… ከመሞታቸው በፊት የተጻፈ
አቤ ቶክቻው
ከላይ በርዕሱ እንደተገለፀው ለዛሬው የፍትህ ጋዜጣ ጨዋታችን በዋነኛነት ይዤ የመጣሁት ጉዳይ መሪዎቻችን እነማን እንደሆኑ የሚጠይቅ ነው። ያው እንደተለመደው ሌሎች ጨዋታዎችም ይኖሩናል። አውራ ርዕሱ ግን “መሪዎቻችን እነማን ናቸው… አርቲስቶቹ ወይስ ታጋዮቹ?” የሚለው ይሆናል። “ለፓርቲ አውራ እንዳለው ሁሉ ለጨዋታም አውራ አለው።” እንልና ገዢው ፓርቲን ገልመጥ እናደርጋለን…
ለበርካታ አመታት በኤርትራ እስር ቤት እየማቀቀ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ አውሮፕላን አብራሪ በዛብህ ጴጥሮስ እንዲፈታ ሲል ታዋቂው አርቲስት ታማኝ በየነ በቅርቡ ለኤርትራ መንግስት ልመና አቅርቧል። እርሱን በሰማን በስንተኛው ቀን ድግሞ ሌላው ታዋቂ እና ተወዳጅ አርቲስት ቴዲ አፍሮ በሶማሌ ፑንት ላንድ ታስሮ ሞት ሊፈረድበት ጥቂት የቀረውን ወጣት አስመሮምን ሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ከፍሎ አስፈትቶታል። በእውነቱ እነዚህ አርቲስቶቻችን እያከናወኑ ያሉት እንደ አርቲስት ሳይሆን እንደ መንግስት ነው። የመንግስት ዋና ሰዎቻችን ደግሞ በየ ፓርላማው እና በየ መድረኩ የሚሰበስቡትን ሰው በሳቅ ሲያፈርሱ ስናይ “ታጋዮቹ አርቲስት፤ አርቲስቶቹ ደግሞ መንግስት ሆኑ እንዴ?” ያሰኛል። ቆይ ቆይ ይችን ታህል ለመግቢያ ካልን በመጀመሪያ አንዳንድ መልዕክቶች አሉኝ በአዲስ መስመር ላይ እንገናኝ… ታድያ ቀጠሮ ይከበር…
አዲስ መስመር፤
ከሳምንት ቆይታ በኋላ ከኮምፒውተሬ ጋር ተገናኘሁ። የኢንተርኔት ማምጫ ገመዴንም ሰካሁት። “ኢንተርኔት ማግኘት ትችላለህ” የሚል ምልክት ባየሁ ግዜም፤ አለም እንዴት እንደሰነበተች ለመቃኘት መስኮቴን ከፈትኩት። የኢንተርኔት ነገር በመስኮት ውስጥ መስኮት ነውና፤ በኢንተርኔቱ ውስጥ ሆኜ የፌስ ቡኬን መስኮትም ከፈትኩት።
በመልዕክት ማስቀመጫ ሳጥኔ ውስጥ በርካታ መልዕክቶች ተቀምጠዋል። በወንድሜ ድንገተኛ ሞት ብዙዎች አብረውኝ ደንግጠዋል። መልዕክቶቹን እያንዳንዳቸውን ለማየት ሙከራ አደረግሁ… በጣም ብዙ የሀዘን መግለጫዎች ደርሰውኛል። በጣም ብዙ…! ከፌስ ቡክ መልዕክት ሳጥኔ ዘወር ስል፤ የፌስ ቡክ ግድግዳዬን ቃኘሁ።
እዚህም እጅግ በጣም ብዙ ወዳጆቼ የሀዘን መግለጫቸውን ለጥፈውልኛል። ከዛም በ”ያሆ” አድራሻዬ የተላኩ መልዕክቶቼን አየሁኝ። በርካታ የማከብራቸው ታላላቅ ሰዎች እንዲሁም እኩያ ባልንጀሮቼ የሀዘኔ ተካፋይ መሆናቸውን መልዕክት ሰደውልኛል።
በስደት ላይ ሆነው እንዲህ ያለውን አስደንጋጭ ሀዘን መስማት እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው። በተለይም እንደኔ ስደተኝነቱን እንኳ በቅጡ ላላመነ አዲስ ስደተኛ በእንዲህ ያለው ግዜ መሰደዱ በደንብ ይገባዋል።
ነገር ግን “አይዞህ ሀዘንህ ሀዘናችን ነው” የሚሉ ሰዎች በዙሪያው እንዳሉ ባወቀ ግዜ መፅናናቱ ግድ ነው።
የወንድሜ አሟሟት ድንገተኛ ከመሆኑ አንፃር አንዳንድ ነገሮችን የጠረጠሩ በርካታ ወዳጆቼ ናቸው። እኔስ ብትሉ ምን ያልጠረጠርኩት አለ? ነገር ግን፤ እንዲህ ይሆንን? የለም እንዲህ ነው የሚሆነው… ምናልባት… ከእንትን ጋር የተያያዘ ይሆን… ማን ያውቃል እነ እንትና እንደሆነ አይታመኑ…? እያልኩ አብዝቼ ባብሰለሰልኩ ቁጥር ራሴን ከመታመም የዘለለ ፋይዳ አላገኘሁም። ቤተሰቦቼም ቢሆኑ፤”አንተን የሚያሳስብ ጉዳይ አይደለም” ከማለት ውጪ ዘርዘር ያለ ነገር አልነገሩኝም።
በእንዲህ አይነቱ ጭንቅላትን በሚያዞር የጭንቅ ግዜ አንድ ጥሩ መላ አለ… “እርሱ ያለው ሆነ!” የሚል የመፅሐፍ ጥቅስ። አዎ… የምንኖረው የተፃፈልንን ነው። የምናልፈውም በተፃፈልን ነገር ነው። ይህንን ማሰብ እና ማመን እንድንፅናና ያደርገናል።
የሆነ ሆኖ በደረሰብኝ እንደ አለት የከበደ ሀዘን ከእኔ እና ከቤተሰቤ ጋር አብራችሁ ያዘናችሁ እና እንድንፅናና የፀለያችሁ ወዳጆቼ በርካታ ናቸሁ። እናም እነሆ… ምስጋና በትልቁ…! እርሱም አይበቃም። ከጎኔ እንደቆማችሁ… ሺ በክንፉ ሺ ባክናፉ ከጎናችሁ ይቁም! ብዬ እመርቃለሁ።
እዝችው ጋር ያ ሳምንት ሌላም ሀዘን ተሸከሞ ነበር የመጣው። ተወዳጁ የስነ ፅሁፍ ደራሲ ሽማግሌው ስብሀት ለአብ አረፈ አሉ። ያሳዝናል።
በልጅነታችን እኔ እና ጓደኞቼ የለየልን የስብሀት አድናቂዎች ነበርን። አድናቂ ብቻ ሳንሆን ተከታዮቹም ጭምር፤ እንደውም ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ስንወጣ ስብሀት የስነ ፅሁፍ ማኅበር የሚባል አንድ መሰባሰቢያ መስርተን ነበር። ከቆይታ በኋላ “ስብሀት የሚለው ስም ከተለያዩ ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች ጋር ህብረተሰቡ እያገናኘው ነው እናም የማኅበሩን ስም ብትቀይሩት…” የሚል ምክር የራሱ የጋሽ ስብሀት እኩያ የሆኑ ሰዎች መከሩን። እኛም የትልቅ ሰው ምክር መስማት መልካም ነው ብለን በታላቁ ደራሲ የሰየምነውን ማኅበር ስም ወደ ሌላ ቀየርነው።
እንደዛም ሆኖ በተለይ እኔ የስብሀት ስራዎች ተመሳጭ ነበርኩ። አንዳንድ ግዜ… የጋሽ ስብሀትን ገፀ ባህሪዎች በእውን የተዋወቅኋቸው ይመስል፤ “አቶ አላዛር ኮምቡጥርን ምን አሉት መሰላችሁ…?” ብዬ ጨዋታ ስጀምር ጓደኞቼ “የልቦለድ ገፀ ባህሪያትን በእውን እንዳሉ አድርጎ በመቁጠር ወንጀል” ይከሱኝ ነበር። በኔ ጭንቅላት ውስጥ ግን ስብሀት የሳላቸው ገፀባህሪያት በእውን ያሉ መስሎ ነው የሚሰማኝ። አጋፋሪ እንደሻው፣ አላዛር፣ ኮምቡጡር፣ አርመኑ ሰውዬ፣ ሚስቱ እትዬ አልታዬ ሁሉም በኔ ጭንቅላት ውስጥ የእውነት ያሉ ይመስል በጠራራ ፀሐይ እና በውድቅት ለሊትም ስፈልጋቸው ኖሪያለሁ። ስብሀት ገብረእግዚአብሄር እኔ “ስቶሪ ቴለር ነኝ እንጂ ፈጥሬ ፅፌ አላውቅም።” ሲል ይደመጣል። እኔ ግን እለዋለሁ፤ “ስብሀት ፈጣሪ ነበር። አላዛርን እና ውሻቸው ኮምቡጥርን በአማርኛ ያግባባ፤ አጋፋሪ እንደሻውን ከሞት ጋር ያሯሯጠ ድንቅ ፈጣሪ ነበር። ምን ዋጋ አለው፤ ለፈጣሪም ፈጣሪ አለውና እርሱ አጋፋሪ ላይ የጫነባቸው የሞት ጥላ አይነት እግዜር ደግሞ በርሱ ላይ አጥልቶ ኖሮ ይህው በዛ ሳምንት “በቃ” ብሎት ሲጠቀልለው እኛንም ተራኪ አሳጣን… ነብስ ይማር እንጂ ሌላ ምን ይባላል?
የኔ ነገር ከላይ የጀመርኩትን አውራ ወሬ ሳላወራ ልሰናበትዎ ምን ቀረኝ ወዳጄ…? አውራው ወሬ የሚጀምረው ስለ አውራው ፓርቲ ሊቀመንበር በማውጋት ነው።
በዛ ሰሞን ፓርላማ ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርቲ ጓደኞቻቸውን ሰብስበው በተለያዩ ቀልዶች ፍርስ ሲያደርጓቸው ነበር። ነብሱን ይማረውና ተስፋዬ ካሳ ቢኖር ኖሮ “ማፍረሻ አድርጎ ፈጥሯቸው” ይላቸው ነበር። የምር ግን የጠቅላይ ሚኒስትራችን ቀልድ እና ተረት አዋቂነት አይደንቃችሁም…? ሳስበው በአለም ላይ ቀልድ አዋቂ ጠቅላይ ሚኒስትር እርሳቸው፤ ሳቅ እና ጨዋታ የበዛበት ፓርላማም እርሳቸው የሚመሩት የአራት ኪሎው ፓርላማ ነው የሚመስለኝ። እውነቴን እኮ ነው… እርስዎ ልብ ብለው እንደሆን እንጃ እንጂ፤ የፓርላማ አባላቱ ራሳቸው እኮ ገና ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገር ሲጀምሩ “መቼም ሳያስቁን አይለቁንም” ብለው ነው መሰል፤ ፈገግ ብለው ነው የሚያዳምጧቸው። እውነትም ታድያ እርሳቸውም አያሳፍሯቸውም… “አንድ ሌባ… ፈረስ ሰረቀ…” ብለው ተረቱን ገና ሲጀምሩት ሳቁ ይጀመራል። ተረቱን ተርትረው ሲጨርሱ የፓርላማ አባላቱም በሳቅ ይፈርሳሉ… “ማፍረሻ አድርጎ ፈጥሯቸው!”
አንዳንድ ግዜማ እንግዳ ሰው የእኛን ፓርላማ ሳቅ ጨዋታ ቢመለከት ሲኒማ ቤት ሳይመስለው አይቀርም ብዬ እጠረጥራለሁ። ታድያ ከዚህ የተነሳ ነው እንግዲህ አሽሟጦ አዳሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአርቲስቶችን ሚና እየተጫወቱ ነው ሲሉ የሚያሸሙሯቸው።
እንግዲህ ይህ አሽሙር እየተናፈሰ ባለበት ወቅት ነው አርቲስቶቹ ደግሞ መንግስት ሊሰራው የሚገባውን ስራ በመስራት መሪዎቻችን ማን እንደሆኑ ግራ ያጋቡን… እኛም ጠየቅን መሪዎቻችን እነማን ናቸው…? አርቲስቶቹ ወይስ ታጋዮቹ? (“ካጠፋሁ ልጥፋ” ይላል ሰካራም… የልብን ተናግሮ መጥፋት እንደመጥፋት አይቆጠርም… እንጂ ይላሉ የኛ ሰፈር ሰዎች!)
ከላይ እንዳልኩዎ… ታማኝ በየነ ኤርትራ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኘውን የጦር አውሮፕላን አብራሪ በዛብህ ጴጥሮስ… እንዲፈታ ለኤርትራ መንግስት ተማፅኖ አድርጓል። በነገራችን ላይ ይህ ሰው የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ወንድም ሲሆን፤ ለምርኮ የተዳረገው የዛኔ በኢትዮ ኤርትራ ግጭት ግዜ ግዳጅ ላይ በነበረበት ወቅት ነው። ታድያ መንግስት ነብሴ ብዙ ግዜ በዜጎቹ ጉዳይ ላይ “ጫ” ማለት ልማዱ ነው እያሉ የሚያሙት እውነት ይመስል፤ ይህንን ሁሉ አመት የዚህን አብራሪ ጉዳይ ስብሰባ ላይ እንዳለ ሞባይል ስልክ በ “ሳይለንት” ቢያቆየውም ይህው በኩምክናው የምናውቀው ታማኝ አይኑ በእንባ ተሞልቶ “እባካችሁ ፍቱልን” ሲል ለኤርትራ መንግስት ጥያቄውን አቅርቧል።
ያ ብላቴና ቴዲ አፍሮም “አልበላም አልጠጣም” ብሎ ሰባት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ወጪ አድርጎ የአንድ ኢትዮጵያዊን ነብስ ታድጓል። ይህም በሶማሌ ላንድ ታስሮ ሞት ፍርድ ሲጠባበቅ የነበረ ወጣት ነው። አስመሮም ይባላል። በርግጥ በአስመሮም ጉዳይ መንግስትም ያደረገው አስተዋፅኦ ቢኖርም የአንበሳውን ድርሻ ግን የሚወስደው አርቲስት ቴዲ አፍሮ ነው።
እንግዲህ አርቲስቶቹ በየሰዉ ሀገር እስር ቤት የሚገኙ ዜጎቻችን እንዲፈቱ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እያደረጉ ባሉበት በዚህ ወቅት መንግስት ደግሞ የራሱን ዜጎች “አሸባሪ” ብሎ አስሮ የሚገኝበት ሁኔታ ነው ያለው።(“እሰይ የኔ ኢቲቪ…” ይበሉኝ እንጂ ይቺ “ያለበት ሁኔታ ነው ያለው” የምትለው ቃል የኢቲቪ በተለይም የህትመት ዳሰሳ ፕሮግራም አዘጋጆች ቋሚ ንብረት ናት…ነገር ግን እኛም አንዳንዴ የመጣው ይምጣ ብለን እንጠቀምባታለን…) ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፤ “እና ታድያ “አሸባሪ” የሆነ ሰው ላይታሰር ነው እንዴ…?” ብሎ የሚጠይቅ “ከኔ በላይ ለመንግስት አሳቢ ላሳር” የሚል አይጠፋም። ጥሩ ጥያቄ ነው… ብለን እንመልሳለን…
ጥሩ ጥያቄ ነው ነገር ግን እነ አንዷለም አራጌ የታሰሩት አንሶ እስር ቤት ድረስ ጎረምሳ ገብቶ ሲደበድባቸው ማየት ግን በፊልም እና ድራማ ላይ ብቻ የምንጠብቀው “ትራጀዲ” ነገር ነው… እነ ናትናኤል ከተደበደቡ በኋላ ለፍርድ ቤት “አቤት” ሲሉ “ይሄንን ልንሰማ አልተሰየምንም” መባል ይሄ ደግሞ የለየለት ቀሽም ድራማ ነው… እና ታድያ…? እናማ ታግለው መንበረ ስልጣኑን የያዙት መሪዎቻችን እየመሩን ነው እያማረሩን? ብለን በድፍረት ለመጠየቅ እንገደዳለን።
ደግሞም እንፀልያለን… ለአርቲስቶቹ የሰጠውን ልቦና ለታጋዮቹም ይስጥልን! አሜን…
በመጨረሻም
አማን ያሰንብተን!
No comments:
Post a Comment