ዳንኤል ክብረት
click here for pdf
እስኪ ተዪው አሉኝ ያልደረሰባቸው
click here for pdf
ኢትዮጵያ ከቦትስዋና ጋር ስትጫወት ተገቢ ያልሆነ ተጨዋች አሰልፋችኋልና ሦስት ነጥብ ታጣላችሁ ብሎ ፊፋ የሚባል ቡዳ አገሩን ቀወጠው፡፡ እንደ አውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ነገር ማድረግ የሌለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ፊፋ ከአድኅሮት ኃይሎች ጋር ካልተሰለፈ በቀር ሌላ ምክንያት ሰጥቶ ኢትዮጵያን መጣል ይችል ነበር፡፡ ለኛ የኢትዮጵያ ነጥብ መቀነስ አይደለም ችግራችን፤ ነጥቡ መቀነሱን ሕዝቡ መስማቱ ነው፡፡ እኛኮ ቀስ አድርገን ‹ኪራይ ሰብሳቢዎች የሀገራችንን የስፖርት ራእይ ለማደናቀፍ ከፀረ ሕዝብ ኃይሎች ጋር በመሆን የደቀኑብን ሤራ ነው› ብለን ሕዝቡን ማሳመን እንችል ነበር፡፡
መጀመሪያ ከበላዮቻችን ጋር እንነጋገራለን፤ ሂስ ከተሰጠንም ሂሳችንን እንውጣለን፣ ግምገማችንንም እንቀበላለን፣ ዋናው ይሄ አይደለም፤ አንዴት አድርገን ለሕዝቡ እንንገረው? የሚለው ነው፡፡ ሕዝብ እንደነገርከው ነው፡፡ እንደ አሰማሙ ነው፡፡ አቀናብረን ከነገርነው አቀናብሮ ይሰማል፡፡ ግን ምን ያደርጋል፣ ፊፋ የሚባል ቡዳ ለሕዝብ መነገር የሌለበትን ለሕዝብ ተናገረና መከራ አሳየን፡፡
አሁን አዳሜ ዕድል ስታገኝ ጊዜ ‹ለምን ሥልጣን አትለቁም› ትላለች፡፡
እንዲህ በቀላሉ የሚተው መስሏቸው
አለች የሀገሬ ዘፋኝ፡፡ ሥልጣን እንዲህ በቀላሉ የሚተው መስሏቸዋል፡፡ እኛ በቀጣዩ ምርጫ እንዴት አድርገን ተመልሰን እንደምንመጣ እያሰብን እነርሱ ሥልጣን ልቀቁ ይሉናል፡፡ ‹ከአንድ ሙዚቃ በኋላ ተመልሰን እንገናኛለን› አሉ የኤፍ ኤም ጋዜጠኞች፡፡
ስለ ሥልጣን መልቀቅ እዚህ ሀገር የሚያስብ ሰው ካለ የመጨረሻው ጅል እርሱ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ስለ ሥልጣን አያውቅምና፡፡ ‹‹አቤቱ የሚናገሩትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው››፡፡ እነዚህ ሰዎች ሥልጣንን ያልቀመሷት ሰዎች ናቸው፡፡ ቢቀምሷት ኖሮ ‹አጥብቃችሁ ያዟት› ይላሉ እንጂ ‹ልቀቋት› አይሉም ነበር፡፡ መንፈሳውያን ነን፣ ዓለምን ንቀናል የሚሉት አባቶች እንኳን ለሥልጣን በሚታገሉባት ሀገር እኛን ዓለማውያኑን ‹ሥልጣን ልቀቁ› እንደማለት ያለ የዓመቱ ምርጥ ቀልድ የለም፡፡
ጎበዝ እዚህ ሀገር ባለ ሥልጣን ማለትኮ ትንሽ ፈጣሪ መሆን ማለት ነው፡፡ ሰው የሚሰግድልህ ሥልጣን ሲኖርህ ነው እንጂ ዕውቀት ሲኖርህ አይደለም፣ ሰው የሚኮራብህ ሥልጣን ሲኖርህ እንጂ ችሎታ ሲኖርህ አይደለም፡፡ እስቲ የትኛው የአክስትህ ልጅ ነው እገሌ የተባለው ሳይንቲስትኮ ዘመዴ ነው ብሎ የሚኮራው? የባለሥልጣን ግን እንኳን ዘመዱ ድመቱም አረማመዱ የተለየ ነው፡፡ ጅል- ሥልጣን ልቀቁ ይላል እንዴ፡፡ ሥልጣን የሻሂ ቤት ወንበር መሰላችሁ እንዴ፡፡