"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Thursday, 24 January 2013

ልማታዊው ኪስ አውላቂ (ክንፉ አሰፋ)

የ ‘ህዳሴው ቦንድ’ ግዢ ግርግር ሞቅ ብሎ በነበረበት ሰሞን ይነገር የነበረ አነድ ቀልድ አለ። የ‘ማረሚያ’ ቤት ፖሊሶች እና ታጋዮች 500 ብር በሰረቀ ሌባ ላይ ውይይት ያደርሉ። ተከሳሹ ብሩን ያላግባብ ይስረቅ እንጂ በገንዘቡ የህዳሴውን ቦንድ መግዛቱ ነው ጉዳዩን ለውይይት የዳረገው። ይህ ሌባ መታሰር የለበትም የሚሉት ታጋዮች፡ ለፖሊሶቹ ያቀረቡት መከራከሪያ ነጥብ ልማታዊ ሃሳብ ነበር። እንዲህ ነበር ያሉት፡ ‘ይህ ልማታዊ ኪስ አውላቂ ነው። እንዲያውም እንደዚህ አይነቶቹን ሌቦች የበለጠ እንዲሰሩ ማበረታታት ነው ያለብን።…’ ሁሉም በዚህ ሃሳብ ተስማሙና ሌባውን በያዘው ልማታዊ ተግባር የበለጠ እንዲሰራበት መክረው ለቀቁት።
ይህ እነግዲህ ቀልድ ነው። ቀልድ ደግሞ በመጠኑም ቢሆን የእውነታ ነጸብራቅ እነጂ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ክስተት አይደለም። ‘ልማታዊ’ የሚለው ቃል ትርጉሙ ተዛብቶ ምን ያህል እየተቀለደበት መሆኑን ከዚህ ቀልድ ግንዛቤ እንወስዳለን። በዚህ ላይ ወደሗላ እመለስበታለሁ።
ቀልዱን በቀልድ እንለፈውና አንድ ምሽት በኢ.ቲ.ቪ. ያየሁትን እውነታ ላውጋችሁ። ኢ.ቲ.ቪ. በሚያዘጋጀው የትምህርት ቤቶች ጥያቄና መልስ ውድድር ላይ ‘ቦንድ ማለት ምን ማለት ነው?’ የሚል የ500 ብር ጥያቄ ቀርቦ ነበር። ከተወዳዳሪዎቹ አንዱ መልስ ሰጠ። እነዲህ ሲል፣ “ቦንድ ማለት፡ መንግስት በህዝብ እጅ ያለውን ጥሬ ገንዘብ ለአንድ አላማ ወደ ባንክ እንዲገባ ለማድረግ የሚጠቀመበት ዘዴ ነው።”
“ጥያቄው በትክክል ተመልሷል!” የሚል መልስ ነበር ህዘብ ከጠያቂ ጋዜጠኛው ይጠብቅ የነበረው። ጠያቂው ግን ተወዳዳሪው ትክክል እንዳልመለሰ ተናግሮ፡ ጥያቄውን ተመልካቾች እንዲመልሱለት ጋበዘ። አነዱ ‘ልማታዊ’ ተመልካች ከመሃል ተነስቶ “ትክክል” የተባለለትን መልስ ሰጠ። መልሱ ይህ ነበር፣ “ቦንድ ማለት ወለዱ ከግብር ነጻ የሆነ የቁጠባ ዘዴ ነው። ”
በዚህ ልማታዊ ጋዜጠኛ የተሳሳተ የቦንድ ትርጉም ተወዳዳሪ ተማሪው ብቻ ሳይሆን፤ የቴሌቭዥኑ ታዳሚዎችና ተመልካቾችም በሙሉ ቀልጠዋል። ይህ ጥያቄ በትምህርት ቤት ፈተና ላይ ቢመጣ ተመሳሳይ ‘ልማታዊ’ መልስ ያልሰጡ ተማሪዎች አያልፉም ማለት ነው።
በአጭር አነጋገር ቦንድ ማለት፤ ህዝቡ እንዲቆጥብ ታስቦ ሳይሆን መንግስት የገንዘብ እጥረት ሲኖርበት ከህዘብ ላይ በብድር መልክ የሚሰበስበው ገንዘብ ማለት ነው። ቦንድ መሸጥ አዲስ ነገርም አይደለም። የምእራቡ አለም መንግስታትም በአንደኛው እና በሁለተኛው የአለም ጦርነቶች ወቅት የገንዘብ እጥረታቸውን ለመሸፈን ለሕዝብ ቦንድ ይሸጡ ነበር። ዩናይትድ ስቴትስ ለሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ገንዘብ ስላስፈለገ፤ ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት የተጠቀሙት ዘዴ ‘የነጻነት ቦንድ’ ያሉትን ኩፖን በመሸጥ ነበር። ጀርመን፣ እንግሊዝና ካናዳም በተሳካለት የጦር ቦንድ ሽያጭ የሚጠቀሱ ሃገሮች ናቸው።
ወደ ዋናው ነጥብ ስንገባ ልማታዊ መንግስት የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ የመነጨው በ20ኛው ክፍለዘመን መገባደጃ አካባቢ ከነበሩ የምስራቅ ኤሽያ ሃገሮች ነው። እነዚህ በወቅቱ እጀግ ደካማ የሚባሉ የኤሽያ ሀገሮች፡ በመንግስት የሚመራ የማክሮ ኢኮኖሚ እቀድ በማውጣት የሃገራቸውን ኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ስልጣን አጥብቀው በመያዝ ወደ ምጣኔ ሃብት እድገት ያመሩ ናቸው።
ልማታዊ ነን የሚሉ እነዚህ መንግስታት የብዙሃን ፓረቲ ዲሞክራሲን፣ የፕሬስ ነጻነትንና የመሳሰሉ መብቶቸን በመጠኑም ቢሆን ያፈኑ ቢሆኑም ‘ልማት ከሰብአዊ መብት ይቀድማል!’ ከሚሉት ከኛዎቹ ገዚዎች ፍጹም የተለዩ ናቸው። ልማታዊ መንግስታት ከህዝባቸው ጋር ሆድና ጀረባ በመሆን ከህዝባቸው ጋር ጦርነት ሲገጥሙ አላየንም። እነዚህ ሃገሮች ትኩረታቸውን በሙሉ በኢኮኖሚ እድገት ላይ በማድረግ ህዝባቸው በምግብ ራሱን እንዲችል ከማድርግ አልፈው የአብላጫው ህዝብ የኑሮ ሁኔታ በእጀጉ እንዲሻሻል ረድተዋል።
ዛሬ የደቡብ ምስራቅ እሺያ ሀገሮች እና የቻይና ዜጎች የፖለቲካ ተሳትፏቸው እጅግ ዝቅተኛ ይሁን እነጂ የኑሮ ደረጃቸው በእጅጉ ተሻሽሎ እናያለን። በአንጻሩ በልማታዊው የኢህአዴግ ስርአት በግልጽ የማይታይ የሁለት አሃዝ እድገት መጠን ከማውራት ያላለፈ እድግት ባሻገር የህዝቡ የኑሮ ደረጃ ሲብስ እንጂ ሲሻሻል አይታይም። በልማታዊ መንግስት ስም 80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዘብ ከነጻነቱም፣ ከኑሮውም ሳይሆን አሁንም በባሰ የኑሮ ጉስቁልና ውስጥ ይገኛል።
በቅርብ ከኢትዮጵያ የመጣ አንድ ሰው፡ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ከአንድ የእግር ኳስ ስታዲየም ጋር በማስመሰል ይገልጸዋል። በአንድ የእግር ኳስ ስታዲየም ውስጥ ያሉ ሰዎች በሶስት ምድቦች ይከፈላሉ፤ ተጫዋቾች፣ አጫዋቾች እና ተመልካቾች። የኢትዮጵያም ህዝብ እንደዚሁ በሶስት ምድብ ይከፈላል። ባለስልጣናቱ አጫዋቾች፣ አጫፋሪዎቹ (ለባለስልጣናቱ አየር ባየር ቢዝነስ የሚሰሩት) ተጫዋቾች – ሲሆኑ ህዝቡ ደግሞ የዚህ ጨዋታ ተመልካች ሆኗል።
ሕዝቡ የሃገር ሃብት ነው። ህዝብን ሳያሳትፉ ስለ እድገት ማውራት ከቶውንም የሚቻል አይሆንም። በተለይ ደግሞ ዲያስፖራውን። የምስራቅ ኤሸያ እድገት ሚስጥር ዲያስፖራው መጠነ ሰፊ ገንዘብ እና እውቀትቱን ይዞ በሃገሩ መስራት መቻሉ ነበር።
ህወሃቶች እንደሚሉት ‘ቶክሲክ’ (መርዘኛ) ዲያስፖራ እያሉ የሃገር ሀብት የሆነውን የዲያስፖራ ሃይል ቢሳደቡ ኖሮ እስያውያን እዚህ ደረጃ ባልደረሱ ነበር። በተማረ የሰው ሃይል፣ በቴክኖሎጂ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ ሆኖ ዲያስፖራውን በጅምላ ጠላት ማድረግ ከእብደት ውጭ ሌላ ትርጉም አይሰጠውም። የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የሰራው ወንጀል ቢኖር ‘ሰብአዊ መብት በሃገሪቱ ይከበር!’ ብሎ መጮሁ ብቻ ነው።
በአንድ ሃገር ኢኮኖሚ ላይ የዲያስፖራውን ሚና ለማሳየት ምሳሌ ሊሆነን የሚችለው የሲንጋፖር የእድገት ታሪክ ነው። ሲንጋፖር ከታላቋ ብሪታንያ ቅኝ ግዛት ነጻ በወጣች ማግስት ህዝቧ በድህነት ውስጥ ነበር። ሲንጋፖር አንዳች የተፈጥሮ ሃብት የሌላት ፍጹም ድሃ የሆነች ደሴት ነበረች። ከዚህ ድህነቷ ለመላቀቅ የነበራት አማራጭ የተማረ የሰው ሃይሏን መጠቀም ብቻ ነበር። አንድ የሲነጋፖር ዜጋ እነዲህ ብሎ ነበር ያጫወተኝ።
‘ሲንጋፖር በተፈጥሮ ሃብት ያልታደለች የትናንሸ ደሴቶች ክምችት ነች። ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ እንደወጣች የመጠጥ ውሃ እንኳን አልነበራትም። በወቅቱ የተረፈን ጭንቅላታችን ብቻ ነበር – የተማረ የዲያስፖራ ሃይል። ከባዶ በመነሳት ሲንጋፖር አሁን ያለችበት ደረጃ እንድትደርስ ያደረጉት እውቅት እና ቴክኖሎጂ ይዘው የመጡ የዲያስፖራ ምሁራን ናቸው።’
‘የሲነጋፖር ምሁራን ከጎረቤት ሃገር ከማሌዢያ የሚፈሰውን ቆሻሻ ውሃ በቱቦ አማካይነት ወደ ሃገሪቱ እንዲገባ ካደረጉ በሗላ፡ ውሃውን እያጣሩ ለማሌዥያ መልሰው መሸጥ ጀመሩ።…’
የእውቀት ኢኮኖሚን የያዘ የዲያስፖራ ሃይልዋን ያልናቀችው ሲንጋፖር ዛሬ የኢንዱስተሪ ሃገር ናት። አንባገነንነቱ እና ሙስናው እነደተጠበቀ ሆኖ፡ ይህቺ ደሴት የበርካታ ሀገሮች የእድገት ምሳሌ (ሞዴል) ለመሆንም በቅታለች።
የኤርትራው ኢሳያስ አፈወረቂ እንኳን፤ በትረ ስልጣናቸውን የጨበጡ ሰሞን ‘ኤርትራን የአፍሪካ ሲንጋፖር እናደርጋታለን።’ ብለው ነበር። ይልቁንም ከ21 አመታት በሗላ ኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራን ሲን ጋፖር ሳይሆን ‘ሲንግል ኤንድ ፑር’ አደረጓት እያሉ ተቺዎች ይቀልዱባቸዋል። የኢትዮጵያም የእድገት ማነቆ ምስጢሩ በስብአዊ መብት አፈናው ሳቢያ ለተማረ የሰው ሃይል እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ቦታ ካለመስጠቱ ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ልማታዊ መንግስት ነን ይበሉ እነጂ፤ የልማታዊነት ትርጉሙ እንኳን የገባቸው አይመስልም። አሁን የተያዘው የኮብል ሰቶን ልማትን እንመልከት። የኮበልስቶን ስራን ሊሰራ የሚችል ያልሰለጠነ የሰው ሃይል በገፍ ባለበት ሃገር፤ በባችለር እና በማስተርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቅ ዜጋ ሁሉ ድንጋይ መፍለጥ፣ መጥረብ እና መዘርጋት እንዲሰራ መደረጉ ለብዙዎች እንግዳ ነገር ነው። የተማረ እና የሰለጠነ የሰው ሃይልን በጉልበት ስራ የሚያሰማራ ልማታዊ መንግስት በኢትዮጵያ ብቻ ነው የታየው። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝም በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው በባችለር እና በማስተርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ለሚመረቁ ተማሪዎች የኮብል ሰቶን ስራ አዋጭ ስራ መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል። አዋጪ ስራ መሆን አንድ ነገር ነው። የሃገር እድገት ደግሞ ሌላ። የሚያሳዝነው አማራጭ ያጡ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የዚህ የተሳሳተ ልማታዊ አስተሳሰብ ሰለባ መሆናቸው ብቻ ነው።
የህንጻ እን የከተማ መንገድ ግንባታ የከተማን ውበት ሊያሳምር ይችል ይሆናል። በህንጻ ግንባታ ከተማ ልትቀየር ትችልም ይሆናል። ይህ ግን ከሃገር እድገትና ከዜጎች የኑሮ መለወጥ ጋር ፈጽሞ ሊገናኝ አይችልም። ምሁራኑ ድንጋይ ሲፈልጡ፣ ሲጠርቡ እና ሲያነጥፉ፡ የነሱን የሙያ ቦታ ያልተማሩ ካድሬዎች እነዲይዙት ማድረግ። ሃገር በዚህ አይነት ሂደት ታድጋለች የሚል የልማታዊ መንግስት ፍልስፍና የለም። ይህ እንዲያውም በልማት ስም የሚሰራ መንግስታዊ ወንጀል ነው። ኪስ አውልቆ ቦንድ ከመግዛት የማይተናነስ ወነጀል።

No comments:

Post a Comment