"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Saturday 10 May 2014

ለፌስቡክ ባለንጀሮቼ ብቻ የተጻፈ)


ባለፈው፣በቤተ-መንግስት መውጫ፣ በሸራተን መውረጃ መንገድ ላይ የተሰቀለ ፖስተር አየሁ፡፡‹‹ባፍሪካ የመጀመርያው የሳቅ ትምርት ቤት››ይላል፡፡የዘመኑን መንፈስ ከሚያሳዩ ተቋሞች ዋናው መሆን አለበት ብየ አሰብኩ፡፡በዘመኑ ዝም ብሎ መሳቅ ከባድ ነው፡፡እንድያውም በዘመኑ ከልቡ የሚስቅ ሰው ከተገኘ እንደ ስድስት ኪሎ አንበሳ በቅጽር ከልለን ልንጎበኘውና ልናስጎበኘው ይገብባል፡፡
በረንዳ ላይ ተቀምጠህ ምሳ ስትበላ ከወገቡ በላይ ሥጋ ከወገቡ በታች የመኪና ጎማ የለበሰ ተመጽዋች ወደ ጠረጴዛህ እግር እየተንፏቀቀ ቀርቦ ልመና ይሁን ትእዛዝ ባልለየለት ድምጽ‹‹አጉርሰኝ››ሲልህ እንዴት ትስቃለህ፡፡የቤት አከራይህ ከጓሮህ ያለውን የቀለበት መ...ንገድ ከራሳቸው ኪስ አውጥተው ያስገነቡት ይመስል‹‹አካባቢውን እድገት ግምት ውስጥ በማስገባት ተዛሬ ጀምሮ በኪራዩ ላይ አንድ ሺህ ብር ጨምሬያለሁ›› ብለው ሲያረዱህ እንዴት ትስቃለህ፡፡ኮሌጅ እንዲበጥስ የሰደድከው ታናሽ ወንድምህ ለራዛ ዘመቻ የወጣ ይመስል፤ባውቶብስ ሂዶ በወሳንሳ ሲመለስ እንዴት ትስቃለህ፡፡የሳቅ ትምርትቤት መስራች አቶ በላቸው ገብቶታል፡፡ሳቅ እንደ ሂሳብ ወይም እንደ እደ ጥበብ ውጤቶች በልምምድና በጥናት ካልሆነ በቀር በዋዛ የሚገኝ አልሆነም፡፡ይህ ትምርትቤት ወደ ፊት በቢኤና በፒኤችዲ ማስመረቅ ሲጀምር ሰዎች እንደየደረጃቸው ይስቃሉ፡፡‹‹ያ ሰውየ ፍርርርስ ሲል አየከው? ከበላቸው ግርማ ትምርትቤት ማስተርሱን ስለ ሠራ እኮ ነው›› የምንልበት ቀን ሩቅ አይመስለኝም፡፡