"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Thursday 2 May 2013

የአቡነ ጵጥሮስ ሃውልት መነሳት በበውቀቱ ስዩም አገላለጽ

ማለዳ መነሣት አልወድም፡፡ዛሬ ግን አቡነ ጴጥሮስ ከመታሰቢያቸው ዙፋን ሲወርዱ ለመታዘብ በማለዳው ካልጋየ ጨክኘ ወረድሁ፡፡ለአቡነ ጴጥሮስ ፍቅር ስል የማለዳ እንቅልፌን ብሰዋ አይቆጨኝም፡፡በቅርቡ በሚከፈተው ጦማሬ ላይ ስለ ጀግናው ጴጥሮስ በሰፊው የመጻፍ ሐሳብ አለኝ፡፡
በቦታው ስደርስ፣የጴጥሮስ ሀውልት በጣውላ ተገንዞ ቆሟል፡፡ድብርት ተጫጫነኝ፡፡ምናልባት አያቶቼ አቡኑ ሲረሸኑ በተመለከቱበት ሰአት የተሰማቸው ስሜት እንዲህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የራስ ቁር የደፉ የቀን ሠራተኞች በአቡኑ ትክሻ ላይ እንደ ወፍ ሰፍረዋል፡፡ ወደ መርካቶ በሚሄዱ ተሳፋሪዎች የተሞሉ ሚኒባሶች አደባባዩን ታክከው ሽው ይላሉ፡፡ ተሳፋሪዎቹ፣ በመስታውት አሻ......ግረው የሚመለከቱት ትእይንት ብዙ የመሰጣቸው አይመሰልም፡፡በፋሲካ አስፈሪ የዶሮ ዋጋ ለተጠመደ አእምሮ ታሪክ ምኑ ነው??
ከተመልካቹ በላይ የፖሊሱ ቁጥር የሚበልጥ መሰለኝ፡፡አንድ ፒካፕ መኪና ስትበር መጣችና ቁና ሙሉ ፌደራል ፖሊስ አራገፈች፡፡ሰብሰብ ብለን በቆምንበት አንዱ ፖሊስ ጠጋ አለና‹‹ እናንተን አይመለከታችሁም ከዚህ ሂዱ›› አለ፡፡ካጠገቤ የቆመ ጎበዝ ‹‹ማየት መብታችን ነው›› ብሎ መልሶ ጮከበት፡፡አሀ! የጴጥሮስ መንፈስ አልከሰመም ማለት ነው፡፡ፖሊሱ ምንም ሳይመልስ ከሬድዮ መገናኛው ጋር እየተመካከረ ካካባቢው ራቀ፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጋዜጠኛ ጓደኞቼ ካሜራቸውን ታጥቀው ደረሱና ተቀላቀሉኝ፡፡ ሀውልቱን ማስቀረት ስላልቻሉ ምስሉን ቀርጸው ለማስቀረት ተሯሯጡ፡፡
ድንገት ቀና ብየ ሳይ ከሀውልቱ ፊትለፊት ጅማ በር የሚባል ፣ጣልያን የሠራው አሮጌ ሕንጻ ይታየኛል፡፡ባቡሩ የአቡነ ጴጥሮስን መታሰቢያ ደቅድቆ ሲያልፍ፣ጣልያን ሠራሹን ግንብ ንክች አያደርገውም፡፡ጉደኛ ባቡር!!!
በጣውላ የተገነዘውን የአቡኑን ሀውልት ለመሸከም አንድ አዳፋ ረጅም ተጎታች መኪና ብቅ አለ፡፡ዳይኖሰር የመሰለ ክሬን ሀውልቱን ነቅሎ ሲያንጠለጥለው፣ሀውልቱ የነበረበት ቦታ ጥርስ የወለቀበት አፍ መሠለ፡፡ቀሪውን የማየት ፍላጎት ስላልነበረኝ ከጓደኛየ ጋር ወደ ፒያሳ አቀናሁ፡፡ብዙ ነገር እዬተለወጠ መሆኑን አየሁ፡፡የጥንቱ መሀሙድ መዚቃ ቤት ወደ ቡቲክ መቀየሩን አስተዋልሁ፡፡የጥንቱ አያሌው ሙዚቃ ቤት ፍራፍሬ መሸጫ ሱቅ ሆኗል፡፡ከጥቂት ወራት በፊት ብርቱካኔ የሚለው ሙዚቃ ይንቆረቆርበት የነበረው ቦታ ፣አሁን ብርቱካን በኪሎ ይሸጥበታል፡፡
አዲስአበባ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያለጥርጥር፣ባቡር ይኖራታል፡፡ቀለበት መንገዶች ይኖሯታል፡፡አሪፍ ህንጻዎች ይኖሯታል፡፡ነገር ግን፣ ትናንት የሚባለው ነገር አይኖራትም፡፡ A city without past ላዲስ አበባ የተገባ ቅጽል ነው፡፡
ወደ ሰፈሬ የሚሄድ ታክሲ ስፈናጠጥ፣ የሚከተሉት የጸጋየ ገብረመድህን ግጥሞች ሽው አሉብኝ፡፡
….መጭው ደመና ጥቁረቱ፣
ጮቁ ፣ማጡ፣የክረምቱ፣አቤት ዝቅጠቱ ማስፈራቱ
የኛስ ትውልድ አከተመ፣አገራችንን አምክነን
የነገስ ዘር ምን ይበለን፣ስንተወው ሲኦል አውርሰን

የእነ አንዱዓለም አራጌ ይግባኝና የዛሬው የፍርድ ቤት ብይን

ኢትዮጵያ

 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፤ በእነ አንዱዓለም አራጌ መዝገብና በሌሎች መዝገቦች ፤ በአሸባሪነት ተከሠው ይግባኝ የጠየቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአመራር አባላትና የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጉዳይ መርምሮ፣ ከአንደኛው በስተቀር የሁሉንም የእሥራት ብይን እንዲጸና አድርጓል።
የክንፈ ሚካኤል በየነ እሥራት ፤ ከ 25 ዓመት ወደ 16 ዓመት ዝቅ እንዲል ወስኗል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአሸባሪነት የተወነጀሉት እና ከአለፈዉ ዓመት ጀምሮ እስር ላይ ያሉትን፤ አምደኛ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲሁም የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዉ አንዱአለም አራጌ፤ ያቀረቡትን ይግባኝ ዉድቅ አደረገ።
«ብይኑ አሁንም ትክክል ነዉ፤ ምንም አይነት ቅነሳ አይኖርም ሲሉ» የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ደጀኔ መላኩ ተናግረዋል። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በዲፕሎማቶች በዘመድ እና በጓደኛ በተሞላዉ ብይን ላይ ከዉሳኔዉ በኋላ « እዉነት አንድ ቀን ይወጣል» ሲል በስሜት መናገሩ ተገልጾአል።
Anwalt Abebe Guta im Prozess Journalist Eskinder Nega und Oppositionellen
Andualem Arage 020513.
Foto: Yohannes G/Egziabher DW Korrespondent 2013 ጠበቃ አበበ ጉታ
እስክንድር ነጋ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያዉቅ የምንፈልገዉ እዉነት እራሱ በግዜዉ ይወጣል፤ የግዜ ጉዳይ ብቻ ነዉ» ብሎአል። አንዱአም አራጌ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከመንግስት ተቃዋሚ ቡድን ግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለዉ እስክንድር የ 18 ዓመት ጽኑ እስራት አንዱዓለም ደግሞ የእድሜ ልክ እስራት ተበይኖባቸዋል። በአሁኑ ወቅት በእሥር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር እጎ እ 2012 ዓ,ም ዓለም አቀፉ የደራስያን ድርጅት ፔን በዓለምአቀፍ ደረጃ በሥራቸው ምክንያት ለታሠሩ ወይም አደጋ ላይ ለወደቁ ደራስያንና ጋዜጠኞች የሚበረከተዉን የመፃፍ ነፃነት ሽልማት ማግኘቱ ይታወቃል። ዝርዝሩን ዮሃንስ ገ/እግዚአብሄር ወኪላችን ተከታትሎታል።
ዮሃንስ ገ/እግዚአብሄር
ተክሌ የኋላ