የዳንኤል እይታዎች
ሁለት ተማሪዎች አንድ የቤት ሥራ ተሰጣቸው፡፡ የቤት ሥራው የተማሪዎችን ችሎታ ለመፈተን በከተማ ደረጃ የተዘጋጀ የዕውቀት መለኪያ ፈተና ነበር፡፡ ይህ ፈተና በሁለት ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎች ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ አንደኛው ተማሪ አባቱ የናጠጡ ነጋዴ ሲሆኑ እናቱም አሜሪካ ተወልደው አድገው በአንድ የውጭ ድርጅት ለመሥራት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ናቸው፡፡ እርሱም የሚማረው ‹‹አበባ የቀጠፈና አማርኛ የተናገረ ይቀጣል›› የሚል ማስታወቂያ በተለጠፈበት አንድ የግል ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሁለተኛው ተማሪ አባቱ የቀን ሥራ በመሥራት የሚተዳደሩ እናቱም ዶሮ የሚያረቡ ናቸው፡፡ ልጁም የሚማረው ከተቋቋመ ከሦስት ዓመቱ ጀምሮ መስኮቱ ተዘግቶ በማያውቅ አንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ ነው፡፡
የቤት ሥራው እንዲህ ይላል ‹‹ዶሮን በተመለከተ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እናንተ ከምታውቁትና ከወላጆቻችሁ ጠይቃችሁ መልሱ››
ሁለቱም ተማሪዎች ወደቤታቸው ከገቡ በኋላ የቤት ሥራውን መሥራት ጀመሩ፡፡
የነጋዴው ልጅ ‹‹ዶሮ›› የሚለው ነገር ግልጽ አልሆነለትምና እናቱ ከሥራ ስትገባ ጠብቆ ጠየቃት፡፡ ‹‹ዶሮ፣ ምን መሰለህ፣ ኦ ማይ ጋድ፣ ቺክን ማለት ነው›› አለችው፡፡ ልጁም ፈገግ አለና ‹‹ኦኬ፤ ታደያ ለምን ቺክን አላሉትም›› አለና ጠየቃት፡፡ ‹‹ቺክን እዚህ ሀገር ውድ ስለሆነ ብዙ ሰው ቺክን አይበላም፡፡ ለዚያ ነው ዶሮ ያሉት›› ስትል አስረዳችው፡፡
የመጀመርያው ጥያቄ እንዲህ ይላል ‹‹አንዳንድ እንስሳት አካላቸው በፀጉር የተሸፈነ ነው፤ ሌሎቹም በላባ ይሸፈናል፡፡ የዶሮ አካል በምን የተሸፈነ ነው?›› የዶሮ አርቢዋ ልጅ ከት ብሎ በመሳቅ በጥያቄው ተገረመና ‹‹ ዶሮ በላባ የተሸፈነች ናት›› ሲል መልሱን ጻፈ፡፡ የነጋዴው ልጅ ደግሞ ‹‹ዶሮ በሁለት ነገር ትሸፈናለች፡፡ ከላይ በላስቲክ የምትሸፈን ሲሆን ከሥር ደግሞ በነጭ ካርቶን ትሸፈናለች›› ሲል ሱፐር ማርኬቱን እያስታወሰ መልሱን በኩራት ጻፈው፡፡
ከዚያም ሁለቱም በየቤታቸው ሆነው ወደ ሁለተኛው ጥያቄ ተዘዋወሩ፡፡ ‹‹ዶሮ የሚገኘው ከየት ነው?›› ይላል ጥያቄው፡፡ የዶሮ አርቢዋ ልጅ ፈጠን ብሎ ‹‹ዶሮ የሚገኘው ከዕንቁላል ተፈልፍሎ ነው›› ሲል በደብተሩ ላይ አሠፈረ፡፡ የነጋዴውም ልጅ ሳቅ አለና ‹‹ዶሮ የሚገኘው ከኒውዮርክ ሱፐር ማርኬት፣ ከፍሎሪዳ ሱፐር ማርኬት፣ ከሆላንድ ሱፐር ማርኬት፣ ከኤክስ ዋይ ሱፐር ማርኬት ፍሪጅ ውስጥ ነው›› ሲል በኩራት መልሱን ጻፈ፡፡
ጥያቄው እንደ ቀጠለ ነው፡፡
‹‹ውሻ ሲጮኽ ‹ዋው፣ ዋው› ይላል፡፡ ላም ‹እምቧ› ብላ ትጮኻለች፤ ጅብ ‹አውውውው› ብሎ ይጮኻል፡፡ ለመሆኑ ዶሮ ሲጮኽ ምን ይላል?››
የነጋዴው ልጅ አንገቱን ነቀነቀና ‹‹ዶሮ ድምጽ የላትም፤ ኢት ኢዝ ኦልሬዲ ዴድ›› ሲል ሞላ፡፡ የዶሮ አርቢዋም ልጅ ‹‹ዶሮ ሲጮኽ ኩኩሉ ይላል›› ብሎ ጻፈ፡፡
‹‹በባህላችን ዶሮ አሥራ ሁለት ብልቶች አሏት ይባላል፡፡ ከወላጆቻችሁ ጠይቃችሁ ስማቸውን ዘርዝሯቸው፡፡›› ይላል ቀጣዩ ጥያቄ፡፡
የዶሮ አርቢዋ ልጅ ወደ እናቱ ጠጋ ብሎ ጠየቃት፡፡ ‹‹አይ የኔ ልጅ ዶሮኮ ድሮ ነበር እንጂ ዛሬ ከአሥራ ሁለት የሚበልጥ ብልት ሊኖራት ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ምን ያልጨመረ ነገር አለ፡፡ ወይም ደግሞ እንደ ድኻ ኑሮ ቀንሳ ከሆነም ቁጥሩ ቀንሶ ሊሆን ይችላል፡፡ ማን አይቷት ብለህ ነው፡፡ እኔ እንደተሸፈነች ነው የምሸጣት፡፡ ዛሬ ዛሬኮ ዶሮ የሚሸጥ፣ ዶሮ የሚያይና ዶሮ የሚበላ ተለያይተዋል፡፡ ዶሮ የሚሸጥ ዶሮ ያረባል እንጂ አይበላም፡፡ ቢበዛ ዕንቁላሏ ይበቃዋል፡፡ ዶሮ የሚያይ ደግሞ ገበያ ሲወጣ ዶሮ ከማየት ውጭ ዶሮም ዕንቁላልም በልቶ አያውቅም፡፡ ዶሮ የሚበላ ግን ዶሮ ከየት እንደምትመጣ ባያውቅም ዶሮ ይበላል፡፡ እኛ ዶሮዋ ተሸፍና ስለምንሸጣት ብልቷን ረስተነዋል፡፡ እነርሱ ደግሞ ስለ ብልቷ ስለማይጨነቁ አያውቁትም፡፡ አሁን ይህንን ጥያቄ ብለው የሰጧችሁ እንድትጓጉ ካልሆነ በቀር ምን ይጠቅማችኋል? በል ሂድና እመይቴ የዝናሽን ጠይቃቸው፡፡ እርሳቸው የደጃች ዘመዱ ወጥ ቤት ነበሩ፡፡
ልጁ ወደ እመይቴ የዝናሽ ዘንድ ሄደ፡፡ ‹‹አዬ ልጄ አሁንማ ረስቼ፡፡ ዶሮ በሁለት መቶ ብር እየተሸጠ ማን ብልት ያስታውሳል ብለህ ነው፡፡ አታጓጓኝ እባክህ፡፡ እኔኮ ዶሮ ሲያምረኝ ድሮ የበላሁትን እያስታወስኩ ነው የምጽናናው፡፡ ‹ድኻ በሕልሙ ቅቤ ባይጠጣ› ሲባል አልሰማህም፡፡ በል እስኪ ጣፍ ትዝ ካለኝ፡፡ አጭሬ ሁለት፣ መላላጫ ሁለት፣ ፈረሰኛ አንድ፣ መቋደሻ አንድ፣ ክንፍ ሁለት፣ እግር ሁለት፣ አቃፊ አንድ፣ ጉሮሮ አንድ፣ አሥራ ሁለት አልሆነም፡፡ ወደፊትኮ የዶሮ ቅርጫ ካልተጀመረ ዶሮ እንዳማረን መቅረቱ ነው፡፡ ዱሮማ የዶሮ ዳቦም እንሠራ ነበር፡፡ ወዳጄ ዛሬ እንኳን ዶሮ ያለበት ዳቦ ባዶውም ዳቦ አልተገኘ› አሉና ሸኙት፡፡
የነጋዴው ልጅ ሁለት ነገር አልገባውም ‹‹ብልት›› ምንድን ነው? አለ ለራሱ፡፡ አሥራ ሁለት ብልት የሚባል ነገር ሰምቶ አያውቅም፡፡ ወደ እናቱ ሄደና ‹‹ማማ የቺክን አሥራ ሁለት ብልት ምንድን ነው?›› አለና ጠየቃት፡፡ ‹‹አይዶኖ፡፡ እስኪ ጉግል ላድርግ›› ብላ ወደ ኮምፒውተሯ ሄደች፡፡
‹‹ቆይ ብልት በእንግሊዝኛ ምንድን ነው? ሌት ሚ ሰይ ፓርትስ››
‹‹ትዌልቭ ፓርትስ ኦፍ ቺክን›› ብላ ጉግል ላይ ጻፈችና ሰርች አደረገችው፡፡
‹‹እንደዚህ የሚባል ነገር የለም›› አላት ጉግል፡፡
‹‹የሌለ ነገር ነው እንዴ የሚሰጧችሁ፡፡ ትዌልቭ ፓርት የሚባል የዶሮ ነገር የለም›› ትንሽ አሰበችና
‹‹እስኪ ቆይ ዲክሽነሪ ሪፈር ላድርግ›› ብላ ወደ ሳሎን ሄደች፤ አንድ የአማርኛ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላትም አወጣች፡፡ ‹‹ቆይ ‹በ› ከማን ቀጥሎ ነው፡፡›› ከ‹ሀ› ጀምራ ወደ ‹በ› ለመድረስ አልቻለችም፡፡ ‹‹ሚኪ ‹በ› ከማን አጠገብ ነው ያለው?›› ብላ ልጇን ጠየቀችው፡፡ ‹‹ከ‹ቡ› ጎን›› አለና መለሰላት፡፡
ከመጀመርያው ገጽ ጀምራ እያገላበጠች በመዝገበ ቃላቱ ላይ መፈለግ ጀመረች፡፡ ‹‹አማርኛ መሻሻል አለበት፡፡ ከ‹ኤ› ቀጥሎ ‹ቢ› እንዲመጣ ማድረግ አለባቸው፡፡›› ብላ አማረረች፡፡ ከዚያም በስንት ፍለጋ እንደምንም ብላ ‹ብ›ን አገኘችው፡፡ ‹‹ብልት›› ለሚለው ቃል መጀመርያ የተሰጠውን ትርጉም አየችና፡፡ ‹‹ማነው ግን ይህን ሆም ወርክ የሰጣችሁ›› አለችው ልጇን፡፡ ‹‹ሆም ሩም ቲቸር ነው›› ‹‹ባለጌ ነው፡፡ ብልት የሚል ቃል አሁን ለልጅ ይሰጣል፡፡ በቃ ዶሮ እንኳን አሥራ ሁለት አንድም ብልት የላትም ብለህ ጻፍለት›› አለችው ተናድዳ፡፡
ልጁም እንደ እናቱ ተገርሞ ወደ ቀጣዩ ጥያቄ አመራ፡፡
‹‹የዶሮን ልዩ ልዩ ጥቅሞች ግለጡ›› ይላል፡፡
የዶሮ አርቢዋ ልጅ እናቱን ጠየቃትና እንዲህ መለሰችለት ‹‹ዶሮ ለሦስት ነገር ትጠቅማለች፡፡ አንደኛ ጠዋት ጠዋት ለመቀስቀስ ይጠቅማል፡፡ ሁለተኛ ተሽጦ ገንዘብ ይገኝበታል፡፡ ሦስተኛ ደግሞ ዕንቁላል ያስገኛል፡፡›› ልጁም ጻፈ፡፡
የነጋዴውም ልጅ እንዲህ ሲል መልሱን ሰጠ ‹‹ዶሮ ለወጥ፣ ለአሮስቶ፣ ለግሪል፣ ከሩዝ ጋር ለመብላት፣ ለሰላጣ ትጠቅማለች፡፡ አንዳንድ ሬስቶራንት ደግሞ እግሯን ለብቻ፣ ክንፏን ለብቻ ግሪል አድርገው ይሸጧታል፡፡ ዕንቁላሏ ደግሞ ለሳንዱች፣ ለዕንቁላል ፍርፍር፣ ለጥብስ፣ ለፓን ኬክ ይጠቅማል››
ጥያቄዎቹ ቀጠሉ፡፡
‹‹ዶሮ ተመግባችሁ የምታውቁ ከሆነ ስለ ጣዕሙ ግለጡ›› ይላል፡፡
የዶሮ አርቢዋ ልጅ ወደ እናቱ ተጠጋና ነገራት፡፡ ‹‹ወይ ጣጣ፤ እኔኮ አንተን የላክሁህ እንድትማር እንጂ እንድትራቀቅ አይደለም፡፡ አሁን ይሄ ልጅን ማጓጓትና ማሳቀቅ ትምህርት ይባላል፡፡ ለመሆኑ ራሳቸው መምህራኑስ የዶሮ መግዣ ዐቅም አላቸው? እኔኮ ስንት እንደምሸጠው ዐውቃለሁ፡፡ በሁለት መቶ ብር ለሦስት ወር የሚበቃ ሽሮ መግዛት ስችል የአንድ ቀን ዶሮ በልቼ የት ልደርስ ነው? በል ልጄ ‹ዶሮ ትሸጣለች እንጂ አትበላም በላቸው፡፡›› አለችው፡፡
ወዲያው ልጁ ቀበል አደረገና ‹‹እንዴ እማዬ መምህራችንኮ ዶሮ ይበላል ብሎናል›› አላት፡፡
‹‹እኛ ዶሮ አንበላም፡፡ ፈረስ የሚበሉ አሉ፡፡ እኛ ግን አንበላም፡፡ እንትኖች ውሻ ይበላሉ ሲባል እሰማለሁ፡፡ እኛ ግን አንበላም፡፡ አይጥ የሚበሉ አሉ፤ ዝንጀሮ የሚበሉ አሉ፤ ዕባብም የሚበሉ አሉ፡፡ ታድያ እኛ እነዚህን እንበላል?›› አለችና ጠየቀችው፡፤
የጠራችው ዝርዝር እያቅለሸለው ‹‹ኧረ አንበላም›› አላት፡፡
‹‹አየህ ልክ እንደዚሁ ነው፡፡ ዶሮም የሚበሉ ይኖራሉ፡፡ እኛ ግን አንበላም›› አለችው፡፡
‹‹ለምንድን ነው ግን እኛ ውሻ፣ አይጥ፣ ዝንጀሮ ያልበላነው?››
‹‹ሃይማኖታችን አይፈቅድማ››
‹‹ዶሮስ የማንበላው?››
‹‹እንደዚያው ነው ልጄ››
‹‹ታድያ እነ አካሉኮ ይበላሉ››
‹‹አየህ የሀብታሞችና የድኾች ሃይማኖት እዚህ ሀገር ይለያያል፡፡ ሀብታሞች መብልን እኛ ደግሞ ጦምን እናበዛለን፡፡ እነርሱ በደም ብዛት እኛ በደም ማነስ እንታመማለን፣ እነርሱ በስኳር ብዛት እኛ በስኳር እጥረት እንቸገራለን፣ እነርሱን ውፍረት እኛን ክሳት ያስቸግረናል፡፡ የነርሱ ልጆች አልበላም ብለው የኛ ልጆች እንብላ ብለው ይገረፋሉ፡፡ እነርሱ ገብርኤልን እኛ ሚካኤልን እንዘክራለን፡፡ በዚህ ምክንያት ሃይማኖታችን ተለያይቷል፡፡››
No comments:
Post a Comment