"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Wednesday 20 March 2013

የእግዚአብሔር ጥሪ

ድንገት ነው ባንኜ የነቃሁት፡፡ በሌሊት ወደ ጂቡቲ የሚጓዘው ባቡር ሲያልፍ የተኛሁባትን ትንሽዬ መደብ አንገጫገጫት፡፡ ሽንሌ ውስጥ አልለምድ ያልኩት ነገር ቢኖር የሚያፍነው ሙቀቷንና ይህን የባቡር ድምጽ ነው፡፡ ሰዓቴን ተመለከትኩ ከንጋቱ 11 ሰዓት ነው፡፡ የለበስኩት ልብስ በላቤ ከሰውነቴ ጋር ተጣብቆ ከባሕር አምልጬ የወጣሁ አስመስሎኛል፡፡ እንደ ምንም ተነሣሁና መስኮቱን ከፈትኩት የሌሊቱ ቀዝቃዛው ነፋስ በጆሮዬ ስር እያፏጨ ሲያልፍ የሚንጓጓ ነገር እንደሰማሁ ሁሉ ላዳምጠው ቆም አልኩ፡፡
በርበሬ የተደፋባት የምትመስለው ሰማይ ጥቁር ጃኖ ከደረበው ተራራ ጋር ወግ የያዘች ትመስላለች፡፡ ረጃጅሙ የበቆሎ እርሻ እርስ በርሱ እየተማታ ይቃለዳል፡፡ ራቅ ራቅ ብለው የቆሙት ያፈር ክዳን ጎጆዎች ግን የተከዙ ይመስላሉ፡፡
አይ ሽንሌ . . .
አሁን በዚህ ሰዓት እዚህ መሆኔን ሳስበው ግርም ይለኛል፡፡ ከመሃል አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተሰቦቼን ትቼ ክልል 5 በመምህርነት ስመደብ ፍጹም ሕይወቴ እንዲህ ይሆናል የሚል ዕምነት አልነበረኝም፡፡ ቤተሰቦቼ ርቀቱ ብቻ ታይቷቸው ሴትነቴም አሳስቧቸው አትሄጂም ሲሉኝ እኔ ደግሞ ሄጄ ልየው ብዬ ደስ ሳይላቸው ከቤቴ ወጣሁ፡፡ የክልል 5 ትምህርት ቢሮም “ሽንሌ” የምትባል ቦታ መድቦኝ ቦታዋን ያየኋት ዕለት የተሰማኝ ስሜት ግን እስከ ህይወቴ ፍጻሜ የምረሳው አይመስለኝም፡፡ ሻንጣዬን ይዤ ከመኪና ላይ እየወረድኩ “. . . ነገ ከዚህ አገር መውጣት አለብኝ” እላለሁ፡፡ ቤት ለመከራየት እየፈለኩ “እንዴት እኔ እዚህ አገር ውስጥ እኖራለሁ …?” እያልኩ አስባለሁ፡፡ ብቻ ውስጣዊውና ውጫዊው እኔነቴ አንድ መሆን አልቻለም፡፡ ውስጤ ሽንሌ የመኖሬን ነገር አምኖ አልተቀበለኝም፡፡ እንዲያውም ተጫዋችና ተግባቢ የነበርኩት ልጅ ዝምተኛና ጭምት፣ ስለ ምንም ነገር ላለማሰብ እራሴን በሥራ የምጠምድ ሰው ሆንኩ፡፡ መለወጤ ሲገባኝ ደግሞ ይበልጥ ይጨንቀኝ ጀመር፡፡ ሁሌም ወደ ትውልድ ሃገሬ ለመመለስ አስብና የምቀበለው የወር ደመወዜን እንዴት አንደማጠፋው ሳላውቅ ባዶዬን እቀራለሁ፡፡ “. . . በሚቀጥለው ወር ደመወዜን እንደተቀበልኩ . . . ” እላለሁ፡፡
አይ እኔ . . .? አሁን ሳስብ ግርም ይለኛል፡፡ ምንም ነገር እኮ አያስደስተኝም ነበር፡፡ ያገሬው ሕዝብ መሳቅ መቻሌን እንኳ ይጠራጠር ነበር፡፡
አንድ ቀን ነው ክፍል ገብቼ የማስተምርበት ሰዓት እስኪደርስ ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብዬ ፊቴን ኮሶ የጠጣ እንዳስመሰልኩት መጽሐፍ ላይ አፍጥጫለሁ፡፡ ማንበብ አስጠልቶኛል በዕለቱ እንደውም ክፍል ባልገባ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ቢሮ ውስጥ ያለችውን መምህርት ሕሊናን ቀና ብዬ አየኋት በተመስጦ ታነባለች፡፡ ታነብ . . . ታነብና ደግሞ በእርጋታ ትጽፋለች፡፡ እኔ ይህችን ልጅ ባየኋት ቁጥር ግርም ትለኛለች፡፡ በዚህ በረሃ ውስጥ ይሄ ሁሉ እርጋታ ከየት የመጣ ነው? ደግሞ ምን የሚያስደስት ነገር አለና ነው ከሁሉም ጋር በፈገግታና በሥርዓት የምትግባባው? ዐይኗ ስለከዳት ነው መሰል ቀና ስትል ዐይን ለዐይን ተጋጨን፡፡ እንደወትሮዋ ፈገግ ብላ “መስዬ ዛሬ ማንበብ አስጠልቶሻል ልበል? . . .” ትኩር ብላ እያየችኝ፡፡ “ሁሌም እንዳስጠላኝ ነው በንባቡ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ እዚህ በረሃ ውስጥ መኖሬንም አልወደድኩትም” አልኳት፡፡ ለምን? በሚል አስተያየት አየችኝ፡፡ “ምክንያቱም . . .’’ የሚሰማኝን ሁሉ ነገርኳት፡፡ ከልቧ አዘነች እናም ብዙ ብዙ ነገርን ነገረችኝ ፡፡ “እግዚአብሔር አምላክ አንቺ ስለ አንቺ ከምታስቢው የበለጠ ያስብልሻል” አለችኝ፡፡ “ራስሽን ከምትወጂው የበለጠ ይወድሻል፡፡ ፈጥኖ እዚህ ያደረሰን አምላክ ችላ የሚለን አይምሰልሽ እዚህ ያመጣን ለምክንያት ነው” አለችኝ፡፡ አነጋገሯ ልቤን ነካው፡፡ ሽንሌ ከገባሁ ተመስጬ የሰማሁት የሕሊናን ንግግር ነበር፡፡ ከዚህች ቀን በኋላ እየተቀራረብን መጣን፡፡ ቤተሰቤ ጋር እያለሁ በበዓላት ጊዜ ብቻ የማውቃትን ቤተክርስቲያን ቤተክርስቲያን በሌለበት አሕዛብ በበዛበት በዚያች በረሃ ሆኜ በጭንቅላቴ ትስልብኝ ጀመር፡፡ እግዚአብሔር ጥሪው በተለያየ መንገድ ነው፡፡ አገሬ እያለሁ የሞቀ አልጋ ውስጥ ሆኜ የምሰማው የቅዳሴ ድምጽ ዛሬ ያንገበግበኝ ጀመር፡፡ ቤተክርስቲያን ገብቼ ማስቀደስ ሳይሆን ቁጭ ብዬ ፀጥታውን ብቻ መስማት ናፈቀኝ፡፡
አይ ሽንሌ . . . ቤተ ክርስቲያን ባይኖርም ስለ ቤተክርስቲያን ያወቅሁት እዚህ ነበር፡፡ ተንቀሳቃሽ የሕይወት መጽሐፍ የሆኑት፣ ሁሌም ተነበው የማያልቁት በጣም ጥቂት ግን ጠንካራዎቹ የሽንሌ ክርስቲያኖችን መቼም አልረሳቸውም፡፡ ዘወትር ከቀኑ 11፡30 ሰዓት ላይ በትንሿ አፈር ቤት ውስጥ በእመቤታችን፣ በፃድቃንና ሰማዕታት ሥዕል ፊት ቆመው ውዳሴ ማርያም ያደርሱና የሚያስተምራቸው ካገኙ ተምረው አልያም መዝሙር ዘምረው ይለያያሉ፡፡ መተሳሰባቸውን፣ ብርታታቸውን፣ ፅናታቸውን ሳስብ በመጽሐፍ ብቻ የማውቀው የአባቶቻችን ታሪክ ዛሬም በዘመናችን እንዳለ አስባለሁ፡፡ ገና መሰባሰብ የጀመሩ ሰሞን አሕዛቡ “እዚህ ቤተክርስቲያናቸውን ሊሠሩብን ነው” ብለው በድንጋይ ሲያሳድዷቸው፣ የልጆቻቸውን የአንገት ማተብ እየበጠሱ ሲያስለቅሷቸው “አምላከ እስጢፋኖስ እኛንም አፅናን” ሲሉ በቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ ዕለት፣ ወር በገባ 17 የቅዱስ እስጢፋኖስን ፅዋ ይጠጡ ጀመር፡፡ እርሱ በድንጋይ ተወግሮ እንደሞተ እኛም የእርሱ ልጆች ነን ሲሉ፡፡
ይህ ሁሉ ለኔ አዲስ ነበር፡፡ እኔ ደስታ ማለት ባማረ ቤት ውስጥ መኖር የላመ የጣመ ተመግቦ መኖርና አማርጦ መልበስ ይመስለኝ ነበር፡፡ ግን እየተራቡ መጥገብ፣ ሳይጠጡ መርካት፣ በድካም ውስጥም እረፍት፣ በመከራ ውስጥም ደስታ እንዳለ ተረዳሁ፡፡ ዛሬ ከምንም በላይ እርጋታና ሰላም ይሰማኛል፡፡ ቤተክርስቲያን ባይኖርም ሁሌ ተገናኝተን በእመቤታችን ሥዕል ሥር የምንጸልየው ጸሎት፣ ዘምረን የምንለያየው መዝሙሮች ለእኔ አዲስ ህይወት ሆነውኛል፡፡ እውነተኛ መተሳሰቡና መከባበሩ በእርግጠኝነት በአሕዛብ መከበባችንን አስረስተውኛል፡፡ “ . . . ያለ ምክንያት አልመጣንም . . .” ነበር ያለችኝ ሕሊና?.... እውነቷን ነበር፡፡
ደማቋ ፀሐይ በጠዋቱ ፏ ብላ ወጥታለች፡፡ ከርቀት የከብቶች ድምጽ ይሰማኛል፡፡ ሰዓቴን ተመለከትኩ 11፡30 ፡፡ በፍጥነት መለባበስ ጀመርኩ ዛሬ እኮ እሑድ ነው ከጠዋቱ 12፡00 ላይ የጸሎት መርሃ ግብር አለን በዚያች በትንሿ የአፈር ቤታችን፡፡               ወስብሃት ለእግዛቤር

No comments:

Post a Comment