ሌላ ምክንያት ሰጥቶ ኢትዮጵያን መጣል ይችል ነበር፡፡ ለኛ የኢትዮጵያ ነጥብ መቀነስ አይደለም ችግራችን፤ ነጥቡ መቀነሱን ሕዝቡ መስማቱ ነው፡፡ እኛኮ ቀስ አድርገን ‹ኪራይ ሰብሳቢዎች የሀገራችንን የስፖርት ራእይ ለማደናቀፍ ከፀረ ሕዝብ ኃይሎች ጋር በመሆን የደቀኑብን ሤራ ነው› ብለን ሕዝቡን ማሳመን እንችል ነበር፡፡
መጀመሪያ ከበላዮቻችን ጋር እንነጋገራለን፤ ሂስ ከተሰጠንም ሂሳችንን እንውጣለን፣ ግምገማችንንም እንቀበላለን፣ ዋናው ይሄ አይደለም፤ አንዴት አድርገን ለሕዝቡ እንንገረው? የሚለው ነው፡፡ ሕዝብ እንደነገርከው ነው፡፡ እንደ አሰማሙ ነው፡፡ አቀናብረን ከነገርነው አቀናብሮ ይሰማል፡፡ ግን ምን ያደርጋል፣ ፊፋ የሚባል ቡዳ ለሕዝብ መነገር የሌለበትን ለሕዝብ ተናገረና መከራ አሳየን፡፡
አሁን አዳሜ ዕድል ስታገኝ ጊዜ ‹ለምን ሥልጣን አትለቁም› ትላለች፡፡ 
 እስኪ ተዪው አሉኝ ያልደረሰባቸው
እንዲህ በቀላሉ የሚተው መስሏቸው
አለች የሀገሬ ዘፋኝ፡፡ ሥልጣን እንዲህ በቀላሉ የሚተው መስሏቸዋል፡፡ እኛ በቀጣዩ ምርጫ እንዴት አድርገን ተመልሰን እንደምንመጣ እያሰብን እነርሱ ሥልጣን ልቀቁ ይሉናል፡፡ ‹ከአንድ ሙዚቃ በኋላ ተመልሰን እንገናኛለን› አሉ የኤፍ ኤም ጋዜጠኞች፡፡
ስለ ሥልጣን መልቀቅ እዚህ ሀገር የሚያስብ ሰው ካለ የመጨረሻው ጅል እርሱ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ስለ ሥልጣን አያውቅምና፡፡ ‹‹አቤቱ የሚናገሩትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው››፡፡ እነዚህ ሰዎች ሥልጣንን ያልቀመሷት ሰዎች ናቸው፡፡ ቢቀምሷት ኖሮ ‹አጥብቃችሁ ያዟት› ይላሉ እንጂ ‹ልቀቋት› አይሉም ነበር፡፡ መንፈሳውያን ነን፣ ዓለምን ንቀናል የሚሉት አባቶች እንኳን ለሥልጣን በሚታገሉባት ሀገር እኛን ዓለማውያኑን ‹ሥልጣን ልቀቁ› እንደማለት ያለ የዓመቱ ምርጥ ቀልድ የለም፡፡
ጎበዝ እዚህ ሀገር ባለ ሥልጣን ማለትኮ ትንሽ ፈጣሪ መሆን ማለት ነው፡፡ ሰው የሚሰግድልህ ሥልጣን ሲኖርህ ነው እንጂ ዕውቀት ሲኖርህ አይደለም፣ ሰው የሚኮራብህ ሥልጣን ሲኖርህ እንጂ ችሎታ ሲኖርህ አይደለም፡፡ እስቲ የትኛው የአክስትህ ልጅ ነው እገሌ የተባለው ሳይንቲስትኮ ዘመዴ ነው ብሎ የሚኮራው? የባለሥልጣን ግን እንኳን ዘመዱ ድመቱም አረማመዱ የተለየ ነው፡፡ ጅል- ሥልጣን ልቀቁ ይላል እንዴ፡፡ ሥልጣን የሻሂ ቤት ወንበር መሰላችሁ እንዴ፡፡

Saturday, 29 June 2013

ተመስገን ደሳለኝ ለማን ደስ ይበለው ብሎ ጠፋ!?

ባለፈው ጊዜ አንድ ወዳጄ ጋር አዲሳባ ስልክ ደውዬ ሳናግረው በአካባቢው ከእርሱ ድምጽ ጎልቶ የሚሰማ የመኪና ጥሩንባ ሰማሁና ይሄ ሁሉ የመኪና ጥሩምባ ምንድነው… ብዬ ጠየኩት፡፡
ሃይለማሪያም ደሳለኝ እየገቡ ወይም እየወጡ ነው መሰለኝ መንገድ ተዘጋግቷል፡፡ አለኝ፡፡
ወዲያውም ቀጠል አድርጎ፤  እንደ ሀቁ ቢሆን ኖሮ መንገድ መዘጋጋት የነበረበት ለሀይለማሪያም ደሳለኝ ሳይሆን ለተመስገን ደሳለኝ ነበር… አለኝና በቁጭት፤ ይሄው የሚያጅቡትን አያቀውቁምና… እልኩ እያታዘብኩ ነው…! ሲል አወጋኝ!
ተመስገን ደሳለኝ ገዢውም ተገዢውም ፓርቲ ሊያመሰግነው የሚገባ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ነገር ግን ገዢዎቻችን ማመስገን የሚቆጥር ይመስል ሰውን ማመስገን አይወዱም፡፡  ስለዚህ ተሜንም በማመስገን ፈንታ ከሰሱት፡፡ ጎሽ በማለት ፈንታ እንደ ጎሽ ሊወጉት ቀንዳቸውን አሾሉበት፡፡ እሰይ በማለት ምትክ ሰይ ባንከረባብት ብለው ለሁለቱም አሰቡት፡፡ (ለማሰርም ለማሰደድም) (ሰይ ባንከረባብት በልጅነታችን ብይ ጨዋታ ላይ ተወርዋሪዋ ብይ ጉድጓዳ ውስጥ ብትገባም የተቃራኒውን ብይ ብትመታም ነጥቡ እንዲያዝልን ውል የምንገባባት ቃል ነበረች፡፡)
ተመስገን ደሳለኝ እንዲሰደድ መንግስት ከፀሎት ጀምሮ ሁሉንም አይነት የትግል ስልቶችን እንደተጠቀመበት ትዝ ይለኛል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ጊዜ ምንም የቀጠሮ ወረቀት ወይም መጥሪያ ሳይሰጠው በራዲዮን፤ “ተመስገን ደሳለኝ በሌለበት የፍርድ ሂደቱ ታየ ለሚቀጥለው ጊዜ ፖሊስ ይዞ እንዲያቀርበው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል!” የሚል አይነት ዜና በሰላም ቁጭ ብሎ ሻይ በሚጠጣበት ካፌ ውስጥ ሰማ፤ (እናጋን ካልን ደግሞ ዜናውን እንደውም ያነበቡት ተሜ ልክ ዜና ሲሰማ አይተው ነው…! ማለት እንችላለን…) የዚህ ዜና አላማ ግልፅ ነበር፡፡ ተሜ ደንግጦ ፖሊስ ሳይዘው በፊት መንገዱን እንዲያያዘው ማድረግ ነበር፡፡ ወዳጃችን ግን፤ ብታስሩኝ ባለ ጊዜም ባለ ብረትም ናችሁና እግሬ እምቢ ማለት አይቻለውም፡፡ ለመሰደድ ግን እሺ የሚል እግር የለኝም፡፡ ብሎ እንቅጩን ነገራቸው እና የመጣው ምጣ ብሎ ቁጭ አለ…

Sunday, 23 June 2013

ጭፈራችንን መልሱልን ሰኔ 11/2005 (ለምስኪኑ ህዝባችን

ጭፈራችንን መልሱልን
ያገር ብርድ ሲቆነድደን
ኳስ ሜዳውን አልቤርጐ አርገን
ድንጋይ ጠርዙን ተንተርሰን
የታክሲ ውስጥ አልጋ አንጥፈን
... ሌት በዋዜማ አልመን፣ ነገን በዕውነት ልናበራ፤
ባንዲራ እንደደመራ
ከምረን በየኳስ ጐራ፤
ተውለብልበን አውለብልበን
ላንቃችን እስኪበጣጠስ፣ ሆ ብለን በማታ በቀን፤
በጭለማ ድል ጐስመን

Tuesday, 4 June 2013

Mesfin Wolde-mariam


  • Mesfin Wolde-mariamጦርነት እንኳን ገና በልቶ ላልጠገበ ሕዝብና ለጥጋበኞቹም አይመጭም፤ የተራበ ሕዝብ በጠገቡ መሪዎች ሲነዳ ግን ጦርነት ለአጉል ጀብደኛነት ዝና የሚጠቅም መስሎ ይታያቸዋል፤ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ለመግጠም በሚያሰፈስፉበት ጊዜ በርቱ እያሉ የሚያቅራሩ ሞልተው ነበር፤ ዛሬ አቀራሪዎቹም ሆኑ ጀብደኖቹ በኤርትራ ጦርነት ያለቀባሪ ስለቀሩት ሰዎች፣ ጠዋሪ ስላጡ እናቶችና አባቶች፣ አሳዳጊ ስለሌላቸው ልጆችና አካለ-ጎደሎ ለሆኑት የሚያስብላቸው አለ ወይ? የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት መነሣትና በኢጣልያ የግራዚያኒ ሐውልት እን...ዳይሠራ የተጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ከልክሎ ለሰልፍ የወጡትን አስሮ ያሳደረ አገዛዝ ለአገራቸው ለሞቱት ኢትዮጵያውያን የሚሰጠውን ዋጋ በመጠኑም ቢሆን ያሳያል፤ ስለዚህም ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ሲወዱ ራሳቸው በልጽገው ለልጆቻቸው ብልጽግናን እንዲያወርሱ ሕይወታቸውን ቢጠብቁ ለአገራቸውም ክብር ይሆናሉ፡፡
    ለፍቅር መተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለጠብም መተዋወቅ ያስፈልጋል፤ የተሟላ መረጃ ቢኖረን የጥንት ታሪክ እየጠቀስን ሰዎችን ለጦርነት እንቀሰቅስም ነበር ብዬ አምናለሁ፤ ስለዚህም አንዳንድ አስፈላጊ መረጃዎችን ላቅርብ፤ ---

    1. የግብጽ የጦር ኃይል በዓለም አሥረኛ ነው፣ በአፍሪካና በመሀከለኛው ምሥራቅ የሚወዳደረው የለም፤ አንድ ሚልዮን ተኩል ያህል የጦር ኃይል አለው፤ በዓየር ኃይልም ከዓለም አሥራ አራተኛ ነው፤ በታንክ ብዛት አራተኛ ነው፤ በባሕር ኃይል ሰባተኛ ነው፤ በጦር በጀት አርባ ሦስተኛ ነው፤
    2. በኢትዮጵያ ዙሪያ ጂቡቲ፣ ሶማልያ፣ ሱዳን የአረብ ማኅበር አባሎች በመሆናቸው ለግብጽ ማኅበረተኞች ናቸው፤ በወያኔ ፈቃድ የተገፋችው ኤርትራም የዚሁ ማኅበር ታዛቢ አባል ነች፤ ከቀይ ባሕር ማዶ ያሉት አገሮች ሁሉ ሀብታሙንና ኃይለኛውን ሳኡዲ አረብያንም ጨምሮ የግብጽ ማኅበርተኞች ናቸው፤ በዚህ ሁሉ መሀከል የተከታተፈች ኢትዮጵያ ብቻዋን ነች፤
    3. የቤንዚን ሀብትና ከሀብቱም ጋር የሚገኘውን ወዳጅና ጡንቻ አንርሳ፤

    ይህ ማስታወሻ ለማስፈራራት አይደለም፤ ማስፈራራትን አላውቅበትም፤ እንዲያውም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ‹‹አትፍሩ›› ብሏቸዋል ተብዬ ተከስሼ ታስሬአለሁ፤ ስለዚህ አላስፈራራም፤ ጦርነት ከመጣብን ልናስቀረው እንሞክር፤ ሌላው ቢቀር እንድንዘጋጅ ጊዜ እናገኛለን፤ ገፍቶ ከመጣ ግን እንቋቋመዋለን፤ ለጦርነት አንቸኩል፤ ለኤርትራም ጊዜ ተናግሬ ነበር፤ የሰማኝ የለም፤ ጥጋብ ላይ ያሉ የሚርባቸው ዝና ነው፤ የሚያገኙት ግን ውርደትን ነው፡፡

Thursday, 16 May 2013

አንጋፋዋ ድምጻዊ አበበች ደራራ አረፈች


Ethiopian singer Abebech Deraraለረጂም ዓመታት በራስ ቴአትር በድምጻዊነት ስትሰራና ለአድማጮችዋ ዜማዎችን ስታቀርብ ኖራ በስተመጨረሻው ወደ እስራኤል ሀገር ከትማ ስትኖረ የነበረችው ታዋቂዋ ድምጸ መልካሟ አበበች ደራራ ዛሬ ሜይ 16 ቀን ባደረባት ህመም ሳቢያ ሕይወቷ አልፏል፡፡
አበበች ደራራ በሕመም ተይዛ ለበርካታ ወቅት በአልጋ ላይ ከመቆየቷም ባሻገር ጨርሶ ከሰዎች ጋር ግንኙነት አቋርጣ በሽታዋን ለብቻዋ ስታስታምም እንደነበረች በቅርብ የሚያውቋት ይናገራሉ፡፡
የአበበች ደራራ አስከሬን በኖረችበት የቴል አቪቭ ከተማ በዛሬው እለት ከቀኑ 3.00PM ላይ ወደ ቀብር በወዳጅ ዘመዶች ታጅቦ በመሄድ ሥርአተ ቀብርዋም ይፈጸማል፡፡ 
ለወዳጅ ዘመዶቿ መጽናናትንፈጣሪን ይስጣቸው ዘንድ እለምናለሁ፡፡
አርቲስት ደበበ እሸቱ በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳስቀመጠው።