ታሪክን የኋሊት ‹‹ለትግራይ ተወላጆች የቀረበ ጥሪ››
(አንድ አድርገን ሚያዚያ 11 ፤ 2004 ዓ.ም) ፡- ቀኑ ህዳር 6 1985 ዓ.ም ነበር ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰሜን አቅጣጫ በምትገኝው በመንበረ መንግስት ቁስቋም ቤተክርስትያን ብዙ ህዝበ ክርስትያን ተሰብስቧል ፡፡ ምክንያቱ በዓለ ቁስቋምንና የጾመ ጽጌን ፍቺ በዓል ለማክበር ነበረ ፡፡ የዕለቱም አስተማሪ አለቃ አያሌው ታምሩ ነበሩ፡፡ አለቃ ‹‹በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን›› ብለው ጀመሩ፡፡ በትምህርታቸውም ስለ እመቤታችን ስደት ፤ ስለ ቁስቋም ታሪክ ፤ ወደ እየሩሳሌም ስለ መመለሷ ፤ ከእመቤታችን 300 ዓመት በኋላ በግብጽ ስለተሰራው የመታሰቢያ ቤተክርስትያን ፤ በዚህ በዓል ምክንያት ኢትዮጵያውያን ነገስታትና ንግስታት ስላደረጓቸው መንፈሳዊ ተሳትፎዎች ፤ ስመ ጥሩዋ ኢትዮጵያዊት ንግስት እቴጌ ምትዋብ በጎንደር ስላሰሯት የደብረ ቁስቋም ቤተክርስትያን ፤ ስለ ጾመ ጽጌ ፤ ስለ ማህሌተ ጽጌ በዝርዝር አስተማሩ፡፡ ከዚያም በመቀጠል ፤ በእመቤታችን በቅድስት ማርያምና በልጇ ስደት በረከትን ካገኙ የኢትዮጵያ አውራጃዎች አንዱ የሆነው ምድረ ትግራይ ከሌሎች ቅዱሳን የኢትዮጵያ መካናት ጋር የተጣመረ የታሪክ ተዛምዶ ያለው ከመሆኑ ባሻገር ከታቦተ ጽዮን ጀምሮ ለኢትዮጵያ ለተሰጡ ልዩ ልዩ ስጋዊ እና መንፈሳዊ በረከቶች ምንጭና ቦይ ሆኖ የኖረ ነው ፡፡ ዋልድባ ገዳምም ይህን መንፈሳዊ በረከት ከሚገኝባቸው ቦታዎች አንዱ ነው ፤ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ የተሰጠውን ስጋዊ ስልጣን አገሪቱንና ቤተክርስትያንን ከውድቀት ለማንሳት ሊሰራበት ይገባል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ህዝብና እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ስራ ቢሰራ ግን ትዝብትና የታሪክ ተወቃሽነትን ያተርፋል ፤ ያለው ሰፊት ትምህርት ሰጥተዋል ፡፡(የአለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ ገጽ 26)