"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Saturday, 29 December 2012

የሳልሃዲን እርምጃዎች …[ቃለ ምልልስ]


* ሳላ አሁን የት ነው ያለኸው?
በቤልጅየም ዋና ከተማ ብራሰልስ፡፡

* ብራሰልስ ምን ትሠራለህ?
የግብፅ ሊግ መቋረጡን ተከትሎ ክለቤ ዋዲ ደግላ ከእንቅስቃሴ እንዳይርቅ ለዝግጅት ግጥሚያዎች ወደ አውሮፓ አቅንቷል፡፡ የእኔም ጉዞ ከዚያ ጋር በተያያዘ ነው፡፡

* የዋዲ ደግላ እግር ኳስ ክለብ ባለቤት ወይም አስተዳዳሪ ማነው?
የክለቡ ባለቤት ቤልጅየም ሀገር የሚኖር ማጌድ ሳሚ የተባለ ግብፃዊ ባለፀጋ ነው፡፡ ሳሚ በግብፅ ከተሳካላቸው የንግድ ሰዎች አንዱ ሲሆን ዋዲ ደግላ የተባለ ግዙፍ ኩባንያ ካይሮ ውስጥ አለው፡፡ ይህ ኩባንያ በሪል ስቴት፣ በመንገድ ግንባታ፣ በውጪ ንግድ እና ገዘፍ ባሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ የተሰማራ ነው፡፡ እኔ የምጫወትበት ዋዲ ደግላም የሚተዳደረው በዚሁ ኩባንያ ሥር ነው፡፡ ዋዲ ደግላ ልክ እንደ ኢትዮጵያው ሚድሮክ ቁጠረው፤ በሥሩ በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን አቅፎ ይዟል፡፡

* የዋዲ ደግላ እና የቤልጅየሙ ሊርስ አንድነት ምንድነው?
ማጌድ ሳሚ ከአንድ ዓመት በፊት ኪሳራ ውስጥ የተዘፈቀው ሊርስን ዕዳውን ከፍሎ ገዝቶታል፡፡ ስለዚህ እኔ የምጫወትበት ክለብ እና ሊርስ ንብረትነታቸው የአንድ ሰው ነው፡፡ በቅርቡ በቤልጅየም ሶስተኛ ዲቪዚዮን የሚወዳደረው ቱርንሃውት የተባለው ክለብም የግብፃዊው ንብረት ሆኗል፡፡

* ወደ ብራሰልስ ከመጣህ ስንት ጊዜ ሆነህ?
ቡድኑን የተቀላቀልኩት አስር ቀን ዘግይቼ ነው፡፡ የቀለበት ፕሮግራም ሀገር ቤት ስለነበረኝ ቡድኑ ወደ ብራሰልስ ከመንቀሳቀሱ ከቀናት በፊት ወደ አዲስ አበባ ሄድኩኝ፡፡ ከዚያም በታህሣሥ የመጀመሪያ ሳምንት ወደ ቤልጅየም መጣሁ፡፡

* በብራሰልስ ልምምድ ብቻ ነው የምታደርጉት ወይስ ግጥሚያ አግኝታችኋል?
ሁለቱንም፡፡ እኔ ከመጣሁ እንኳን በሁለት ጨዋታዎች ተሰልፌያለሁ፡፡ አንዱን አርባ አምስት ደቂቃ ስጫወት በሌላኛው ለአስራ አምስት ደቂቃ ተሰልፌያለሁ፡፡ የምንገጥመው በቤልጅየም ፕሮ ሊግ (አንደኛ ዲቪዚዮን) የሚገኙ ቡድኖች ሁለተኛ ስብስባቸውን ነው፡፡ በተጨማሪም ከሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲቪዚዮን ቡድኖች ጋር ተጫውተናል፡፡

* ሁኔታው ለምን ያህል ጊዜ ይቀጥላል?
የግብፅ ሊግ እስኪጀመር ነው፡፡ ስንመጣ የአንድ ወር ተኩል ፕሮግራም ነበር የተያዘው፡፡ አሁን ግን ዕቅዱ ተለውጦ ቤልጅየም የምንቀርበት ዕድል እየተመቻቸ ነው፡፡

* የግብፅ ሊግ ዘንድሮ አይጀምርም ማለት ነው?
የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ይጀመራል የሚል ግምት አለ፡፡

* ቤልጅየም መቅረት ሲባል እንዴት ነው?
ሊርስ እና የሶስተኛ ዲቪዚዮኑ ቱርናውት የሚተዳደሩት በዋዲ ደግላው ባለቤት ነው፡፡ በዋዲ ደግላ አሰልጣኝ ጥቆማ ስድስት ልጆች ወደ ሊርስ እንዲዛወሩ ተደርጓል፡፡ የቀሩት ደግሞ ለቱርንሃውት እንዲጫወቱ የሥራ ፈቃድ እየተመቻቸላቸው ነው፡፡ (በነገራችን ላይ የሊርስ አሰልጣኝ የቀድሞ የግብፅ ዕውቅ ተጫዋች ሃኒ ራምዚ ነው)

* አንተ ከስድስቱ ውስጥ የለህም?
የለሁበትም፡፡ ሲጀመር እዚህ የመጣነው ለአንድ ወር ተኩል ነበር፡፡ እኔ ደግሞ በብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት እና በአፍሪካ ዋንጫ የተነሳ ቢያንስ ለአንድ ወር ከቡድኑ እርቃለሁ፡፡ በዚህም የተነሳ ከስድስቱ ውስጥ እንዳላካተተኝ አሰልጣኙ ነግሮኛል፡፡ እኔ ለአፍሪካ ዋንጫ ስለምሄድ አንድ አጥቂ እንደሚፈልግም አስታውቆኛል፡፡

* ምክንያቱ ይህ ብቻ ነው?
ዋናው ምክንያት ይህ ቢሆንም በምሰለፍበት ቦታ ከአሰልጣኙ ጋር አልተግባባንም፡፡ እርሱ ተደራቢ አጥቂ ሆኜ እንድጫወት ይፈልጋል፡፡ እኔ ደግሞ በዚያ ቦታ ጥሩ አይደለሁም፡፡ ወደ መሐል ተስቤ ስጫወት ጎል የማግባት ብቃቴ ይቀንሳል፡፡ ለስልጠናው ዓለም አዲስ እንደመሆኑ ልምዱም አናሳ ነው፡፡ በዚያ ላይ ሲያሰራ ንግግሩ ይበዛል፡፡ በአጠቃላይ የአሰልጣኝ ለውጥ ከተደረገ በኋላ ዋዲ ደግላ አልተመቸኝም፡፡ ከቀድሞው አሰልጣኝ ጋር ጥሩ ተግባብተን ነበር፡፡ ቤልጅየማዊው ተሰናብቶ ግብፃዊው ከመጣ በኋላ ግን ነገሮች እንደበፊቱ አልሆኑም፡፡

* መጪው ጊዜ ምን ሊሆን ይችላል?
ክለቡ ለሶስተኛ ዲቪዚዮኑ ቱርንሃውት እንድጫወት ጠይቆኛል፡፡ የእኔ ፍላጎት ደግሞ ሊርስ ነው፡፡ በዚህ መሐል የአፍሪካ ዋንጫ አለ፡፡ መጪውን ጊዜ ከአፍሪካ ዋንጫ በኋላ አብረን ብናይ አይሻልም?

* እስከዚያ ክለቡ ይታገስሃል?
ገና የአንድ ዓመት ተኩል ውል ይቀረኛል፡፡ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሳልሄድ ምላሼን እንዳሳውቃቸው ነግረውኛል፡፡ እኔም ሶስተኛ ዲቪዚዮን ወርጄ እንደማልጫወት አሳውቄያቸዋለሁ፡፡

* ሌሎች ክለቦች የዝውውር ጥያቄ አላቀረቡልህም?
የሱዳን ክለቦች ገፍተው መጥተዋል፡፡ በተለይ ሜሪክ እና አል አህሊ ሻንዲ አሁንም ድረስ እየጠየቁኝ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ከአፍሪካ ዋንጫ መልስ የምወስነው ይሆናል፡፡

* የእግርህ ጤንነት አንዴት ነው?
በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡

* ጉልበትህን በደንብ ተሸሎሃል?
አዎን፡፡

* አዲስ አበባ ላይ ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ስትጫወት የተጎዳኸውሳ?
እርሱ በግራ እግሬ እና በመቀመጫዬ መጋጠሚያ ላይ የደረሰብኝ የጡንቻ መሳሳብ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት እዚያ አካባቢ የሚሰማኝ ነገር የለም፡፡

* በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከጊኒ ጋር ኮናክሪ ላይ የተጎዳኸው ጉልበትህን ነበር?
የቀኝ ጉልበቴ ላይ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳት በእግር ኳስ ዘመኔ አይቼ አላውቅም፡፡ ሜዳው ጭቃ ነበር፡፡ ከኋላ ሲጠልፉኝ በጉልበቴ ጭቃው ላይ ተሰካሁኝ፡፡ የተጎዳው ከኋላ የጉልበቴን ሎሚ አቅፎ የሚይዘው አንደኛው ጅማት (ሊጋሜንት) ነው፡፡ ከጉልበት ጀርባ ሁለት ጅማቶች አሉ፡፡ ጭቃው ላይ በሙሉ ኃይል ስወድቅ አንዱ ጅማት ተበጠሰ፡፡ እርሱን ለማስታመም ስድስት ወር ፈጅቶብኛል፡፡

* ጉዳቱ የዋዲ ደግላ ቆይታህ ላይ ተፅዕኖ አላሰረፍብህም?
ለዋዲ ደግላ ፈርሜ አዲስ አበባን እንደለቀኩኝ ካይሮ በሚገኘው የክለቡ ማዕከል ቀለል ያሉ ልምምዶችን እያደረኩ ነበር፡፡ ከዚያም ወደ ጨዋታ ሳልገባ ጊኒን ለመግጠም ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፤ ጉልበቴንም ተጎዳሁ፡፡ ጉዳቴን አስታምሜ ስመለስ የግብፅ ሊግ ተቋረጠ፡፡ ይህን ተከትሎ ብቃቴን በግብፅ ሜዳዎች ለማሳየት የነበረኝ ህልም ተጨናግፏል፡፡ ሆኖም በጉዳት ወደ ካይሮ ስመለስ ክለቡ ልዩ እንክብካቤ አድርጎልኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡

* ለምን ያህል ጊዜ ነበር ከሜዳ የራቅከው?
ስድስት ወር፡፡ ከሶስት ወር በኋላ አገግሜ ወደ ሜዳ ስመለስ እንደገና ተጎዳሁ፡፡ ጉዳቱ የደረሰብኝ ሳይሻለኝ ቶሎ ወደ ጨዋታ በመግባቴ ነበር፡፡ ድጋሚ ከተጎዳሁ በኋላ ለሶስት ወራት ከሜዳ ርቄያለሁ፡፡

* ጉልበትህ ላይ ቀዶ ጥገና አድርገሃል፡፡ ወጪውን ማነው የሸፈነው?
ለሕክምና ከኪሴ ሰባት ሺህ ዶላር አውጥቻለሁ፡፡ ቀሪውን የቻለው ክለቡ ነበር፡፡ የክለቡ ድርሻ በዛ ይላል፡፡

* በአፍሪካ ዋንጫ አዲስ የዝውውር ጥያቄ ቢመጣስ?
ዋዲ ደግላ እና ፈላጊው ክለብ ይነጋገሩና የእኔ ፍላጎት ተጠብቆ ዝውውሩ ይፈፀማል፡፡ የእዚህ ሀገር ዝውውር የተደበቀ ነገር የለውም፡፡ ሁሉም ነገር ፊት ለፊት በሚደረግ ድርድር የሚፈፀም ነው፡፡ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ለዋዲ ደግላ ስፈርም በውላችን ላይ የተጠቀሰ ነገር አለ፤ የተሻለ ክፍያ የሚሰጠኝ ክለብ ከመጣ ሊለቁኝ፡፡ እንደውም ለካይሮው ክለብ በዋናነት የፈረምኩት ወደ አውሮፓ መሸጋገሪያ ይሆነኛል በሚል ነው፡፡ ይህም ጉዳይ በውላችን ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡

* ከቡድኑ አባላት ጋር በምን ትግባባለህ?
ዓረቢኛ እሞክራለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment