"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Tuesday 13 November 2012

የቦንጋው ሰው

 


(ተመስገን ደሳለኝ)
ቅድመ ታሪክ:- እናንተ ጊዜው እንዴት ይሮጣል፡፡ የዛሬ 8 ወር ትህሳስ 28ቀን 2003ዓ.ም በወጣችው ፍትህ ጋዜጣ ላይ ..የቦንጋው ሰው.. በሚል ርዕስ አንድ ፅሁፍ ፅፌ ነበር፡፡ የፅሁፌ መነሻ የነበረው ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ በ23/4/03 ከወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ ..ዶ/ር አሸብር ፓርላማው ተመችቷቸዋል.. በሚል ርዕስ ታትሞ ማንበቤ ነው፡፡ ሆኖም ያንን ፊቸር ጽሑፍ ዶ/ሩ ካነበቡ በኋላ ..ሀሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብቱ ነው.. ብለው አላለፉትም፡፡ ወይም ለእኔ ፅሁፍ መልስ የመስጠት መብታቸውን ተጠቅመው መልስ አልፃፉም፡፡ ያደረጉት ነገር ቢኖር ምንድር ነው? በቀጥታ ጠበቃቸውን ጠርተው፤ በእኔ ላይ ክስ መሰረቱ፡፡ የፌደራል ፖሊስም ማዕከላዊ ምርመራ ጠርቶኝ የተከሳሽነት ቃሌን እንድሰጥ አድርጎ በዋስ ለቀቀኝ፡፡ በዋስ ከተለቀኩ ከቀናት በኋላ ደግሞ የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ችሎት ተጠርቼ ክሱ መታየት ጀመረ፡፡ ፍርድ ቤትም በቀረብኩ የመጀመሪያው ቀን 5ሺ ብር ለዋስትና እንዳሲዝ፤ አሊያም ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆኜ እንድከራከር አማራጭ አቀረበልኝ፡፡ እንደምንም ብዬ 5ሺዋን አስይዤ ተፈታሁ፡፡ ከዛስ? ከዛማ ከዶ/ሩ ጋር ሽምግልና ተቀመጥኩ፡፡ ዶ/ሩም ሽምግልናውን በቀናነት ተቀብለው መነጋገር ጀምረን፤ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠው ሳለ ፍርድ ቤቱ ከክሱ ነፃ አድርጎ በነፃ አሰናበተኝ፡፡ ጉዳዩም በዚሁ ተዘጋ፡፡
ያንጊዜ ዶ/ሩ እኔን ለመክሰስ የበቁት ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና የዴሞክራሲ እድገት የተናገሩት ስላልተዋጠልኝ ንግግራቸውን በመተቸቴ ነው፡፡ እነሆም ከ8 ወር በኋላ ሌላ ቃለ መጠይቅ፤ ከሌላ ጋዜጣ ጋር አደረጉ፡፡ አሁንም የዶ/ሩ ምላሽ በፍፁም ሊዋጥልኝ አልቻለም፡፡ እናም እረጋ ብዬ አሰብኩ፡፡ ገና ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ስመጣ ለእራሴ የገባሁትን ቃልም በተመስጦዬ ደጋግሜ አንሰላሰልኩት፡፡ ..በታማኝነት፣ በሚዛናዊነት እና በሃቅ ሀገሬን አገለግላለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ ለማስፈራራት፣ ለክስ፣ለመደለያ እና ለመሳሰሉት ተፅዕኖዎች አልንበረከክም.. የሚል ነበር፡፡ አሁን አዲስ ፈተና ከፊቴ ተደቅኖአል፡፡ የዶ/ሩ ቃለ-መጠየቅ፡፡ አሁንም ዶ/ሩ የተናገሩት ሙሉ በሙሉ አልተዋጠልኝም፡፡ ሆኖም እንዳልተዋጠልኝ ጠቅሼ ሀሳባቸውን (የተናገሩትን) ብተች እንደአለፈው ጊዜ ሊከሱኝ ይችላሉ፡፡ በዝምታ ባልፈው ደግሞ ለህሊናዬ የገባሁትን ቃል ልጥስ ነው፡፡ ከክስ እና ህሊናን ከማታለል የቱ ይሻላል ብዬ ደግሜ አሰብኩ፡፡ አንሰላሰልኩ፡፡ በመጨረሻም የተናገሩት (ቃል የገቡት) ከሚጠፋ የወለዱት...ስለዚህም ምንም እንኳን ጋዜጣው ከታተመ በኋላ ሊከሱኝ ይችሉ ይሆን እንዴ? የሚል ስጋት ቢኖርም፤ ከህዝብ እና ከሀገር በላይ የለም፡፡ (እዚህ ሀገር ህግ ቢኖር ግን የሚከሰሰው እኔ ሳልሆን የዋሹት ደክተር እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡) እናም የመጣው ቢመጣ ህዝብን ለማሳሳት የሚሰጥ ፕሮፓጋንዳን፣ ያውም በአገጠጠ ውሸት ላይ የተመሰረተን፣ ያውም በሬ ወለደን... ሀሳብ እንተቻለን ፡፡
የቦንጋው ሰው 2
ማክሰኞ ነሐሴ 3 ቀን 2003ዓ.ም የወጣው መሰናዘሪያ ጋዜጣ ከተከበሩ የፓርላማ አባል ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ጋር የአደረገውን ቃለ መጠይቅ ..እኔ ፈፅሞ ጥገኛ አይደለሁም፤ ህዝቡም ጥገኛ አልመረጠም.. እና ..በደቡብ በኩል ያለው ድርቅ ሳይሆን በአብዛኛው ወደ ውጭ ገበያ ማመዘኑ ነው..በሚሉ ርዕሶች ለንባብ ማብቃቱ ነው ..የቦንጋው ሰው ዋ..ን እንድጽፍ ያነሳሳኝ ወይም የገፋፋኝ፡፡
በመጀመሪያ ግን .. ዶ/ር ሒኖቴ ዎዳ ቤቴ .. ስል በከፊቾ ቋንቋ ሰላምታ አቀርባለው፡፡ .. ሰላምታውን ወደ ፌደራል ቋንቋ ስንመነዝረው ዶ/ር እንደምን ኖት እንደማለት ነው..፡፡ ...ከዚህ በኃላ በቀጥታ ወደ ጉዳያችን እንግባ፡፡ዶ/ሩ ከወራት በፊት በዛው ጋዜጣ ላይ የሰጡትን ቃለ መጠይቅ ተከትሎ ጋዜጠኛው ሰዎች ..ዶ/ር አሸብር ከኢህአደግ ባለስልጣን የበለጠ ስለኢህአደግ ተሟጋች ሆኑ እያሉ ተችተዋል፡፡ ይህንን እንዴት አዩት?.. የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው እንዲህ ሲሉ መለሱለት .....ለዚህች ሀገር ትልቅ ልማት ያስመዘገበ ፓርቲ፤ እንደገና በአፍሪካ ደረጃም የአለም ህዝብም ተቀባይነት የሰጣቸው ትልቅ መሪ ያለበት ሀገር፤ ፓርቲውን በመደገፍ መቀጠል እፈልጋለሁ፡፡ ...ከዚህ አኳያ እኔ ከኢህአዴግ ጋር ዛሬም ተቃዋሞ የለኝም፤ ወደፊትም አይኖረኝም የሚል እምነት ነው ያለኝ.. የሚል መልስ መለሱ፡፡ ከሞላ ጎደል፡፡ መጀመሪያ ዶ/ሩ የተናገሩት ስለኦባማ ..ዴሞክራት.. ፓርቲ መስሎኝ እውነት ነው ብዬ ላልፍ ነበር፡፡ ስለ እኛው ኢህአዴግ መሆኑን ሳውቅ ግን...
የተከበሩ ዶ/ር አሸብር ለመሆኑ ..ለዚህች አገር ትልቅ ልማት ያስመዘገበ ፓርቲ.. ሲሉ ምን ማለትዎት ይሆን? የእርሶ ልማት መኖር እና ልማት ያለመኖር መስፈርትስ ምን ይሆን? ...እኔም ሆንኩ ሀገሬው የሚያውቀው ኢትዮጵያ በልማትም ሆነ በዴሞክራሲ እንኳን ከአለም ከአፍሪካም ወደ ኃላ የቀረች መሆኗን ነው፡፡ አቶ መለስ በአፍሪካ እና በአለም ተቀባይነት እንዳላቸውስ በምን አረጋገጡ? እስከማውቀው ድረስ እነ ሂዩማን ራይትስ ዎችን የመሳሰሉ አለም አቀፍ ድርጅቶች አቶ መለስን እና አገዘዛቸውን ..አምባገነን.. እያሉ እየተቹ ነው ያለው፡፡ እሺ.. ሌላው ይቅር ..እኔ ከኢህአዴግ ጋር ዛሬም ተቃዋሞ የለኝም.. ያሉትን መብትዎ ስለሆነ እንቀበለው ..ወደፊትም አይኖረኝም.. ያሉት ግን በጣም የወረደ ሀሳብ ነው፡፡ ስለወደፊቱ ምን የሚያውቁት ነገር አለ? ወይስ ነብይ ነኝ ሊሉን ፈልገው ነው?
ወደ ሌላው ጥያቄ እንለፍ ..መሰናዘሪያ፡- ጠ/ሚኒስትር መለስ ከዚህ የፓርላማ ዘመን በኋላ እለቃለሁ ብለው ነበርና አምርረው ይለቃሉ? አሁን ባሉበት ሁኔታ ሃገሪቱ የሚኖራት አቅጣጫስ ምን ሊሆን ይችላል?
ዶ/ር አሸብር፡- ይኼ ነገር በሰፊው መታሰብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ...በአሁኑ ሰዓት ሰው የተዘጋጀ አልመሰለኝም፡፡ ሰፊ የልማት ስራዎችን ጀምረዋል፡፡ የአባይን ግድብ ብትወስድ ስድስት ሰባት ዓመት መጨረስ ያለብን ነው፡፡ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ በአራት አምስት ዓመት ውስጥ መጨረስ ያለብን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ እኔ ጠ/ሚኒስትሩ የጀመሩትን መጨረስ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በሌላ በኩልም ጠ/ሚኒስትሩ የሀገር መሪ መሆን በሚገባቸው ሰዓት አልነበረም መሪ የሆኑት፡፡ በ35 ዓመታቸው ወጣት ሆነው ነው የተረከቡት፡፡... አሁን በትክክለኛው የመሪነት እድሜ ላይ ነው ያሉት፡፡ 50 እና ከ50 አመት በላይ ጥሩ እድሜ ነው፡፡ ...የአፍሪካም የዓለም መንግስታት ሁሉም ጠ/ሚኒስትሩን እንጠቀምባቸው እያሉ ነው ያሉት፡፡ ...ህዝቡን በዚህ ሁኔታ አነሳስተው የት ነው ጥለው የሚሄዱት፡፡ በአገሪቱ በአፍሪካ፣ በዓለም መንግስታትም እየታመነባቸው አርፋለሁ ቢሉ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ እሳቸውም ፓርቲውም ሊያስብበት ይገባል፡፡ በእኔ እምነት ይህችን ሀገር ከእሳቸው ውጭ ባሁኑ ሰዓት አስተካክሎ ሊመራ የሚችል ማንም ኃይል የለም፡፡ ...ማንም የለም፤ አማራጭ የለም መለስ ዜናዊ ብቻና ብቻ ናቸው፡፡ አሁን ህዝቡን በፍቅር እንዳነሳሱት፣ ለልማት እንዳሰባሰቡት እውነቱን ለመናገር ለእያንዳንዱ ህዝብ እኔ አለሁልህ ብሎ የሚመራ መሪ መለስ ብቻ ናቸው፡፡ ...ይህ የሁሉም የእያንዳንዱ ጥያቄ ነው የሚመስለኝ፡፡ ፓርቲው ኢህአዴግም አማራጭ አለኝ ብሎ ሌላ ካሰበ ትልቅ ስህተት ነው የሚሆነው፡፡ እሳቸውም እወርዳለሁ በሚል ሁኔታ ሳይዘናጉ ከወዲሁ እንደድሮው ስለሃገሪቱ ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡ ህዝቡ እሳቸውን ከስልጣናቸው አይለቃቸውም፡፡.. ወዳጄ.. ይሄን ይመስላል የዶ/ር አሸብር መልስ፡፡
የከፋ ሰው እንዲህ አይነት የፈጠጠ፣ የአገጠጠ ውሸት ሲገጥመው ..አሞኔ?.. ሲል ይጠይቃል፡፡ ይህንንም ወደ አማርኛ ስንመልሰው ምንድነው? ማለት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እውነትም ዶ/ር ..አሞኔ?.. አረ ለመሆኑ በአንድ በኩል የኢህአዴግ አባል አይደለሁም እያሉ በአቶ መለስ ቦታ (በኢህአዴግ በኩል) ሰው የተዘጋጀ አይመስለኝም ያሉት በምን አውቀው ነው፡፡ ይችን ትንሽ ፈታ አድርገው ቢያብራሯት? የአባይ ግድብ ትራንስፎርሜሽን ምናምን... የሚባሉ ነገሮች ስለተጀመሩና እስከ ሚያልቁ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣን ላይ ይቆዩ ማለትስ ምን ማለት ይሆን? መንግስት በየአምስት አመቱ የይስሙላም ቢሆን ምርጫ ያካሄዳል፡፡ እርሶ ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ ሰባት አመት የሚፈጀው ግድብ እስኪያልቅ በስልጣን ይቆዩ እያሉን ነው፡፡ ምርጫው ይቅር? የምርጫ ቦርድ ቢሮስ ወደ ክሊኒክ ይቀየርሎት?... አቶ መለስ ለ20 ዓመት በስልጣን ቆይተዋል፡፡ መቼም የዚህን ያህል አመት በአምባገነኖች ሀገር ካልሆነ በቀር ዴሞክራት በሆኑ ሀገራት በስልጣን የቆየ መሪ የለም፡፡ የዶ/ሩ መከራከሪያ መለስ ልጅ ሆነው ስልጣን ስለያዙ እስከ ዛሬ የነበረው አስተዳደር ..የልጅ ጨዋታ ነው.. አሁን ነው የበሰሉት፤ እናም ሌላ 20 ዓመት በስልጣን ይቆዩ ነው፡፡ በድምሩ 40 አመት፡፡ ከጋዳፊ እኩል ማለት ነው፡፡ እንዲህ በሁሉም ነገር አቻ ይሁኑ... ለነገሩ ምን አላት 40 አመት ነገ ትደርሳለች፡፡ ምርጫስ ምን ያደርጋል? አይደል ዶ/ር፡፡ አንድ ሊገባኝ ያልቻለ ነገር አለ፡፡ በባለፈውም ፅሁፌ አንስቼሎት ነበር ..የአፍሪካም የአለምም መንግስታት ጠ/ሚኒስትሩን እንጠቀምባቸው እያሉ ነው.. ያሉት አይነትን ንግግር የሚናገሩት መረጃውን ከየት እያመጡት ነው? የአፍሪካ እና የአለም መንግስታት እንዲህ አይነት ንግግር ሲናገሩስ ለእርሶ ለብቻዎት ነው? ወይስ እንዲህ ብለው ቢናገሩ የሚል ቀና አመለካከት ኖሮት ነው? አለዚያ ህዝብን ማሳሳት ወንጀል መሆኑን ማወቅ አለቦት፡፡ ለእንዲህ አይነት ንግግር ምንጭ መጥቀስ የግድ ነው፡፡ አምባገነንነትንም ውሸታምነትንም አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ ...ዶ/ሩ እንዲህ ሲሉ ደግሞ ለኢህአዴግ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ..እሳቸውም ፓርቲውም ሊያስብበት ይገባል፡፡.. ቀጠሉና ደግሞ ..በእኔ እምነት ይህችን ሀገር ከእሳቸው ውጭ በአሁኑ ወቅት አስተካክሎ ሊመራ የሚችል ማንም የለም.. ሲሉ ጨመሩበት፡፡ እውነት ግን ዶክተር ከእሳቸው ውጭ ማንም የለ? አንድ እንኳ? ያሳዝናል፡፡ያሁሉ ሚንስትርስ ለእርሶ ሰው ሆኖ አልታዮትም? በእኔ እምነት ግን እንዲህ አይነት አስተዳደር፤ ህዝብን እያስራቡ እና እየቀጠቀጡ ማስተዳደር ለማንም ይከብደዋል ብዬ አላስብም፡፡ ለእርሶም ቢሆን፡፡ ለእኔም ቢሆን፡፡
በድሮ ጊዜ በርካታ አፋሽ አጎንባሾች በአድርባይነት አምባገነን አገዛዝ እንዲቀጥል የቻሉትን ያህል ለፍተዋል፡፡ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴን ..ፀሐዩ ንጉሰ ነገስት..፣ ኮለኔል መንግስቱ ኃ/ማርያምን ደግሞ ..ቆራጡ መሪያችን፣ ኮሚኒስቱ መሪያችን.. እያሉ ማለቴ ነው፡፡ ዶ/ር አሸብር ደግሞ እንዲህ ይላሉ ..ማንም የለም፤ አማራጭ የለም፤ መለስ ዜናዊ ብቻ ናቸው፡፡.. እሺ.. ከጓድ መለስ ዜናዊ ጋር ወደፊት... ..ፓርቲው ኢህአዴግም አማራጭ አለኝ ብሎ ሌላ ካሰበ ትልቅ ስህተት ነው የሚሆነው.. ሌላኛው የዶ/ሩ ውዳሴ፡፡ ከንቱ ውዳሴ ያለው ማን ነበር? ...ዶ/ር እዚህች ጋር ፍሬን ያዙ፡፡ ለምን መሰሎት? ቢያንስ ኢህአዴግ እና አቶ መለስ ልሳናቸው እስኪዘጋ ስለ..መተካካት.. ካወሩት ጋር ሊጋጩ ስለሚችሉ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እኮ ግራ ቀኙን አይቶ መናገር መልካም ነው፡፡ ሰው ዝም ሲል የማያውቅ ሆኖ አይደለም፡፡ ይታዘባል፡፡ ይሄ አይነት ንግግር ለአቶ መለስም ቢሆን የሚጥማቸው አይመስለኝም፡፡ ባይሆን ለፉገራም ቢሆን ..ስለመተካካቱ.. እያወሩ ጊዜው ሲደርስ ..አይሰማም.. ቢሉ ነው የሚቀላቸው፡፡ የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብ ምናምን... አቶ መለስ በስልጣን እንዲቆዩ ይፈልጋል የሚሉትን ፕሮፓጋንዳ ለራሶት አድርጉት፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ መቼም እንዲህ ብሎ አያውቅምና፡፡ ለምሳሌ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ መለስ ዛሬ ከስልጣን ቢወርዱ ሺ እጥፍ ጊዜ አደንቃቸውም፤ አከብራቸውም ነበር፡፡ ሀገሬም ተጠቃሚ የምትሆነው ያን ጊዜ ነበር፡፡ ...ዶ/ር ኢህአዴግ ከ5 ሚሊዮን አባላት በላይ አለኝ እያለ ነው፡፡ በርካታ አመራርም አፍርቼያለሁ ብሎ ደጋግሞ ነግሮናል፡፡ እርሶ ደግሞ ከመለስ ውጪ ሰው የለም እያሉ ነው፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? ማነው የዋሸው? በርካታ አመራር አፍርቼአለሁ የሚለው ኢህአዴግ? ወይስ ምንም ተተኪ አመራር አላፈራም የሚሉት ዶ/ር አሸብር?
ዶ/ር አሸብር ጠ/ሚኒስትሩን ሲገልፁ ..መለስ መቶ በመቶ የተሻሉ መሪ ናቸው፡፡ እምነት የሚጣልባቸው ጥሩ አእምሮ ያላቸው እጅግ የተማሩ ሰው፤ ከንባብ የማይለዩ ሰውና ትልቅ መሪ ናቸው፡፡.. እንደው ንፁህ ህሊና ካለው ሰው፤ ያውም ዶ/ር የሚል ተቀጥላ ከስሙ በፊት ካለው ሰው የዚህ አይነት አስተያየት ይሰማልን? አይ.. 8ኛው ሺ ...፡፡ የሆነ ሆኖ መለስ አንባቢ ሊሆኑ ይችሉ እንደሆነ እንጂ እምነት የሚጣልባቸው እንኳ አይመስለኝም፡፡ለዚህ ማስረጃ ከፈለጉ ደግሞ የራሳቸው ጓደኞች በመለስ ደጋግመው ለመታለላቸው የፃፉትን አንብቡ፡፡ ደግሞም እከሌ አንባቢ ነው እያሉ ማድነቅ እውቀት አይሆንም፡፡ እውቀት የሚሆነው ራሶት ሲያነቡ ነው፡፡
ሌላውን የዶ/ሩን አሳፋሪ ንግግር አንብቡ ..ረሀብ ድህነት እንደሆነ እንኳን በኛ ሀገር በነአሜሪካም፣ በነብሪቴን በረንዳ አዳሪ እዛም አለ፤ እዚህም አለ፡፡ ችግሩ ተጠናክሮ ዓለም በከፍተኛ ቀውስ ባለበት ባሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ላይ አይደለችም፡፡ የያዘችው ፖሊሲና አይዶሎጂ ጠቅሞ ቀውሱን ለመቋቋም ችላለች፡፡.. ብታምኑም ባታምኑም ይሄ ንግግር የወጣው ከአንድ ዶክተር ነው፡፡ ዶክተር...... እንኳን ዶክተር ቀርቶ ማንበብ እና መፃፍ የማይችል ሰውም ቢሆን አሜሪካም በረንዳ አዳሪ አለ፤ ብሪታኒያም በረንዳ አዳሪ አለ፤ ኢትዮጵያም በረንዳ አዳሪ አለ ብሎ የራሱን የወረደ እውቀት አያስፎግርም፡፡ እሺ እባኮት.. የእኛ ዶ/ር አሜሪካ እና እንግሊዝ ድህነትን መቋቋም ሲያቅታቸው፤ ኢትዮጵያ በያዘችው ፖሊሲ እና አይዶሎጂ ተቋቋመች? እውነቶትን ነው? ወይስ ቲያትር እየሰሩ መስሎት ነው? ይስሙኛ ዶ/ር.. የቦንጋ ህዝብ እርሶን በመምረጡ ያዘነ ይመስለኛል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ እንኳን እንደዚህ አይሉም፡፡ ለነገሩ... ድሮ ነገስታቶችን እንዲህ አይነት አስተያየት እየሰጡ የሚያስደስቱ ሰዎች ነበሩ፡፡ በእርግጥ እነዚያህ ሰዎች የጥርስ ሐኪም አልነበሩም፡፡ አዝማሪ እንጂ፡፡እናም...
ዶ/ር አሸብር እንዲህ ሲሉ ደግሞ ተመፃደቁ ወይም ዋሹ ..ከጎረቤት ሀገራት በረሃቡ ሳቢያ ወደ እኛ ብዙ ሰዎች መጥተዋል፡፡ ...መንግስት ጥሩ የገንዘብም ሆነ የእህል ክምችት ስላለው ያስተካክለዋል፡፡.. አረ ስለእግዚአብሔር.. መንግስት እህል እየለመነ፤ ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ በአደባባይ ጥሪ እያደረገ እያለ እንዴት እህል ሞልቷል ይላሉ? ወይስ ..ምግብማ ሞልቶአል.. የሚለውን የጥላሁን ገሰሰን ዘፈን መዝፈን ፈልገው ነው?...
የዶ/ሩ ወሬ ማለቂያም የለው፤ ..በእርግጠኝነት ከደህነት እንወጣለን፡፡ ድህነት አይኑር አይባልም.. ይሉሃል፡፡ የእኛ ዶክተር፡፡ እኔ ግን እልሃለው ..ድህነት ለዘላለሙ አይኑር....፡፡ እንዲህ አይነት ቀልደኛ የፓርላማ አባልም ለዘላለም አይኑር ስል እጨምራለው፡፡
የዶ/ሩ የወረደ እና ንባብ አይቶት የሚያውቅ የማይመስለው ቃለ መጠይቅ ቀጥሎአል፡፡ ..መሰናዘሪያ፡- ድሮ ረሀብና ድርቅ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ብቻ ነበር፡፡ አሁን ደናማዎቹ ደቡብ እና ኦሮሚያ ናቸው የተጠቁት ይህንንስ እንዴት ያዩታል?
ዶ/ር አሸብር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ምርት የለም አይደለም፡፡ ትልቁ ችግሩ በአብዛኛው ወደ ውጭ ልኮ መሸጡ በዝቷል፡፡ እያንዳንዱ ገበሬ አብዛኛው የእርሻ መሬት በአዋጭና በውጭ ንግድ በሚሆን ምርት ላይ ማዋሉ ችግር የፈጠረ ይመስለኛል፡፡ ደቡብም ብትል በጣም በብዙ ይመረታል፡፡ በመሀል ሀገራትም በገፍ ይመረታል፡፡ ህዝቡ ምርቱን በቤቱ መያዙ፤ ምርቱን በማስቀመጥ በይበልጥ ለውስጥ ገበያ ቢያቀርብ ተጠቃሚ መሆኑን ማሰቡና ለገበያ አለማውጣቱ አንድ ችግር ነው፡፡ ሆኖም ይህ በራሱ የእድገታችን ውጤት ነው፡፡.. አሁንም እደግመዋለሁ ይሄን አስተያየት፤ ያነበበ ሰው አስተያየት ሳይሆን ዝም ብሎ በስማ በለው የሚወራ ..ጆሮ ጠገብ.. እውቀት ያለው ሰው የሚሰጠው አስተያየት ብቻ ነው፡፡ ጆሮ ጠገብ.. በየትኛውስ አለም ያለ አርሶ አደር ነው ያመረተውን ጎተራው ቆልፎ፤ አይኑ እያየ፤ ጆሮው እየሰማ ራሱን እና ህፃናት ልጆቹን በረሀብ የሚገለው? እውነቴን ነው የምለው፤ ብዙ የኢህአዴግ አባላት እና ደጋፊዎች የሚሰጧቸውን አስተያየት ተከታትያለው፡፡ የእነሱ ከእርሶ በጣም የተሻለ ነው፡፡ መንደር ላይ ያለ ጠርናፊ እንኳ ከዚህ በብዙ የተሻለ አስተያየት ይሰጣል፡፡ ትንሽ ሊያሳምን የሚችል፡፡ የእርሶ ግን ጋዝ ጋዝ የሚል፤ ደረቅ ውሸት፡፡ ሆድ የሚያሰማም፡፡ ምንም አይነት ብስለትም ሆነ እውነትነት የማይታይበት፡፡ ...ዶ/ር እንዴት ሆኖ ነው ገበሬው የተራበው? የአመረተውን ለውጭ ገበያ ስላቀረበ? ለውጭ ገበያ ካቀረበ እኮ በምርቱ ምትክ ደህና ገቢ ያገኛል፡፡ በአገኘው ገቢ ደግሞ ለኑሮ የሚያስፈልገውን ያሟላል፡፡ ዛሬ በሀገራችን የተራበው ገበሬ ግን አምርቶ ብቻ ሳይሆን ገዝቶም መብላት የማይችል ስለሆነ ነው፡፡ ጥጥ እና ሰሊጥ የሚያመርቱ ገበሬዎች አይራቡም፡፡ ጥጡን እና ሰሊጡን ሸጠው በሚያገኙት ገንዘብ ምግብ ይገዛሉና፡፡ ገበሬ የግድ ጤፍ እና ስንዴ ብቻ ማምረት የለበትም፡፡ ይሄንን ካላወቁ የሚያውቅ ሰው ጠይቁ፡፡ አንድ የወዳጅነት ምክር ልስጦት፤ ጋዜጠኛ ለቃለ መጠይቅ ሲጠይቆት መጀመሪያ እውቀት ያለውን ሰውን አማክሩ፡፡ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ እውቀት ባይኖሮት፤ ለምን እውቀት የሎትም ተብለው አይወቀሱም፡፡ አለማወቅ ደግሞ ሀጢያት አይደለም፡፡ ሀጢአት የሚሆነው የማያውቁትን ሲዘባርቁ ብቻ ነው፡፡...እንጨት እንጨት ከሚለው ከዶ/ሩ ቃለ መጠይቅ የተመቸችኝ ይህች ብቻ ነች ..እኔ ኢህአዴግን ተቃውሜ አልገባሁም፡፡ የተቃወምኩት ግለሰቡን ነበር፡፡ የኔ ሚሽን የተሳካ ነው ብየነው የማምነው፡፡ አሁን ግን እራሴም በሰፊው አስቤበት፤ ከቤተሰቦቼም ከማምናቸው ሰዎችም ከተመካከርኩ በኋላ ከፓርላማው ይልቅ ተመልሼ በሙያዬ ብሰራና ብቀጥል ደስ ይለኛል፡፡.. በእውነቱ ከሆነ ከፓርላማው ለመውጣት ምንም እንኳ ..ከመረጠኝ ህዝብ ተመካክሬ.. ባይሉም፤ አለማወቅ ነውና እንደ ስህተት ሳንቆጥረው በውሳኔዎ በጣም ደስተኛ መሆኔን እገልፅሎታለሁ፡፡ አንዴ ልድገመውና ..ከፓርላማው ይልቅ ተመልሼ በሙያዬ ብሰራና ብቀጥል ደስ ይለኛል.. ያሉት በእጅጉ የሚያስመሰግኖት ነው፡፡... ለዚህ ውሳኔዎ ያለኝን ክብር ለመግለፅ ደግሞ አንድ ሙዚቃ ልገብዞ ..አሁን አየ አይኔ፣ አሁን አየ አይኔ.....
ማስታወሻ
የተከበሩ የፓርላማ አባል እና የጥርስ ሐኪም ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ሆይ.. የህዝብ ወኪል ነኝ እስካሉ ድረስ፤ ህዝብን እና ሀገርን በሚመለከት በሰጡት አስተያየት ትችት ሲቀርብቦት ወደ ክስ መሮጡ ይበልጥ ያስገምቶታል፡፡ ከቻሉ ሀሳብን በሀሳብ መመከት ነው ያለቦት፡፡ ካልቻሉ ደግሞ ወይ ከፓርላማው መልቀቅ፤ አሊያም ትችትን በፀጋ መቀበል፡፡ ምን አልባት ለዚህ አይነቱ ድክመቶት ከአቦይ ስብሓት ነጋ ቢማሩም መልካም ነው፡፡ ሰው የሚማረው አንድም ከመከራ አንድም ከፊደል ነው ያለው ማን ነበር...እንጃ፡፡

No comments:

Post a Comment