"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Sunday, 16 September 2012

ጥሩነሽ ዲባባ የመጀመሪያዋ በሆነው የግማሽ ማራቶን ውድድር አሸነፈች



የመጀመሪያዋ በሆነው የግማሽ ማራቶን ውድድር አሸናፊ ታላቋ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ከወጡት ኬኒያዊቷ ኪፕላጋት እና ኢትዮጵያዊቷ ቲኪ ገላና ጋር
በለንደን ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ፣ በ5 ሺህ ሜትር ደግሞ የነሀስ ሜዳሊያ ያገኘችው ኢትዮጵያዊቷ ታላቅ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ለመጀመሪያ ጊዜ የግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ ተሳትፋ ርቀቱን በአንድ ሰአት ከ07 ደቂቃ ከ35 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ አሸንፋለች። ኬኒያዊቷ የአለም የማራቶን ሻምፒዮን ኤድና ኪፕላጋት ጥሩነሽን ተከትላ ሁለተኛ ስትወጣ፣ በለንደን ኦሎምፒክ የማራቶን ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ኢትዮጵያዊቷ ቲኪ ገላና ሶስተኛ በመሆን አጠናቃለች።

ኒውካስል ውስጥ በተካሄደው በዚህ የታላቁ ሰሜን ሩጫ ግማሽ ማራቶን ውድድር ጥሩነሽ ልክ ለረጅም ጊዜ በበላይነት በተቆጣጠረችው የትራክ ውድድር ላይ እንደምታደርገው ሁሉ ከመሪዎቹ ጋር በመቀላቀል እና ብዙም ሳትርቅ ከኋላ እየተከተለች በመሮጥ ነበር ውድድሩን የጀመረችው። ርቀቱ ሊጠናቀቅ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ሲቀረው ከኪፕላጋት እና ቲኪ አፈትልካ በመውጣት በጎዳና ውድድሮች ላይ ከእርሷ የተሻለ ልምድ ያላቸው ሁለቱ አትሌቶች እንዳይደርሱባት ሩጫውን  ካፈጠነች በኋላ 400 ሜትር ሲቀረው የበለጠ ፍጥነቷን የቀየረችው ጥሩነሽ በታሪክ የመጀመሪያዋ በሆነው ውድድር የመጀመሪያ ጣፋጭ ድሏን ልታገኝ ችላለች።

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ በኦሎምፒክ በርካታ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ቁጥር አንድ የሆነችው ጥሩነሽ ዲባባ ቀጣይ አላማዋ ማራቶንን ጨምሮ በጎዳና ውድድሮች ላይ ድርብ ድሎችን ማግኘት ሲሆን፣ በቀጣዩ የአትሌቲክስ ውድድር አመት ማራቶንን ለመሮጥ እቅድ እንዳላት ከግማሽ ማራቶኑ ድሏ በኋላ በሰጠችው አስተያየት ይፋ አድርጋለች።

“የዛሬው ውድድር በጣም ፈጣን ነበር። ነገር ግን ወደውድድሩ ማብቂያ አካባቢ የጣለው ዝናብ አየሩ በመጠኑም ቢሆን ቀዝቃዛ እንዲሆን በማድረጉ በውድድሩ ላይ መጠነኛ አሉታዊ ተጽእኖ እንዲኖረው አድርጓል” ያለችው ጥሩነሽ፣ “በቀጣዪ አመት ትንሽ ሞቅ ይላል በሚል ተስፋ ከዚህ በተሻለ ሰአት ውድድሩን ለማሸነፍ እሞክራለሁ” ብላለች።

በወንዶቹ የግማሽ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው የማነ መርጋ ሶስተኛ ደረጃን አግኝቶ ሲያጠናቅቅ፣ በለንደኑ ኦሎምፒክ በማራቶን የነሀስ ሜዳሊያ ባለቤት ኬኒያዊው ዊልሰን ኪፕሳንግ ርቀቱ ሊጠናቀቅ 10 ሜትር ያህል ብቻ ሲቀረው የሀገሩ ልጅ ሚካ ኮጎን በፍጥነት በመቅደም በ59 ደቂቃ ከስድስት ሰከንድ በሆነ ጊዜ አጠናቆ አሸንፏል።

No comments:

Post a Comment