October 26, 2012 12:29 pm By Editor 5 Comments
“ላለፉት ሶስት ዓመታት ማንም ሳያውቀን ታስረናል። አሁን ጉዳያችን ለዓለም መድረሱን ሰማን።የተፈታን መስሎናል” የሚሉት እስራኤል ራምሌ በሚባ እስርቤት ከሶስት ዓመት በላይ ታስረው ያሉት ወገኖች ናቸው። ይህ የሆነው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር በርዕስ ለእስራኤል ጠ/ሚኒስትር በግልባጭ ደግሞ ከጉዳዩ ጋር አግባብ ላላቸው ለተለያዩ የአገሪቱ ባለስልጣናት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የመገናኛዎች አውታሮች ያሰራጩትን ደብዳቤ ተከትሎ በእስር ላይ ያሉት ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ በመንቀሳቀሱ ነው።
በእስራኤል የኢትዮጵያን እናድን አንድነት ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ሳሙኤል አለባቸው አድማሱ ለጎልጉል እንዳስታወቁት ከእስር ቤት በስልክ ያነጋገሯቸው ወገኖች የደብዳቤውን መልዕክት ሰምተው አስታዋሽ በማግኘታቸው ደስታቸውን ገልጸዋል። አቶ ኦባንግ ሜቶ በበኩላቸው “ማድረግ የሚገባንን ማከናወን ጀምረናል የሚሆነውን እናያለን” በማለት በቅርቡ ከእስራኤል መንግስት ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር ወደ ስፍራው እንደሚያመሩና እስር ላይ የሚገኙትን ወገኖቻቸውን እንደሚጎበኙ አስታውቀዋል።
ኦክቶበር 16 ቀን 2012ዓም በኢትዮጵያ ወቅታዊ የመወያያ (ECADF) የፓልቶክ መድረክ አንድ እንግዳ ቀርቦ ነበር። ጠያቂዋ ሙያዬ ምስክር መናገርና መጠየቅ ተስኗት አምላኳን እየተማጸነች ድምጿ ጠፋ። በሱዳን በኩል በስደት ካገራቸው የሚወጡ ኢትዮጵያዊያን በሲና በረሃ የደረሰባቸውን አሰቃቂ ግፍ የሚናገረው ወጣት ፍቅሩ፣ በረሃ ላይ ስለሚደርስባቸው ዘግናኝ ግፍ ሶስት ዓመት ከሶስት ወር ከታሰረበት እስር ቤት ውስጥ የኑዛዜ ያህል የወገኖቹን ስቃይ አስተጋባ
።
በረሃ ውስጥ የሚያገኟቸው አረቦች ገንዘብ ሲያጡ ኩላሊታቸውን ይወስዳሉ። አንዳንዴም አራትና ሶስት በመሆን “የኔን ውሰደው እነሱን ተዋቸው” በማለት ራስን ለእርድ የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ። ኩላሊትና ልብ ለመልቀም ከጎረቤት አካባቢ እንደሚመጡ የተቆሙት የህክምና ባለሙያዎች የአካል ክፍላቸውን አውልቀው የወሰዱባቸው ወገኖቻችንን አካላቸው ተወስዶ ሲያበቃ አምጥተው ይዘረግፏቸዋል። ከአስራ አራት እስከ አስራ ስድስት ዓመት የሚሆናቸውን ታዳጊ እህቶቻችንን ክብራቸውን በመከራ ውስጥ ተገስሰዋል። ከዚህ ሁሉ መከራና ሞት ተርፈው ከለላ ፍለጋ እስራኤል የገቡት ወገኖች የገጠማቸው ህይወት እጅግ አሳዛኝ ነው።
አቶ ሳሙኤል እንደሚሉት የኢትዮጵያውያኑ መታሰር እንዲታወቅ አይፈለግም ነበር። ተገደው ማመልከቻ በመጻፍ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከተደረጉት ውጪ በእናታቸው እቅፍ ላይ ያሉትን ጨምሮ ከሶስት መቶ በላይ ወገኖች በጠረፍ ድንኳን ውስጥ ከታሰሩ አራትና ሶስት ዓመታትን አስቆጥረዋል።
አቶ ኦባንግ ከሁሉም በፊት የሚያነሱት ነጥብ “ለኢትዮጵያዊያን አዲስ ኢትዮጵያ ትሰራለች።አሁን ስደት ላይ ያሉት ወገኖች የጠየቁት ጊዜያዊ ከለላ ነው። በ1997 የጄኔቫ ኮንቬንሽን መሰረት ጉዳያቸው ሊጣራ ይገባል” የሚል የህግ ጥያቄ ነው። አቶ ሳሙኤልም አቶ ኦባንግ የሚሉትን ይጋራሉ።
በእስር የሚማቅቁት ወገኖች ድምጽ ይፋ መሆኑን ተከትሎ አቶ ኦባንግ የጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ግልባጭ የተደረገላቸው ታዋቂ የሚዲያ አካላት ስፍራው ድረስ ይደርሳሉ፣ እስረኞቹን አነጋግረውና ጎብኝተው የደረሰባቸውን በደል ለዓለም ያጋልጣሉ የሚል ፍርሃት መፈጠሩን፣ ለዚህም አንዳንድ ምልክቶች መታየታቸውን አቶ ሳሙኤል አለባቸው ይናገራሉ። ለጉዳዩ ቅድሚያ የሰጡትን ሚዲያዎችና ተቋማት በማመስገን ጥሪ የሚያስተላልፉት አቶ ሳሙኤል “በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚሰሩ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች፣ ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ አገርና ወገን ወዳዶች…” ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ያሰራጨውን ግልጽ ደብዳቤ በመደገፍ ጫናውን እንዲያበረቱ ጥሪ አቅርበዋል። አቶ ኦባንግ በጋራ ንቅናቄው በኩል አቤቱታ (ፒቴሽን) እንዲያስፈርሙም ተጠይቀዋል። በግል መልዕክት የላኩላቸው ክፍሎች እንዳሉም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያዊ ስደተኞች በኬንያ፣ በጃፓን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ እስራኤል፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ … በመሳሰሉት አገሮች ለሚደርስባቸው በደል “አገራችሁ እንደ ሶማሊያና ኤርትራ አይደለችም እያሉ የተባበሩት መንግስታትን መመሪያ ይጠቅሳሉ” የሚሉት አቶ ኦባንግ ድርጅታቸው (አኢጋን) ወደ ጃፓን፣ ሜክሲኮ፣ ኖርዌይ፣ ማልታ፣ ስዊድን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ … የተጓዘውና መልዕክተኛ የላከው ይህንን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር እንደሆነ አመልክተዋል።
በሌሎች የዓለም ክፍሎች እንዳደረጉት ሁሉ በቅርቡ የጋራ ንቅናቄው በአካባቢው ከሚገኙ ቅርንጫፍ (ቻፕተር) አመራሮች ጋር በመነጋገር ወደ እስራኤል በመጓዝ ከሚመለከታቸው የእስራኤል ባለስልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ያስታወቁት አቶ ኦባንግ “የትም ይሁን የትም፣ የየትኛውም ብሄር አባል ቢሆን፣ ህጻናትም ሆኑ አዋቂዎች ኢትዮጵያዊያን ሁላችንም አንድ አካል ነን። ከታሰሩ ሁላችንም ታስረናል፣ ከተገረፉ ሁላችም ያመናል፣ ከተራቡ ሁላችንም ይርበናል፣ ሲጠሙ ሁላችንም ይጠማናል። የአንድ ወገናችን ስቃይ የሁላችንም ስቃይ በመሆኑ አቅማችን በፈቀደ ሁሉ የሚቻለንን ለማድረግ ዝግጁ ነን” ብለዋል። ይህ አስተሳሰብ “ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ነጻ አይወጣም” ከሚለው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መሰረታዊ መርህ የሚነሳ መሆኑንም አመልክተዋል።
በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ወገኖቻችን እየተሰቃዩ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ በቅርቡ ታላላቅ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፤ ሂውማን ራይትስንም ጨምሮ ወደ እስራኤል፣ ሲና በረሃና ኬንያ እንደሚጓዙ አመልክተዋል፡፡ አቶ ኦባንግ ከተቋማቱ ጋር ድርጅታቸው በተለይ ስለሚሰራው ሥራ አላብራሩም።
የተጀመረውን ዘመቻ ተከትሎ “ትምህርት እናስተምራቸዋለን” በሚል ህጻናትን ወደ ሌላ ስፍራ ማዘዋወር መጀመሩን፣ የእስራኤል ባለስልጣናት የጉብኝት ቀጠሮ መያዛቸውን፣ ያመለከቱት አቶ ሳሙኤል፣ አቡነ መርቆሪዎስ ስደተኞቹን ባሉበት ቦታ በመገኘት ለመጎብኘት ጊዜ መያዛቸውን ተናግረዋል። በልዩ ሁኔታ ጉብኝታቸውን ለማዘጋጅት ሙከራ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
“በፍርድ ቤት የተፈረደበት እስረኛ ፍርዱን ሲጨርስ እንደሚለቀቅ ስለሚያውቅ ቀኑን ይጠብቃል። የእኛ አይታወቅም። እኛ ያለነው መደበኛ እስር ቤት አይደለም። ዓለም በቃኝ ነው…” ፍቅሩ ከሙያዬ ምስክር ጋር ባደረገው አሳዛኝ ቃለ መጠይቅ ወቅት የተናገረው ቃል ነው። ከሲና በረሃ ስቃይ በኋላ ሌላ ሲኦል!! ኦባንግ ሜቶ “ለሁላችንም መፍትሄ የምትሰጥ አገር አለችን። እሷም አዲሲቷ ኢትዮጵያ ናት። መሰረቷም ቅድሚያ ለሰብዓዊነት ይሆናል። አዲሲቷ ኢትዮጵያ እስክትሰራ ባለንበት ልንከበርና ችግራችንን ተገንዝበው ሊያስተናግዱን ይገባል” ይላሉ።
በተመሳሳይ ዜና አቶ ኦባንግ በኖርዌይ ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ለመነጋገር ወደ ኦስሎ ያመራሉ። በኖርዌይ የሚገኙ ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በየጊዜው የሚደረግባቸው ጫና እንዲቆም በየአቅጣጫው ጥረት ሲደረግ መቆየቱ በተለያዩ መገናኛዎች መገለጹ አይዘነጋም።
No comments:
Post a Comment