የፋሽስቱ ግራዚያኒን ሐውልት መሠራት ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ በአ.አ. ታሰሩ
”ይህ የጤንነት አይመስለኝም!” ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም
(እሁድ መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም. March 17, 2013)፦ የፋሽስቱን ግራዚያኒ ሐውልት በጣሊያን ሀገር በመሠራት ላይ መሆኑን በመቃወም በአዲስ አበባ ሰልፍ ለማድረግ የወጡ ከ35 በላይ ኢትዮጵያውያን ታሰሩ። ከእነዚህም ውስጥ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም፣ አቶ ታዲዮስ ታንቱ፣ እንዲሁም የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ይልቃል ጌትነት ጨምሮ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አመራር አባላት በዛሬው ዕለት ታስረዋል።
ይህንኑ በጣሊያን ሀገር አፎል ከተማ በግፈኛው ግራዚያኒ ስም ሙዚየምና ሐውልት መሠራቱን በመቃወም ዛሬ ስድስት ኪሎ ከሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት በመነሳት እስከ ጣሊያን ኤምባሲ ድረስ ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የተቃውሞ ሰልፉን የጠሩት “ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽ ኮሚቴ”፣ “ሰማያዊ ፓርቲ” እና “ባለራዕይ ወጣቶች ማኅበር” ነበሩ። እነዚህን ሠላማዊ ዜጎች ያሰሯቸው የፌዴራል ፖሊሶች ሲሆኑ፤ ለእስሩም ምክንያት የሰጧቸው “የሰልፍ ፈቃድ የላችሁም” በሚል እንደሆነ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የደረሰው መረጃ ያስረዳል። ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጆቹ በሕጉ መሠረት ለሚመለከተው አካል ሰልፍ እንደሚያካሂዱ አሳውቀው እንደነበር ለማወቅ ችለናል።
ከሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ስለሺ ፈይሳ፣ የሕግ ጉዳይ ኃላፊው አቶ ይድነቃቸው ከበደ፣ የፓርቲው የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ ወ/ሮ ሃና ዋለልኝ፣ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ያቶ ጌታነህ ባልቻ መታሰራቸው ታውቋል። ከባለራዕይ ወጣቶች ማኅበር ውስጥ ደግሞ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበሩ አቶ ብርሀኑ ተክለያሬድ፣ የማኅበሩ ዋና ፀሐፊ አቶ ያሬድ አማረ የታሰሩ ሲሆን፤ እስካሁን የታሳሪዎቹ ቁጥር ከ35 በላይ ሲሆን፣ የታሰሩትም ገዳም ሰፈር በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ መሆኑን ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።
ሠላማዊ ሰልፉ የተጠራው “የጣሊያ ፋሽስት እንደራሲ በኢትዮጵያ የነበረው ፊደል ማርሻል አዶልፍ ግራዚያኒ በህዝባችን ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋና ግፍ ታሪክ ከመዘገበው በላይ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ሆኖ ሳለ ለዚህ ግፈኛ ፋሺስት በጣሊያኗ አፊል ከተማ ሙዚየምና ሀውልት በስሙ ተገንብቶለታል። ይህ ድርጊትም የኢጣሊያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን ንቀት የሚያሳይ በመሆኑ በዕለቱ ማለትም መጋቢት 8 ቀን ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ማንኛውም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ሰማዕታት ሀውልት ዙሪያ በመሰባሰብ የዚህ ሠላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ እንዲገኙ በግፍ ባለቁ ኢትዮጵያዊያን ስም በአክብሮት ተጋብዘዋል።” በሚል እንደሆነ ታውቋል።
ይህን የዛሬውን የፌዴራል ፖሊስን ድርጊት አስመልክቶ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም በፌስ ቡክ ገጻቸው የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።
“የዛሬው ጉድ ነው፤ በኢጣልያ የግራዚያኒ ሐውልት እየተሠራ መሆኑን ለመቃወም የተለያዩ አገር ወዳድ ወጣቶች ከስድስት ኪሎ ወደኢጣልያ ኤምባሲ ሰልፍ ለማድረግ ጠርተው ነበር። ግራዚያኒ በየካቲት አሥራ ሁለት በቦምብ ካቆሰለ በኋላ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያስጨፈጨፈ አረመኔ ፋሺስት ነበር። ለዚህ ሰው ኢጣልያኖች ሐውልት መሥራታቸው የዛሬውን የኢትዮጵያ ትውልድ መናቅ ብቻ ሳይሆን ከኢጣልያ ጋር የተዋደቁትን ኢትዮጵያውያን ማዋረድ ነው፤ ስለዚህ ዛሬ መጋቢት 8/2005 ተቃውሞ ለማሳየት ታቅዶ ነበር። ፖሊሶች ሰልፉ እንዳይደረግ መከልከል ይችሉ ነበር፤ የተሰበሰቡትን በሰላማዊ መንገድ መበተን ይቻል ነበር። ፖሊሶች የመረጡት እየያዙ ማሰርን ሆነ። በአሁኑ ጊዜ ብዙ ወጣቶች ሴቶችና ወንዶች በየፖሊስ ጣቢያዎች ታስረዋል። ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያምንም ይዘውታል። በዓይኔ ባላየው ለማመን ትንሽ ያስቸግረኝ ነበር። እንዲያውም የተያዙትን ለመጠየቅ ሄጄ፤ የፖሊስ ጣቢያው በር ላይ ያገኘሁትን ነጭ ለባሽ ዛሬ የታሰሩ ሰዎች እዚህ መጥተዋል ወይ ብዬ ብጠይቀው “ምናባክ አውቅልሃለሁ፣ ግባና ጠይቅ” አለኝ። በሩ ላይ የነበሩ ሴት ፖሊሶች “አለቆቹ ስለሌሉ በኋላ ተመለስ” አሉኝ። ለማናቸውም እስረኞቹ በረንዳ ላይ ታጉረው አየኋቸው። እኔ ይህ የጤንነት አይመስለኝም!”
No comments:
Post a Comment