"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Tuesday 17 April 2012

ለኢትዮጵያዊ ወገኑ ማነው?

            ለኢትዮጵያዊ ወገኑ ማነው?                                                                                                             በተለይ ጥቂት በማይባሉ የአፍሪካ አገሮችና በመካከለኛው ምስራቅ ባጠቃላይ ደግሞ በዓለም ደረጃ የኢትዮጵያዊ ማንነቱ በእንግዳ ተቀባይነቱ እና በጀግንነቱ ሲለካ እንደኖረ አሌ የማይባል ሀቅ ነው። በሃይማኖት መጽሐፍትና ሌሎች ቀደምት ድርሳናት በጥልቀት ሲወሳለት የኖረው እንግዳ አስተናጋጅነቱ እና ጥሩ ጉርብትናው ዛሬ እንዳልነበር ሆኖ ለመስማት በሚዘገንን ርሃብ፣ ስደትና የነጻነት እጦት ሲተካ፤ ኢትዮጵያዊ በየሄደበት ከልክ በላይ ሲናቅና ሲገፋ፤ ከሰው በታች ተደርጎ ጠቆጥሮ አንገቱን ቀና ለማድረግ እንኳ የመንፈስ ጥንካሬ አጥቶ ቁልቁል ሲሽቀነጠር አይዞህ ብሎ ከጎኑ የቆመ ማነው?
ሲሆን ሲሆን የወገኖቹን የቀደመ በጎ ስራ አስታውሶ ካልሆነም በሰብአዊነት ለኢትዮጵያዊው እኔ አለውህ ያለው ማን ነው? ከሩቅ ምስራቋ ጃፓን እስከ ላቲን አሜሪካዋ ሜክሲኮ፣ ከአውስትራሊያ እስከ ካናዳ፣ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ምራብ አውሮፓ ኖርዌ፣ ከአረቡ ዓለም መካከለኛው ምስራቅ አስከ ሙሉ እስያ በሁሉም ቦታ በሚባል መልኩ ይዘቱና ምክንያቱ ይለያይ እንጅ ኢጥዮጵያዊ ይሰቃያል፣ ይታሰራል፣ መብቱ ይረገጣል የሰቀቀን ኑሮን እንዲገፋ ይደረጋል። ከዚህ እጅግ በከፋ መልኩ ደግሞ በሀገር ውስጥ በህዝባችን ላይ የሚደረገውን ግርፋትና ሰቆቃ እስርና መጉላላት መፈናቀልና ሞት ስናስታውስ በእርግጥ ለኢትዮጵያዊ ወገኑ ማነው? እንድንል ያደርገናል። በጣም ከትንሿ ኢፍትሃዊ ስራ ብንጀምር አስፋልት ዳር ቁጭ ብሎ በፀሓይ ሃሩር እየተቃጠሉ በነፋስ እየተገረፉ የአካባቢው አየር ያመጣውን ማንኛውንም አይነት ጠረንና አቧራ እየማጉ ጥቂት የድንች፣ የቃሪያ የቲማቲምና የመሳሰሉትን የአትክልት ውጤቶችን ለመቸርቸር ቢፈልጉ ወያኔ መሆን የግድ ይልዎታል። ጥራታቸው እየሞተ ካሉት የወያኔ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ስራ ለመቀጠር ቢፈልጉ፤ ይህም ወያኔያዊ መስፈርት አሉት። አንዳንዴ ወያኔ ከመሆንም ባሻገር የቱባ ወያኔ ባለስልጣን ወገን መሆንም ሊያስፈልግ ይችላል። ይህ ማለት ደግሞ ባለስልጣኖች እነማን እንደሆኑ በጣም ግልጽ ነውና ማን ለመቀጠር ሙሉ መብት እንዳለው ለመገመት እሩቅ ማሰብ አስፈላጊ አይመስለኝም። ለአንድ ክፍት የስራ ቦታ የሚጠይቀውን አሟልቶ እራስን ለገበያው እንደሚመች አድርጎ ማቅረብና በነፃ ገበያ ተወዳድሮ የገባያውን ውሳኔ መቀበል የሚለው ዲሞክራሲያዊ ሂደት፤ በኢትዮጵያ በወረቀት ላይ ብቻ ያለ ለእርዳታ ሰጭ የውጭ ሀገራት ፎጆታ ብቻ የተቀመጠ እንጂ በመንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የሚተገበር ነገር አይደለም እጅግ በጣም ቢያንስ አሁን ባለው የሀገራችን አሰራር። ይህን መሰሉ የወያኔ አሰራር የዱር እንሰሳትን እና አኗኗራቸውን ያስታውሰኛል። የዱር እንሰሳት የራሳቸውን ክልለ ግዛት አስረግጠው ለማወቅና ለመቆጣጠር እንዲሁም ሌሎች የእንስሳ ዝርያዎች ወደ እነሱ ክልል እንዳይገቡ ለመከላከል የሚኖሩበትን ክልል በጠረናቸው ያጥራሉ። ስለዚህም በዚያ የተለየ ክልል ከነሱ ዝርያ በቀር እንዲዘዋወር አይፈቀድለትም ማለት ነው፤ ሲዘዋወር ከተገኘም ጥቃት ይሰነዘርበታል። ይህን አይነቱን የዱር አውሬዎች ዘዴ ነው እንግዲህ ወያኔ በእኛ ላይ እየተገበረ ያለው። መለስ ዜናዊ ልክ እንደ ዱር እንሰሳት የራሱን ወገኖችና እሱ እንደሚፈልገው የሚሰሩ የሚታዘዙና የሚተገብሩትን ብቻ በዙሪያው ያሰባስባል። ከወያኔ የዘር ሀረግ ውጭ የሆኑና የወያኔን የዘረኝነት አከሄድ ያልተቀበሉ የሚፈልጉትን አያገኙም። ያገኙም ካሉ የተለያየ ምክንያት ተለጥፎባቸው ይባረራሉ፤ እድለኛ ከሆኑ ማለቴ ነው አለዚያ ግን መጨረሻቸው ወህኒም ሊሆን ይችላል። ወያኔ የኔ ከሚለው የዘር ሀረግም ቢሆኑ ወያኔያዊ አሰራርን ማመንና መተግበር ይጠበቅበዋታል። የወር ክፍያ ደመወዝ አንሶናልና ይጨመርልንን ለመሳሰሉ እጅግ በጣም ቀላል የመብት ጥያቄዎች ሁኔታውን አጥንቶ ተገቢ መልስ መስጠት ይገባ ነበር ያም ባይሆንና አሉታዊ መልስ መስጠት እንኳ ቢያስፈልግ በቀላሉ ሊመለሱ ሲችሉ ወያኔ ግን የሚወሰደው እጅግ የከፋውን ነው። ይህንና ተመሳሳይ ጥያቄ የጠየቁ የዘር ጀርባቸው ይጠናል እንደቀረቤታቸውም የግንቦት7፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ወይም የሌላ አሸባሪ ቡድን አባላት ተብለው ይፈረጃሉ ከስራም እስከነአካቴው ይባረራሉ ወይም ይታሰራሉ። እድለኛ ሆነው ወደስራ መመለስ ከቻሉ በወያኔ ተቀነባበሮ በተዘጋጀና ከዚህ በሗላ በቀሪ ዘመናቸው ምንም የመብትም ሆነ የሌላ ጥያቄ እንዳይጠይቁ በሚያደርግ አስገዳጅ የይቅርታ ውል ላይ እንዲፈርሙ ይደረጋሉ። ለእነሱ የተከለከለ የደመወዝ ጭማሪም እነሱ ሲያገኙት ከነበረው በሶስትና አራት እጥፍ አብላጫ ደመወዝ ችሎታቸው ከዜጋው ያነሰም ቢሆን የውጭ ዜጋ ይቀጠርበታል። ይህ እንግዲህ ባለፉት የወያኔ አገዛዝ ዘመናት የታየ እውነታ ነው። ታዲያ ይህን የተመለከተ አንድ ሰው ለኢትዮጵያዊ ወገኑ ማነው ብሎ ቢጠይቅ የሚያስደንቅ ሊሆን ይችላል? ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተደራጅቼ መንግስትን እገዳደራለሁ የሚሉ ፓረቲዎችና የአባሎቻቸው እጣፈንታ በአሰቃቂ ሁኔታ አደጋ ላይ ነው። ለወያኔ ጨዋታ ተመቻችተው ጭፈራውን ሞቅ ደመቅ እስካደረጉ ድረስ ፓርቲዎችም ሆኑ አባላት ዳጎስ ያለ የድጎማ ገንዘብ እየተሰጣቸው ያለስጋት ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ ካልሆነ ግን ከላይ እንደገለጽኩት መጨረሻቸው ያማረ አይሆንም። እንዲያው ለነገሩ አልኩ እንጂ ባገር ውስጥ ሰላማዊ የሚባል ትግል አለ ብየ አላምንም። ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ለመጥራት እንኳ የማይችል ቡድን ህዝብን ነፃ ያወጣል የሚል እምነትም ምኞትም የለኝም። ሌላው ቀርቶ የግል አስተሳሰቡን አጠንክሮ የሚገልፅ ግለሰብ ለወያኔ አሸባሪ እንጅ ሰላማዊ ታጋይ ስላልሆነ ሀገር ውስጥ ያለው ሰላማዊ የሚባለው እንቅስቃሴ በኔ እምነት የሞተ ነው። በወያኔ መቶ በመቶ ቁጥጥር ስር ነውና። ባሁኑ ሰአት ከጥቂት ምርጥ የመለስ ዜናዊና የወያኔ አቀንቃኞች በስተቀር በየትኛውም መመዘኛ ነፃነት የሚሰማው ትውልድ በሀገር ውስጥ እንዲታይ አየፈለግም ። በመሆኑም በኢኮኖሚ እራሱን የቻለ ዜጋ መብቱን ለማስከበር ወደ ሗላ የሚጎትተው ነገር እንደሌለ የተገነዘበው የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት አንጻር ሁሉም ዜጋ በኢኮኖሚ እራሱን ችሎ እንዳይቆምና ሁሌም የወያኔ ትርፍራፊ ለቃሚ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ላለፉት ሃያ ዓመታት በትጋት ሰርቷል አሁንም እየሰራ ይገኛል። ይህ ኢትዮጵያዊያንን የወያኔ ጥገኛ የማድረግ ስራ ቀጥሎ ያገሬ ከተሜ ተፈጥሯዊ የሆነውን ሰብአዊ መብቱን እንኳ ሳይቀር ለወያኔ ሸጦና አስረክቦ በለውጥ ያስቀራትን፣ አለችኝ የሚላትንና ምንም ባጣ ለልጄ አወርሳታለሁ ሲላት የነበረች የበሬ ግንባር የምታክል መኖሪያ ቦታውን እንኳ ሳይቀር ወያኔ ሰሞኑን ያወጣውን አዲስ የሊዝ ፖሊሲ መሰረት በማድረግ እና በመንጠቅ ህዝባችንን ሲያስለቅስ እየተመለከትን ነው። በጋንቤላና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች፤ ገዳማትንና የቀብር ቦታዎችን ጨምሮ ለልማት በሚል ሰበብ የሚደረገው የቦታ መንጠቅ፣ ከመኖሪያ ቅየ ማፈናቀል፣ ያለትክ ቦታ ይትም ግባ ብሎ ማባረር፣ ማንገላታትና መብት ገፋፋ ሲታይ በእርግጥ ሀገራችንን እየመራን ነው የሚሉት ዘረኛው መለስ ዜናዊና ወያኔዎች ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን አጠያያቂ ያደርገዋል። ከዚህ በፊት በወያኔ ትእዛዝ በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ ከትግራይ ክልል የመጡ የሀገር ውስጥ ሰፋሪዎች በሁመራና በወልቃይት ጸገዴ አካባቢ ለዘመናት የኖረውን ህዝብ ከቅየው ገፍተው አስወጥተው ሃብት ንብረት ቦታውን ነጥቀው ባገሩ በወንዙ ስደተኛ በማድረግ እነሱ ግን የቦታው እውነተኛ ባለቤቶች ሆነው መቀጠላቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ይህ ሁሉ ስቃይና መከራ፣ የመብት ጥሰትና ጭቆና እስርና ሞት አንገፍግፎት ሀገር ጥሎ የኮበለለው ዜጋ ደግሞ በሄደበት ሁሉ ሌላ ግፍ ሌላ ሰቆቃ ይጠብቀዋል። ድሮስ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዳ አይቀበለውም አይደል የሚባለው። በሄደበት አገር ሁሉ በተለይ ደግሞ በአረቡ ዓለም እንደባሪያ እንደአገልጋይ ከመታየቱም ባሻገር ግፉ በጣም ሲከፋ ደግሞ እሱ ሞቶ ሌሎች ሃብታሞች በህይዎት እንዲኖሩ አካሉ እየተቀደደ የውስጥ ብልቱ እየተመረጠና ተበልቶ እየወጣ በጥቁር ገበያ እየተቸበቸበ ይገኛል “Who cares for the dead fish” አይደል ፈረንጆች የሚሉት። የሀገራችን ዜጋ በውጭው ዓለም እንዲህ እንደተፈለገ የማንም መጫወቻ ሲሆን አንድ እንኳ ሃይ ባይ ድርጅት ወይም ተቆርቋሪ ግለሰብ መጥፋቱ በጣም ያሳዝናል። አሁን ሰሞኑን በድረገጽ መስኮቶች ላይ እንደተመለከትነው እንኳ በአረብ ሀገር በስቃይ ላይ ከሚገኙት እህቶቻችን አንዷ በሀገራችን ቆንስላ ጽ/ቤት ፊት ለፊት አይሆኑ ስትሆን ማንም ሊያስጣላት ቀርቶ ባግባቡ ችግሯን የጠየቀላት አልነበረም (ይህን የጀመርኩትን ጽሁፍ ሳልጨርስ ይህችው ልጅ እራሷን ማጥፋቷን በተለያዩ ዜናዎች እየተዘገበ መሆኑን ሰምቻለሁ)። ጎበዝ በግቢውና በመንደሩ ከሆነ እኮ ውሻ እንኳ ጀግና እኮ ነው! ምነው ታዲያ የቆንስላው ሃላፊዎች? ለነገሩ አልኩ እንጅ ኢትዮጵያዊ በዓለም ፊት ዋጋው ከወረደ ቆይቷል። ዋጋችን ከመነሻችን በወያኔ የወረደ ነው። በሀገራችን ከእኛ የልቅ በእዳን የተሻሉ ሆነው የሚታዩበት፣ ከኛ ይልቅ ባእዳን ለሀገራችን ጥሩ ያስባሉ ተብሎ የሚቆጠሩበት ጊዜ ከሆነ ቆየ፤ ኤይ ወያኔ!!! ይህ በአንዱ ወይም በሌላው ምክንያት እየተገፋ ወደ ውጭ የፈለሰው ኢትዮጵያዊ ደግሞ በሚኖርበት ሀገር ያለውን የዲሞክራሲ መብት በመጠቀም በሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች አማካኝነት ድምጽ አጥቶ ታፍኖ ላለው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ድምጽ ለመሆን በርትቶ በመስራት ላይ ቢሆንም ለዚህም ዘረኛው መለስ ዜናዊ ሁነኛ መላ አላጣም። ልክ ሰሞኑን ከኖርዌ መንግስት ጋር ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ያደረገውን አይነት ውል በመዋዋል ይህ ብቸኛ ድምፅ ጸጥ እንዲል በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራ ይገኛል። የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ በተመሳሳይ በሱዳን፣ በኬንያ በጅቡቲ እና በሱማሌ ላንድ የሚገኙትንም ኢትዮጵያዊ ስደተኞችን በግዳጅ ወደ ሀገር በመመለስ የፈለገውን ሲገርፍ፣ ሲያስርና ሲያሰቃይ ቀሪዎችን የት እንዳደረሳቸው ግልጽ ያለ መረጃ የለም። እንግዲህ ይህን ሁሉ ስንመለከት ኢትዮጵያዊው ወገናችን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ መቀመጫ መላወሻ ያጣ ሁሌ ባካኝ ሁሌ በርጋጊ ሆኗል ለማለት እንችላለን። ከትምህርት እስከ ቢሮ ስራ፣ ከንግድ እስከ ግብርና ሁሉም በወያኔ የተያዘ አልያም የተነጠቀ ሆኗል። ህዝባችን የኔ የሚለው አንዳች ነገር የለውም ዛሬ። መኖሪያ ቦታው ነብረቱ ብቻ ሳይሆን እሱ ራሱ ወያኔ እንደሚያዘው ካልኖረ ተስፋ የሌለው ብኩን መሆኑ የሚታወቅና የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። በስደት ዓለምም ቢሆን ሁነኛ የሆነ ልብ የሚያረጋጋና መንፈስ የሚያጠነክር አንዳች ነገር አልተገኘም። ታዲያ ዛሬ ኢትዮጵያዊ ወገኑ ማነው? ቢባል ወገን የሌለው ባካኝ ተብሎ ቢመለስ ስህተት ይሆን? የሆነው ሆኖ አንድን ትንሽ ድመት እንኳ ሁሉንም ማምለጫ በሮችና መስኮቶችን ዘግቶ ለመግረፍ በማይቻልበት ሁኔታ እንዴት ወያኔ ሁሉንም መንገዶች ዘግቶና ተቆጣትሮ እኛን እንደፈለገ ሊያደርገን ቻለ? ከሀገር ካባረረንም በሗላ በያለንበት እየመጣ ለማተራመስስ እንዴት ተሳካለት? ብለን ብንጠይቅ መልሱ አጭር ነው፤ ትብብር ስለሌለን ነው። “ፍየል አስር ሆና አንድ ነብር በላት” አይነት መሆኑ ነው። እኛ ብንተባበር ወያኔ ዲሞክራሲ በሰፈነበትና በምኖርበት ሀገር ይቅርና በሀገራችንም ቢሆን እንደፈለገ አይሆንም ነበር። እንደተፈለገ የሚገፋው የሚታሰረውና የሚሰቃየው ስደተኛ በያለበት ሀገር ዓለምአቀፋዊ ህጎችን ተጠቅሞ እራሱን መከላከል በቻለ ነበር። በተለይ ባሁኑ ጊዜ ሁላችንም ብቸኝነታችን እንጅ አንድነታችን አይታወቅም ስንለያይ እንጅ ስንተባበር አንስተዋልም ስለሆነም በየሄድንበት ለጥቃት የተጋለጥን ነን። እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ ላቅርብ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በግረድፍ ግምት ከሶስት ሚሊዮን በላይ ይገመታል ነገር ግን ስለእኛም ሆነ ስለህዝባችን መብት መረጃዎችን በማቅረብ እየወደቀና እየተነሳ በመታገል ላይ ያለው ኢሳት ቴሌቪዥንን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠል ከዚህ ሁሉ ህዝብ ውስጥ ቋሚ የሆኑና በወር 20 የአሜሪካን ዶላር ብቻ የሚከፍሉ 3750 ቆራጥ ሰዎች አጥቶ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን ስንሰማ በእርግጥ እንተዋወቃለን? ትብብርስ አለን? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። ይህን ለምሳሌ ያህል አቀረብኩት እንጅ ብዙ አጋጣሚዎችን ብናስተውል በክፉ ዘመን የምንጯጯህ በሀሴታችን ግን የማንጠያየቅ ብዙዎች ነን። እንደብዛታችንና በውጭው ዓለም ለብዙ ዘመን እንደመኖራችን የራሳችን የሆነ ስለመብታችን ሊከራከርልን የሚችል ጠንካራ ዓለማቀፋዊ ተቋም የለንም። እዚህጋም ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር ቢኖረን እንኳ ይህም የስራ ማስኬጃ ገንዘብ የሚያስፈልገው መሆኑን ነው። ስለዚህ ለማጠቃለል ያህል ኢትዮጵያዊ ወገኑ ወያኔ ሊሆን አይችልም ኢትዮጵያዊ እንጅ። እስርኤሎች አሁን የደረሱበት ደረጃ የደረሱት ቢጣሉም ቢጋጩም ቢገዳደሉም ስለሀገረቻው ግን እንድ በመሆናቸው ነው። ሀገራቸውን ለድርድር አያስገቡም። ሀገራቸው ከሁሉም በላይ ናት። ከዚያ ሁሉ እልቂታቸው መከራቸውና ስደታቸው ዞረው የሚገቡባት ሀገር አገኘን ብለዋልና ስለሀገራቸው አንድ ናቸው። እኛም ልዩነቶች ሊኖሩን ይችላሉ ልንጋጭ ልንፋጭ ልንከራከር እንችላለን ነገር ግን ሀገራችንን በተመለከተ አንድ ሆነን ተባብረን እስካልተገኘን ድረስ ገና ወደፊትም መቀለጃ መሆናችን አይቀርም ፤ከእስከአሁኑ መከራ የባሰ ካለ ማለቴ ነው። ስለዚህም ከእንዲህ አይነቱ መከራና ችግር ለመዳን እንተባበር በማንኛውም ጊዜ አንረዳዳ ለኢትዮጵያዊ ወገኑ እኛ ለእኛም ወገኖች እኛ ነንና። አበቃሁ።

No comments:

Post a Comment