"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Thursday, 24 January 2013

ብሔራዊ ቡድኑን የስነልቦና ቀውስ ውስጥ ለመክተት ሕወሓት እየሰራ ነው!!

 

የትግራይ ልማት ማህበርና ኢትዮጵያ ኢምባሲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በስነልቦና እየጉዱት ነው

የደደቢት 5 ተጫዋቾች የአቶ መለስን ቲሸርት ከማሊያ ስር እንለብሳለን ሲሉ 18ቱ ተጫዋቾች ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አታጣሉን እያሉ ነው

በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በስታዲየሙ ውስጥ የአቶ መለስን ቲሸርት የለበሰ ተጫዋች ካየን ተቃውሟችንን እናሰማለን ብለዋል
“ኢቲቪ ኳሱን ሰርቆ ማስተላለፉ አሳፍሮናል”

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የትግራይ ልማት ማህበር እና የኢትዮጵያ ኢምባሲ በጋራ የአቶ መለስ ዜናዊን ቲሸርት በማሰራት የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች በቡኪና ፋሶውና በናይጄሪያው ጨዋታ ለብሰው እንዲጫወቱ በማስገደድ ላይ እንደሆኑና በአሁኑ ወቅት ቲሸርቱን እንለብሳለን፤ አንለብስም በሚሉ መካከል ብሔራዊ ቡድኑ እንደተከፈለ የደቡብ አፍሪካ የዘ-ሐበሻ የዜና ዘጋቢዎች አጋለጡ።
የትግራይ ልማት ማህበር በደቡብ አፍሪካና የኢትዮጵያ ኢምባሲ የአቶ መለስ ቲሸርትን አሰርተው ተጨዋቾቹ ለብሰው በመግባት በተለይ ጎል ሲያገቡ ቲሸርቱን ገልጠው እንዲያሳዩ ቢጠይቁም 18ቱ የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች እንዳልተስማሙና ለትግራዩ ደደቢት ክለብ የሚጫወቱት ተጫዋቾች ግን ቲሸርቱን እንለብሳለን በሚል ለሁለት መከፈላቸውን ያጋለጡት የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች በተለይ ይህ ሚስጢር ከወጣ በኋላ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ማስከተሉን ዘግበዋል።

ልማታዊው ኪስ አውላቂ (ክንፉ አሰፋ)

የ ‘ህዳሴው ቦንድ’ ግዢ ግርግር ሞቅ ብሎ በነበረበት ሰሞን ይነገር የነበረ አነድ ቀልድ አለ። የ‘ማረሚያ’ ቤት ፖሊሶች እና ታጋዮች 500 ብር በሰረቀ ሌባ ላይ ውይይት ያደርሉ። ተከሳሹ ብሩን ያላግባብ ይስረቅ እንጂ በገንዘቡ የህዳሴውን ቦንድ መግዛቱ ነው ጉዳዩን ለውይይት የዳረገው። ይህ ሌባ መታሰር የለበትም የሚሉት ታጋዮች፡ ለፖሊሶቹ ያቀረቡት መከራከሪያ ነጥብ ልማታዊ ሃሳብ ነበር። እንዲህ ነበር ያሉት፡ ‘ይህ ልማታዊ ኪስ አውላቂ ነው። እንዲያውም እንደዚህ አይነቶቹን ሌቦች የበለጠ እንዲሰሩ ማበረታታት ነው ያለብን።…’ ሁሉም በዚህ ሃሳብ ተስማሙና ሌባውን በያዘው ልማታዊ ተግባር የበለጠ እንዲሰራበት መክረው ለቀቁት።
ይህ እነግዲህ ቀልድ ነው። ቀልድ ደግሞ በመጠኑም ቢሆን የእውነታ ነጸብራቅ እነጂ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ክስተት አይደለም። ‘ልማታዊ’ የሚለው ቃል ትርጉሙ ተዛብቶ ምን ያህል እየተቀለደበት መሆኑን ከዚህ ቀልድ ግንዛቤ እንወስዳለን። በዚህ ላይ ወደሗላ እመለስበታለሁ።
ቀልዱን በቀልድ እንለፈውና አንድ ምሽት በኢ.ቲ.ቪ. ያየሁትን እውነታ ላውጋችሁ። ኢ.ቲ.ቪ. በሚያዘጋጀው የትምህርት ቤቶች ጥያቄና መልስ ውድድር ላይ ‘ቦንድ ማለት ምን ማለት ነው?’ የሚል የ500 ብር ጥያቄ ቀርቦ ነበር። ከተወዳዳሪዎቹ አንዱ መልስ ሰጠ። እነዲህ ሲል፣ “ቦንድ ማለት፡ መንግስት በህዝብ እጅ ያለውን ጥሬ ገንዘብ ለአንድ አላማ ወደ ባንክ እንዲገባ ለማድረግ የሚጠቀመበት ዘዴ ነው።”
“ጥያቄው በትክክል ተመልሷል!” የሚል መልስ ነበር ህዘብ ከጠያቂ ጋዜጠኛው ይጠብቅ የነበረው። ጠያቂው ግን ተወዳዳሪው ትክክል እንዳልመለሰ ተናግሮ፡ ጥያቄውን ተመልካቾች እንዲመልሱለት ጋበዘ። አነዱ ‘ልማታዊ’ ተመልካች ከመሃል ተነስቶ “ትክክል” የተባለለትን መልስ ሰጠ። መልሱ ይህ ነበር፣ “ቦንድ ማለት ወለዱ ከግብር ነጻ የሆነ የቁጠባ ዘዴ ነው። ”
በዚህ ልማታዊ ጋዜጠኛ የተሳሳተ የቦንድ ትርጉም ተወዳዳሪ ተማሪው ብቻ ሳይሆን፤ የቴሌቭዥኑ ታዳሚዎችና ተመልካቾችም በሙሉ ቀልጠዋል። ይህ ጥያቄ በትምህርት ቤት ፈተና ላይ ቢመጣ ተመሳሳይ ‘ልማታዊ’ መልስ ያልሰጡ ተማሪዎች አያልፉም ማለት ነው።

Tuesday, 22 January 2013

የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ ኢትዮጵያ መንግስትን አስጠነቀቀ


 የ ኢትዮጵያ መንግስት  ንስሀ መግባት አለበት

 ጥር ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- በኢትዮጵያና በዛምቢያ መካከል ትናንት ምሽት የተደረገውን እግር ኳስ ጨዋታ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከማሰራጫ ቻናል በድብቅ በመውሰድ ማስላለፉን ደርሸበታለሁ ሲል የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን(ካፍ) መግለጹን ኒው ቢዝነስ ኢትዮጵያ ዘገበ
እንደ ዘገባው የ ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሌሎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚያሰራጩትን ጨዋታ በመስረቅ ጫዋታውን እንዳስተላለፈ የተደረሰበት በእረፍት ሰዓት የጨዋታው ስፖንሰር እንደሆኑ አድርጎ የበርካታ ድርጅቶችን ማስታወቂያ ሢሰራ ነው።
በካፍ መግለጫ መሰረት የ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የፈጸመው ማጭበርበር ሁለት መልክ ያለው ነው።
... አንዱ ማጭበርበር ጫዋታውን ክፍያ ሳይፈጽም በድብቅ ማስተላለፉ ሲሆን፤ሁለተኛው ደግሞ በዚያው በተሰረቀ የ አየር ሰ ዓት <<ይህን ጨዋታ ስፖንሰር በመሆን ያስተላለፉላችሁ እነ እገሌ ናቸው” እያለ የበርካታ ድርጅቶችን ማስታወቂያ መሥራቱ ነው።
ይህ የ ኢቲቪ ድርጊትም በሁለተኛው ግማሽ በጨዋታው ኮሜንታተር ሁለት ጊዜ ተጋልጧል እንደ ጋዜጣው ዘገባ ።
ጨዋታውን ለማስተላለፍ ፈቃድ ያለው የቴሌቪዥን ጣቢያም በቸዋታው መሀል በፃፈው <<ቴክስት>> የ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራዲዮ ድርጅት ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይፈጽም ጨዋታውን እያስተላለፈ ነው።>> በማለት ድርጅቱ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ አሣስቧል።
የ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ 31 ዓመት በሁዋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ቢያልፍም፤ መንግስት ለቴሌቪዥን ስርጭት ከፍተኛ ገንዘብ ተጠይቄያለሁ፤ ይህም ዋጋ በጣም ተወዶብኛል>> በማለት ላለማስተላለፍ መወሰኑ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በዘርፈ-ብዙ ሙስና በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ብር የሚዘረፍባትና ለስርዓቱ ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች ሳይቀሩ በሆነ ባልሆነው ከፍተኛ ገንዘብ የሚያፈሱባት አገር መሆኗን የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ።
በጉዳዩ ዙሪያ ቀደም ካሉት ቀናት አንስቶ አስተያዬት ሢሰጡ የነበሩ ሰዎች፡<< 18 ሚሊዮን ብር እንኳን ለመንግስት ለዘመኑ ባለሀብቶች ቀላል ነው፤ በዚያ ላይ ሁሉንም ባይሆን የተወሰነውን ከ አገር ውስጥ ማስታወቂያ መሸፈን ይቻላል።መንግስት ማሳዬት ያልፈለገው በ እርግጥ ገንዘብ አጥቶ ነው?ወይስ በደቡብ አፍሪካ የሚካሄድን ተቃውሞ በመፍራት ነው?>>በማለት ሲጠይቁ ነበር።
ለኢትዮጵያ መንግስት የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ የተመለከቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን፦<< በልጆቻችን በኮራንበት ቀን ለማይረባ ገንዘብ ሲል ተራ ማጭበርበር ውስጥ በገባው መንግስት አፈርን፤ ግለሰብ ቢሰርቅ በህግ ይጠየቅ እንል ነበር። የሰረቀው <<ሌባ መቀጣት አለበት>>የሚል ህግ የፃፈው መንግስት ነው ሲባል ግን ከማፈር በስተቀር ምን እንላለን?>> ብለዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ መንግስት የሰጠው አስተያየት የለም።


በኤርትራ መንግሥት አልተገለበጠም አሜሪካ ለዜጎቿ መመሪያ ሰጠች
January 22, 2013 03:08 am By Editor 2 Comments

“ኩዴታ ሲደረግ በቅድሚያ በቁጥጥር ስር ሊውል የሚገባው የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያ ነው። በአስመራ  ይህ ስለመሆኑ የተባለ ነገር የለም። ታዲያ እንዴት ነው ኩዴታ ተከናውኗል ሊባል የሚችለው? በርግጥ ገለልተኛና ነጻ የውጪ ሚዲያዎች አለመኖራቸው የመረጃውን መጠንና ጥራት ቢገድበውም እስካሁን የሚወጡት መረጃዎች እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅ እንጂ የማስገደድ አይመስልም። በዚህ መነሻ ኢሳያስ ሙሉ በሙሉ አደጋ ውስጥ ናቸው ማለት አይቻልም። ግን የመደራደር ነገር ሊኖር ይችላል” አውሮፓ የሚኖር ኤርትራዊ ለጎልጉል የተናገው ነው።

አስር ሺህ የሚደርሱ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሏት የሚነገርላት ኤርትራ ዛሬ አመሻሹ ላይ አዲስ ዜና አሰምታለች። የተቀየሙ የጦር ሃይሎች የማስታወቂያ ሚኒስቴርን ከበው የፖለቲካ እስረኞች እንዲለቀቁ በማስገደድ ላይ እንደሆኑ የተለያዩ የዓለም መገናኛዎች እየዘገቡ ነው። የመፈንቅለ መንግሥት መደረጉንና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ እንዳበቃላቸው የገለጹም አሉ። ተቃዋሚዎችን ጨምሮ፡፡

የጎልጉል ዝግጅት ክፍል በቀጥታ አስመራ በመደወል ባገኘው መረጃ መሰረት ዋናውን አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቁጥራቸው ከፍተኛ የተባለ ወታደሮች ተቆጣጥረውታል። ወታደሮቹ አፍቃሪ ኢሳያስ የሚባሉት ይሁኑ፣ አፈነገጡ የተባሉት ለማጣራት ግን አልቻለም። “ከተለመደው ውጪ በርካታ ወታደሮች ይመላለሳሉ። አውሮፕላን ጣቢያው ጤነኛ እንቅስቃሴ አይታይበትም” በማለት የተመለከተውንና የታዘበውን ይገልጻል። አያይዞም በከተማዋ ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከወትሮው የተለየ እንደሆነ ተናግሯል።

የቴሌቪዥን ጣቢያ የአገር ውስጥ ስርጭቱ እንደተቋረጠ የነገረን የአስመራ ነዋሪ፣ ህዝቡ ሁኔታውን የተረዳና አንድ ነገር እንደሚፈጠር የተረዳ በሚመስል መልኩ ተረጋግቶ ሁኔታዎችን እየተከታተለ እንደሆነ አስታውቋል። በኤርትራ ሁለተኛ ታላቅ ከተማ የምትባለው ባጽዕ (ምጽዋ) ኩዴታ ባከናወኑት ሃይሎች እጅ እንደሆነች መስማቱንም ይናገራል።

አዲስ አበባ መቀመጫቸውን ያደረጉት የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ተቃዋሚዎች ለአልጃዚራ እንደተናገሩት የጦር ሃይሉ በኑሮ ውድነት ተማሯል። እለት እለት እየተባባሰ በመጣው የኑሮ ቀውስ መንግስትና ወታደሩ አለመተማመን ደረጃ መድረሳቸውን ከመጠቆም ውጪ በትክክል ምን እየተደረገ እንደሆነ አልገለጹም።

አስመራ የውጪ አገር መገናኛዎችና ገለልተኛ የዜና ወኪሎች ባለመኖራቸው እስካሁን ትክክለኛና ሁሉንም ወገኖች ያካተተ መረጃ አልተሰማም። ይሁን እንጂ በተባበሩት መንግስታት የኤርትራ አምባሳደር አርአያ ደስታ “ምንም ችግር የለም፣ ሁሉም ነገር መፍትሄ ተበጅቶለታል። ሁሉም ነገር መልካም ነው” ሲሉ ለአልጃዚራ አስታውቀዋል።

ታዛቢዎች እንደሚሉት የታሰሩት የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ከሚጠይቁት ውጪ የመፈንቅለ መንግሥት ይዘት እንደማይታይ ይናገራሉ። በሌላ በኩል ግን ኢሳያስ አስመራ እንደማይገኙና ምን አልባትም ምጽዋ እንደሚገኙ የሚጠቁሙት ክፍሎች የኤርትራ መንግስት ኮማ ውስጥ ስለመሆኑ ከበቂ በላይ ምልክቶች እንዳሉ ይናገራሉ። ከአስመራ በስልክ ያነጋገርነው የከተማዋ ነዋሪ እንዳለው ባጽዕ (ምጽዋ) ያለው ሃይል ከከዳ በርግጥም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ችግር ውስጥ ናቸው ማለት እንደሆነ ገልጾዋል።

በመጨረሻ ባገኘነው መረጃ ኤርትራ ውስጥ መንግስት እንዳልተገለበጠና መንግስትን ለመገልበጥ የሚያስችል እንቅስቃሴ አለመስተዋሉን ነው። ፕሬዚዳንቱ በትክክል ያሉበት ባይገለጽም በቅርብ በመከታተል መመሪያ በመስጠት ላይ እንደሆኑ ከአስመራ በስልክ ሰምተናል። አፈንጋጮቹን ለሚመሩት  የጦር መኮንኖች የፖለቲካ እስረኞች የሚፈቱበት አግባብ እንደሚመቻች ቃል መግባታቸውም ተነግሯል።

የአሜሪካ ሬዲዮ አላዝቦ ያቀረበው ዜና  አማጺ ያላቸው ወታደሮች የማስታወቂያ ሚኒስቴርን በመቆጣጠር የታሰሩ እንዲፈቱ፣ እኤአ በ1997 የተዘጋጀው ህገመንግስት ይከበር የሚል መግለጫ በማስገደድ ማስነበባቸውን አስደምጧል።ዘግይቶ የደረሰን ዜና በማለት አሜሪካ ዜጎቿ ወደ አስመራ የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲገድቡ ትዕዛዝ መስጠቷን ተናግሯል።

አፈንጋጮቹ በግዳጅ ላይ ካለው የጦር ሃይል ዘንድ ስላላቸው የጠበቀ ግንኙነት እስካሁን የተባለ ነገር የለም። ይሁን እንጂ የማስታወቂያ ሚኒስቴርን በመቆጣጠር አስገድደው ያስነበቡትን መግለጫና የፖለቲካ አስረኞች ይፈቱ ጥያቄ ተከትሎ ከዋናው ስቱዲዮው በመቀበል ዜናውን የሚያሰራጨውን መስመር (ዋናውን አንቴና) እንዲቋረጥ በታዘዘው መሰረት ዜናው የጦር ሃይሉና ህዝብ ጆሮ በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተዳረሰ ለማወቅ ተችሏል። አስመራ ያልተለመደ የወታደሮች እንቅስቃሴ ከመታየቱ በቀር ሁሉም ነገር የተረጋጋና የመንግስት ማስወገድ እንቅስቃሴ አለ የሚያስብል አይስተዋልም።


የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ግጥሚያና ሁኔታዬ

 

adane
ጎል ጎል ጎልልልልልል
የእግር ኳስ ጨዋታ ለኢትዮጵያዊያን ከረጅም ርቀት ሩጫ ውድደር ጋር ከፍተኛ ቦታ የያዘ ነው። በእድሜያችን ገፋ ላልነው፤ የነመንግሥቱ ወርቁ የኳስ ጥበብ፤ የኢታሎና ሊቻኖ . . . በታሪክ  ሰምተን ሰናልፍ በአይናችን ደሞ  ሙልጌታ ከበደ ፤ሙልጌታ ወልደየሰን ፤ ኤልያስ ጁሀርን ኧረ ስንቱን በትዝታ ዓለም መጎብኘት ይቻላል። ብቻ ለሁሉም ያንን እንዳስታውስ ያደረገኝ፤ በዛሬው ዕለት ከቤቴ ተቀምጨ ያየሁት የኢትዮጵያ ቡድንና የዛምቢያ ቡድን ጨዋታ ነው። ቡድናችንን በሀገራችን ካለው ዘረኛ አገዛዝ ነፃ አውጥቶ ለብቻው ማየት መቻል ከባድ ነው። ነገር ግን አደረግነው። ስንደቅ ዓላማችንን እንኳ በመሐከሉ ላይ ያስቀመጠውን ጉድፍ ረሳነው። የዘረኛውን የስንደቅ ዓላማ ጉድፍ ለዚች ቀን ከሰንደቅ ዓላማችን ላይ ተሰቅሎ ሲውለበለብ ዝም ብለን ዓየን፤ ትኩረታችን በተጫዋቾቻችን ላይ ነበርና።
ከጎኔ ሆነው የባራክ ኦባማን የፕሬዘዳንትነት ምርጫ ስነ ሥርዓት እያዩ ሲጯጯሁብኝ፤ ኮምፒውተሬን ይዤ ክፍሉን ለቀቅኩላቸው። ለነገሩ እነሱን አማሁ እንጂ፤ እኔ እግሮቼን እንደ ተጫዋቾቹ ሳፈራግጥና አቀብለው እያልኩ ስጮህ፤ የበለጠ በጥባጭ ነበርኩ። በስድሳ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ፤ አዳነ ግርማ ግብ ሲያስቆጥር፤ የቤቱን ጣራ አነቃነቅሁት። ያለሁበትን አላቋጠርኩትም። ዓይኖቼን ጨፍኜ ነበር። ከመቀመጫዬ መነሳቴ ትዝ ይለኛል፤ ተነስቼ ምን እንዳደረግኩ ግን አላስታውስም። ለአንድ ቀን፤ ባንድ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪቃና እዚሁ ካለሁበት ሀገር፤ ከሶስቱም ቦታ ተገኘሁ። አንድም ሶስትም ሆንኩ። ከተጫዋቾቹ ጋር በሜዳው፣ ከተመልካቾቹ ጋር በስታዲየሙ፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ኢትዮጵያ ተገኘሁ። ዓይኖቼን ስገልጥ እንኳን ደስ አልህ የሚለኝና የምለው ፈለግሁ፤ አልተገኘም። ደስታዬን ግን ቅንጣት አልቀነሰብኝም። ተጫዋቾቹ የኢትዮጵያን ሕዝብ ነበር የወከሉት። ተጫዋቾቹ ኢትዮጵያን ነበር የወከሉት። ተጫዋቾቹ ለሀገራቸው ነበር የተጫወቱት። ተመልካቾቹ ለሀገራቸው ነበር የጮሁት።
የነገዋ ኢትዮጵያ ያማረች ትሆናለች። አሁን ያለንበት የፖለቲካ ሀቅ ውጥንቅጡ ብዙ፤ የደፈረሰና መያዣ መጨበጫ የሌለው ቢሆንም፤ በኢትዮጵያዊነት ላይ ምንም ብዥታ የለንም። ደስ ብሎኛል። ለወደፊት የምትመጣዋን ኢትዮጵያ እንዳይ ረድቶኛል።

Monday, 21 January 2013

ሰበር ዜና በኤርትራ መፈንቅለ መንግስት ተካሄደ።


Image
ኢ.ኤም.ኤፍ. – የኤርትራ መከላከያ ሰራዊተ በዛሬው እለት (ሰኞ 21 ጃንዋሪ) በፕ/ት ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ መፈንቅለ-መንግስት ማድረጉን ኢ.ኤም. ኤፍ. ከአስመራ በስልክ አረጋግጧል:: ሰራዊቱ በአሁን ሰዓት ማስታወቂያ ሚኒስትሩን የተቆጣጠረ ሲሆን እስካሁን ምንም አይነት ደም መፋሰስ እንደሌለ ዘጋቢያችን ገልጿል::
ኢሳያስ አፈወርቂ የት እንዳሉ የታወቀ ነገር የለም::ምንጮች እንደሚሉት ኢሳያስ አፈወርቂ ለስራ ጉብኝት ምጽዋ ሲሆኑ ከአስመራ-ምጽዋ የሚወስደው መንገድም በወታደሮች ዝግ ሆኗል::ወታደሮቹ በተለይ የኤርትራ ጋዜጠኞች ምንም እንቅስቃሴ እንዳያድርጉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል:: ጋዜጠኛዋ የኢሳያስ አፈወርቂ ልጅም እንደታገተች ተገልጿል::
እንደ ሪፖርተራችን ዘገባ ህዝቡ እንዲረጋጋነ እቤቱ እንዲቀመጥ ሰራዊቱ እየተናገረ ሲሆን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሙሉ ተቋርጠዋል::ምንም ደም መፋሰስ ሳይኖር ማስታወቂያ ሚ/ርን እስከመቆጣጠር መድረስ ያልተለመደ መፈንቅለ-መንግስት ነው::
የአፍሪካ ጥናት አኤክስፐርት የሆነው ማርቲን ፕላውት ዲፕሎማቲክ ምንጮችን በመጥቀስ መፈንቅለ መንግስት እየተካሄደ መሆኑን በድረ-ገጹ ጽፏል:: ከፈረንሳዩ ኤ.ኤፍ.ፒ. በስተቀር አለም አቀፍ የዜና ምንጮች ዜናውን አልዘገቡትም: