ምን ነካው? የማይባለው ሰለሞን ተካ! (አቤ ቶኪቻው)
ምንም ቢሆን ባለትዳር ናቸውኮ! እውነቱን ለመናገር ሰለሞን ተካ ለኢህአዴግ በጋዜጠኝነት እሰራለሁ ማለቱን ማንኛውም ለድርጅቱ አሳቢ የሆነ ግለሰብ ሊያስቆመው ይገባል። የምሬን ነው የምለው ድርጅቱ ስንት የሚተችበት ጉዳዮች እያሉት በማንም ሰርጎ ገብ የሚብጠለጠልበት ምክንያት አለ ብዬ አላስብም። ቀጥሎ ያለው አንቀፅ ለኢህአዴግ ከልብ በመቆርቆር የተሰነዘረ ነው። እንደኔ እምነት ሰለሞን ተካ በቅፅል ስሙ “ብሪቱ” እልም ካለው የተቃውሞ ጎራ ወደ ኢህአዴግ ደጃፍ መምጣቱ ለኢህአዴግ ጥሩ ነው። ነገር ግን “ደርሶ ከኔ በላይ ኢህአዴግ ላሳር” ማለቱ እና በየአደባባዩ ድርጅቱን የሚወክል ወሬ ማውራቱ ለኢህአዴግም መልካም ገፅታ አይበጅም። አረ በድንብ ስሙት ጎበዝ ሰውየው እኮ እሳት ይቀረዋል። ስለ እውነት እላችኋለሁ አልበሰለም። ታድያ በሳል ሰው ከየት እናምጣ? ካላችሁ ድርጅቱ ራሱ ተሀድሶ ያስፈልገዋል ማለት ነው። አለበለዛ ግን “ሃይ” ባይ ሰው ያስፈልጋል። ልክ ተቃዋሚዎች “መለስ በቃ” እንደሚሉት አይነት የኢህአዴግ ሰዎች ይበልጡኑም ለድርጅቱ አሳቢ የሆኑቱ “ሰለሞን በቃ” ብለው ሊያስቆሙት ይገባል። ከልቤ ነው የምላችሁ። (ከፈለጋችሁ ንግግሬ ላብራቶሪ “ቼክ” ይደረግ) ለማንኛውም ሰለሞን ተካ ሰሞኑን ራሱን መንግስት አድርጎ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫውም “መጅሊስ ይውረድ መንግስት በእምነታችን ጣልቃ አይግባ” ሲሉ ፍፁም ሰላማዊ የሆነ ተቃውሞ እያሰሙ ያሉ ሙስሊም ወዳጆቻችንን “የአልቃኢዳ ቅጥረኞች” ብሏቸዋል። ሰለሞን ይህንን ነገር ከየት አመጣው ያልን እንደሆነ ባለፈው ግዜ ጠቅላይ ሚንስትራችን “በአርሲ እና ጅማ አካባቢ የአልቃይዳ ሴል ተገኝቷል” በማለት የተናገሩትን ለመኮረጅ ሞክሮ ነው። ሰሌ በእብደቱ ተዓምር በየ ጁምዓው ተቃውሞ የሚያሰሙ ሙስሊሞችን በሙሉ “የአልቃይዳ ቅጥረኛ” ብሏቸዋል። አላህ ምህረቱን ያውርድልህ እንጂ ይሄ የጤና አይደለም። “ፍሬንዴ” የአልቃይዳ ቅጥረኛ ቢሆኑማ በአንድ ቦንብ “እምጷ” ያደርጉህ ነበር። በመጨረሻም አንድ ጥያቄ እኔ የምልህ ሰለሞን ተካ ባለፈው ግዜ እኮ “ከዚህ ቀጥሎ ቤተሰቤን ይዤ መጥቼ አዲሳባ መኖር እጀምራለሁ” ብለህ የአዲሳባ ህዝብ በጉጉት እየጠበቀህ ነው። እኔ የምልህ ያንግዜ ካዛንቺስ አካባቢ የጎሻሸሙህ ነገር አናትህን ነክቶት ይሆን እንዴ!? ያልከውንም አስረሱህ የምትናገረውንም አቀዣበሩብህ እኮ! ሌላ ደግሞ ራስህን “አርቲስት” እያልክ ስተጠራ ሰምቼ ለዚህ ጨዋታ የሚሆን ፎቶ ፍለጋ “ጎግል ኢሜጅ” ውስጥ ገባሁልህና “አርቲስት ሰለሞን ተካን” አፋልገኝ ብለው ብሰራው አንዴ አበበ ተካን ሲያመጣልኝ፤ አንዴ ሰለሞን ቦጋለን ሲያመጣልኝ ስሰማ ተሳስቼ ይሆናል ብዬ ደመደምኩ። ይቅርታ ትደግምልኛለህ… ምን “…ቲስት” ነኝ ያልከው?
No comments:
Post a Comment