"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Monday, 31 December 2012

አክሱምን ወላይታ አገኘሁት!!!



(ናትናኤል ፈለቀ)
40 minch
ኅዳር 12 ቀን 2005 ዓ.ም በሥራ ጉዳይ ወደ ጋሞ ጎፋ ዞን ዋና ከተማ አርባ ምንጭ መሄድ ነበረብኝ፡፡ ለሁለት ቀን ተኩል የሚበቃኝን  ሸክፌ ከመሥሪያ ቤቴ በተመደበልኝ መኪና ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ ለሚነሳው በረራ ለመድረስ ወደቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ በቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን በኩል ወደ ቦሌ የሚወስደውን መንገድ ይዘን ስንጓዝ ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ ላይ የተደረደሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት አቀባበል ወይንም ሽኝት የሚደረግለት ባለሥልጣን/እንግዳ እንዳለ ስለጠቆመኝ መንገዱ ሳይዘጋ ቦሌ ለመድረስ ጥረት እንዲያደርግ ለሹፌሩ ጠቆምኩት፡፡ ብዙም ሳንጓዝ አትላስ ሆቴል የትራፊክ መብራት ላይ ስንደርስ በስፍራው የነበሩት የትራፊክ ፖሊሶች ወደ ቺቺንያ ወይንም ወደ ቦሌ ሩዋንዳ የሚወስደውን መንገድ እንድንጠቀም አስገደዱን፡፡ ወዲያውኑ ሰዓቴን ተመለከትኩ፤ ለሰባት ሰዓት ሩብ ጉዳይ ይላል፤ ብዙም አልተረበሽኩም፡፡ በስተቀኝ በኩል ታጥፈን በውስጥ ለውስጥ አቋራጭ መንገድ ጥቂት ከሄድን በኋላ መልሶ ዋናውን መንገድ ስላገናኘን መኪናውን አቁመን እንግዳውን እስኪያልፍ መጠባበቅ ጀመርን፡፡
በዚያው ሰሞን ወደ ሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ሄዶ የነበረ አንድ የሥራ ባልደረባችን በአምስት ቀን ቆይታው ሁለት ጊዜ በመንገድ ያለፋቸው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በከተማው መንገድ ላይ ሲጓዙ እሳቸው ከሚጓዙበት አቅጣጫ በተቃራኒው የሚወስደው የመንገዱ ጎን ክፍት እንደሚሆን የነገረኝን ለሹፌሩ እያጫወትኩት ሳይረን እያሰማ የሚከንፈውን ሞተረኛ ተከትለው ካልተሳሳትኩ አምስት መኪኖች በፍጥነት ወደ ቦሌ የሚወስደውን መንገድ ይዘው ሲያልፉ አየን፡፡ ካለፉት መኪናዎች ሦስቱ ባለግርማ ሞገሶቹ ጥቋቁር ሼቭሮሌቶች ነበሩ፡፡ ያለፉት ባለሥልጣን ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መሆን አለባቸው (በእርግጥም ነበሩ፤ ለሥራ ጉብኝት ወደ ጎረቤት ሀገር ኬንያ እያቀኑ)፡፡ እንደ ሥራ ባልደረባችን ከሆነ ፕሬዝዳንት ካጋሜን የሚያጅቡት አንድ ሞተረኛ ፖሊስ ከፊት እና አንድ መኪና ከኋላ ሆነው ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ይህን ሁሉ ጥበቃ የሚደረግላቸው ከፕሬዝዳንት ካጋሜ ይልቅ ለደኅንነታቸው የሚሰጉ መሪ ስለሆኑ ነው? ወይስ ኢትዮጵያዊያን ከሩዋንዳዊያን ይልቅ አስፈሪ ሕዝብ ስለሆንን? ይህንን እቆቅልሽ እያሰላሰልኩ መንገዱ ተከፍቶ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የአገር ውስጥ በረራ የሚደረግበት ጣቢያ ቁጥር 1 ደረስኩኝ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ቀልቤ አይወደውም፡፡ ምናልባት የመጀመርያ በረራ ባደረኩበት ወቅት በድርጅቱ እንዝላልነት ምክንያት ያጋጠመኝ በሕይወቴ ከዛ በፊትም ሆነ በኋላ አጋጥሞኝ የማያውቅ እንግልት ተፅዕኖ አድርጎብኝ ይሆናል፡፡ ጥሎብኝ ደግሞ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምሰጣቸው የቤተሰብ አባላት እና የቅርብ ጓደኞቼ ለአየር መንገዱ ተቀጥረው ሠርተዋል/እየሠሩ ነው፡፡ አየር መንገዱ ላይ ያለኝ አቋም ከነዚህ ወዳጆቼ ጋር አልፎ አልፎ ቅራኔ ውስጥ ይከተኛል፡፡
ተርሚናሉ ውስጥ ገብቼ በመፈተሻ መሳሪያው ካለፍኩ በኋል የያዝኩት ሻንጣ ማሽኑን አልፎ እስኪመጣ ቀበቶዬን እያጠለኩ ስጠባበቅ ‹‹ወደ አርባ ምንጭ ስለሆነ እንጂ ሌላ ቦታ ቢሆን አይፈቀድም›› የሚለው ከማሽኑ ጀርባ ተቀምጣ ሻንጣዎች ውስጥ ያለውን እቃ በምስል የምትከታተለው የጥበቃ ባለሙያ ንግግር ቀና አደረገኝ፡፡ ‹‹አቤት›› አልኳት በተገረመ ድምፅ፡፡ ‹‹አይ አንተን አይደለም›› አለችን በአገጯ ከአጠገቤ የቆመውን ሰው እየጠቆመችኝ፡፡ ሰውየው ስሙ ያልተጠራው እሱ ሻንጣ ውስጥ ያለው እቃ ምን እንደሆነ ገብቶታል፡፡ ተረጋጋሁ፡፡ ወዲያው ደግሞ ሌላ ሐሳብ ገባኝ፤ ሌላ በረራ ላይ የማይፈቀድ ነገር ግን አርባምንጭ ስለሆነ የሚፈቀድ እቃ ምንድን ነው?
የአየር መንገዱ ሠራተኞች የ‹ቼክ-ኢን› ሰዓታቸው የደረሱትን በረራ ተሳፋሪዎችን በሁለት መስኮቶች እያስተናገዱ ነበር፡፡ ከሚያስተናግዱት የአየር መንገዱ ሠራተኞች መካከል አንደኛዋ ፀጉሯን መሸፈኛ (በእስልምና እምነት ሥርዓት) ‹ሂጃብ› አድርጋለች፡፡ ‹ሂጃቡ› ከለበሰችው የአየር መንገዱ ሰራተኞች የደንብ ልብስ ጋር አብሮ እንዲሄድ መደቡ ነጭ ሆኖ አረንጓዴ መስመሮች ያሉበት ሲሆን በቀጭኑ ‹የኢትዮጵያ/Ethiopian› የሚል ጽሑፍ አርፎበታል፡፡ ብዙ ድርጅቶች እንኳን ለሠራተኞቻቸው ይቅርና ለሚያገለግሏቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች ምቾት እምብዛም እንደማይጨነቁ ስለማውቅ በአየር መንገዱ እርምጃ ተደሰትኩኝ፡፡ ወድያውኑ ስልኬን አውጥቼ ብዙ ግዜ በአየር መንገዱ ላይ የማማርርባት ጓደኛዬን ቁጥር መታሁ፡፡ ስልኩ ሲነሳም በአየር መንገዱ ውስጥ እንዳለሁ ጠቅሼ የደወልኩት እንደበፊቱ ለማማረር ሳይሆን ባየሁት ነገር ደስ ስላለኝ እንደሆነ፤ ጥፋት ሲሆን እንደማማርረው ሁሉ በቀጣሪዋ ሥራ ስደሰትም ማመስገን እንዳለብኝ ጉራ ቢጤ ቸበቸብኩ፡፡
ከፊቴ ከነበሩት ሰዎች ቁጥር አንፃር ሰልፍ ላይ ረጅም ሰዓት ያሳለፍኩ ስለመሰለኝ ‹ቼክ-ኢን› አገልግሎት የሚሰጠት ሠራተኞችን መከታተል ጀመርኩ፡፡ ጥርጣሬዬ ልክ ነበር፡፡ እኔ ስደርስ ቀድመውኝ ከፊቴ ከነበሩት መንገደኞች መካከል ከሦስት በላይ ተሳፋሪዎች ‹ቼክ-ኢን› ጨርሰው ወደ እንግዳ መቆያ ስፍራ አልተመሩም፡፡ ችግሩን ለማጣራት ሞክሬ ጥፋቱ የደንበኞች አገልግሎት የሚሰጡት ሠራተኞች እንዳልሆነ ተረዳሁኝ፡፡ ችግሩ ሠራተኞቹን የሚረዳቸው ‹ሲስተም› እክል ስለገጠመው ነበር፡፡ የመንገድ መዘጋቱን ተከትሎ አብዛኛው ተሳፋሪ ዘግየት ብሎ በመድረሱ ምክንያት ሰልፉ በርከት ብሏል፡፡ የደንበኞች አገልግሎት ሰራተኞቹ ደንበኞቻቸውን በቶሎ ማስተናገድ ስላልቻሉ ኮምፒውተር እየቀያየሩ ይሞክራሉ፣ ስልኮቻቸውን እያነሱ ችግሩን ለበላይ ሰዎች ለማስረዳት ይሞክራሉ፣ ፊታቸው ላይ መጨነቃቸው ያስታውቃል፡፡ እዛው ሰልፍ ላይ ሆኜ ለስምንት ሰዓት አስራ አምስት ደቂቃዎች ብቻ ቀሩት፡፡ አርባ ምንጭ ስራዬን የምጀምረው በማግስቱ ስለነበር ማርፈድ አላስጨነቀኝም፡፡ ነገር ግን ከአየር መንገዱ የተሰጣቸውን ሰዓት ተንተርሰው የሥራ ወይንም ሌላ ቀጠሮ የያዙ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ገመትኩኝ፡፡ ‹‹ቀድሞ ማመስገን ኋላ ለሐሜት ይቸግራል›› የሚለውን የሀገሬን አባባል አስታወስኩኝ፡፡
ስምንት ሰዓት ሊሆን ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት አንድ በአካባቢው ከዛ ቀደም ያላየሁት በእጁ መገናኛ ሬድዮ (ዎኪ-ቶኪ) የያዘ የአየር መንገዱ ሠራተኛ (የቅርብ አለቃ ይመስለኛል) ወደ ጅማ እና አርባ ምንጭ የምንሄድ ተሳፋሪዎችን ጠይቆ ከሰልፉ ውስጥ ለይቶ ‹ቼክ-ኢን› በ‹ማንዋል› እንዲሰራልን አዝዞ ወደ አውሮፕላኑ በቀጥታ እንድንሳፈር አደረገ፡፡
የወሰደኝ ጢያራ
አውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፍረን ቦታ ቦታ ከያዝን በኋላ የበረራ አስተናጋጆቹ የሻንጣ ማስቀመጫ ሳጥኖቹን መዝጋት ጀመሩ፡፡ ከተቀመጥኩበት ወንበር ቀጥሎ የነበረው ወንበር አናት ላይ የነበረው ሻንጣ ማስቀመጫ እንደሌሎቹ በቀላሉ ሊዘጋ አልቻለም፡፡ የበረራ አስተናጋጅዋ መዝጊያው ላይ ኃይል ጨምራ ወረወረችው፡፡ ለጆሮዬ የሚረብሽ ድምፅ ነበር፡፡ በመጀመርያ ሙከራዋ መዝጋት ስላልተሳካላት የበለጠ ኃይል ተጠቅማ ሞከረችው፡፡ ቁጣ የሞላው ፊት ይዤ ዞርኩኝ፡፡ አስተናጋጇ አልዘጋ ካለው ሻንጣ ማስቀመጭ ስር ትይዩ የተቀመጡትን መንገደኞች (በእርግጠኝነት ድምፁ ከኔ በላይ ይረብሻቸዋል) ፈገግታ የተሞላበት ይቅርታ ጠይቃ ወደ መውጫው በር አመራች፡፡ ስትመለስ በግሪስ የተበላሸ ነጭ ቱታ የለበሰ መካኒክ አስከትላ መጣች፡፡ የሻንጣ ማስቀመጫውን ለመዝጋት የመጀመርያ አማራጭ አድርጎ የወሰደው አስተናጋጇ ስታደርግ የነበረውን መድገም ነበር፡፡ ለሱ ተሳካለትና እየተንጎማለለ ወረደ፡፡
ጉዞ ለመጀመር አውሮፕላኑ ወደ መንደርደሪያው ሲያመራ ከበረራ አስተናጋጆች ውስጥ አንዷ በድምፅ ማጉያው ሰላምታ አስቀድማ ‹‹ይህ በረራ ከአዲስ አበባ በጅማ አድርጎ ወደ አርባምንጭ የሚሄድ ነው…›› አለችን፡፡ ‹ወቸ ጉድ› አልኩኝ በሆዴ ትኬቱን ለማግኘት ሻንጣዬን እየከፈትኩኝ፡፡ ትኬቱ ላይ እንዲህ የሚል ተጽፏል፤
DATE  BRDOFF      TIME
21NOV ADDAMH     1400
ከዚህ ውጭ አርባ ምንጭ ከመድረሳችን በፊት ጅማ እንደምናርፍ የተጻፈ ነገር የለውም፡፡ በረራዬን ሳስመዘግብም ሆነ (በኋላ ጠይቄ እንደተረዳሁት) የመሥሪያ ቤቴ ጉዳይ አስፈፃሚ ትኬቱን ሲገዛ ይህ መረጃ አልተሰጠኝ/ንም፡፡ ምናልባት ከመሳፈሬ በፊት የበረራ መነሻ እና መድረሻ ሰዓት የሚያሳዩት የቴሌቪዥን መስኮቶች ላይ በረራው በጅማ በኩል አድርጎ ይጓዛል የሚል መረጃ ከነበረ አላስተዋልኩም፡፡ ኖሮ ከነበረም ከአዲስ አበባ አርባ ምንጭ ለመድረስ የሚፈጅብን 65 ደቂቃ መሆኑ ቀርቶ ከሁለት ሰዓት በላይ መሆኑን በመጨረሻ ሰዓት ማወቅ ለውሳኔ የሚረዳ መረጃ አይደለም (It’s Irrelevant)፡፡
አውሮፕላኑ ምድርን ለቆ የአየር ጉዞ ጀምረን የወንበር ቀበቷችንን መፍታት እንደምንችል ከተነገረን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አንድ ተሳፋሪ ከመቀመጫው ተነስቶ ሻንጣውን ከፈተና በላስቲክ የታሸገ ነገር አውጥቶ ወደወንበሩ ተመለሰ፡፡ ከተቀመጠ በኋላ የወንበር ማስደገፊያውን (ጠረጴዛ) አወረደና ላስቲኩን ፈትቶ አስቀመጠው፡፡ ዓይኔን ማመን አቃተኝ፡፡ ሰውየውን አስታወስኩት፡፡ በር ላይ የጥበቃ ባለሙያዋ በረራው ወደ አርባ ምንጭ ስለሆነ እንዲያሳልፍ የፈቀደችለት ጫት ነበር፡፡ ከበረራ አስተናጋጆቹ አንዷ ጫቱን ባየች ጊዜ ወደ ተሳፋሪው ጠጋ ብላ ሹክ አለችው፡፡ ወድያውኑ ላስቲኩን ጠቀለለና ወደ ሻንጣው መለሰው፡፡ አየር መንገዱ ተሳፋሪዎች በረራ ላይ ትንባሆ ማጨስ የሚከለክል መሆኑን አውቃለሁ፤ ጫት እንዳይቅሙ የሚከለክል መመርያ እንዳለው ግን አላውቅም፡፡ የጥበቃ ባለሙያዋ ለምን እንደፈቀደች እና የበረራ አስተናጋጅዋ ለምን እንደከለከለችው (በግምት ነው) ግልፅ አልሆነልኝም፡፡
ጅማ አርፈን የጅማ ተሳፋሪዎችን አወረድንና አዳዲስ ሰዎች ወደ አውሮፕላኑ ገብተው በወረዱት ሰዎች ምትክ ሞሉት፡፡ ከጅማ ወደ አርባ ምንጭ ለዛውም በአውሮፕላን የሚሄዱ ይህን ያክል ሰዎች መኖራቸው አልዋጥልህ አለኝ፡፡ እንደተለመደው የበረራ አስተናጋጅዋ ‹‹…ይህ በረራ ከጅማ ተነስቶ በአርባ ምንጭ ወደ አዲስ አበባ የሚሄድ ነው …››፡፡ አሁን ‹ይህቺ ነገር የተለመደች ናት ማለት ነው› አልኩኝ ለራሴ፡፡
የማይደረስ የለም እና አርባ ምንጭ ደረስኩኝ፡፡ ከአውሮፕላኑ ወርደን ወደ ጣብያው እንግዳ ማረፍያ ስንገባ ሁለት የሰማይ ስባሪ የሚያካክሉ ነጮች የመገናኛ ሬድዬናቸውን ወገባቸው ላይ አንጠልጥለው ከአውሮፕላኑ የወረደውን ሰው በዓይኖቻቸው ይመረምራሉ፡፡ የወታደር ሱሪያቸው የዘነጋሁትን ነገር አስታወሰኝ፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ‹በወዳጅ› ሀገራት ካቋቋማቸው ሚሳኤል ተሸካሚ ሰው አልባ በራሪዎች (ድሮን) ከሚያስነሳበት ጣብያ አንዱ አርባ ምንጭ አየር ማረፊያ ላይ ይገኛል፡፡
ለምለም ካሉስ – አርባምንጭ
ከአርባ ምንጭ አየር ማረፊያ አንስቶ ከተማ ድረስ የሚወስደው መንገድ ‹ኢትዮጵያ ሀገሬ ልምላሜሽ ማማሩ› የሚለውን ዘፈን ያስታውሳል፡፡ ናሽናል ጂዮግራፊ ላይ ድሮ የታንዛንያ ፓርኮችን አይቼ በተፈጥሮ ውበታቸው የቀናሁት አርባ ምንጭን ስላላየኋት ብቻ እንደሆነ ገባኝ፡፡ ግራ ቀኙ አረንጓዴ ነው፡፡
አርባ ምንጭን በአካል ሄጄ ሳያት የመጀመርያዬ ነበር፤ ሆኖም ዞር ዞር ብዬ ከተማዋን ለማየት ከሄድኩበት ሥራዬ የሚተርፍ በቂ ጊዜ አላገኘሁም፡፡ ከተማዋ የሁለት ‹ክፍለ ከተሞች› ውጤት ናት – ሲየቻ እና ሲቀላ፡፡ ሲየቻ የአርባ ምንጭ ከተማ ንግድ እንቅስቃሴን የሚመራው ክፍል ሲሆን ሲቀላ ደግሞ የዞኑን ጽሕፈት ቤት እና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ጊቢን ጨምሮ የመንግስት ተቋማትን አቅፎ የያዘው የከተማው ክፍል ነው፡፡
አርባ ምንጭ
‹‹ኑድሬ ጋሞ ጎፋ ኦይቻ አርባ ምንጭ፤
ምዝሪ ካልሲሪ የዴስ አባያ ጫሞ ሙሌ››
(ትርጉሙ፡- ‹‹ ሀገሬ ጋሞ ጎፋን ጎብኙ አርባ ምንጭን ኑ እዩ፣ አባያ እና ጫሞ ሙሉ ናቸው ጠግባችሁ ጠጥታችሁ ትመለሳላችሁ› እንደማለት ነው) ሲል አዚሞ ከተማዋን እና ነዋሪውን ላሞገሰበት እና ላስተዋወቀበት ውለታው ለአርቲስት አቡሌ ጫቦ ሲየቻ መሐል አደባባይ ላይ የመታሰቢያ ሀውልት አቁማለታለች – ይህ ሀውልት ለከተማው ብቸኛው ነው፡፡
አርባ ምንጭ በርካታ ውኃ ሀብት ባለቤት ናት፡፡ ከአርባ ምንጭ የአየር ማረፊያ ወደ ከተማው ሲሄዱ የሚያገኙት የኩልፎ ወንዝ ከገፀ-ምድር የውኃ ሀብቶቿ የመጀመርያው ነው፡፡ አባያ እና ጫሞ ደግሞ በዓሳ ምርታቸው በመላው ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው ሀይቆች ናቸው፡፡ ከዚህ ላይ ደግሞ የከተማዋ ስም መነሻ የሆኑት አርባዎቹ ምንጮች አሉ፡፡ ሁለቱ ሀይቆች ብዛት ላላቸው አዞዎችም መኖርያ ናቸው፡፡ በሲየቻ በኩል ለማግኘት የሚቀለውን ጫሞን ጠጋ ብዬ አይቻለሁ፡፡ ሀይቁ የከተማው ሰው በተለምዶ የእግዜር ድልድይ ብሎ የሚጠራው ጉብታ ጋር ትግል ላይ ይመስላል – ከመንትያው የአባያ ሀይቅ  ጋር ለመቀላቀል፡፡ የጫሞ ሀይቅ አዞዎች የዋሆች ናቸው ይላቸዋል ሀገሬው፤ ከአባያ  ሀይቅ አዞዎች አይምሬነት ጋር እያነፃፀረ፡፡
ከተማዋ ውስጥ ያለው የፈረንጆች ብዛት ያስገርማል፡፡ እንደዚህ ብዛት ያላቸው የውጭ ሀገር ተወላጆች በብዛት የሚገኙበት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ሌላ ከተማ ማየቴን እጠራጠራለሁ፡፡ የድሮን ማዘዣ ጣብያውን ተከትሎ የመጡት አሜሪካውያን ናቸው ከተማዋን ያጥለቀለቋት ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ነገር ግን ብዛታቸው እና የሚያወሩት ቋንቋ ቅይጥ መሆን ግምቴን አፈረሰው፡፡ እንደውም በኋላ ጠይቄ እንደተረዳሁት የአሜሪካን ወታደሮች ከከተማው ሰው ጋር የሚገናኙት ለገበያ እና ለመዝናናት ከሚኖሩበት ካንፕ ሲወጡ ነው፡፡ የሚኖሩበት ካምፕ ፓራዳይዝ ሎጅ ይባላል፡፡ እጅጉን የሚጠበቀው ይህ ሎጅ ከአሜሪካኖቹ ውጭ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎችን ነው በአንድ ጊዜ ለማስተናገድ የሚችለው፡፡ ባለቤቶቹ ከአሜሪካ መንግስት ምን ያህል ገቢ ሊያገኙ እንደሚችሉ አስቤ ተደመምኩ፡፡ ባለቤቶቹ የሚታወቁ እነደሆን ጠየቅኩኝ፡፡ ሎጁን ያሠራው በአካባቢው ለብዙ ዐሥርት ዓመታት ነዋሪ የነበረ እያሱ የሚባል ሰው እንደሆነ ነገር ግን ከአሜሪካን ወታደሮች መምጣት ጋር ተያይዞ አንድ ሕዝብ በደንብ የሚያውቃቸው ‹እመቤት› ባለቤትነቱን እንደተጋሩ ጥርጣሬ እንዳለ ተነገረኝ፡፡
አክሱምን ላገኘው ነው…
ከቀኑ ዐሥራ አንድ ሰዓት አካባቢ የመሥሪያ ቤቴ አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ደርሼ በማግስቱ ለምጀምረው ሥራ የሚያስፈልጉኝን ወረቀቶች ወስጄ ወደ ማረፊያዬ አቀናሁኝ፡፡ በማግስቱ ለሥራዬ የማገኛቸውን ሰዎች ሥም ዝርዝር ሳገላብጥ አንድ ሥም ቀልቤን ሳበው – አክሱም ኦናሞ (የአባቱ ስም ለዚህ ጽሑፍ ኢባል የተቀየረ)፡፡ እስካገኘው ድረስ ጓጓሁ፡፡
በማግስቱ በጥዋት ወደ ሥራ አመራሁኝ፡፡ ከአርባ ምንጭ ሙቀት ጋር አድካሚ የሥራ ቀን ነበር፡፡ የሥራ ባልደረባዎቼ ግን ‹እንደውም በደህና ወቅት መጥተህ ነው፤ ትንሽ ገፋ አድርገህ ብትመጣ ኑሮ ምን ልትሆን ነበር? እያሉ ማበረታቻ መሰል ማስፈራሪያ በፈረቃ ሲለግሱኝ ዋሉ፡፡ ወደ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል አካባቢ ተራው ከአክሱም ጋር የምገናኝበት ሆነ፡፡
አክሱም ተወልዶ ያደገው ኮንሶ በምትገኘው ልዩ ስሟ ኮልሜ ተብላ በምትጠራ ስፍራ ነው፡፡ በጊዜው ግዳጅ ላይ የነበሩት አባቱ ከትግራይ ክፍለ ሀገር አክሱም አካባቢ ግዳጃቸውን ጨርሰው ሲመለሱ ተወልዶ የጠበቃቸውን ሦስተኛ ልጃቸውን አክሱም ብለው ስም እንዳወጡለት አጫወተኝ፡፡ ሐሳብ ገባኝ፡፡ ኮንሶ ተወልደው፣ አድገው፣ ወልደው ለብሔራዊ (የኢትዮጵያ) ግዳጅ ትግራይ ለሄዱት አቶ ኦናሞ አክሱም ልጃቸው ነው! ይህን ሳይሰሙ የሞቱት አንድ ሰው ትዝ አሉኝ፡፡ ስለ አክሱም ሃውልት እና ስለ ወላይታ ሕዝብ ምንድን ነበር አሉ የተባለው? …
ዕለቱ በውጥረት ተጠናቀቀ፡፡ በማግስቱ ጠዋት በከተማው ወደሚገኝ አንድ ጥሩ ሆቴል ቁርስ ለመመገብ ጎራ አልኩኝ፡፡ ቁርስ አብራኝ ለመመገብ የቀረበችው እንስሳ ቀልቤን ገፈፈችው፡፡ ከዚያ ቀን በፊት እንደዚች ዓይነት እንስሳ አጋጥሞኝ አያውቅም ነበር፡፡ ስጋ በል ትሁን ዕፅዋት ተመጋቢ ግራ ገብቶኝ ነበር፡፡ በአቅራቢያዬ የነበሩት ሰዎች መረጋጋት ነበር ብዙም እንዳልደነግጥ የረዳኝ፡፡ እንስሳዋ ከሚዳቆ ጋር የምትቀራረብ ሲሆን ሰስ ትባላለች፡፡
በአርባ ምንጭ የነበረኝ ቆይታ ሰዓታት ብቻ ቀርተውታል፡፡ የመጣሁበትን ሥራ በጊዜ አጠናቅቄ ዞር ዞር ማለት ፈለኩኝ፡፡ ወደ ቢሮ አቅንቼ ሥራዬን አጣድፌ ለመጨረስ ሞከርኩኝ፡፡ የመጨረሻዋን ፊርማ አኑሬ ሰዓቴን ተመለከትኩኝ፡፡ ምሳ በልቼ፣ አርባዎቹን ምንጮች አይቼ፣ አዞ እርባታ ደርሼ ትኬቱ ላይ በተመለከተው ጊዜ ለመልስ ጉዞዬ በረራ ለመድረስ ያለኝ ጊዜ አንድ ሰዓት ተኩል ነበር፡፡ የምሄድባቸውን ቦታዎች መቀነስ እንዳለብኝ ወስኜ ባልደረባዎቼን አማከርኩ፡፡ የአዞ እርባታው ከአየር ማረፊያው ብዙም ስለማይርቅ አሱን አይቼ ማለፍ እንደሚሻል የሰጡኝን ሀሳብ ተቀብዬ ከምሳ በኋላ ወደዛው አመራሁ፡፡
አዞ እርባታ በደቡብ ክልል መንግሥት የሚተዳደር ተቋም ሲሆን ዕድሜያቸው አምስት ዓመት የሞላቸው አዞዎችን ቆዳ ገፍፎ ከሀገር ውጪ እየላከ በመሸጥ አዞዎች ለሀገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆኑ መስዕዋት ያደርጋቸዋል፡፡
የአዞ እርባታ ጉብኝቴን ጨርሼ ወደ አርባ ምንጭ አየር ማረፊያ ሄድኩኝ፡፡ አየር ማረፊያው ስደርስ እንድደርስ ከተነገረኝ ሰዓት አንድ ሰዓት አርፍጄ ለረበራው አርባ አምስት ደቂቃ ሲቀረው ነበር፡፡ ወደ አውሮፕላኑ መሳፈር የሚያስችለኝን ወረቀት (boarding pass) ከተቀበልኩ በኋላ አንዱን ጥግ ይዤ የጀመርኩትን ተከታታይ ፊልም መኮምኮም ጀመርኩ፡፡ አውሮፕላኑ መጥቶ ለመሳፈር ስንነሳ የተከታታይ ፊልሙን ሁለት ክፍሎች (እያንዳንዳቸው አርባ ደቂቃ ይፈጃሉ) ጨርሼ ሦስተኛውን አጋምሼ ነበር፡፡ እንደአካሄዴ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 134/5 ከአዲስ አበባ ተነስቶ ጅማ ላይ ተሳፋሪዎች አውርዶ እና ከጅማ ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ ሰዎችን አሳፍሮ ነበር አርባ ምንጭ ከተፍ ያለው፡፡
የመለሰኝ ጢያራ
ወደ አውሮፕላኑ ስንገባ የሚገርም ሙቀት ተቀበለን፡፡ ‹‹ቤታችሁን ሞቅ ሞቅ አድርጋችሁ ነው የጠበቃችሁን›› ስትል አፌዘች ከጀርባዬ በመሳፈር ላይ የነበረች ተሳፋሪ በር ላይ ቆማ እንኳን ደህና መጣችሁ እያለች ለምትቀበለን የበረራ አስተናጋጅ፡፡ በመጀመርያ ያገኘሁትን ክፍት ወንበር ሰው እንደሌለበት አረጋግጬ ተቀመጥኩኝ፡፡
መንቀሳቀስ ከመጀመራችን በፊት ከፊቴ የነበረው ወንበር ላይ የተቀመጠችው ፈረንጅ ሴት ወደኋላዋ ዞራ አጠገቤ የተቀመጠውን ፈረንጅ አንድ ያልተሰማኝን ጥያቄ ጠየቀችው፡፡ ሰውየው እጁን ወደወንበሩ ስር ከሰደደ በኋላ ‹‹No, but we are gone be fine, don’t worry›› አላት፡፡ ደግማ ዞራ ‹‹But, we should complain to the company, or something…›› አለችው በአስቂኝ የጣልያንኛ ቅላፄ፡፡ ሰውየው ወደ ፊቱ አዘንብሎ ድንገት ያስቆጣኝን ንግግር ተናገረ ‹‹This is Ethiopia!›› ይህችን ይወዳልና! ምን ብላ ይሆን የጠየቀችው መጀመርያ? ምን ለማለት ፈልጎ ነው እሱስ? ኧረ ቆይ ልክህን ባልነግርህ ብዬ ወሬ ለመጀመር አጋጣሚ መፈለግ ጀመርኩኝ፡፡
ሙቀቱ ከአቅሜ በላይ ስለሆነብኝ ማቀዝቀዣ ንፋስ ማስገቢያውን እስከመጨረሻው ከፈትኩት ምንም ተጨማሪ ቅዝቃዜ ሊሰማኝ አልቻለም፡፡
ዞር አልኩና ጅማ ይሆን አርባ ምንጭ የተሳፈረው ጠየኩት፡፡
‹‹አርባ ምንጭ›› አለኝ፡፡
‹‹ማቀዝቀዣው ይሥራ አይሥራ እርግጠኛ አይደለህማ፣ ምናልባት የአውሮፕላኑ በሙሉ ኃይሉ መብረር ሲጀምር ይሰራ ይሆናል›› አልኩት፡፡
‹‹ምናልባት›› ሲል መለሰ፡፡ ‹አለቅህም!› አልኩኝ በሆዴ፡፡
‹‹ይቅርታ ይህንን በመጠየቄ፣ ምንድን ነበር ቅድም ሴትየዋ የጠየቀችህ?›› ከፊታችን ወዳለችው ሴትዮ እየጠቆምኩኝ፡፡
‹‹ኦ፣ የጠየቀችኝ ወንበሩ ስር ውሀ ላይ ለመንሳፈፍ የሚረዳ ልብስ እንዳለ ነበር››፡፡ (እያንዳንዱ ወንበር ጀርባ የሕይወት አድን ልብስ ከወንበሩ ስር እንደሚገኝ የሚገልጽ ጽሑፍ አለ)
‹‹አንተ ደግሞ ‹ይሄ ኢትዮጵያ ነው› አልካት፤ ምን ለማመልከት ፈልገህ ነበር?›› ጥያቄዬን ቀጠልኩ ከለስላሳ ፈገግታ ጋር፡፡
‹‹ለማለት የፈለኩት እዚህ ሀገር ነገሮች የሚከሰቱት በዝግታ ነው፡፡ በጣም በዝግታ! አርባ ምንጭ የመጣሁት የቆላ ዝንብን ለማጥፋት የሚረዳ መድኃኒት ለመርጨት ነበር፡፡ አውሮፕላን ማረፊያው ላይ ቆመው ያየሀቸው አራት ትንንሽ አውሮፕላኖች ለዚሁ ሥራ የመጡ ናቸው፡፡ (አውሮፕላኖቹ ለአሜሪካን ወታደሮች የአደጋ ጊዜ ማምለጫ ነበር የመሰሉኝ) የጉምሩክ መሥሪያ ቤት የሚረጨውን መድኃኒት ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባት ከሁለት ሳምንት በላይ ስለፈጀበት አብረውኝ የመጡት 10 ባለሙያዎች ሆቴል ቁጭ ብለው እየተቀለቡ ነው፡፡ ከጤና ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ወደ ኢትዮጵያ እንድንመጣ የሚጋብዝ ደብዳቤ ለመጻፍ 10 ቀን እንደፈጀባቸው ታምናለህ?… እዚህ ሀገር የሚማርክ የመሬት አቀማመጥ፣ እጅግ በጣም እንግዳ አክባሪ እና ተቀባይ ሕዝብ እንዲሁም በሕይወቴ ከቀመስኳቸው ቢራዎች በጣም ምርጥ ከሆኑት የምመድበው ቢራ (ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ) አለ፡፡ ነገር ግን ነገሮች የሚከናወኑበት ፍጥነት እልህ አስጨራሽ ነው፡፡››
የቅድሙ ወኔ የት እንደገባ ጠፋ፡፡ ‹‹በሕዝባችን እና በተፈጥሮ ውበታችን ያስደሰትንህን ያክል በሚቀጥለው ስትመጣ ምናልባት በቢሮክራሲያችን ፍጥነትም ተሻሽለን እናስደስትህ ይሆናል›› አልኩት፡፡
‹‹ያ እንደሚሆን በጣም እጠራጠራለሁ›› አለኝ፡፡ ተስፋ እንኳን እንዲኖረው ለማድረግ ለማግባባት የሚበቃ ወኔ ውስጤ አጣሁ፡፡
ጨዋታ ቀየርን፡፡ ስማችንን ተቀያየርን፡፡ ኤድዊን ይባላል፤ ደቡብ አፍሪካዊ ነው፡፡ ጥሩ ይቀልዳል፡፡ በተለምዶ የሀገር ውስጥ በረራዎች ላይ ሁለት የበረራ አስተናጋጆች እንደሚኖሩ ዛሬ በተለየ ሁኔታ አራት እንደሆኑ እና እርስ በእርስ በተደጋጋሚ አየተገጫጩ እንደሆነ ትዝብቴን አጫወትኩት፡፡ ‹‹አራቱም ቆንጆዎች ስለሆኑ ረብሻቸው ችግር የለውም (we don’t mind their stumbling in to each other)›› ሲል አሾፈ፡፡ በሚገርም ሁኔታ በዛ ሙቀት እንቅልፍ ወሰደው፡፡ በሙቀቱ መንገላታቴን ያስተዋለች አንዷ የበረራ አስተናጋጅ ‹‹የሚጨመር ነገር አለ?›› አለችኝ፡፡ ‹‹ውሃ›› አልኳት – እግዜር ይስጥሽ፡፡
ከሙቀቱ የተገላገልነው አዲስ አበባ አርፈን በሩ ሲከፈት ነበር፡፡ ‹‹Thank God›› አለ እድዊን – የአዲስ አበባን አየር ሲተነፍስ፡፡
በመውረድ ላይ ሳለን ከፊታችን ተቀምጣ የነበረችው ጣልያናዊ ሴት በሩ ላይ ቆማ የምታሰናብተው የበረራ አስተናጋጅን ‹ወንበሩ ላይ ከወንበሩ ስር የሕይወት አድን ልብስ እንዳለ ተጽፏል፤ ልብሱ ግን የለም› ስትል ጠየቀቻት፡፡ አስተናጋጇ ‹በረራው በውሀ ላይ ስላላለፈ…› ጠያቂዋ ሴት መልሷን አላስጨረሰቻትም፤ ጥላት ሄደች፡፡
ከአርባ ምንጭ አየር ማረፊያ ተነስተቶ አንድ ደቂቃ እንኳን ሳይበር ነው አውሮፕላኑ የአባያ ሀይቅን ሰንጥቆ የሚያልፈው፡፡

No comments:

Post a Comment