"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Saturday, 23 March 2013

የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ - ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን

 



የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ

ተስፋ ባጣ ምድረ በዳ
ያንድ እውነት ይሆናል ዕዳ፡፡
እና ትንፋሼ አልሆነሽም፥ ሆኜብሽ መራር መካሪ
“ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ፣”
እውነት ላንቺ መች ተስፋ ናት፥ ጉስቁል ልሳንሽን ነክሳሽ
ክንድሽን ካዘለ ቅርስሽ፥ መጠላለፍ ሲሆን እጣሽ
ከእንግሊዝ የሞት አማልክት፥ መተናነቅ ሲሆን ድርሻሽ
መልመጥመጡ፥ መሽቆጥቆጡ፥ መስሎሽ ድንገት የሚያዋጣሽ
የኔ እውነት ሆነብሽ ዕዳሽ ፡፡ …..
ወራሪም ፈጣሪን ላያቅ
የጣለውን በስሏል እንጂ፥ ወድቋል ብሎ ግፉ ላያልቅ
መች ትተርፊያለሽ ኢትዮጵያ፥ ሕዋስሽ አብሮኝ ካልሠራ
አንገትሽ ብቻ መቅደላ፥ አፋፍ ወጥታ ብታበራ
የቀረው ሠራ-አከላትሽ፥ በየጥሻው ተዘርሮ
ከአባት በወረሽው ንፍገት፥ ነብዞ ደንዝዞ ተቀብሮ
ባጉል ወጌሻ ታጅሎ
እጅና እግርሽ ታሽቶ ዝሎ
እኔን ለጥንብ አንሳ ጥሎ፤
ከደቀቀ ከደከመ፥ ክንድሽ አልነሣ ካለ
ሞት እንጂ ለኔስ ምን አለ?.....
ሆኖም ጐስቋላ አልምሰልሽ፥ የሚያዝንልኝ አልፈልግም
ጠላትሽን በክንድሽ እንጂ፥ በእንባሽ ወዝ ባላሸንፍም
የልቤን ፍቅር በሰተቀር፥ እማወርስሽም ውል የለኝ
የኮሶ ሻጭ ልጅ ደሃ ነኝ፡፡ …..

ደሞም ያላንቺ የለኝና
ድሌም የተሰፋ ጐሕ ባይሆን፥ ከሞት ጋር ትግል ነውና
ከዚህ ሌላ ትእዝብት ውረሽ፥ ሳይነጋ እንዳስመሸሽብኝ
ጊዜና ትውልድ ይፍረደን፥ ሳልነቃ እንዳስረፈድሽብኝ፡፡
ያም ሆኖ ለራስሽ እንጂ ለኔ ከቶም አታልቅሺ
አንቺ ነሽ እንባ እምትሺ፤ …..
የእምነትሽ መተሣሰሪያ፤ ውልሽ ለተላቀቀብሽ ላንቺ ነው እንባ እሚያሰፈልግሽ፡፡
አዎን፥ ይኽን እወቁልኝ፥ ምስክር ሁኑኝ ሰማዕታት
ለሷ ነው እንባ የሚያስፈልጋት፡፡
ከጠላቶቹ ጭብጥ ውስጥ፥ ትንፋሼን በጄ ስነጥቃት
ሞቴን ከመንጋጋቸው ውስጥ፥ መንጭቄ እኔው ስሞታት
ላገሬ ብድር ልከፍላት
የነፈገቺኝን ፍቅር፥ በራሴ ሞት ልለግሳት!.....ያኔ ነው እንባዋ የሚያጥራት፡፡
ሰለዚህ ለራስሽ እንጂ፥ ልቅሶሽ ለኔ ምን ሊረባ
ብቸኛ ምሬት ነው ኃይሉ፥ ወኔ መሰለቢያው ነው እንባ፡፡
እና ለራስሽ እዘኚ
እንጂ ከቶ ለኔ እትባክኚ፡፡ …..ይልቅስ ተረት ልንገረሽ፥ የተላከ ከእንግሊዝ ዘንድ
እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ፥ እጅ ተይዞ ሊወሰድ፥
ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ?አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ፡፡ …..ዳዊት እንዲያ በበገናው፥ ማልቀስ ማላዘን መያዙ
ይኽ የጐልያድ ውላጅ፥ ቢበዛበት ነው መዘዙ
ምንጩ እንደአሽን እየፈላ፥ አገሩን ምድሩን ማንቀዙ
ቸግሮት ነው፥ መጋፈጡ፥ ከስንቱ መወናጨፉ
በባላንጣው ሳቢያ ምክንያት፥ የራሱን ወገን ማርገፉ፡፡ …..ታድያ እንግዲህ አንቺ ኢትዮጵያ፥ እኛስ ልጆችሽ ምንድነን
አመንኩሽ ማለት የማንችል፥ ፍቅራችን የሚያስነውረን
ዕዳችን የሚያስፎክረን
ግፋችን የሚያስከብረን
ቅነነት የሚያሳፍረን፥ ቂማችን የሚያስደስተን
ኧረ ምንድነን? ምንድነን?አሜከላ እሚያብብብን፥
ፍግ እሚለመልምብን፥
ከአረም ጋር ያፈራን ጊንጦች፥ ከእንክርዳድ ያልተለየን ዘር
ግርዱ ከምርቱ ተማጥቆ፥ ከቶ ያልተበራየን መከር
ምንድነን? ምንድነን እኮ?አረጋዊውን ባንቀልባ፥ ከምንሽከም እንኮኮ
ጐልማሳውን ከወኔ ጣር፥ ካልፈታን ከፍርሃት ምርኮ
እንደ ወዶ ገባ ወደል፥ መጠለሉን ከሴት ታኮ …..ካቃተን፥ ምንድነን እኮ?.....አየሽ እንቺ እማማ ኢትዮጵያ፥ አየሽ አንቺ እናት ዓለም
ቃል የእምነት ዕዳ ነው እንጂ፥ ያባት የናት እኮ አይደለም፡፡ …..

ያም ይቅርና መርዶ ላርዳሽ፥ ስሚው እኔ እንደሰማሁት
እርም በልተሽ ከምትቀሪ፥ ስሚው ገብርዬንም ጣሉት፡፡ …..እስቲ እንግዲህ በይ ፍረጂኝ፥ ከእንግዲህ እኔ ፍሬ አላይም?
ዘርቶ መቃም ወልዶ መሳምአባባል ለኔ አይባልም?እስቲ ገብርዬን መሰል ዘር፥ ፍሬው ከቶ አይለመልምም?እኔስ ዘር ዘራሁ አልልም? …..ምነው ፍንጭትክን ገብርዬ፥ ያን ፍንጭትክን አጨለሙት
እንደ ሬት ልግ አከሰሉት
እንደ ኮሶ አስመረሩት? ......ከጡቶችሽ እቅፍ ነጥቀው፥ ከማኅፀንሽ ፍቅር ቆርጠው
እውነትን ሲገሉ እንዲህ ነው፥ ፈገግታውን አጨልመው፡፡
እስቲ እባክህን ገብርዬ፥ የዛሬን እንኳ ስቀህ ሙት
በዕድል ጥቀርሻ እንደአጀሉት
እንደ ወላድ ጣውንት ጡት
አርማ ጉሳ እንደቀለሙት
ፈገግታህን አያጥቁሩት፡፡
እምቢ በላቸው ገብርዬ፥ በአባት ሤራ እንዳስገዘቱት
በመሃላ እንዳሳገዱት
የነፍሰህን ጮራ ብርሃን፥ ከገጽህ እንደቀበሩት
ዘለዓለም ላያጨልሙት
ወንድምዬ እምቢ በላቸው፥ የዛሬን እንኳ ስቀህ ሙት፡፡ …..ያለፈ ጥረታችንን፥ ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ፥ ያልሞከረነው ነው እሚቆጨኝ፡፡
እና በኔ ይሁንብህ፥ መጣሁ፥ ስቀህ ተቀበለኝ
እኔም ላዋይህ አድምጠኝ …..እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ፥ እጅ ተይዞ ሊወሰድ
ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ?አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ፡፡ …..


ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን
እሳት ወይ አበባ

Thursday, 21 March 2013

እንዳይነግርህ አንዳች እውነት !

 /ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን
-----------
ደንስ ጎበዝ ! ደንስ ጀግና
ክራቫትህን አውልቅና
ሃሳብህን ልቀቀውና
... ኮትክን ሸሚዝክን ጣልና
ርገጥ ፣ ጨፍር ፣ ደንስ ጀግና !

ያን የሙዚቃህን ናዳ ፣ የኮንትራባሱን መብረቅ
ልቀቀውና ይድብለቅለቅ
ምድር በሆይታ ይጥለቅለቅ !
ምንም-ምንም እንዳታስብ ፣ ሁሉን-ሁሉን እንድትረሳ
ደንስ ! ካካታው ይነሳ
ጨፍር ፣ ወለሉ እስኪበሳ ....

ሃይ-ሃይ ! ዋይ ! ሃይ-ሃይ ! በልበት
የጃዝ ፋንፋር አንኳኳበት
ራስክን እንዳታስብበት ፤
ሆ ! በል እሪ ! በል ምታበት
ፎክርበት ፣ አቅራራበት
አናፋበት ፣ ሸልልበት
የሲቃ ሳቅ አስካካበት
ሆያ-ሆዬ ! በል ጩኽበት
ኡኡታህ መንኮራኩርክን ፣ እስኪያሰጥመው አጓራበት
ጭንቅላትክን ግዘፍበት ፣ ውቀጥበት ፣ ውገርበት ፣ ....
ዝግ ብሎማ ያሰበ እንደሁ ፣ ይነግርሃል አንዳች እውነት !
----------

ታምራት ላይኔና አማረ (ክፍል-2)

                                                 (ከኢየሩሳሌም አ.)
     አማረ አረጋዊ በማስታወቂያ ሚ/ር የኢቲቪ ስራ አስኪያጅ ሃላፊ እያለ በጣም አፀያፊ ተግባራትን በየእለቱ ይፈፅም ነበር። እሱ...ን ጨምሮ አራት የሕወሐት ሃላፊዎች ተመሳሳይ ወራዳ ተግባር ይፈፅሙ ነበር፤ አንዱ ዋሽንግተን የሚገኝና የፓርቲው ሰላይ ሲሆን አንዱ የሻዕቢያ ተላላኪ ሆኖዋል፤ ሌላው ሹም በርካታ ሴቶችን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ ሆን ብሎ በማስያዝ አገር ቤት እንዳለ (እስከ 2000ዓ.ም) አውቃለሁ፤ አሁን ግን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ መረጃው የለኝም።…
በወቅቱ ባለስልጣን የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ጉዳዩን ሰምተው አማረን ግምገማ ይጠራሉ፤ ቃል በቃል እገልፀዋለሁ፥ « አማረ ቢሮ ውስጥ (office sex) ትፈፅማለህ፤ ..» በማለት በማስረጃ አስደግፈው ሲነግሩት፣ የሰጠው መልስ ፥ « በረሃ አይደለም ያለሁት፤ ስራዬን እስካልበደልኩ ድረስ የፈለኩትን ማድረግ እችላለሁ፤ መብቴ ነው..» የሚል ነበር። በዚህም ምክንያት በታምራት ትእዛዝ አማረ ከሃላፊነት እንዲነሳ ተደረገ።.. በእርግጥ አማረ ኢቲቪ እያለ ለጋዜጠኞችና ለፕሮግራም አዘጋጆች ሙያዊ ነፃነት በመስጠት በኩል ስሙ በበጎ የመነሳቱን ያክል፣ በአንፃሩ ለዜና አንባቢነት..ወዘተ ለመቀጠር የምትመጣ ሴት እንደግዴታ የሚቀርብላት ገላዋን ለአማረ <ማቅረብ> ነበር። በሕዝብ የሚታወቁና የተጎበኙ በዝርዝር ማንነታቸውን መግለፅ ቢቻልም ለዛሬው ማለፍን መረጥኩ። በነገራችን ላይ አንድ ሴት በግሩፕ ጭምር ቢሮ ውስጥ ያማግጡ እንደነበር ሳልጠቁም አላልፍም።…በተጨማሪ በወቅቱ የማ/ሚ/ር የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ « ዳንዲ» በሚለው መፅሃፍ እንደገለፁት « በስነምግባር ጉድለት የተገመገሙና እርምጃ የተወሰደባቸው እንዳሉ..» ጠቁመው ነበር። ያውም በጨዋ አገላለፅ!! ስም ግን አልጠቀሱም። አንዱ ግን አማረ ነበር።….
አማረ በአቶ ታምራት ውሳኔ በተላለፈበት ሰሞን እንዳጋጣሚ አቶ መለስ ለጉብኝት አውሮፓ ነበሩ። ሲመለሱ የጠየቁት « አማረ የታለ?» ብለው ነበር። የተፈጠረው ሁኔታ ተነገራቸው። አማረን አስጠርተው አነጋገሩት። ከዛም አማረ ጋዜጣ መጀመር እንደሚፈልግ ገለፀ። በሃሳቡ ተስማሙ። ጋዜጣው «እንደ መነፅር ሆኖ መንግስትን፣ፓርቲውን..» ማገልገል እንዳለበት ተስማሙ። በአቶ መለስ ቀጭን ትእዛዝ ለ<ሪፖርተር> ወይም « ኤም.ሲ.ሲ» ማስጀመሪያ አንድ ሚሊዮን ብር (በወቅቱ ምንዛሬ ከሁለት መቶ ሺህ የሚበልጥ ዶላር) እንዲፈቀድለት አደረጉ። ለገንዘቡ መፈቀድ የተሰጠው ሽፋን ወይም ምክንያት < የግልጋሎት ዘመን > የሚል ነበር። በአንፃሩ የእርሱን ሁለት ወንድሞች ጨምሮ 36ሺህ የፓርቲው ታጋዮች በመለስ ዜናዊ « ጓሓፍ » ወይም <ቁሻሻ> ተብለው ጎዳና በጅምላ የተጣሉት አንዳች ሳንቲም ሳይሰጣቸው ነበር። የትና ለማን ነው አማረ ያገለገለው?..ስንት አመት?..ሴቶች እህቶቻችን <ገላ> ላይ እንዳሻው <ስለተገለገለ> ?...የሚሉ አስገራሚ ጥያቄዎች መነሳታቸው ግድ ነው።
ያም ሆነ ይህ አማረ ከመለስ በተበጀለት የህዝብ ገንዘብ ..በግል ፕሬስ ሽፋን የሚነግድበትን <ጋዜጣ> ጀመረ። እንደተባለው <መነፅር> ሆኖ ቀጠለ። የአየር መንገድ ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አህመድ ቀሎ ከሃላፊነት ሲነሱ በ<ጦቢያ> ጋዜጣ ላይ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ « እኔን ያባረረኝ መንግስት ሳይሆን..ለመንግስት መስተዋት ሆኖ በሚያገለግለው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው» ብለው ነበር።…አማረ ሲበዛ ቂመኛ ሰው ነው፤ ታምራት ላይኔን እስኪበቃው በጋዜጣው ተበቅሏቸዋል። ከታሰሩ በኋላ ፥ < ከመኖሪያ ቤታቸው ቁምሳጥን ውስጥ የተገኘ የፍቅር ደብዳቤ…» እያለ በየሳምንቱ ዘምቶባቸዋል።
(ይቀጥላል)

Wednesday, 20 March 2013

የእግዚአብሔር ጥሪ

ድንገት ነው ባንኜ የነቃሁት፡፡ በሌሊት ወደ ጂቡቲ የሚጓዘው ባቡር ሲያልፍ የተኛሁባትን ትንሽዬ መደብ አንገጫገጫት፡፡ ሽንሌ ውስጥ አልለምድ ያልኩት ነገር ቢኖር የሚያፍነው ሙቀቷንና ይህን የባቡር ድምጽ ነው፡፡ ሰዓቴን ተመለከትኩ ከንጋቱ 11 ሰዓት ነው፡፡ የለበስኩት ልብስ በላቤ ከሰውነቴ ጋር ተጣብቆ ከባሕር አምልጬ የወጣሁ አስመስሎኛል፡፡ እንደ ምንም ተነሣሁና መስኮቱን ከፈትኩት የሌሊቱ ቀዝቃዛው ነፋስ በጆሮዬ ስር እያፏጨ ሲያልፍ የሚንጓጓ ነገር እንደሰማሁ ሁሉ ላዳምጠው ቆም አልኩ፡፡
በርበሬ የተደፋባት የምትመስለው ሰማይ ጥቁር ጃኖ ከደረበው ተራራ ጋር ወግ የያዘች ትመስላለች፡፡ ረጃጅሙ የበቆሎ እርሻ እርስ በርሱ እየተማታ ይቃለዳል፡፡ ራቅ ራቅ ብለው የቆሙት ያፈር ክዳን ጎጆዎች ግን የተከዙ ይመስላሉ፡፡
አይ ሽንሌ . . .
አሁን በዚህ ሰዓት እዚህ መሆኔን ሳስበው ግርም ይለኛል፡፡ ከመሃል አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተሰቦቼን ትቼ ክልል 5 በመምህርነት ስመደብ ፍጹም ሕይወቴ እንዲህ ይሆናል የሚል ዕምነት አልነበረኝም፡፡ ቤተሰቦቼ ርቀቱ ብቻ ታይቷቸው ሴትነቴም አሳስቧቸው አትሄጂም ሲሉኝ እኔ ደግሞ ሄጄ ልየው ብዬ ደስ ሳይላቸው ከቤቴ ወጣሁ፡፡ የክልል 5 ትምህርት ቢሮም “ሽንሌ” የምትባል ቦታ መድቦኝ ቦታዋን ያየኋት ዕለት የተሰማኝ ስሜት ግን እስከ ህይወቴ ፍጻሜ የምረሳው አይመስለኝም፡፡ ሻንጣዬን ይዤ ከመኪና ላይ እየወረድኩ “. . . ነገ ከዚህ አገር መውጣት አለብኝ” እላለሁ፡፡ ቤት ለመከራየት እየፈለኩ “እንዴት እኔ እዚህ አገር ውስጥ እኖራለሁ …?” እያልኩ አስባለሁ፡፡ ብቻ ውስጣዊውና ውጫዊው እኔነቴ አንድ መሆን አልቻለም፡፡ ውስጤ ሽንሌ የመኖሬን ነገር አምኖ አልተቀበለኝም፡፡ እንዲያውም ተጫዋችና ተግባቢ የነበርኩት ልጅ ዝምተኛና ጭምት፣ ስለ ምንም ነገር ላለማሰብ እራሴን በሥራ የምጠምድ ሰው ሆንኩ፡፡ መለወጤ ሲገባኝ ደግሞ ይበልጥ ይጨንቀኝ ጀመር፡፡ ሁሌም ወደ ትውልድ ሃገሬ ለመመለስ አስብና የምቀበለው የወር ደመወዜን እንዴት አንደማጠፋው ሳላውቅ ባዶዬን እቀራለሁ፡፡ “. . . በሚቀጥለው ወር ደመወዜን እንደተቀበልኩ . . . ” እላለሁ፡፡
አይ እኔ . . .? አሁን ሳስብ ግርም ይለኛል፡፡ ምንም ነገር እኮ አያስደስተኝም ነበር፡፡ ያገሬው ሕዝብ መሳቅ መቻሌን እንኳ ይጠራጠር ነበር፡፡
አንድ ቀን ነው ክፍል ገብቼ የማስተምርበት ሰዓት እስኪደርስ ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብዬ ፊቴን ኮሶ የጠጣ እንዳስመሰልኩት መጽሐፍ ላይ አፍጥጫለሁ፡፡ ማንበብ አስጠልቶኛል በዕለቱ እንደውም ክፍል ባልገባ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ቢሮ ውስጥ ያለችውን መምህርት ሕሊናን ቀና ብዬ አየኋት በተመስጦ ታነባለች፡፡ ታነብ . . . ታነብና ደግሞ በእርጋታ ትጽፋለች፡፡ እኔ ይህችን ልጅ ባየኋት ቁጥር ግርም ትለኛለች፡፡ በዚህ በረሃ ውስጥ ይሄ ሁሉ እርጋታ ከየት የመጣ ነው? ደግሞ ምን የሚያስደስት ነገር አለና ነው ከሁሉም ጋር በፈገግታና በሥርዓት የምትግባባው? ዐይኗ ስለከዳት ነው መሰል ቀና ስትል ዐይን ለዐይን ተጋጨን፡፡ እንደወትሮዋ ፈገግ ብላ “መስዬ ዛሬ ማንበብ አስጠልቶሻል ልበል? . . .” ትኩር ብላ እያየችኝ፡፡ “ሁሌም እንዳስጠላኝ ነው በንባቡ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ እዚህ በረሃ ውስጥ መኖሬንም አልወደድኩትም” አልኳት፡፡ ለምን? በሚል አስተያየት አየችኝ፡፡ “ምክንያቱም . . .’’ የሚሰማኝን ሁሉ ነገርኳት፡፡ ከልቧ አዘነች እናም ብዙ ብዙ ነገርን ነገረችኝ ፡፡ “እግዚአብሔር አምላክ አንቺ ስለ አንቺ ከምታስቢው የበለጠ ያስብልሻል” አለችኝ፡፡ “ራስሽን ከምትወጂው የበለጠ ይወድሻል፡፡ ፈጥኖ እዚህ ያደረሰን አምላክ ችላ የሚለን አይምሰልሽ እዚህ ያመጣን ለምክንያት ነው” አለችኝ፡፡ አነጋገሯ ልቤን ነካው፡፡ ሽንሌ ከገባሁ ተመስጬ የሰማሁት የሕሊናን ንግግር ነበር፡፡ ከዚህች ቀን በኋላ እየተቀራረብን መጣን፡፡ ቤተሰቤ ጋር እያለሁ በበዓላት ጊዜ ብቻ የማውቃትን ቤተክርስቲያን ቤተክርስቲያን በሌለበት አሕዛብ በበዛበት በዚያች በረሃ ሆኜ በጭንቅላቴ ትስልብኝ ጀመር፡፡ እግዚአብሔር ጥሪው በተለያየ መንገድ ነው፡፡ አገሬ እያለሁ የሞቀ አልጋ ውስጥ ሆኜ የምሰማው የቅዳሴ ድምጽ ዛሬ ያንገበግበኝ ጀመር፡፡ ቤተክርስቲያን ገብቼ ማስቀደስ ሳይሆን ቁጭ ብዬ ፀጥታውን ብቻ መስማት ናፈቀኝ፡፡
አይ ሽንሌ . . . ቤተ ክርስቲያን ባይኖርም ስለ ቤተክርስቲያን ያወቅሁት እዚህ ነበር፡፡ ተንቀሳቃሽ የሕይወት መጽሐፍ የሆኑት፣ ሁሌም ተነበው የማያልቁት በጣም ጥቂት ግን ጠንካራዎቹ የሽንሌ ክርስቲያኖችን መቼም አልረሳቸውም፡፡ ዘወትር ከቀኑ 11፡30 ሰዓት ላይ በትንሿ አፈር ቤት ውስጥ በእመቤታችን፣ በፃድቃንና ሰማዕታት ሥዕል ፊት ቆመው ውዳሴ ማርያም ያደርሱና የሚያስተምራቸው ካገኙ ተምረው አልያም መዝሙር ዘምረው ይለያያሉ፡፡ መተሳሰባቸውን፣ ብርታታቸውን፣ ፅናታቸውን ሳስብ በመጽሐፍ ብቻ የማውቀው የአባቶቻችን ታሪክ ዛሬም በዘመናችን እንዳለ አስባለሁ፡፡ ገና መሰባሰብ የጀመሩ ሰሞን አሕዛቡ “እዚህ ቤተክርስቲያናቸውን ሊሠሩብን ነው” ብለው በድንጋይ ሲያሳድዷቸው፣ የልጆቻቸውን የአንገት ማተብ እየበጠሱ ሲያስለቅሷቸው “አምላከ እስጢፋኖስ እኛንም አፅናን” ሲሉ በቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ ዕለት፣ ወር በገባ 17 የቅዱስ እስጢፋኖስን ፅዋ ይጠጡ ጀመር፡፡ እርሱ በድንጋይ ተወግሮ እንደሞተ እኛም የእርሱ ልጆች ነን ሲሉ፡፡
ይህ ሁሉ ለኔ አዲስ ነበር፡፡ እኔ ደስታ ማለት ባማረ ቤት ውስጥ መኖር የላመ የጣመ ተመግቦ መኖርና አማርጦ መልበስ ይመስለኝ ነበር፡፡ ግን እየተራቡ መጥገብ፣ ሳይጠጡ መርካት፣ በድካም ውስጥም እረፍት፣ በመከራ ውስጥም ደስታ እንዳለ ተረዳሁ፡፡ ዛሬ ከምንም በላይ እርጋታና ሰላም ይሰማኛል፡፡ ቤተክርስቲያን ባይኖርም ሁሌ ተገናኝተን በእመቤታችን ሥዕል ሥር የምንጸልየው ጸሎት፣ ዘምረን የምንለያየው መዝሙሮች ለእኔ አዲስ ህይወት ሆነውኛል፡፡ እውነተኛ መተሳሰቡና መከባበሩ በእርግጠኝነት በአሕዛብ መከበባችንን አስረስተውኛል፡፡ “ . . . ያለ ምክንያት አልመጣንም . . .” ነበር ያለችኝ ሕሊና?.... እውነቷን ነበር፡፡
ደማቋ ፀሐይ በጠዋቱ ፏ ብላ ወጥታለች፡፡ ከርቀት የከብቶች ድምጽ ይሰማኛል፡፡ ሰዓቴን ተመለከትኩ 11፡30 ፡፡ በፍጥነት መለባበስ ጀመርኩ ዛሬ እኮ እሑድ ነው ከጠዋቱ 12፡00 ላይ የጸሎት መርሃ ግብር አለን በዚያች በትንሿ የአፈር ቤታችን፡፡               ወስብሃት ለእግዛቤር

Tuesday, 19 March 2013

የአማረ አረጋዊ ገመና ሲጋለጥ


                                                     (ከኢየሩሳሌም አ.)
አዲስ አበባ አየር ማረፊያ፣ ነሃሴ 13 ቀን 1997ዓ.ም ፣ ምሽት 2 ሰዓት…ለእረፍት መጥቶ የነበረ ጓደኛዬን ለመሸኘት በስፍራው ተገኝቻለሁ። ..እንዳጋጣሚ በቅርብ ርቀት የ<ሪፖርተር> ጋዜጣ ባለቤት አማረ አረጋዊን አየሁት፤ ወደርሱ አምርቼ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ < ወደ አሜሪካ ለእረፍት የላከውን ልጁን ለመቀበል እንደተገኘ > ገለፀልኝ። …ከዛም ወደ ወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት በመግባት ወሬ ቀጥልን፤ በመሃከሉ አማረ ፥ « ..ሲሳይና እስክንድር የጋዜጠኝነት ካባቸውን አውልቀው ለምን በግልፅ ፖለቲከኛ አይሆ...ኑም? » ሲል በሹፈት አይነት ጠየቀኝ። « ምን ማለት ነው?» ስል መልሼ ጠየቅኩት፤ ..« በግልፅ የሚፅፉትን አታይም እንዴ?..የቅንጅት ዋና አቀንቃኞች ሆነዋል እኮ..» ካለ በኋላ አያያዘና « ..ይህችን አገር ልደቱና ሃይሉ ሻውል እንዲመሯት ነው የሚፈልጉት?...ልደቱ ነው አገር ለመምራት የሚቀመጠው?..» ሲል ያቺ የማውቃት የአማረ ፌዝና ሹፈት ፈገግታ በስሱ እያሳየኝ፤ …በዛ ሰሞን አማረ <አቋሙን> ይፋ አውጥቶ በቅንጅትና በጋዜጦች በተለይም በኢትኦጵና ምኒልክ ጋዜጦች ላይ በየሳምንቱ ..ለገዢው ፓርቲ የወገነ የቃላት ጦርነት የገጠመበት ወቅት ነበር።
አዳምጬው ሳበቃ እንዲህ አልኩት፥ « አማረ በምርጫው ማግስት ምን ብለህ ነበር የፃፍከው?..የሽግግር መንግስት ይቋቋም..ብለህ አልነበር?.. አሁን አቋምህን ለምን እንደቀየርክ አውቃለሁ!..» ስለው አይኑን በልጥጦ፥ « ምንድነው የምታውቀው?» አለኝ።.. < አዜብ መስፍን በቢቲ ማስታወቂያ ባለቤት ፀጋዬ በኩል አስጠርታህ ሌላ አራተኛ ሰው ጭምር ባለበት ምንድነውየተነጋገራችሁት?..አዜብ ከባለቤቷ የተላከ መልክት ነገረችህ፤ እንዲህ ስትል፥ « ሁሉም ጋዜጦችና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተጠራርገው እስር ቤት ይገባሉ። አንተም መግባት ትፈልጋለህ ወይ?..በማለት መለስ ንገሪው ብሎኛል፤» ብላ ነግራሃለች። ከዛም አቋምህን ቀየርክ፤ » አልኩት።...ግንባሩን አጨማዶ ገላመጠኝ። ..አያያዝኩና፥ « ደግሞስ አገሪቷን ማን ይምራ ነው የምትለው?..ሕዝብ የመረጠው ማንም ይሁን ማን…ድምፁ መከበር አለበት። አንተ ግን ካለ ሕወሐት/መለስ ሌላ ሊመራ አይችልም ..እያልክ ነው..» አላስጨረሰኝም..ጥሎኝ ሄደ። በወቅቱ ጉዳዩን በኢትኦጵ ጋዜጣ ላይ ፃፍኩት..
አማረ፥ ከማስታወቂያ ሚ/ር ለምን፣ እንዴትና በማን ተባረረ?...« ሪፖርተር » ጋዜጣ በመለስ ዜናዊ <ልዩ> ትእዛዝ እንደተቋቋመ ያውቃሉ?..አሁን የቲቪ ስርጭት እንዴትና በማን ትእዛዝ ሊጀምር ቻለ?...ከነደብረፂዮን ጀርባ በምስጢር የሚሰጠው ድጋፍና ለፓርቲው የሚያደርገው ስውር ተጋድሎ….በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ እመለስበታለሁ።

Monday, 18 March 2013

ሃገሬ ............የገብረክርስቶስ ደስታ ግጥም።



አገሬ ውበት ነው...........
ለምለምና ነፋስ የሚጫወትበት
ጸሃይ የሞላበት፣ ቀለም የሞላበት።
አገሬ ቆላ ነው፣ ደጋ ወይና ደጋ
እዚያ ብርሃን አለ ሌሊቱ ሲነጋ።
አገሬ ተራራ ሸለቆ ረባዳ
አገሬ ጅረት ነው ገደልና ሜዳ።
ውሸት ነው በበጋ ጸሃይ አትፋጅም
ክረምቱም አይበርድም፣
አይበርድም፣ አይበርድም።
አገሬ ጫካ ነው
እንሰሳት አራዊት የሚፈነጩበት
በወጥመድ ሳይገቡ ሳይነካቸው ጠላት።
እዚያ አለ ነጻነት።
በሃገር መመካት፣
በተወላጅነት፣
በባለቤትነት፣
እዚያ አለ ነጻነት።
አገሬ ሃብት ነው።
ጎመኑ ስብ ጮማ፣ ቆሎ ክትፎ ስጋ
ድርቆሹ ፍትፍት ነው፣ ቃሪያው ሙክት ሠንጋ።

Sunday, 17 March 2013

የፋሽስቱ ግራዚያኒን ሐውልት መሠራት ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ በአ.አ. ታሰሩ

የፋሽስቱ ግራዚያኒን ሐውልት መሠራት ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ በአ.አ. ታሰሩ
”ይህ የጤንነት አይመስለኝም!” ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም
(እሁድ መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም. March 17, 2013)፦ የፋሽስቱን ግራዚያኒ ሐውልት በጣሊያን ሀገር በመሠራት ላይ መሆኑን በመቃወም በአዲስ አበባ ሰልፍ ለማድረግ የወጡ ከ35 በላይ ኢትዮጵያውያን ታሰሩ። ከእነዚህም ውስጥ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም፣ አቶ ታዲዮስ ታንቱ፣ እንዲሁም የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ይልቃል ጌትነት ጨምሮ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አመራር አባላት በዛሬው ዕለት ታስረዋል።
ይህንኑ በጣሊያን ሀገር አፎል ከተማ በግፈኛው ግራዚያኒ ስም ሙዚየምና ሐውልት መሠራቱን በመቃወም ዛሬ ስድስት ኪሎ ከሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት በመነሳት እስከ ጣሊያን ኤምባሲ ድረስ ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የተቃውሞ ሰልፉን የጠሩት “ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽ ኮሚቴ”፣ “ሰማያዊ ፓርቲ” እና “ባለራዕይ ወጣቶች ማኅበር” ነበሩ። እነዚህን ሠላማዊ ዜጎች ያሰሯቸው የፌዴራል ፖሊሶች ሲሆኑ፤ ለእስሩም ምክንያት የሰጧቸው “የሰልፍ ፈቃድ የላችሁም” በሚል እንደሆነ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የደረሰው መረጃ ያስረዳል። ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጆቹ በሕጉ መሠረት ለሚመለከተው አካል ሰልፍ እንደሚያካሂዱ አሳውቀው እንደነበር ለማወቅ ችለናል።
ከሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ስለሺ ፈይሳ፣ የሕግ ጉዳይ ኃላፊው አቶ ይድነቃቸው ከበደ፣ የፓርቲው የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ ወ/ሮ ሃና ዋለልኝ፣ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ያቶ ጌታነህ ባልቻ መታሰራቸው ታውቋል። ከባለራዕይ ወጣቶች ማኅበር ውስጥ ደግሞ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበሩ አቶ ብርሀኑ ተክለያሬድ፣ የማኅበሩ ዋና ፀሐፊ አቶ ያሬድ አማረ የታሰሩ ሲሆን፤ እስካሁን የታሳሪዎቹ ቁጥር ከ35 በላይ ሲሆን፣ የታሰሩትም ገዳም ሰፈር በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ መሆኑን ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።
ሠላማዊ ሰልፉ የተጠራው “የጣሊያ ፋሽስት እንደራሲ በኢትዮጵያ የነበረው ፊደል ማርሻል አዶልፍ ግራዚያኒ በህዝባችን ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋና ግፍ ታሪክ ከመዘገበው በላይ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ሆኖ ሳለ ለዚህ ግፈኛ ፋሺስት በጣሊያኗ አፊል ከተማ ሙዚየምና ሀውልት በስሙ ተገንብቶለታል። ይህ ድርጊትም የኢጣሊያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን ንቀት የሚያሳይ በመሆኑ በዕለቱ ማለትም መጋቢት 8 ቀን ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ማንኛውም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ሰማዕታት ሀውልት ዙሪያ በመሰባሰብ የዚህ ሠላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ እንዲገኙ በግፍ ባለቁ ኢትዮጵያዊያን ስም በአክብሮት ተጋብዘዋል።” በሚል እንደሆነ ታውቋል።
ይህን የዛሬውን የፌዴራል ፖሊስን ድርጊት አስመልክቶ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም በፌስ ቡክ ገጻቸው የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።
“የዛሬው ጉድ ነው፤ በኢጣልያ የግራዚያኒ ሐውልት እየተሠራ መሆኑን ለመቃወም የተለያዩ አገር ወዳድ ወጣቶች ከስድስት ኪሎ ወደኢጣልያ ኤምባሲ ሰልፍ ለማድረግ ጠርተው ነበር። ግራዚያኒ በየካቲት አሥራ ሁለት በቦምብ ካቆሰለ በኋላ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያስጨፈጨፈ አረመኔ ፋሺስት ነበር። ለዚህ ሰው ኢጣልያኖች ሐውልት መሥራታቸው የዛሬውን የኢትዮጵያ ትውልድ መናቅ ብቻ ሳይሆን ከኢጣልያ ጋር የተዋደቁትን ኢትዮጵያውያን ማዋረድ ነው፤ ስለዚህ ዛሬ መጋቢት 8/2005 ተቃውሞ ለማሳየት ታቅዶ ነበር። ፖሊሶች ሰልፉ እንዳይደረግ መከልከል ይችሉ ነበር፤ የተሰበሰቡትን በሰላማዊ መንገድ መበተን ይቻል ነበር። ፖሊሶች የመረጡት እየያዙ ማሰርን ሆነ። በአሁኑ ጊዜ ብዙ ወጣቶች ሴቶችና ወንዶች በየፖሊስ ጣቢያዎች ታስረዋል። ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያምንም ይዘውታል። በዓይኔ ባላየው ለማመን ትንሽ ያስቸግረኝ ነበር። እንዲያውም የተያዙትን ለመጠየቅ ሄጄ፤ የፖሊስ ጣቢያው በር ላይ ያገኘሁትን ነጭ ለባሽ ዛሬ የታሰሩ ሰዎች እዚህ መጥተዋል ወይ ብዬ ብጠይቀው “ምናባክ አውቅልሃለሁ፣ ግባና ጠይቅ” አለኝ። በሩ ላይ የነበሩ ሴት ፖሊሶች “አለቆቹ ስለሌሉ በኋላ ተመለስ” አሉኝ። ለማናቸውም እስረኞቹ በረንዳ ላይ ታጉረው አየኋቸው። እኔ ይህ የጤንነት አይመስለኝም!”