"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Thursday 15 November 2012

ስማችንን ተውልን ወለላዬ ከስዊድን


ተሹመሃል አሉ ሰማን …እንደው ሥልጣንህ ምን ይሆን?
ስምህ ተለውጦ ተሾምክ?  ወይስ በዛው ላይ ደረብክ?
ከለወጡህስ ማን አሉህ?   በምንስ አጥበው አለቀለቁህ?
ለምንስ አንተን ፈለጉ      እንዳይቀር ይሆን የሥልጣን ወጉ?
ቃለ መላህንም ሰማን፣               ወሬ አይደበቅ ነገሩን
የሳቸውን ራዕይ ላሟሽ            ኢትዮጵያዊነትን ላኮላሽ
ዘለአለማዊ ሕይወታቸውን መስክሬ     ኃይልና ሥልጣናቸውን አክብሬ
በሳቸው ድርጅት እጠለላለሁ        እንደጻፉልኝ አነባለው                                                                                                             እንዳሳደሩኝ ውዬ አድራለሁ        ብለህ ነው አሉ የሾሙህ
ይሄ ነው አሉ መኃላህ    አጀብ! ጉድህን ሰማንልህ
ይሄን ታዲያ ምን ብዬ ለእናታችን ላውራት?      እንዴት ብዬ ልንገራት?
በዕድሜዋ የመጨረሻ ዘመን፣      አንተን በመውለዷ እንዴት ትዘን፣
እንዴትስ ይሄን ጉድ ተሸክማ፣    መቃብር ትውረድ እማማ
እባክህን ስሟን ብቻ ተውላት፣        የሱ እናት ናት አታስብላት
እንኳን እሷ የሞተው አባባ፣           ባንተ ተግባር ስሙ በመቃብር ቢጠነባ፣
ዛሬ ነው የሞተው ተብሎ ፈሰሰለት ትኩስ ዕንባ          አዎን! ዛሬ ነው የሞተው፣
አጥንቱን ሳይቀር አስወቀስከው።        እኔም ወንድሙ ነው መባሉ፣
እያቅለሸለሸኝ ነው ቃሉ፣           እንዳተው ስደበቅ፣
እንዳተው ሰው ስርቅ            ኮርቶ ነው ይሄ ብጣሻም ተባልኩ፣
በምኔ ነው የምኮራ፣               አሳፍሮኝ እንጂ ባንተ ስም ስጠራ
እናም ሁሉም ይቅርብኝ፣               ወንድምነትህን ተወኝ፣      ስጋነትህን ፋቅልኝ
ያንተን ስም ማንሳት የጠሉት፣       እናንተ እኮ እያሉኝ በድፍረት      በጦር ዓይናቸው አጥንቴን ሳይቀር ወጉት
ከፊሉም ትቶኛል አኩርፎ፣        ያንተ ወንድም መሆኔን ተጠይፎ
አንዳንዱ ደግሞ አላጋጭ፣               ገና ሲያገኘኝ በግላጭ፣
እንደሰላምታ ትከሻዬን ገጭቶኝ፣          ወይም የመንከስ ያህል ስሞኝ፣
እንዴት ነው ቤት ቀየርክ?        መኪና ገዛህ ለወጥክ?         ልጆችህን ውጭ ላክ?
ብሎ በአበሻ ወግ ሽሙጡ፣     ይለመጥጠኛል በቅጡ
ሌላውማ አያድርስ ከቶ፣    አንተን ያገኘ ይመስል ደሙ ፈልቶ፣
ሊዘለዝለኝ ያምረዋል፣         ሊከታትፈኝ ይዳዳዋል
ምነው! አንተን አግኝቶ በገላገለን፣       የስምህ ክርፋት ከሚጠነባን፣
ሞትህ ነበር የሚሻለን።         ወይም ያኔ ድሮ ድሮ፣       የያዘህ በሽታ አሳርሮ፣      ምናለበት በገላገለህ በገላገለን ኖሮ።
ከለጠፍክብኝ አጉል ስም፣       ይሻለኝ የነበር የሟች ወንድም
አሁንም ከዚህ ስምህ አውጣኝ፣        ወንድምነትህን አንሳልኝ፣
ምንህንም አንፈልግ እኔና እናቴ፣        ከስምህ ብቻ አድነን በሞቴ
እኛን እኮ ነን ባንተ ጥፋት ህዝብ የሸነቆጠን፣       ባላጠፋን የቀጣን ባልበደልን የረገመን፣
አሁንም እባክህን ለኛ ስትል፣          አጎብዳጅነትህን እንቢ በል
ደ ግሞስ ያንተ ሹመት ለማነው የሚሆነው ተስፋ፣          እንዲህ በሃገርና በውጪ ስምህ እየከርፋ
እናታችንን ልታይ ስትመጣ በድብቅ፣        ጎረቤቱን አፍረን ከምንሳቀቅ
ምነው የደም ጮማህ ቀርቶብን በበላን አሹቅ      እናታችን ስሟ ተከብሮ፣
ሰዉ ወዷት እንደድሮ፣           እየበላች ሌጣ ሽሮ፣
መኖሩ ነው የሚሻላት፣        ካገር ከሰው አትነጥላት፣
እባክህን ስሟን ተዋት።       ትንሹ ልጃችን እንኳን ትምህርት ቤት፣
የእከሌ ልጅ እኮ ነው እያሉት፣          ሊጫወት ሲል እየሸሹት፣      እንዳዋቂ ነገር ገብቶት፣
ፈዞ ቀርቷል ጨምቶ፣      ልጅነቱን ተቀምቶ
እናም በቁሜ ነው የገደልከኝ ወንድሜ፣        በስምህ ተቀብቼ አለስሜ
ለኔና ለቤተሰባችን፣       ስምህን አንሳልን ከላያችን
እንደቢጤአችን እንኑር፣       ደስ ብሎን እንቸገር
ወንድምነትህ ላያኮራ፣          ሹመትህ ለሐገር ላይሰራ፣
እስከስምህ ተለየን፣           አንጠጋህ አትጠጋን
እንለያይ ወንድሜ፣            ይሻለኛል ደሃ ስሜ
ለናታችንም ስሟን መልስላት፣      የዛ እናት ናት አታስብላት፣      ካገር ከሰው አትነጥላት
የሥልጣንህ ክርፋታም ፍግ       መደበቂያ መሄጃ ጥግ፣
ከሚያሳጣን እኛን ተወን፣      ከህዝብ ጋር የኖርን ነን።
ይሄውና ወዳጅ ዘመድ፣      ና ካላልነው ጠርተን በግድ፣
እንዳያየን ፊቱን ዞሮ፣        ያልፍ ጀመር በኛው ጓሮ
የስም ክፉ ጥፈህብን፣    እንደኮሶ ተጣብተኸን፣
አድባር ሸሸን፣ ቆሌ እራቀን፣         እባክህን ስምክን ተወን።
ያልተወለደችህ እንኳን ባለቤቴ፣       በደወለች ቁጥር ያንተ እሜቴ
ድምጿን መስማት እየፈራች፣        እያለችም እቤት የለች።
እንደዚህ ነው ያሳፈርከን፣          መግቢያ መውጫ ያሳጣኸን
እናም ወዶ ገቡ ወንድሜ፣       የጎለትከኝ አለስሜ፣
እንደጫኑህ ሰቅለው ከቆጥ          እስኪያወርዱህ በመዘርጠጥ
እኛን ቀድመህ አትግደለን፣        ካገር ጉያ አታግልለን፣       ስማችንን ብቻ ተወን

የመለስ ውርስ እና ራዕይ

ሰሞኑን በመስቀል አደባባይ ሳልፍ የአዲስ አበባን 125ተኛ አመት አከባበር አስመልክቶ (የበአሉ አከባበር ራሱ ሌላ ጽሁፍ ይወጣዋል) አዲስ ቅርጻ ቅርጾች ተቀምጠው ተመልክቼ ነበር፡፡ እነዚህ የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾች (125 የሚል ጽሁፍ ሌላ 31 የሚል ምን ለማለት እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ የፈጀብኝ ሌላ ጽሁፍ የቀድሞው መሪ አቶ መለስ ፎቶ በእያንዳንዳቸው ላይ የተቀመጠባቸው ሌሎች ቅርጾች) ከሌላ ጊዜው በተጨማሪ የመለስን መንፈስ በአደባባዩ ሞልተውታል፡፡ በትልልቅ ባነሮች ብቻ ይታይ የነበረው የሟች ጠ/ሚኒስትሩ መስቀል አደባባይ ላይ መገኘት አሁን አደባባዩን መሬት ሞልቶታል፡፡ይህ በመስቀል አደባባይ እና በመላው አዲስ አበባ የሚታዩት የመለስ ምስሎችሁሉም ማለት ይቻላል ውርሳቸውን ለማስቀጠል እና ራእያቸው ስለማሳካት የሚያወሩ ናቸው፡፡ በእርግጥ ጥቂት መንፈሳዊ መልእክት መሰል መልእክት የያዙ ጽሁፎችም አልጠፉም( “ለህዝብ የተፈጠረ ለህዝብ የኖረ እና ለህዝብ የሞተ…”ከነዚህ ውስጥ ይጠቀሳል)

የአቶ መለስ ሞት በይፋ ከታመነበት ጊዜ አንስቶም ከፓስተሮች ጀምሮ እስከ ፓርላማው ውይይት ድረስ የሚነሳው ቃል ራእይ እና ውርስ(ሌጋሲ) ሆኗል፡፡ አገሪቷም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ራእይን የማሳካት ታላቅ የማሃላ ስነ ስርአት ላይ ያለች ይመስል ከሩጫ እስከ ቢሮ ስራ ከእንጀራ መጋገር እና ዝቅተኛ የስራ መስኮች ጀምሮ እስከ ታላላቅ ቦታዎች ተተኪ አመራሮች ድረስ “የእናሳካለን መሃላ”ን ስራችን አድርገን ይዘነዋል፡፡ የማይተማመን ባልጀራ ………ነገር ነው ብለን መደምደማችንን ብንተወው እንኳን ሁላችንም የምንግባባበት የአቶ መለስ ውርስ እና ራእይ አለ ወይ የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡
የውርስ እና ራዕይ ስብከት
አቶ መለስ ሞት በፊት ሲያቆጠቁጥ የነበረው ግለሰባዊ ገጽታ ግንባታቸው ተጠናክሮ ከሞታቸው በኋላ በሁሉም የመንግስት ሚዲያዎች አልፋና ኦሜጋ ሁሉን ቻይ ሆነው ቀርበዋል፡፡ በከፍተኛ የመንግስት አመራር ደረጃ ሳይቀር ከእርሳቸው ውጪ የሚሰራ ምንም ነገር እንዳልነበር ሲነገረን ከርሞአል፡፡ይህ የሃዘን ማግስት የሟች ገጽታ ግንባታ ደረጃውን በፍጥነት በማሳደግ ራእይህን እናሳካለን ውርስህን እናስቀጥላለን ወደሚል አገራዊ መሃላም ተቀይሯል፡፡ ይህ የራእይ እና የውርስ ማስቀጠል ማሃላ እና ስብከት ከተባበሩት መንግስታት ስብሰባ እስከ ፓርላማ፣ ከዜና እስከ ወረዳዎች አመራር ንግግር ሳይቀር ሲነገር እና ሲወራ ነበር፡፡ ሚዲያውም የካድሬዎችን ንግግር ቅርጽ በማስያዝ የራሱን ሚና ሲወጣ ነበር፡፡ ኢቲቪ እንኳን ከዜናው ጀርባ ታላቁን መሪ ካስቀመጠ ስንት ጊዜው?ለዛውም “ታላቁ አባታችን መከረን ……”ከሚል ጽሁፍ ጋር!!

አምባሳደር ተወልደ ዓጋመ ከፓርቲው ለቀቁ

(እየሩሳሌም አርአያ          የሕወሐት /ኰሚቴ አምባሳደር ተወልደ ገብሩ (በቅጽል ስማቸው ተወልደ ዓጋመ) በገዛ ፈቃዳቸው ከፓርቲው እንደለቀቁ ምንጮች አረጋገጡ። ባለፈው በተካሔደው የፓርቲው ጉባኤ ላይ የመልቀቂያ ጥያቄ አቅርበው ከማ/ኰሚቴ አባልነት እራሳቸውን እንዳገለሉ አስታውቀዋል። በአምባሳደርነት ሲያገለግሉ የቆዩት ተወልደ «አጋሜ» 1993.ም በሑዋላ ተዛውረው በአትሌቲክስ ፌዴረሽን ያለሙያቸው ተመድበው ቆይተዋል።
በተጨማሪ ባለቤታቸው ሮማን ገ/ስላሴ በፓርቲው ሊ/መንበር « አይኖዋን ማየት አልፈልግም» ተብለው ከፓርቲው ርቀው እንደነበር ምንጮቹ አስታውሰዋል። የሕወሃት አንጋፋ ሴት ታጋይ የነበሩት ሮማን የተሓድሶ «አቀንቃኝ» ሆነው ወደ መድረክ በመውጣታቸው በትግራይ የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ተደርገው በመለስ ከመሾማቸው ባሻገር በፓርቲው ማ/ኰሚቴ አባልነት መካተታቸውን ጠቁመዋል። አምባሳደር ተወልደ ለረጅም አመት ይበሳጩና ብዙውን ጊዜ በዝምታ ያሳልፉ እንደነበር የቅርብ ምንጮች ጠቁመው፤ እርሳቸው ከፓርቲው ሲለቁ ባለቤታቸው ሮማን ግን እንዳለቀቁ አያይዘው ገልጸዋል።
በሌላም በኩል በሕወሓት ማ/ኰሚቴ ዙሪያ ያለውን ቤተሰባዊ ስብስብ በተመለከተ የቅርብ ምንጮች እንዲህ ብለዋል፤
የሻዕቢያ ከፍተኛ የጦር አዛዥ ጄ/ል ስብሃት ኤፍሬም ባለቤት ታጋይ ሩት ሃይሌ ትባላለች። ሩት ሃይሌ እና የሕወሓቱ ሽማግሌ ስብሃት ነጋ የቅርብ ስጋ ዝምድና እንዳላቸው ምንጮች አረጋግጠዋል።
ሌላው ዶ/ር ሰለሞን እንቑይ ይጠቀሳሉ፤ ፓርቲውን የተቀላቀሉት በ1983.ም ሲሆን ቀደም ሲል በለንደን ይኖሩ ነበር።በወቅቱ የ «..» ሃላፊነት ቦታ ተቆናጠጡ። በ1993.ም የትግራይ አፈ-ጉባኤ ተደርገው ተሾሙ፤ የድርጅቱ ማ/ኰሚቴ አባልነትን ጨምሮ 5 ቁልፍ ሃላፊነቶችን እንዲጨብጡ ተደረገ። በ1994.ም መጋቢት ወር ከፓርቲው ልሳን ጋር በትግርኛ ቁዋንቑ ባደረጉት ቃለምልልስ አስመራ ተወልደው እንዳደጉ የገለጹት ዶ/ር ሰለሞን የሻዕብያው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ የአጎት ልጅ መሆናቸው ምንጮች አረጋግጠዋል።
1995.ም በመቀሌ በተነሳ ተቃውሞ፡ አምስት ሰላማዊ ነዋሪዎች መገደላቸውን ተከትሎ ፦ በሺህ የሚቆጠር ህዝብ የዶ/ር ሰለሞንን መኖሪያ ቤት ከማውደሙም በተጨማሪ « የሻዕብያ ወኪል እኛን አይመራንም» በሚል የተቃውሞ ድምጹን አሰምቶዋል። ( በነገራችን ላይ ይህ ጉዳይ « በኢትኦጵ» ጋዜጣ በወቅቱ በዝርዝር መረጃው ቀርቦ ነበር።)
ሌላው የሻዕቢያ አባል የነበረው ኤርትራዊው ሳሙኤል ገ/ማሪያም ሲጠቀስ፤ የ ጠ//ሩ አማካሪ ሆኖ የተመደበው በ1993.ም ነበር። ከሁለት አመት ቆይታ በሁዋላ የአድዋ ከተማ ዋና አስተዳዳሪ ተደርጎ ተዛወረ። በ1996.ም ወደ ኢሮብ ወረዳ ያቀናው ሳሙኤል የአካባቢውን ሕዝብ ሰብስቦ በአቶ መለስ በወቅቱ የረቀቀውን ባለ 5 ነጥብ አጀንዳ ተብዬ ለነዋሪው ለማስረዳት ይሞክራል።
በፅኑ ኢትዮጲያዊነቱና በጀግንነቱ የሚታወቀው የኢሮብና አካባቢዋ ነዋሪ የሳሙኤልን ማንነት አብጠርጥሮ በመናገርና አጀንዳውን በማብጠልጠል ተቃውሞ ያሰማል። ሳሙኤል ገ/ማሪያም ስብሰባውን በማቑዋረጥ በመጣበት ኮብራ መኪና ተሳፍሮ ጥቂት እንደተጉዋዘ.. በአካባቢው ነዋሪ በ12 ጥይት ተደብድቦ ተገደለ።
በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው የሚመሩት ወ/ሮ ሒሩት ናቸው። ኤርትራዊ የሆኑት ሒሩት የአባዲ ዘሞ ባለቤት ሲሆኑ፤ የሂሩት ወንድም እያብ (የቀድሞ መጠሪያ ስሙ ሱራፌል) ከአራት አመት በፊት ም/ሚንስትርና የጠ//ሩ አማካሪ ተደርጎ በመለስ መሾሙን ምንጮች ጠቁመዋል። ኤርትራዊው እያብ ትምህርት የሌለው፤ ምንም አይነት ችሎታና ብቃት እንደሌለው እየታወቀ ሃላፊነት በሚጠይቅ ትልቅ ቦታ መመደቡ አስገራሚ ነው ያሉት ምንጮች አሁንም በጠ//ር ሃ/ማሪያም ካቢኔ መቀጠሉን አክለው ገልጸዋል።
በማስከተል በሕወሓት ማ/ኰሚቴ ያለውን ቤተሰባዊ ግሩፕ ምንጮቹ እንደሚከተለው አስቀምጠዋል፤
ቅዱሳን ነጋ፡ ፀጋዬ በርሄ፡ ፈትለወርቅ ገ/እግዚያብሄር ከማ/ኰሚቴ አባላት ቅድሚያ ይጠቀሳሉ። ቅዱሳን የሽማግሌው ስብሃት ነጋ እህት ስትሆን የጸጋዬ ባለቤት ናት። ፈትለወርቅ ደግሞ የስብሃት ወንድም ልጅ ናት። ፈትለወርቅ የአባይ ፀሓዬ ባለቤት ነበረች። አንድ ልጅ አፍርተዋል፤ ከተለያዩ ቆይቶዋል። አባይ ፀሃዬ ወጣት ኮረዳ ተሞሽረው በሙስና የደለበ ኑሮ ይገፋሉ ብለዋል ምንጮች። በአደገኛ
ሰላይነታቸው የሚታወቁት ብርሃነ ኪ/ማርያም (በቅፅል ስማቸው ብርሃነ ማረት) ከስብሃት ነጋ ጋር የጋብቻ ዝምድና ያላቸው ሌላው የማ/ኰሚቴ አባል ናቸው።
የአዲስአለም ባሌማ ባለቤት ፀሓይ እቁባይ ትባላለች፤ የአርከበ እቁባይ እሕት ናት። የአርከበ ባለቤት ደግሞ ንግስቲ ገ/ክርስቶስ ስትሆን፡ የብርሃነ ገ/ክርስቶስ እሕት ናት።

Wednesday 14 November 2012

ኢህአዴግ በፖለቲካ ወለምታ ውስጥ!!

 

አባተ ኪሾን መልሶ ለመሾም ውስወሳ ተጀምሯል
eprdf
 
ኢህአዴግ በ“ፖለቲካ ወለምታ” ውስጥ እንደሚገኝ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የኢህአዴግ ዲፕሎማት ለጎልጉል ተናገሩ። በከፊል ኢህአዴግን የተለዩ የሚስሉት ዲፕሎማት በጎልጉል የቅርብ ሰው አማካይነት ድምጻቸው ሳይቀረጽ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት የተፈጠረው የፖለቲካ ወለምታ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል አመልክተዋል። የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት በመካከለኛ አመራሩ ውስጥ የመጠራጠር ስሜት መፈጠሩን በፓርቲ ግምገማ ላይ በግልጽ መናገራቸው የዲፕሎማቱን አስተያየት የሚያጠናክር ሆኖ ተገኝቷል።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የአቶ መለስን ሞት ደብቀው በመያዝና ማስተባበያ በመስጠት ጊዜ የወሰዱት ይኸው የተባለው የፖለቲካ ወለምታ እንዳይፈጠር ለማድረግ በማሰብ እንደነበር ዲፕሎማቱ ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ አቶ መለስ ሁሉንም ጉዳይና ሃላፊነት ብቻቸውን ይዘውት ስለነበር በድንገት ማለፋቸው ፓርቲው ውስጥ አሁን በየደረጃው የሚታየው የመተርተር አደጋ መከላከል ግን አልተቻለም።
የፖለቲካ ወለምታ ስለመከሰቱ ማንም ማስተባበያ ሊያቀርብ አይችልም የሚሉት ዲፕሎማት በእርሳቸው እይታና ባላቸው መረጃ መሰረት ድርጅትን መክዳት፣ ድርሻዬ በሚል ገንዘብ ማሰባሰብ፣ ቤተሰብን በተለያዩ ምክንያቶች ማሸሽ፣ በቁልፍ የመከላከያ ሃላፊዎች ላይ ማነጣጠር፣ በግምገማ ስም ካድሬውን ማመስ፣ በስልጠና ስም የበታች አመራሮችን መደለል፣ ከሁሉም በላይ ማንኛውም ውሳኔ ሲወሰን በተናጠል እንዳይሆን የሚከለክል አሰራር መከተል የመሳሰሉት ተፈጠረ ለተባለው “ወለምታ” ዋና መግለጫዎች ናቸው።
ፓርቲያቸው ኢህአዴግ የመለሰን ምስል እየለጠፈ “የታላቁን መሪ ውርስ ሳይበረዝ እናስቀጥላለን” የሚለው ውሸት እንደሆነ በመግለጽ ተጨማሪ ማሳያ የሚያክሉት ዲፕሎማቱ፣ “ይህ ሁሉ ግርግር ካድሬውን ንዶታል፣ የምንቀራረብ ዲፕሎማቶችና ባለስልጣናት የምንቀያረውን መልዕክት ህዝብ ቢሰማ በመሪዎቹ ያፍራል። ካድሬውም ራሱን ይጠላ ነበር” በማለት ተናግረዋል።
“ዲፕሎማቶች እርስ በርሳችን ሃሜት ከጀመርን ቆይተናል” በማለት ሃሜት አንዱ የፖለቲካ ወለምታ ማሳያ እንደሆነ የሚናገሩት የኢህአዴግ ሰው፣ መለስን ታላቅ መሪ እያሉ የጋራ አመራር መሰየማቸው በካድሬውና በፓርቲው የተለያዩ አመራሮች ዘንድ ማፌዣ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ሲያብራሩም “የመለስ መስመር ሳይበረዝ እናስቀጥላለን እያሉ እየማሉ አገሪቱ በጋራ አመራር እንደምትመራ ይፋ ማድረጋቸው አቶ መለስ በጋራ አመራር የማያምኑ፣ አምባገነን፣ የስልጣን ጥመኛ፣ የዲሞክራሲ ባህል የሌላቸው፣ ከዚህ ቀደም የተቃወሙዋቸው የሚሉት ሁሉ ትክክል እንደሆነ መቀበልና አስተዳደራዊ መልካቸው የተበላሸ እንደነበር የማወጅ ያህል ነው” ብለዋል፡፡
ኢህአዴግ መለስን በአደባባይ እያወገዘ እንዳለ ሁሉም እንደሚረዳ ማረጋገጫው በእህት ፓርቲዎች ውስጥ በተካሄደው ግምገማ ከፍተኛ ባለስልጣናት ውስጣዊ ችግር እንዳለባቸው ማስታወቃቸው እንደሆነ ያመለከቱት እኚሁ ዲፕሎማት በቅርቡ “በታሪክ አጋጣሚ ተሾምኩ” በማለት ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመደቡትን አቶ ደመቀ መኮንን የተናገሩትን ያጣቅሳሉ።
የብአዴን ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ ባህር ዳር በተካሄደው የድርጅት ጉባዔ ላይ የአቶ መለስ ህልፈትን ተከትሎ ተፈጠረ የሚባለውን የፕሮፖጋንዳ መነቃቃት “የዘመቻ ውጤት” ብለውታል። አያይዘውም “የልማት ሰራዊት መገንባትና ማደራጅት አልተቻለም” በማለት የሚሰራውንና ተሰራ የተባለውን ስራ “ሸንኮራ ቆረጣ” እንዳስመሰሉት አስተያየት ሰጪው ይናገራሉ።በማያያዝም የክልሉ ምክትል ሊቀመንበር “የመጠራጠር መንፈስ አለ” በማለት ስጋታቸውን መግለጻቸውን ያክልሉ። አቶ በረከትም ተመሳሳይ አስተያየት መስጠታቸውን ጨምረው ገለጸዋል።አንዳንድ የስራ ባልደረቦቻቸው እንደገለጹላቸው ከሆነ በቅርቡ ብወዛ፣ ሹም ሽርና በመተካካት ስም ማስወገድ እንደሚደረግ በማውሳት አስተያየታቸውን የሰጡት የኢህአዴግ ሰው፣ በደቡብ ክልል ኦህዴድ ውስጥ የተፈጠረው አይነት ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚል ቅድመ ጥናት መደረጉን ይፋ አድርገዋል። ለዚህም ይመስላል በሙስና ተወንጅለው ለዓመታት ከታሰሩ በኋላ በነጻ የተለቀቁት አባተ ኪሾን መልሶ ለመሾም የማግባባት ስራ (ሎቢ) ተጀምሯል ብለዋል።
“ወደ አገር ቤት ይመለሳሉ?” ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ “በተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆነ በዳያስፖራ ዘንድ ለኢህአዴግ ሰዎች የሚሆን ቦታ ስለመኖሩ ሰምተው” እንደማያውቁ በመጠቆም ለመመለስም ሆነ ለመቅረት ስጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ “ከተቃዋሚዎች በኩል ሁሉንም የኢህአዴግ ሰዎች በአንድነት በመፈረጅ “ወዮልህ” የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች መብዛታቸው ለስርዓቱ ኃይል እንደሆነው” አመለክተው “ወለምታው እኔንም ይመለከተኛል። እኔም እንደ ባልደረቦቼ ወጌሻ ያስፈልገኛል” የሚል መልስ ሰጥተዋል። አያይዘውም የተፈጠረውን ወለምታ ለመጠቀም ምላጭ ፖለቲከኛ መሆን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ምላጭ ፖለቲከኞች ምን መምሰል እንዳለባቸው ግን አላብራሩም። አቶ መለስን አስመልክቶ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ በቀጣይ እናቀርባለን።
ጎልጉል ባለው መረጃ በደቡብ ክልል አብላጫ ቁጥር ያላቸው የሲዳማ ብሄረሰብ ክፍሎች አሁን በቡና ንግድ የተሰማሩትን የቀድሞውን ፕሬዚዳንት አቶ አባተ ኪሾን ይቀበላል። በክልሉ ከሲዳማ ብሄረሰብ ውጪ ፕሬዚዳንት ለማድረግ እንደማይሞከር በተለያዩ ጊዜያት ስለክልሉ ሲዘገብ የተጠቀሰ ጉዳይ ነው።
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ባለፈው አርብ በመስከረም ወር ማድረግ የሚገባውን የመጀመሪያ ሩብ አመት ግምገማ በማካሄድ ያሳለፈው ውሳኔ በድርጅቱ ውስጥ አለ የተባለውን የፖለቲካ ወለምታ የሚያሳይ እንደሆነ ለጎልጉል አስተያየት የሰጡ አስታውቀዋል። የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ በክልል ደረጃ አሉ የተባሉትን ችግሮች አድበስብሶ በጥንካሬ ከገመገመ በኋላ “የክረምቱ ስራ ስላለቀ፣ የበጋው ስራ ባስቸኳይ እንዲጀመር” ሲል የፖለቲካ ውሳኔ ማውረዱን ይፋ አድርጓል። አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ክረምቱ ካለቀ ከሶስት ወር በኋላ “የበጋው ስራ ይጀመር፣ ክረምቱ አልቋል” የሚል ውሳኔ ማሳለፉ ከወለምታም በላይ ነው።(http://www.goolgule.com/)

Tuesday 13 November 2012

“ወይ መዓልቲ” አለ ያገሬ ሰው!

    

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አባል ሀገር ሆና ተመረጠች።
የትኛዋ ኢትዮጵያ!? የትኛው ሰብአዊ መብት!? የትኛው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን!?
እኔ የምለው ኢትዮጵያዊው የዩልኝታ ባህላችን ያለው ህብረተሰቡ ዘንድ ብቻ መሆኑ በጣም አሳሳቢ ችግር አይመስላችሁም? እንዴ መንግስት እኮ ይሉኝታ ቢኖረው ኖሮ “ተመድ የሰባዊ መብት ኮሚሽን አባል አድርጌ መርጨሀለሁ!” ሲለው… “አረ በህግ አምላክ እኔ አልሆናችሁም ሀገር ተሳስታችሁ ነው! ወይ ደግሞ ባታውቁኝ ነው የመረጣችሁኝ…!” ማለት ነበረበት። ነገር ግን መንግስቴ “ምን ይሉኝ” ያልፈጠረበት ነውና አሜን ብሎ መቀበሉ ሲገርመን፤ ጭራሽ በአደባባይ “እንዲህ ነን እኛ ሰብአዊ መብት ጠባቂዎች” ተብሎ ተነገረን!ኢቲቪ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታማሚ አምባሳደር ዲና ሙፍቲን አማካይነት፤ “ድሮውንም እኛ ለሰብአዊ መብት ጥበቃ ዘብ የቆምን ሰዎች ነን!” ብሎናል።
አቶ ዲና በሚወዱት ይማሉልኝ የሚናገሩት የምርዎትን ነው!? ከማሉልኝ ዛሬ ነገ ሳልል ሀገሬ እመጣለሁ። እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም የሰብአዊ መብት ጥሰቱን ፈርቶ የወጣው ኢትዮጵያዊ ሁሉ “ምን አለኝ ሀገሬ” (“ለ“ን አጥብቆ) ዘፍኖ እንደወጣው ሁሉ፤ “ምን አለኝ ሀገሬ” በሚል “ለ”ን አላልቶ ዘፍኖ ይመለሳል። ግን እርግጠኛ ነኝ በሚወዱት አይምልሉንም! ለመሆኑ የሚወዱትስ አለ…!? ወይስ ነፍስ ይማር እንበልልዎ!?
የምር ግን ሰብአዊ መብት ማለት ምን ማለት ነበረ!?
“ወይ መዓልቲ” አለ ያገሬ ሰው!     አቤ ቶክቻው 

የቦንጋው ሰው

 


(ተመስገን ደሳለኝ)
ቅድመ ታሪክ:- እናንተ ጊዜው እንዴት ይሮጣል፡፡ የዛሬ 8 ወር ትህሳስ 28ቀን 2003ዓ.ም በወጣችው ፍትህ ጋዜጣ ላይ ..የቦንጋው ሰው.. በሚል ርዕስ አንድ ፅሁፍ ፅፌ ነበር፡፡ የፅሁፌ መነሻ የነበረው ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ በ23/4/03 ከወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ ..ዶ/ር አሸብር ፓርላማው ተመችቷቸዋል.. በሚል ርዕስ ታትሞ ማንበቤ ነው፡፡ ሆኖም ያንን ፊቸር ጽሑፍ ዶ/ሩ ካነበቡ በኋላ ..ሀሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብቱ ነው.. ብለው አላለፉትም፡፡ ወይም ለእኔ ፅሁፍ መልስ የመስጠት መብታቸውን ተጠቅመው መልስ አልፃፉም፡፡ ያደረጉት ነገር ቢኖር ምንድር ነው? በቀጥታ ጠበቃቸውን ጠርተው፤ በእኔ ላይ ክስ መሰረቱ፡፡ የፌደራል ፖሊስም ማዕከላዊ ምርመራ ጠርቶኝ የተከሳሽነት ቃሌን እንድሰጥ አድርጎ በዋስ ለቀቀኝ፡፡ በዋስ ከተለቀኩ ከቀናት በኋላ ደግሞ የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ችሎት ተጠርቼ ክሱ መታየት ጀመረ፡፡ ፍርድ ቤትም በቀረብኩ የመጀመሪያው ቀን 5ሺ ብር ለዋስትና እንዳሲዝ፤ አሊያም ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆኜ እንድከራከር አማራጭ አቀረበልኝ፡፡ እንደምንም ብዬ 5ሺዋን አስይዤ ተፈታሁ፡፡ ከዛስ? ከዛማ ከዶ/ሩ ጋር ሽምግልና ተቀመጥኩ፡፡ ዶ/ሩም ሽምግልናውን በቀናነት ተቀብለው መነጋገር ጀምረን፤ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠው ሳለ ፍርድ ቤቱ ከክሱ ነፃ አድርጎ በነፃ አሰናበተኝ፡፡ ጉዳዩም በዚሁ ተዘጋ፡፡
ያንጊዜ ዶ/ሩ እኔን ለመክሰስ የበቁት ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና የዴሞክራሲ እድገት የተናገሩት ስላልተዋጠልኝ ንግግራቸውን በመተቸቴ ነው፡፡ እነሆም ከ8 ወር በኋላ ሌላ ቃለ መጠይቅ፤ ከሌላ ጋዜጣ ጋር አደረጉ፡፡ አሁንም የዶ/ሩ ምላሽ በፍፁም ሊዋጥልኝ አልቻለም፡፡ እናም እረጋ ብዬ አሰብኩ፡፡ ገና ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ስመጣ ለእራሴ የገባሁትን ቃልም በተመስጦዬ ደጋግሜ አንሰላሰልኩት፡፡ ..በታማኝነት፣ በሚዛናዊነት እና በሃቅ ሀገሬን አገለግላለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ ለማስፈራራት፣ ለክስ፣ለመደለያ እና ለመሳሰሉት ተፅዕኖዎች አልንበረከክም.. የሚል ነበር፡፡ አሁን አዲስ ፈተና ከፊቴ ተደቅኖአል፡፡ የዶ/ሩ ቃለ-መጠየቅ፡፡ አሁንም ዶ/ሩ የተናገሩት ሙሉ በሙሉ አልተዋጠልኝም፡፡ ሆኖም እንዳልተዋጠልኝ ጠቅሼ ሀሳባቸውን (የተናገሩትን) ብተች እንደአለፈው ጊዜ ሊከሱኝ ይችላሉ፡፡ በዝምታ ባልፈው ደግሞ ለህሊናዬ የገባሁትን ቃል ልጥስ ነው፡፡ ከክስ እና ህሊናን ከማታለል የቱ ይሻላል ብዬ ደግሜ አሰብኩ፡፡ አንሰላሰልኩ፡፡ በመጨረሻም የተናገሩት (ቃል የገቡት) ከሚጠፋ የወለዱት...ስለዚህም ምንም እንኳን ጋዜጣው ከታተመ በኋላ ሊከሱኝ ይችሉ ይሆን እንዴ? የሚል ስጋት ቢኖርም፤ ከህዝብ እና ከሀገር በላይ የለም፡፡ (እዚህ ሀገር ህግ ቢኖር ግን የሚከሰሰው እኔ ሳልሆን የዋሹት ደክተር እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡) እናም የመጣው ቢመጣ ህዝብን ለማሳሳት የሚሰጥ ፕሮፓጋንዳን፣ ያውም በአገጠጠ ውሸት ላይ የተመሰረተን፣ ያውም በሬ ወለደን... ሀሳብ እንተቻለን ፡፡
የቦንጋው ሰው 2
ማክሰኞ ነሐሴ 3 ቀን 2003ዓ.ም የወጣው መሰናዘሪያ ጋዜጣ ከተከበሩ የፓርላማ አባል ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ጋር የአደረገውን ቃለ መጠይቅ ..እኔ ፈፅሞ ጥገኛ አይደለሁም፤ ህዝቡም ጥገኛ አልመረጠም.. እና ..በደቡብ በኩል ያለው ድርቅ ሳይሆን በአብዛኛው ወደ ውጭ ገበያ ማመዘኑ ነው..በሚሉ ርዕሶች ለንባብ ማብቃቱ ነው ..የቦንጋው ሰው ዋ..ን እንድጽፍ ያነሳሳኝ ወይም የገፋፋኝ፡፡
በመጀመሪያ ግን .. ዶ/ር ሒኖቴ ዎዳ ቤቴ .. ስል በከፊቾ ቋንቋ ሰላምታ አቀርባለው፡፡ .. ሰላምታውን ወደ ፌደራል ቋንቋ ስንመነዝረው ዶ/ር እንደምን ኖት እንደማለት ነው..፡፡ ...ከዚህ በኃላ በቀጥታ ወደ ጉዳያችን እንግባ፡፡ዶ/ሩ ከወራት በፊት በዛው ጋዜጣ ላይ የሰጡትን ቃለ መጠይቅ ተከትሎ ጋዜጠኛው ሰዎች ..ዶ/ር አሸብር ከኢህአደግ ባለስልጣን የበለጠ ስለኢህአደግ ተሟጋች ሆኑ እያሉ ተችተዋል፡፡ ይህንን እንዴት አዩት?.. የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው እንዲህ ሲሉ መለሱለት .....ለዚህች ሀገር ትልቅ ልማት ያስመዘገበ ፓርቲ፤ እንደገና በአፍሪካ ደረጃም የአለም ህዝብም ተቀባይነት የሰጣቸው ትልቅ መሪ ያለበት ሀገር፤ ፓርቲውን በመደገፍ መቀጠል እፈልጋለሁ፡፡ ...ከዚህ አኳያ እኔ ከኢህአዴግ ጋር ዛሬም ተቃዋሞ የለኝም፤ ወደፊትም አይኖረኝም የሚል እምነት ነው ያለኝ.. የሚል መልስ መለሱ፡፡ ከሞላ ጎደል፡፡ መጀመሪያ ዶ/ሩ የተናገሩት ስለኦባማ ..ዴሞክራት.. ፓርቲ መስሎኝ እውነት ነው ብዬ ላልፍ ነበር፡፡ ስለ እኛው ኢህአዴግ መሆኑን ሳውቅ ግን...
የተከበሩ ዶ/ር አሸብር ለመሆኑ ..ለዚህች አገር ትልቅ ልማት ያስመዘገበ ፓርቲ.. ሲሉ ምን ማለትዎት ይሆን? የእርሶ ልማት መኖር እና ልማት ያለመኖር መስፈርትስ ምን ይሆን? ...እኔም ሆንኩ ሀገሬው የሚያውቀው ኢትዮጵያ በልማትም ሆነ በዴሞክራሲ እንኳን ከአለም ከአፍሪካም ወደ ኃላ የቀረች መሆኗን ነው፡፡ አቶ መለስ በአፍሪካ እና በአለም ተቀባይነት እንዳላቸውስ በምን አረጋገጡ? እስከማውቀው ድረስ እነ ሂዩማን ራይትስ ዎችን የመሳሰሉ አለም አቀፍ ድርጅቶች አቶ መለስን እና አገዘዛቸውን ..አምባገነን.. እያሉ እየተቹ ነው ያለው፡፡ እሺ.. ሌላው ይቅር ..እኔ ከኢህአዴግ ጋር ዛሬም ተቃዋሞ የለኝም.. ያሉትን መብትዎ ስለሆነ እንቀበለው ..ወደፊትም አይኖረኝም.. ያሉት ግን በጣም የወረደ ሀሳብ ነው፡፡ ስለወደፊቱ ምን የሚያውቁት ነገር አለ? ወይስ ነብይ ነኝ ሊሉን ፈልገው ነው?
ወደ ሌላው ጥያቄ እንለፍ ..መሰናዘሪያ፡- ጠ/ሚኒስትር መለስ ከዚህ የፓርላማ ዘመን በኋላ እለቃለሁ ብለው ነበርና አምርረው ይለቃሉ? አሁን ባሉበት ሁኔታ ሃገሪቱ የሚኖራት አቅጣጫስ ምን ሊሆን ይችላል?
ዶ/ር አሸብር፡- ይኼ ነገር በሰፊው መታሰብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ...በአሁኑ ሰዓት ሰው የተዘጋጀ አልመሰለኝም፡፡ ሰፊ የልማት ስራዎችን ጀምረዋል፡፡ የአባይን ግድብ ብትወስድ ስድስት ሰባት ዓመት መጨረስ ያለብን ነው፡፡ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ በአራት አምስት ዓመት ውስጥ መጨረስ ያለብን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ እኔ ጠ/ሚኒስትሩ የጀመሩትን መጨረስ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በሌላ በኩልም ጠ/ሚኒስትሩ የሀገር መሪ መሆን በሚገባቸው ሰዓት አልነበረም መሪ የሆኑት፡፡ በ35 ዓመታቸው ወጣት ሆነው ነው የተረከቡት፡፡... አሁን በትክክለኛው የመሪነት እድሜ ላይ ነው ያሉት፡፡ 50 እና ከ50 አመት በላይ ጥሩ እድሜ ነው፡፡ ...የአፍሪካም የዓለም መንግስታት ሁሉም ጠ/ሚኒስትሩን እንጠቀምባቸው እያሉ ነው ያሉት፡፡ ...ህዝቡን በዚህ ሁኔታ አነሳስተው የት ነው ጥለው የሚሄዱት፡፡ በአገሪቱ በአፍሪካ፣ በዓለም መንግስታትም እየታመነባቸው አርፋለሁ ቢሉ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ እሳቸውም ፓርቲውም ሊያስብበት ይገባል፡፡ በእኔ እምነት ይህችን ሀገር ከእሳቸው ውጭ ባሁኑ ሰዓት አስተካክሎ ሊመራ የሚችል ማንም ኃይል የለም፡፡ ...ማንም የለም፤ አማራጭ የለም መለስ ዜናዊ ብቻና ብቻ ናቸው፡፡ አሁን ህዝቡን በፍቅር እንዳነሳሱት፣ ለልማት እንዳሰባሰቡት እውነቱን ለመናገር ለእያንዳንዱ ህዝብ እኔ አለሁልህ ብሎ የሚመራ መሪ መለስ ብቻ ናቸው፡፡ ...ይህ የሁሉም የእያንዳንዱ ጥያቄ ነው የሚመስለኝ፡፡ ፓርቲው ኢህአዴግም አማራጭ አለኝ ብሎ ሌላ ካሰበ ትልቅ ስህተት ነው የሚሆነው፡፡ እሳቸውም እወርዳለሁ በሚል ሁኔታ ሳይዘናጉ ከወዲሁ እንደድሮው ስለሃገሪቱ ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡ ህዝቡ እሳቸውን ከስልጣናቸው አይለቃቸውም፡፡.. ወዳጄ.. ይሄን ይመስላል የዶ/ር አሸብር መልስ፡፡
የከፋ ሰው እንዲህ አይነት የፈጠጠ፣ የአገጠጠ ውሸት ሲገጥመው ..አሞኔ?.. ሲል ይጠይቃል፡፡ ይህንንም ወደ አማርኛ ስንመልሰው ምንድነው? ማለት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እውነትም ዶ/ር ..አሞኔ?.. አረ ለመሆኑ በአንድ በኩል የኢህአዴግ አባል አይደለሁም እያሉ በአቶ መለስ ቦታ (በኢህአዴግ በኩል) ሰው የተዘጋጀ አይመስለኝም ያሉት በምን አውቀው ነው፡፡ ይችን ትንሽ ፈታ አድርገው ቢያብራሯት? የአባይ ግድብ ትራንስፎርሜሽን ምናምን... የሚባሉ ነገሮች ስለተጀመሩና እስከ ሚያልቁ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣን ላይ ይቆዩ ማለትስ ምን ማለት ይሆን? መንግስት በየአምስት አመቱ የይስሙላም ቢሆን ምርጫ ያካሄዳል፡፡ እርሶ ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ ሰባት አመት የሚፈጀው ግድብ እስኪያልቅ በስልጣን ይቆዩ እያሉን ነው፡፡ ምርጫው ይቅር? የምርጫ ቦርድ ቢሮስ ወደ ክሊኒክ ይቀየርሎት?... አቶ መለስ ለ20 ዓመት በስልጣን ቆይተዋል፡፡ መቼም የዚህን ያህል አመት በአምባገነኖች ሀገር ካልሆነ በቀር ዴሞክራት በሆኑ ሀገራት በስልጣን የቆየ መሪ የለም፡፡ የዶ/ሩ መከራከሪያ መለስ ልጅ ሆነው ስልጣን ስለያዙ እስከ ዛሬ የነበረው አስተዳደር ..የልጅ ጨዋታ ነው.. አሁን ነው የበሰሉት፤ እናም ሌላ 20 ዓመት በስልጣን ይቆዩ ነው፡፡ በድምሩ 40 አመት፡፡ ከጋዳፊ እኩል ማለት ነው፡፡ እንዲህ በሁሉም ነገር አቻ ይሁኑ... ለነገሩ ምን አላት 40 አመት ነገ ትደርሳለች፡፡ ምርጫስ ምን ያደርጋል? አይደል ዶ/ር፡፡ አንድ ሊገባኝ ያልቻለ ነገር አለ፡፡ በባለፈውም ፅሁፌ አንስቼሎት ነበር ..የአፍሪካም የአለምም መንግስታት ጠ/ሚኒስትሩን እንጠቀምባቸው እያሉ ነው.. ያሉት አይነትን ንግግር የሚናገሩት መረጃውን ከየት እያመጡት ነው? የአፍሪካ እና የአለም መንግስታት እንዲህ አይነት ንግግር ሲናገሩስ ለእርሶ ለብቻዎት ነው? ወይስ እንዲህ ብለው ቢናገሩ የሚል ቀና አመለካከት ኖሮት ነው? አለዚያ ህዝብን ማሳሳት ወንጀል መሆኑን ማወቅ አለቦት፡፡ ለእንዲህ አይነት ንግግር ምንጭ መጥቀስ የግድ ነው፡፡ አምባገነንነትንም ውሸታምነትንም አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ ...ዶ/ሩ እንዲህ ሲሉ ደግሞ ለኢህአዴግ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ..እሳቸውም ፓርቲውም ሊያስብበት ይገባል፡፡.. ቀጠሉና ደግሞ ..በእኔ እምነት ይህችን ሀገር ከእሳቸው ውጭ በአሁኑ ወቅት አስተካክሎ ሊመራ የሚችል ማንም የለም.. ሲሉ ጨመሩበት፡፡ እውነት ግን ዶክተር ከእሳቸው ውጭ ማንም የለ? አንድ እንኳ? ያሳዝናል፡፡ያሁሉ ሚንስትርስ ለእርሶ ሰው ሆኖ አልታዮትም? በእኔ እምነት ግን እንዲህ አይነት አስተዳደር፤ ህዝብን እያስራቡ እና እየቀጠቀጡ ማስተዳደር ለማንም ይከብደዋል ብዬ አላስብም፡፡ ለእርሶም ቢሆን፡፡ ለእኔም ቢሆን፡፡
በድሮ ጊዜ በርካታ አፋሽ አጎንባሾች በአድርባይነት አምባገነን አገዛዝ እንዲቀጥል የቻሉትን ያህል ለፍተዋል፡፡ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴን ..ፀሐዩ ንጉሰ ነገስት..፣ ኮለኔል መንግስቱ ኃ/ማርያምን ደግሞ ..ቆራጡ መሪያችን፣ ኮሚኒስቱ መሪያችን.. እያሉ ማለቴ ነው፡፡ ዶ/ር አሸብር ደግሞ እንዲህ ይላሉ ..ማንም የለም፤ አማራጭ የለም፤ መለስ ዜናዊ ብቻ ናቸው፡፡.. እሺ.. ከጓድ መለስ ዜናዊ ጋር ወደፊት... ..ፓርቲው ኢህአዴግም አማራጭ አለኝ ብሎ ሌላ ካሰበ ትልቅ ስህተት ነው የሚሆነው.. ሌላኛው የዶ/ሩ ውዳሴ፡፡ ከንቱ ውዳሴ ያለው ማን ነበር? ...ዶ/ር እዚህች ጋር ፍሬን ያዙ፡፡ ለምን መሰሎት? ቢያንስ ኢህአዴግ እና አቶ መለስ ልሳናቸው እስኪዘጋ ስለ..መተካካት.. ካወሩት ጋር ሊጋጩ ስለሚችሉ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እኮ ግራ ቀኙን አይቶ መናገር መልካም ነው፡፡ ሰው ዝም ሲል የማያውቅ ሆኖ አይደለም፡፡ ይታዘባል፡፡ ይሄ አይነት ንግግር ለአቶ መለስም ቢሆን የሚጥማቸው አይመስለኝም፡፡ ባይሆን ለፉገራም ቢሆን ..ስለመተካካቱ.. እያወሩ ጊዜው ሲደርስ ..አይሰማም.. ቢሉ ነው የሚቀላቸው፡፡ የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብ ምናምን... አቶ መለስ በስልጣን እንዲቆዩ ይፈልጋል የሚሉትን ፕሮፓጋንዳ ለራሶት አድርጉት፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ መቼም እንዲህ ብሎ አያውቅምና፡፡ ለምሳሌ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ መለስ ዛሬ ከስልጣን ቢወርዱ ሺ እጥፍ ጊዜ አደንቃቸውም፤ አከብራቸውም ነበር፡፡ ሀገሬም ተጠቃሚ የምትሆነው ያን ጊዜ ነበር፡፡ ...ዶ/ር ኢህአዴግ ከ5 ሚሊዮን አባላት በላይ አለኝ እያለ ነው፡፡ በርካታ አመራርም አፍርቼያለሁ ብሎ ደጋግሞ ነግሮናል፡፡ እርሶ ደግሞ ከመለስ ውጪ ሰው የለም እያሉ ነው፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? ማነው የዋሸው? በርካታ አመራር አፍርቼአለሁ የሚለው ኢህአዴግ? ወይስ ምንም ተተኪ አመራር አላፈራም የሚሉት ዶ/ር አሸብር?
ዶ/ር አሸብር ጠ/ሚኒስትሩን ሲገልፁ ..መለስ መቶ በመቶ የተሻሉ መሪ ናቸው፡፡ እምነት የሚጣልባቸው ጥሩ አእምሮ ያላቸው እጅግ የተማሩ ሰው፤ ከንባብ የማይለዩ ሰውና ትልቅ መሪ ናቸው፡፡.. እንደው ንፁህ ህሊና ካለው ሰው፤ ያውም ዶ/ር የሚል ተቀጥላ ከስሙ በፊት ካለው ሰው የዚህ አይነት አስተያየት ይሰማልን? አይ.. 8ኛው ሺ ...፡፡ የሆነ ሆኖ መለስ አንባቢ ሊሆኑ ይችሉ እንደሆነ እንጂ እምነት የሚጣልባቸው እንኳ አይመስለኝም፡፡ለዚህ ማስረጃ ከፈለጉ ደግሞ የራሳቸው ጓደኞች በመለስ ደጋግመው ለመታለላቸው የፃፉትን አንብቡ፡፡ ደግሞም እከሌ አንባቢ ነው እያሉ ማድነቅ እውቀት አይሆንም፡፡ እውቀት የሚሆነው ራሶት ሲያነቡ ነው፡፡
ሌላውን የዶ/ሩን አሳፋሪ ንግግር አንብቡ ..ረሀብ ድህነት እንደሆነ እንኳን በኛ ሀገር በነአሜሪካም፣ በነብሪቴን በረንዳ አዳሪ እዛም አለ፤ እዚህም አለ፡፡ ችግሩ ተጠናክሮ ዓለም በከፍተኛ ቀውስ ባለበት ባሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ላይ አይደለችም፡፡ የያዘችው ፖሊሲና አይዶሎጂ ጠቅሞ ቀውሱን ለመቋቋም ችላለች፡፡.. ብታምኑም ባታምኑም ይሄ ንግግር የወጣው ከአንድ ዶክተር ነው፡፡ ዶክተር...... እንኳን ዶክተር ቀርቶ ማንበብ እና መፃፍ የማይችል ሰውም ቢሆን አሜሪካም በረንዳ አዳሪ አለ፤ ብሪታኒያም በረንዳ አዳሪ አለ፤ ኢትዮጵያም በረንዳ አዳሪ አለ ብሎ የራሱን የወረደ እውቀት አያስፎግርም፡፡ እሺ እባኮት.. የእኛ ዶ/ር አሜሪካ እና እንግሊዝ ድህነትን መቋቋም ሲያቅታቸው፤ ኢትዮጵያ በያዘችው ፖሊሲ እና አይዶሎጂ ተቋቋመች? እውነቶትን ነው? ወይስ ቲያትር እየሰሩ መስሎት ነው? ይስሙኛ ዶ/ር.. የቦንጋ ህዝብ እርሶን በመምረጡ ያዘነ ይመስለኛል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ እንኳን እንደዚህ አይሉም፡፡ ለነገሩ... ድሮ ነገስታቶችን እንዲህ አይነት አስተያየት እየሰጡ የሚያስደስቱ ሰዎች ነበሩ፡፡ በእርግጥ እነዚያህ ሰዎች የጥርስ ሐኪም አልነበሩም፡፡ አዝማሪ እንጂ፡፡እናም...
ዶ/ር አሸብር እንዲህ ሲሉ ደግሞ ተመፃደቁ ወይም ዋሹ ..ከጎረቤት ሀገራት በረሃቡ ሳቢያ ወደ እኛ ብዙ ሰዎች መጥተዋል፡፡ ...መንግስት ጥሩ የገንዘብም ሆነ የእህል ክምችት ስላለው ያስተካክለዋል፡፡.. አረ ስለእግዚአብሔር.. መንግስት እህል እየለመነ፤ ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ በአደባባይ ጥሪ እያደረገ እያለ እንዴት እህል ሞልቷል ይላሉ? ወይስ ..ምግብማ ሞልቶአል.. የሚለውን የጥላሁን ገሰሰን ዘፈን መዝፈን ፈልገው ነው?...
የዶ/ሩ ወሬ ማለቂያም የለው፤ ..በእርግጠኝነት ከደህነት እንወጣለን፡፡ ድህነት አይኑር አይባልም.. ይሉሃል፡፡ የእኛ ዶክተር፡፡ እኔ ግን እልሃለው ..ድህነት ለዘላለሙ አይኑር....፡፡ እንዲህ አይነት ቀልደኛ የፓርላማ አባልም ለዘላለም አይኑር ስል እጨምራለው፡፡
የዶ/ሩ የወረደ እና ንባብ አይቶት የሚያውቅ የማይመስለው ቃለ መጠይቅ ቀጥሎአል፡፡ ..መሰናዘሪያ፡- ድሮ ረሀብና ድርቅ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ብቻ ነበር፡፡ አሁን ደናማዎቹ ደቡብ እና ኦሮሚያ ናቸው የተጠቁት ይህንንስ እንዴት ያዩታል?
ዶ/ር አሸብር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ምርት የለም አይደለም፡፡ ትልቁ ችግሩ በአብዛኛው ወደ ውጭ ልኮ መሸጡ በዝቷል፡፡ እያንዳንዱ ገበሬ አብዛኛው የእርሻ መሬት በአዋጭና በውጭ ንግድ በሚሆን ምርት ላይ ማዋሉ ችግር የፈጠረ ይመስለኛል፡፡ ደቡብም ብትል በጣም በብዙ ይመረታል፡፡ በመሀል ሀገራትም በገፍ ይመረታል፡፡ ህዝቡ ምርቱን በቤቱ መያዙ፤ ምርቱን በማስቀመጥ በይበልጥ ለውስጥ ገበያ ቢያቀርብ ተጠቃሚ መሆኑን ማሰቡና ለገበያ አለማውጣቱ አንድ ችግር ነው፡፡ ሆኖም ይህ በራሱ የእድገታችን ውጤት ነው፡፡.. አሁንም እደግመዋለሁ ይሄን አስተያየት፤ ያነበበ ሰው አስተያየት ሳይሆን ዝም ብሎ በስማ በለው የሚወራ ..ጆሮ ጠገብ.. እውቀት ያለው ሰው የሚሰጠው አስተያየት ብቻ ነው፡፡ ጆሮ ጠገብ.. በየትኛውስ አለም ያለ አርሶ አደር ነው ያመረተውን ጎተራው ቆልፎ፤ አይኑ እያየ፤ ጆሮው እየሰማ ራሱን እና ህፃናት ልጆቹን በረሀብ የሚገለው? እውነቴን ነው የምለው፤ ብዙ የኢህአዴግ አባላት እና ደጋፊዎች የሚሰጧቸውን አስተያየት ተከታትያለው፡፡ የእነሱ ከእርሶ በጣም የተሻለ ነው፡፡ መንደር ላይ ያለ ጠርናፊ እንኳ ከዚህ በብዙ የተሻለ አስተያየት ይሰጣል፡፡ ትንሽ ሊያሳምን የሚችል፡፡ የእርሶ ግን ጋዝ ጋዝ የሚል፤ ደረቅ ውሸት፡፡ ሆድ የሚያሰማም፡፡ ምንም አይነት ብስለትም ሆነ እውነትነት የማይታይበት፡፡ ...ዶ/ር እንዴት ሆኖ ነው ገበሬው የተራበው? የአመረተውን ለውጭ ገበያ ስላቀረበ? ለውጭ ገበያ ካቀረበ እኮ በምርቱ ምትክ ደህና ገቢ ያገኛል፡፡ በአገኘው ገቢ ደግሞ ለኑሮ የሚያስፈልገውን ያሟላል፡፡ ዛሬ በሀገራችን የተራበው ገበሬ ግን አምርቶ ብቻ ሳይሆን ገዝቶም መብላት የማይችል ስለሆነ ነው፡፡ ጥጥ እና ሰሊጥ የሚያመርቱ ገበሬዎች አይራቡም፡፡ ጥጡን እና ሰሊጡን ሸጠው በሚያገኙት ገንዘብ ምግብ ይገዛሉና፡፡ ገበሬ የግድ ጤፍ እና ስንዴ ብቻ ማምረት የለበትም፡፡ ይሄንን ካላወቁ የሚያውቅ ሰው ጠይቁ፡፡ አንድ የወዳጅነት ምክር ልስጦት፤ ጋዜጠኛ ለቃለ መጠይቅ ሲጠይቆት መጀመሪያ እውቀት ያለውን ሰውን አማክሩ፡፡ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ እውቀት ባይኖሮት፤ ለምን እውቀት የሎትም ተብለው አይወቀሱም፡፡ አለማወቅ ደግሞ ሀጢያት አይደለም፡፡ ሀጢአት የሚሆነው የማያውቁትን ሲዘባርቁ ብቻ ነው፡፡...እንጨት እንጨት ከሚለው ከዶ/ሩ ቃለ መጠይቅ የተመቸችኝ ይህች ብቻ ነች ..እኔ ኢህአዴግን ተቃውሜ አልገባሁም፡፡ የተቃወምኩት ግለሰቡን ነበር፡፡ የኔ ሚሽን የተሳካ ነው ብየነው የማምነው፡፡ አሁን ግን እራሴም በሰፊው አስቤበት፤ ከቤተሰቦቼም ከማምናቸው ሰዎችም ከተመካከርኩ በኋላ ከፓርላማው ይልቅ ተመልሼ በሙያዬ ብሰራና ብቀጥል ደስ ይለኛል፡፡.. በእውነቱ ከሆነ ከፓርላማው ለመውጣት ምንም እንኳ ..ከመረጠኝ ህዝብ ተመካክሬ.. ባይሉም፤ አለማወቅ ነውና እንደ ስህተት ሳንቆጥረው በውሳኔዎ በጣም ደስተኛ መሆኔን እገልፅሎታለሁ፡፡ አንዴ ልድገመውና ..ከፓርላማው ይልቅ ተመልሼ በሙያዬ ብሰራና ብቀጥል ደስ ይለኛል.. ያሉት በእጅጉ የሚያስመሰግኖት ነው፡፡... ለዚህ ውሳኔዎ ያለኝን ክብር ለመግለፅ ደግሞ አንድ ሙዚቃ ልገብዞ ..አሁን አየ አይኔ፣ አሁን አየ አይኔ.....
ማስታወሻ
የተከበሩ የፓርላማ አባል እና የጥርስ ሐኪም ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ሆይ.. የህዝብ ወኪል ነኝ እስካሉ ድረስ፤ ህዝብን እና ሀገርን በሚመለከት በሰጡት አስተያየት ትችት ሲቀርብቦት ወደ ክስ መሮጡ ይበልጥ ያስገምቶታል፡፡ ከቻሉ ሀሳብን በሀሳብ መመከት ነው ያለቦት፡፡ ካልቻሉ ደግሞ ወይ ከፓርላማው መልቀቅ፤ አሊያም ትችትን በፀጋ መቀበል፡፡ ምን አልባት ለዚህ አይነቱ ድክመቶት ከአቦይ ስብሓት ነጋ ቢማሩም መልካም ነው፡፡ ሰው የሚማረው አንድም ከመከራ አንድም ከፊደል ነው ያለው ማን ነበር...እንጃ፡፡

Sunday 11 November 2012

‹‹ናፍቆት እኔ ብሞትም አንተ ንብረቴን ታስመልሳለህ›› እስክንድር ነጋ

    
እስክንድር  ከልጁ ከናፍቆት  ጋር አያሳዝንም
(በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ) ከነገ በስቲያ (ማክሰኞ ህዳር አራት) በከፍተኛው ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት የእስክንድር ነጋን ንብረት ለመውረስ ይሰየማል፡፡
በትላንትናው ዕለት የክስ ቻርጅና መንግስት እወርሳቸዋለሁ ያላቸውን የእስክንድር ሁለት ቤቶች ካርታ የተያያዙበት መጥሪያ ደርሶታል፡፡ (በነገራችን ላይ መንግስት ሊወስዳቸው ከተዘጋጁት ቤቶች አንዱ በእናቱ ስም ያለ ሲሆን የዛሬ ዓመት አካባቢ ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል የቤቱን ስም ለማዞር ፈልጋ ‹‹ካርታው የለም›› በሚል አንዴ ቀበሌ፣ ሌላ ጊዜ ክፍለ ከተማ፣ ቀጥሎ አዲስ አበባ መስተዳደር ስትመላለስ ከርማ ሊገኝ ስላልቻለ ሰልችቷት ትታው ነበር፡፡ ትላንት ግን ዓቃቢ ህግ ከክስ ቻርጁ ጋር አያይዞ አቅርቦታል፤ እናም ምንአልባት ያን ግዜ ‹‹ካርታው የለም›› የተባለው ሆነ ተብሎ ተደብቆ ሊሆን ይችላል)
የሆነ ሆኖ እስክንድር ማክሰኞ ፍርድ ቤት ቀርቦ ‹‹ቤቴን አትውረሱብኝ›› ብሎ ስለማይከራከር ‹‹በዕለቱ ፍርድ ቤት መሄድ አልፈልግም›› ሲል ለማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም ማረሚያ ቤቱ ግን ‹‹የግድ ማቅረብ ስላለብን ይዘንህ እንሄዳለን›› የሚል ምላሽ ሰጥተውታል፡፡ እናም እስክንድር በዕለቱ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ምንም አይነት ምላሽ ላለመስጠት ወስኗል፡፡ ባለቤቱም ‹‹የሚስትነቴን ድርሻ አትውረሱብኝ›› ብላ አትከራከርም፡፡ ፍርድ ቤቱ የፈለገውን ይወስን የሚል አቋም ነው ያላት፡፡
በዛሬው ዕለት ሊጠይቀው ቃሊቲ የመጣውን የሰባት ዓመቱን ህፃን ልጁን ጠባቂ ፖሊሶች እየሰሙት ድምፁን ከፍ አድርጎ ‹‹ናፍቆት እኔ ብሞትም አንተ ንብረቴን ታስመልሳለህ፡፡ አይዞህ! ስርዓት ተቀያየሪ ነው፤ ንጉሱ የወረሱት በደርግ ተመልሷል፤ ደርግ የወረሰው በኢህአዴግ ጊዜ ተመልሷል፤ ኢህአዴግ የወረሰው ደግሞ ኢህአዴግ ሲወድቅ መመለሱ አይቀሬ ነው›› ብሎታል፡፡ በ1993 ዓ.ም ግምቱ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ  የሆነ የእስክንድር እናት ቤት በግፍ እንደተወረሰ ይታወቃል፡፡
ዜናውን ያደረሱልን ጋዜጠኛ ተመስገን በመጨረሻ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ “እስቲ አሁን እንኳን ምንአለበት ትንሽ እንደ ሰው አስባችሁ ልጁን የሚያሳድግበትን ንብረት ብትተውለት? …ዛሬም በትላንቱ መንገድ፣ ዛሬም በመለስ ጫማ፣ ዛሬም በመለስ ራዕይ… አቤት! እንዴት ልብ የሚያደማ ነገር ነው! ይህ ምን አይነት ጭካኔ ነው?” ብለዋል።