"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Monday, 11 February 2013

አጭር ልብ ወለድ

የማይቀርበት ስራ እንዳለበት ሰው በጠዋት ተነስታ ከቤትዋ ወጣች፡፡

ፀሃይ ስትወጣ፡ ወፎች ሲዘፍኑ፡ አዲስ አበባ ከእንቅልፏ ስትነቃ ለመጨረሻ ጊዜ የምታይበት ቀን መሆኑን አስባ አልተከፋችም፡፡ ፀሃይ ምን አባትዋ! መሰረት የለችም ብላ ነገ እምቢ አሻፈረኝ አልወጣም አትል፡፡ አለመውጣት ቀርቶ አንድ ሰአት እንኳን አትዘገይም፡፡ ወፎችም እንዲህ የሚያባባ ዘፈን ሲዘፍኑ አይመስሉም እንጂ ገና በማለዳ ከዚህ አለም መሰረዝዋን ሲሰሙ በነጋታው ዘፈናቸውን በሙሾ አይተኩም፡፡ አዲስ አበባም ገደል ትግባ! “መሰረት ከሞተች አበባዬ ረግፏልና አዲስ አበባ አትበሉኝ” አትል፡፡ ሃዘን አያጠወልጋት፡፡ ለነገሩ ሕይወትዋን ሙሉ አዲስ አበባ እሾህ እንጂ አበባ ሆናላት አታውቅም፡፡

“ሕይወት አጭር ናት፡፡ ደስተኛ ሁኚ፡፡ “ይላት ነበር የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ቦይፍሬንዷ፡፡

እሱ ምናለበት! ገንዘብ አይቸግረው፡፡ ደስታ አይቸግረው፡፡ ደስታ ተርፎት “ደስተኛ ሁኑ” እያለ ለከፋው ሁሉ ያከፋፍል ነበር፡፡ እንደሱ ለተደሰተ ሕይወት አጭር ነት፡፡ እንደርሰዋ ከኑሮ ለተኳረፈ፡ አንደርስዋ ከጊዜ ረጅምና ማይበርድ ጠብ ውስጥ ለገባ፡እንደርስዋ ኑሮ የጉልበት ስራ ብቻ ለሆነበት፡ እንደርስዋ ሕይወት ረጅም ቅዠት ለሆነበት ሕይወት ረጅም ናት፡፡ ኑሮ ዘልዛላ ነው፡፡

ቦይፍሬንዷን ሰምታ ደስተኛ ሆና ሕይወት አጭር ናት ከሚሉት ለመመደብ ብዙ ወጣች፡ ብዙ ወረደች፡ ብዙ ተራመደች፡ ብዙ ሮጠች፡፡ ደስታ ስትደርስበት ከርስዋ እንደሚሸሽ ሁሉ የማትነካው፡ የማትደርስበት ህልም ሲሆንባት እንደነገሩ፡ እንደዋዛ በእርሳስ የተፃፈውን ይህን ቀለም አልባ ሕይወትዋ በሞት ላጲስ ልታጠፋው ቆረጠች፡፡

ዛሬ ሕይወቷን በጉልበት የምትቋጭበት ቀን ነው፡፡

እውነቱን ለመናገር ነገሩን ለሳምንታትና ለወራት ስትብሰለስለው አልቆየችም፡፡ እስከ ትላንት ድረስ እንደነገሩ፡ እንደሚሆን እንደሚሆን አድርጌ እኖራለሁ ብላ ወደር በሌለው የግዴለሽነት መንፈስ መኖርን ተለማምዳው ነበር፡፡
ወደር በሌለው የግዴለሽነት መንፈስ ስትኖር ሲርባት ያኘችውን ከመብላት፡ ለመብላት ስትል ያገኘችውን ስራ ከመስራት፡ እንቅልፏ ሲጨቀጭቃት ከመተኛት ያለፈ ታላቅ የሕይወት ግብ አልነበራትም፡፡ መብላት፡ መስራት፡ መተኛት፡ የቀን ቀን አዙሪትዋ ይሄ ነበር፡፡

ትላንትና ግን በድንገት አዙሪቱን የረበሸ ነገር ተከሰተ፡፡

ለሳምንታት ራሷን ሲያማት ገርፏት የማይታክተው የኑሮ ጅራፍ ያመጣው ህመም ውጤት መስሏት ችላ ብላው ነበር፡፡
ለሳምንታት ወደላይ ሲላት የሚያቅራት ኑሮዋ በአፏ ለመውጣት እየተናነቃት መስሏት ከቁምነገር ሳትፅፈው ሰነበተች፡፡
ለሳምንታት በተለየ ሁኔታ አሁንም አሁንም ሲርባት “የምበላው ሳጣ…” ይሉት ተረት በዚህ እከካም እድሏ ምክንያት ልጅ እንኳን ሳይኖራት ደርሶባት መስሏት በለመደችው ግዴለሽነትና ውሃ በመጠጣት ታባርረው ነበር፡፡

ያቺ የማትወዳት የወር እንግዳዋ ለሁለት ወራት ሳትጠይቃት መክረሟ የተከሰተላት ዘግይቶ ነበር፡፡

ሲከሰትላት…
ላብ የማያውቃትን ክፉኛ አላባት፡፡
ትንፋሽ አነሳት፡፡
ለእንባ እንግዳ ያልሆኑት አይኖችዋ በታማኝነት አዳዲስ እምባ ዘረገፉ፡፡

“እኔ በግዴለሽነት መኖር እችላለሁ፡፡ ልጄ ግን አይችልም” ብላ ወሰነች፡፡

ያቺ የችግር ዘመድዋና ደባልዋ ጤና ጣቢያ ሂጂና አረጋግጪ አለቻት፡፡
ሄደች፡፡
ቀድማ ብታውቀውም ልጅ እየሰራች እንደሆነ ሃኪሙ ነገራት፡፡
እንደገና አላባት፡፡
ትንፋሽ አነሳት፡፡

ለአንባ እንግዳ ያልሆኑ አይኖችዋ የዘረገፉት ትኩስና ብዙ እምባዎች ወደ ማዲያታም ጉንጭዋ፡ አጭር አገጭዋ፡ ከዚያም ደግሞ ዘለው ወደ ጭኖችዋ ተከሰከሱ፡፡

“አትፈልጊውም?” ሃኪሙ ጠየቃት፡፡
“አትፈልጊውም?” ብሎ ጥያቄ ምንድነው…?
ልጅ እንዴት እንደሚገዛ እቃ አትፈልጊውም ይባላል…?ልጅ እንዴት አይፈለግም?
“እፈልገዋለሁ፡፡” እምባዋ አልቆመም፡፡
“ደስ ብሎሽ ነው ምታለቅሺው ታዲያ?”

በደስታ ይለቀሳል እንዴ…?ለለቅሶ የሚያደርስ ደስታ ምን አይነት ነው? አታውቀውም፡፡

“አልችልም፡፡ እኔ ልጅ ማሳደግ አልችልም፡፡ “ንፍጧን በሹረብዋ እጀታ ጫፍ እየጠረገች ተናገረች፡፡
“አሁን እፈልገዋለሁ አላልሽኝም እንዴ?”
“እፈልገዋለሁ ግን አልችልም፡፡ “
ሃኪሙ በአልገባኝም አያት፡፡

ሰው እንዴት ሃኪምን ያህል ነገር ሆኖ መፈለግን ከመቻል ያምታታል? ብላ አሰበች፡፡ ምናልባትም ሕይወት ካጠረባቸው ደስተኛ ሰዎች ይሆን ይሆናል፡፡

“አባቱ አብሮሽ ነው…?”
“አባቱ ውጪ ሃገር ነው፡፡ አይመለስም፡፡”
“ብታገኚው አይረዳሽም…?”
ሃኪሙ የሆነ ነገር እየሞነጫጨረ ጠየቃት፡፡
እንደስዋ ያለ ወደር በሌለው ግዴለሽነት የሚኖር ሰው ውጪ የሄደ የቀድሞ ቦይፍሬንድ ፍለጋ አይዞርም፡፡ ልክ አይመጣም፡፡

ብድግ አለችና
“አልችልም አልኩህ ዶክተር!”
“እሺ…እንደዛ ከሆነ እንግዲህ አማራጮች አሉ፡፡”
ብዙ ብሎ፡ ብዙ ዞሮ አንድ ቦታ ደረሰ፡፡ ልጅሽን ግደይው አላት፡፡

አሰበች፡፡

ለኑሮ ጉጉት የላትም፡፡ በራስዋ ላይ ሞት ማወጅን እስከዛሬ አስባው ባታውቅም በምክንያት የመጣ ሞት ላይ የከረረ ቅራኔ የላትም፡፡
ከጤና ጣቢያው ከወጣች በኃላ በየደቂቃው ውስጧ በማደግ ላይ ያለ ልጅዋን ከመግደል ራስዋን መግደሉ በአንፃራዊ ሁኔታ ሃጥያቱ ዝቅ ያለ መሰላት፡፡

ራስዋን ትገድላለች፡፡
እሷ ትሞታለች፡፡
እሷ በመሞትዋ ልጅዋ ይሞታል፡፡
እሷ ራሷን ገደለች እንጂ ልጅዋን አልገደለችም፡፡
የልጅዋ ሞት የእሷ ሞት አሳዛኝ ውጤት እንጂ ግድያ አይሆንም፡፡
ወሰነች፡፡


ልጅ ሆና ስትሰማ “እገሌ እኮ በአስር ሳንቲም ገመድ ተንጠልጥሎ ሞተ!” ይባል ነበር፡፡እንደሌላው ነገር ራስን ማጥፋትም ተወዷል፡፡ ከዛሬ ጋር ያለውን የጊዜ ልዩነት አስልታ “መቼም ቢጨምር ቢጨምር ከ5 ብር አይበልጥም፡፡ “አለችና ከፍራሿ ስር ያስቀመጠችውን ከታጣፊ አልጋዋ ውጪ በስሟ ያለ ብቸኛ ገንዘብዋን አወጣች፡፡ አስር ብሯን በግራ እዿ አፍናና ጨምድዳ ይዛ ወጣች፡፡
“ገመዱን ገዝቼ የሚተርፈኝን አምሰት ብር አምላክ ይቅር እንዲለኝ ለሚካኤል እሰጠዋለሁ” ብላ አሰበች፡፡ በአምስት ብር ገመድ የተሰራ ሓጢያትን የአምስት ብር ስጦታ ይፈታዋል ብላ፡፡

አብዲ ሱቅ ደርሳ ብታይ ማንም አልነበረም፡፡ በመስኮቱ አንገትዋን ገባ አድርጋ “አብዲ!” ብላ ተጣራች፡፡ አብዲ ሳይሆን አንድ አይታው የማታውቅ ትንሽ ልጅ ብቅ አለ፡፡
ቅር አላት፡፡

“አብዲ የለም እንዴ…?”
“የለም፡፡” ልጁ ፈጠን ብሎ መለሰ፡፡
ቢኖር ደስ ይላት ነበር፡፡ ከመሰናበትዋ በፊት ሁሌም እንደ ሙሉ ሰው በሙሉ አይኑ የሚያያትን፡ ሲቸግራት የሚያበድራትን፡ ሲከፋት የሚያስቃትን ፍልቅልቁን አብዲ ብታገኘው ደስ ይላት ነበር፡፡
“ገመድ አለ?” ከማቅለሽለሽ ስሜት ጋር ግብግብ ገጥማ ጠየቀችው፡፡

አውጥቶ ሰጣት፡፡
“ስንት ነው?”
“አስራ ሁለት ብር” አዲሱ ልጅ ከረሜላ ከገዛው ትንሽ ልጅ ብር እየተቀበለ መለሰ፡፡
“አስራ ሁለት…?”
ወደ ላይ አላት፡፡
ትንፋሽ አነሳት፡፡
እምባዋን ግን ገታችው፡፡

“አዎ አስራ ሁለት” ልጁ ከረሜላ ሲያወጣ መሬት የበተናቸው ማስቲካዎች ቦታቸው እየመለሰ መለሰላት፡፡
“እኔ…አስር ብር ነው የያዝኩት፡፡ አስር ብር ሽጥልኝ?” ተለማመነችው፡፡
“ዋጋው አስራ ሁለት ነው አልኩሽ እኮ!”

አስር ብር ስትለው፡ ዋጋው አስራ ሁለት ነው አልኩሽ ሲላት፡ አሰር ብር እንካ ስትለው ሁለት ብር ጨምሪ ሲላት አብዲ ብዙ እቃ ተሸክሞ ወደ ሱቁ ደረሰ፡፡
ደስ አላት፡፡

“አብዲ! “
“መሲዬ! “እቃዎቹን መሬት አስቀምጦ ጨበጣት፡፡
“ባክህ ይሄ ልጅ ይህን ገመድ አልሸጥልሽ አለኝ”
“ምነው አንተ…?!”ልጁ ላይ አፍጥጦ ጮኸ፡፡
“ለመሲ 10 ብር ነው” ብሎ ገመዱን ሰጣትና አስር ብሩን ተቀብሏት ለልጁ ሰጠ፡፡

ይህ አብዲ የሚሰራላት የመጀመሪያው ሳይሆን የመጨረሻ ውለታ ነበር፡፡ የገታችው እምባዋ ካልወጣሁ እያለ ሲታገላትና ስትመለሰው በአፍንጫዋ አድርጎ ወደ አፍዋ እየመጣ ጨው ጨው አላት፡፡
አብዲን ነገ እንደምታገኘው ሁሉ፡ ወግ በሌለው ሁኔታ ተሰናብታው ወደ ቤትዋ ተራመደች፡፡

ቤትዋ ስትገባ ደባልዋ የሰራችውን እህል ቅጠል የማይል ሽሮ እየተናነቃት በልታ ተኝታ እንደማታውቅ ተኝታ አደረች፡፡

ጠዋት…

የካ ሚካኤል ቤተክርስቲያንን ስትሳለም ለምትሰራው ሃጢያት ማሰረያ የምትሰጠው ገንዘብ ስላልተረፋት ግንቡን ተደግፋ ስቅስቅ ብላ አነባች፡፡
በቅቷት ሳይሆን መርፈዱ አሳስቧት ወደ ተራራው የሚወስደውን ቀጭን መንገድ ቀጠሮ እንደረፈደበት ሰው ተጣድፋ ወጣች፡፡
ዛፎች የበዙበትና ጭር ያለ ቦታ ስትደርስ ገመድዋን አውጥታ ጠንካራና በአጭር ቁመቷ የምትደርስበትን ዛፍ ፍለጋ ጀመረች፡፡
አገኘች፡፡

የምትቆምበት ትልቅ ድንጋይ ፍልጋ ሄዳ ይዛ ወደ ሞት ዛፏ ስትመለስ አብዲን አሰበችው፡፡

“በአንተ ገመድ ተሰቀለችና ሞተች!” ሲሉት ምን ይል ይሆን ብላ አሰበች፡፡
“ሁለት ብር ቀንሰህ በሸጥክላት ገመድ ተንጠልጥላ ላትመለስ ሄደች” ብለው ሲወቅሱት ታያት፡፡
ካወቀችው ጀምሮ እስከየመጨረሻው የህይወት ቀኗ ደግነት ያሳያት አብዲ ላይ የጨከነችበት መሰላት፡፡
“ምን አንቀዥቅዦ ከመርካቶ አመጣኝ…?ምናለ ትንሽ ዘግይቼ ቢሆን ኖሮ.!?.ምናለ አይቀንስም፡፡ አያዋጣም ብዬ በመለስኳት ኖሮ!” እያለ በነዛ እምባ በማያውቁ አይኖቹ ሳያቋርጥ ሲያለቅስባቸው፡ ሃዘን ሲያጎሳቁለው፡ ፀፀት ሲያንገበግበው ታሰባትና ለቅሶ ለቅሶ አላት፡፡

ለአብዲ ስትል ዛሬ ባትሞት ተመኘች፡፡
አብዲ እንዳያለቅስ፡ አብዲ እንዳያዝን: አብዲ እንዳይወቀስ ባትሰቀል ፈለገች፡፡
አቅለሸለሻት፡፡
ገመድዋን አንጠለጠለችበት ዛፍ ጋር ስትደርስ አንድ ጠመንጃ የያዘ ሰው ቆሞ አየች፡፡

ደስ ብሏት እንደማያውቅ ደስ አላት፡፡
hiwot

No comments:

Post a Comment