By Bawza Staff
ከኪነ ጥበብ ጓደኞቿ ጋር የእራት ምሽት( ሽኝት)!!!!
በትላንትናው ዕለት በተደረገው የእራት ግብዣ ለዘማሪት አቦነሽ አድነው መሸኛ ብዛት ያላቸው አርቲስት ጓደኞቿ በተሰበሰቡበት ንግግር በማድረግ የዘፋኝነት ስራዋን ለቅቃ ወደ እግዚአብሄርን አመስጋኝነት ወደ ዘማሪነት የተሸጋገረችና ለመጨረሻ ጊዜ የዘፈኑን ዓለም የተወችና ያቆመች መሆኑን ለአርቲስት ጓደኞቿና በዕለቱ ለነበሩት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ተናግራለች።
አቦነሽ ስትናገር እኔ ለ24 ዓመት በሙዚቃው አለም አገልግያለሁ ሙዚቃን በጣም እወድ ነበር ሙዚቃ ለኔ ትልቅ ባለውለታዬ ነው አለምን አዙሮ አሣይቶኛል እኔም አድጌበታለሁ ሙዚቃ ለህይወቴ ብዙ አስተዋፅኦ አድርጎልኛል። ኑሬበታለሁ ቤተሰቦቼን ረድቼ ልጆቼን አሣድጌበታለሁ። ግን ዘማሪ መሆንን የተመኘሁትን ያህል ድምፃዊ መሆንን ተመኝቼው አላውቅም ከአምስት ዓመታት በፊት ጀምሮ ልቤ ሸፍቷል ሁል ጊዜ አስበው ነበር ዘማሪ መሆን እግዚያብሄርን ማገልገል የበለጠ ዋጋ ያለው መሆኑን አውቀው ነበር። እናም እግዚያብሄር ይመስገን ተሳካልኝ ሀሣቤ ሞላልኝ ይሄው ዛሬ በምወዳችሁ የጥበብ ጓደኖቼ መካከል ከአሁን በኋላ ዘማሪ ነኝ! ለወደፊትም መፅሀፍ ቅዱስ ቁጥር እየጠቀስኩ ብዙ ስለ እግዚያብሄር ልነግራችሁ እወዳለሁ ስትል ጓደኞቿን ተማጥና ከዘፈን ዓለም መሠናበቷን አብስራለች። በእለቱ የተሰበሰቡት ጓደኞቿም ለአቦነሽ(አቢቲ) ያላቸውን ክብር ገልፀው። በጭብጨባ የስራ መልቀቂያ ፈቃድ ሰጥተው በዘፈን አለም በነበረችበት ጊዜ አብረዋት ስላሣለፉት ስለ ፅባይዋ በጣም ንፁህ ደግ ቅንና ከበፊትም በዘፈን ዓለም ላይ እያለችም ከአፏ የሚወጡት ከአንደበቷ የሚፈልቁት ቃሎቿ የተቀደሱ ክፉ ነገር የማይወጣት የዘፈነችው የሚያምርባት ስትስቅ ስትጫወት ተወዳጅ የሆነች ትሁት በመሆኗ የመረጠችው መንገድ የሚገባትና ጥሩ የእግዚያብሄር አገልጋይ ልትሆን የምትችል መሆኗን በዕለቱ እየተነሡ ምስክርነት ሰጥተዋል። በምሽቱ የእራት ግብዣ ላይ አብረዋት ሲዘምሩ ሲያሸበሽቡ ብሎም በግጥም ስንኝ የቋጠሩላትም አንጋፋ አርቲስቶችም ነበሩ።
አቢቲ….
ተነሡ ለምስጋና(3)
ለዚህ ላበቃን እንዘምርለት
በዙፉኑ ፊት እንስገድለት!
እያለች አዲስ የሰራችውን መዝሙር በጣፋጭ ድምጿ ስትዘምር ከፊቷ ደስታና ብሩህ ህይወት ይታይባት ነበር።
በዕለቱ ከነበሩት ታላላቅ አርቲስቶች መካከል ታላቋ የኪነ-ጥበብ ሰው አርቲስት አለምፀሃይ ወዳጆ ስለ አቢቲ የሙዚቃ አነሣስና ታሪክ በጥቂቱ እንዲህ ስትል ተደምጣለች።
አቢቲ የተወለደችው በደቡብ ኢትዮጵያ በሃይቆችና ቡታጅራ አዉራጃ በሶዶ ወረዳ ቡኢ በምትባል ትንሽ ገጠር መንደር ሲሆን በጊዜው የነበሩት የሙዚቃ ጥበብ ባለሙያዎች ወደ አቢቲ መንደር ወደ ቡኢ በወረዱበት ጊዜ አቢቲን ለሙዚቃ አጯት። እሷም ሁል ጊዜ በዚህ በኪንጥበብ ሙያ ውስጥ ባለውለታዋ የሆኑትን ኮረኔል ለማ ደምሠውንና አርቲስት አየለ ማሞን ሁልጊዜ ታነሣለች። አቢቲ ገና ሙዚቃን የጀመረችው በድሮው የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡደን ውስጥ ነው ሀ ብላ ሙዚቃን የተቀላቀለችው።
ከዚያ በኋላም ባሳተመችው “ባላገሩ” “ባህሌን” በተሰኙ ሲዲዎቿ ተወዳጀነትን ያተረፈች ሲሆን አቢቲ መቼም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ህይወት ሁላችንም አርቲስቶችም ሆንን የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያውቀው ሙዚቃን ደምቃበታለች፣ አለምን ዞራበታለች፣ ታጅባበታለች፣ ተምነሽንሻበታለች በትላልቅ መድረኮች ላይ የመስራት እድል አግኝታበታለች። በዚያም መጠን ደግሞ ተወቅሣበታለች፣ ተከሣበታለች፣ በሬዲዮ ተወግዛበታለች እናም በተለያዩ ሁኔታዎች በማለፍ የሙያ አስተዋፀኦ አበርክታበታለች። አቢቲ ገና ስትጀምር ጀምሮ ከታላላቅ አርቲስቶች ከነ ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ከነ ብዙነሽ በቀለ እና ሌሎችም በነበሩበት የጀመረች በመሆኑ እስከ መጨረሻው በዚህ በአሜሪካም ከታላላቅ አርቲስቶችና ታላላቅ መድረኮችን የማግኘት እድልም አግኝታለች። በግሏ በአቢቲነቷ በአለም አቀፍ መድረክ እንደነ ኬኔዲ ሴንተር ባሉ ቦታዎች በመገኘት ተጫውታ ሌሎችንም ተከታዮችና አድናቂዎችን ያገኘች አርቲስት ናት።
በእለቱ በነበሩት ወጣት ዘማሪያን መካከል ዘማሪ ቸርነተ ሰናይ ዘማሪ ያሬድ እና የመዝሙር ዜማና የግጥም ደራሲዉ ሊቀ ትጉሃን መኩሪያ ጉግሳና ሰባኪ ቀሲስ ተስፋዬ መቆያ እንዲሁም ዲያቆን ቢኒያም እና ሌሎችም የተገኙ ሲሆን በምሽቱ የተገኙትን አርቲስቶች አመስግነዉ የዛሬዉ ዝግጅት በእናንተ የተዘጋጀ መሸኛ ነዉ።
እኛም የባውዛ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ባልደረቦች በምሽቱ ተገኝተን ተከታትለነው ነበር። ለዘማሪት አቦነሽ አድነው መልካሙን ሁሉ እንመኝላታለን።
No comments:
Post a Comment