በ Naod ቤተሥላሴ
የአሸብር በላይ ‹‹እኔ ነኝ ያለ›› የሚለውን ዘፈን የሰማሁት በቅርቡ ነው፡፡ የቆየ ዘፈን ይሁን አይሁን እንጃ፤ ለእኔ ግን አዲስ ነው፡፡ ባሕላዊ ዘፈን ይሏል ይሄ ነው፡፡ የወንዶቹን እስክስታ አይቼ አልጠገብኩትም፤ የሴቶቹን ኦሪጂናሊቲ አድንቄዋለሁ፤ ፉከራው ደስ ይላል፤ ከሁሉ በላይ ግን የዘፈኑ ታሪክ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ ሀገር መርቆ የሰጠውን ቆንጆ ሚስት የሚከላከል ጀግና አባወራን ጀግንነት የሚተርክ ዘፈን ነው፡፡
እንደ አጭር ልብወለድ የሚነበብ ታሪክ ያለው ዘፈን ወዳጅ ነኝ፡፡ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ስሜት የሰጠኝ ተራኪ ዘፈን ‹‹ቅዳሜ ገበያ›› የሚለው የቤተልሔም ዘፈን ነበር፡፡ ገበያ ልትገበይ ወጥታ፤ ፍቅር ሸምታ የተመለሰችው፡፡ ከልጆቼ ጋር ክብ አየሰራን፤ ስንት ዙር እንደጨፈርን አትጠይቁኝ፡፡
ከሰሞኑ የዘፈን ምርጫየ ባሻገር ግን የባሕል ዘፈን ሳይ የምታዘበው ነገር አለ፡፡
የሰሞኑ ምርጥ ዘፈኔ
በጎ ትዝብት
1ኛ-ነጭ የባሕል ልብስ ባለባቸው ሌሎች ዘፈኖች ላይ የማየው የሴቶች ባሕላዊ ቀሚስ፤ የደረሰበት የፋሽን እና የዲዛይን ጥበብ ደረጃ ያስደስተኛል፡፡ በዚህ በኩል ወንዶች ተበድለናል፡፡ፋሽን ልብስ ሰፊዎች፤ በተለይ የሕንድ የሚመስለውን ቀሚሳችንን ቢያስወግዱልን ጥሩ ነበር፡፡እኔ እንድወድላቸው ከፈለጉ፡፡
2ኛ- ከነጩ ልብስ በላይ ደግሞ የሚስገርመኝ ለየብሔረሰቡ የተሰጡት ዘመነዊ ልብሶች ናቸው፡፡ የጎጃም አረንጓዴ ቁምጣ እና ባለ መስመር ካናቴራ፤ የጉራጌ ደመቁ ቀሚስ እና ሻሽ፤ ወዘተ…እኒህም የተሸሻሉ የባሕል ልብሶች መሆናቸው መሰለኝ፡፡ የዚህም ደጋፊ ነኝ፤ ብዙ እውነት አለውና፡፡
3ኛ- ዘፋኞች በፍቅረኛ እያስመሰሉ የሚታገሉለት ኢትዬጵያዊነት እና አንድነት ይታየኛል፡፡ ስለ አንድነት ማውራት ነውር በሆነበት የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ፤ ከዘፋኞች በቀር አንድነት እና ኢትዬጵያዊነት እንዳይረሳ ለማድረግ የሚታገል አካል አለ ብዬ አላምንም፡፡ በተለይ አሁን አሁን የጀመሩት የቅልቅል ትርዒት ደጋፊ ነኝ፡፡ የአማራ አልባሳት ለብሶ ኦሮምኛ መዝፈን፤ የጋሞ ልብስ ለብሶ ትግሪኛ መጨፈር፤ በጉራጊኛ ዜማ አማርኛ መዝፈን፤ በትግሪኛ ዘፈን ጎንደርኛ እስክስ ማለት ወዘተ…የአንድነት ስብከት ስለሚመስለኝ እወደዋለሁ፡፡ ባህል ተበላሸ የሚሉ ወገኖች እንደሚኖሩ ባልጠራጠርም፤ እኔ ግን ከመልዕክቱ አንጻር ሳየው…የማይቻል ነገር የለም…ዋናው ፍቅሩ ነው…የሚል መልዕክት ያለው ይመስለኛል፡፡ እናም ደስ ይለኛል፡፡
4ኛ-የእስክስታ እድገት ያዝናናኛል፡፡ ወደፊት እንደ ድሮ የገጃም፤ የጎንደር፤ የወሎ የሚባል የጅምላ አጠራር እየቀረ የእገሌ እስክስታ፤ የእገሊት እስክስታ መባል ላይ መድረሱ አይቀርም፡፡ ወንዶቹ በየጊዜው የሚፈጥሩት የጭፈራ እና የእስክስታ ትርዕት ይመስጠኛል፡፡
አሉታዊ ትዝብት
በባሕላዊ ዘፈን ላይ፤ በተለይ የአማራ የባሕል ዘፈን ላይ፤ ቅር የሚለኝ ግን የጦር መሳሪያቸው ነው፡፡ ጎጃም እና ጎንደር ዘለዓለም-ዓለም ቤልጂግ እና አልቤን፤ መውዜር እና ምንሽር፤ ‹ዲሞፍተር› እና ናስማስር ብቻ ይዘው የሚፎክሩበት ምክንያት አይገባኝም፡፡ ክላሽንኮቭ ከተፈጠረ በኋላ ጀግና የለም ማለት ነው? ወይስ እንደፈራሁት ክላሽ ይዞ መዝፈን የሚቻለው በክላሽ ዘመን ተዋግቶ ላሸነፈ ብቻ ነው፡፡ ባሕላዊ ዘፋኞች ይህንን ቢያስቡበት ጥሩ ነው፡፡
ሌላው ቅር የሚለኝ ደግሞ የጀግኖች ነገር ነው፡፡ ጎጃም ከአንድ በላይ ዘለቀ በቀር ጀግና የለውም? በኢሕአዴግ ዘመን ላይኖረው ይችላል፤ አልተዋጋምና፡፡ ግን በደርግ ዘመን በሶማሌ ጦርነት ጊዜ ከፍተኛ ገድል የሰሩ ጄኔራሎች እና መኮንኖች የሉም?፡፡ ሁሉም ብሔር የራሱን ታሪክን መርምሮ፤ ጀግኖቹን፤ አባቶቹን፤ ያልታወቁ ልዩ ነገሮቹን ማስተዋወቅ ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡ ይሄም ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡
አሁን ወደ ዘፈኑ
...እኔ ነኝ ያለ...
ያያት ሲረባረብ፤ ከቶ ማን ሊነጥቀኝ
ጎጃም አይደለም ወይ፤ መርቆ የሰጠኝ፡፡
እርሷን ያለ ደፋር፤ ጎበዝ ጀግናውን
አሳዩኝ እስኪ የታል፤ እኔ ነኝ ያለውን
ጎበዝ…እኔ ነኝ ያለ
ጀግና…እኔ ነኝ ያለ
እኔ ነኝ ያለ
እኔ ነኝ ያለ
እኔ ነኝ ያለ
እኔ ነኝ ያለ
ያዝ እንግዲህ….እንዲያ
No comments:
Post a Comment