እ.አ.አ በ1997 በጨረታ ወደ ግል ንብረትነት ተዛወረ የተባለው የኢትዮጵያውያን ሀብት የተሸጠው 172 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ሽያጩ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ሽያጩን ተከትሎ በርካቶች አርረዋል፤ ተቃጥለዋል። “ዋይ ዋይ ወርቃችን” ብለው አንብተዋል። ህዝብ የፈለገውን ቢል ደንታ የሚሰጠው አካል ስለሌለ የለገደንቢ ወርቅ ማዕድን ከኢትዮጵያ ህዝብ እጅ በአዋጅ ተነጠቀ።
ሽያጩን እውን ያደረገው የኢትዮጵያ የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት የወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሀሰን አሊ ሲሆኑ፣ የአቶ ስዬ አብርሃ ወንድም አቶ አሰፋ አብርሃ የኤጀንሲው ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ነበሩ። ሁለቱም ባለስልጣናት ዛሬ ሃላፊነት ላይ የሉም። ስለ እውነትና ስለ አገር ሲሉ የሚያውቁትን ለመተንፈስ እስከዛሬ ቢጠበቁም ያሉት ነገር የለም። ሃሰን አሊ ሲኮበልሉ፣ አቶ አሰፋ አብርሃ ከወንድማቸው ጋር በሙስና ተወንጅለው የወህኒ ቤት ጊዜያቸውን አጠናቀው እየኖሩ ነው።
ምዕራብ ሃረርጌ አሰበ ተፈሪ መምህር የነበሩትና ኢህአዴግን መንገድ ላይ የተቀላቀሉት ሀሰን አሊ ካገር መኮብለላቸውን ተከትሎ የተለያዩ መረጃዎች ይወጡ ነበር፡፡ በርካቶች ጉዳዩን ከኦነግ ጋር ቢያያይዙትም “ካገር ውጡ ተብለው፣ ሀብትና ንብረት ተዘጋጅቶላቸው ኮብልለዋል” የሚል መረጃ ለባለስልጣናትና ለባለሃብቱ ቅርብ ነን ከሚሉ ወገኖች እንሰማ ነበር። በወቅቱ ኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ውስጥ በነበረኝ ሃላፊነት ሳቢያ ከሰማኋቸው መረጃዎች ውስጥ ሃሰን አሊ “ውጡ” ተብለው እንደ ኮበለሉ የሰማሁት መረጃ ካለኝ ሃላፊነት ጋር ተዳምሮ እንዳጣራው ወሰንኩና ጊዜ ሰጥቼ አነፈንፍ ገባሁ።
የሌሎችን ባላውቅም እንደ ኦሮሞነቴ የለገደንቢ ወርቅ ማዕድን ውድ ንብረት ለሼኽ መሃመድ ሁሴን አላሙዲ መሸጡ ሁሌም ያንገበግበኛል። ሽያጩን አስመልክቶ የተለያዩ ጽሁፎች ቢወጡም እኔ ካሰባሰብኩት መረጃና እውነት ጋር የሚመጣጠን መስሎ ስላልታየኝ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ለመተንፈስ ወሰንኩ።
ሼኽ መሐመድ አላሙዲና ሃሰን አሊ እንዴት ተዋወቁ?
ሼኽ መሀመድ አላሙዲና ሀሰን አሊን እንዳስተዋወቃቸው የነገረኝን ሰው ባንድ አጋጣሚ የማወቅ እድል አጋጥሞኝ ነበር። ተግባሩ ብዙም ደስ ስለማያሰኝ ፊት እነሳው ነበር፡፡ ባለስልጣናትን በገንዘብ እየደለለ ሲሰርቅ ብዙ ጊዜ ስለማውቅ አልወደውም ነበር። የራሱን ትልቅነት ለመግለጽ ድንገት ቢሮዬ በመጣበት ወቅት የነገረኝ ፍንጭ ትዝ ሲለኝ ላገኘው ወሰንኩ። ይህ ሰው ባለኝ ሃላፊነት እንደፈለገኝ ላገኘው ስለምችል፣ እሱም ለሚሰራው ድለላና አየር ባየር ንግድ እኔ ከፈለኩት ቅር ስለማይለው ፊት ነስቼው ያቋረጥኩትን ግንኙነት እንደገና መቀጠል ብቸኛ አማራጬ ሆነ፡፡ይህን ሰው ከተጠቀሙበት በኋላ ወርውረውት በነበረበት ወቅት ላይ ስላገኘሁት የፈለኩትን ለማግኘት አጋጣሚው ተመቻቸልኝ፡፡
ቀደም ሲል ሃሰን አሊን ያውቃቸው እንደነበር፣ አብረው ሃድራ እንደሚያሞቁ፣ የፈለገውን ነገር ማድረግ ከፈለገ ሃድራው በሚሞቅበት ወቅት እዛው በሙቀት እንደሚያከናውኑ አውግቶኛል። ለዚህ ጽሁፍ ስለማይጠቅም እንጂ በርካታ ታላላቅ ጉዳዮች ቢሮ ውስጥ ሳይሆን በተፈረሸ መደብ ላይ እንደሚከናወን በስፋት ስም እየጠቀሰ ነግሮኛል። እንግዲህ ይህ ሰው የ“ባለሃብቱ” ወዳጅ ነበር። ለዚያውም የመጀመሪያ!
በዚሁ ሽርክናቸው ሰውየው ሃሰን አሊን መተዋወቅ እንደሚፈልጉ ባሳወቁት መሰረት ሃሰን አሊን በመያዝ ሳር ቤት አካባቢ አገናኛቸው። ባለሃብቱ በወቅቱ ብዙም የሚያውቃቸው ባልነበረበት ወቅት ሃሰን አሊን አስቀድመው ተወዳጁ። በመኖሪያ ቤት ሃድራ ላይ የተመሰረተው ወዳጅነት ጠበቀ። በኦሮሚያ በኩል አድርገው ዋናውን ሳሎን ወረሱ።
ሀሰን አሊ ከኦሮሚያ ፕሬዚዳንትነታቸው ለቀው ስደትን ለምን መረጡ?