የቴዲ አፍሮ “ጥቁር ሰው”
እና ጥቂት የተዛቡ የታሪክ እውነቶች (ዴቪድ ካርል) ይህንን አጭር የታሪክ ማስታወሻ ለመጻፍ ምክንያት የሆነን፤
“ጥቁር ሰው” የተሰኘው አዲሱ የቴዲ አፍሮ ዘፈን ነው። በዚህ ዘፈን ውስጥ
በተለይም አጼ ምኒልክን የጥቁር ሰዎች ንጉሥ አድርጎ፤ በዙፋናቸው ላይዙፋን ጨምሮ… አግንኖ እና አጉልቶ ስላሳየን፤ አልበሙንም ለአጼ ምኒልክ፣
ለእቴጌ ጣይቱ እና ታሪካቸው ላልተነገረላቸው ጀግኖች በማድረጉ… ለቴዲ
አፍሮ ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው።
““ከኢትዮጵያ ሞት በፊት እኔን ያስቀድመኝ” በሚል የኦሮምኛ ስንኝ
የተዋበው ይህ የ”ጥቁር ሰው” ዘፈን ፤ በሙሾ እና በጀግና ሆታ የተቃኘ
ነው። በሙሾው እነዚያ ለአገራቸው የወደቁ ኢትዮጵያዊያንን እንድናስብ፣
በሆታው ደግሞ የጀግንነት ዜማ እንድናቀነቅን ያደርገናል። ይሄ እንዳለ ሆኖ
በዚህ ስራ ውስጥ የተከሰቱ ስህተቶችን በመቃኘት፤ ስራው ለወደፊት
በመድረክ ሲቀርብ ወይም በዲቪዲ ሲሰራ በሲዲው ላይ የታየው ስህተት
እንዳይደገም እርምት እንዲደረግበት ነው… የዚህ ማስታወሻ ዋና አላማ።
በዚህ ማስታወሻችን ላይ ዋና ዋናዎቹን ስህተቶች እንግለጽ።
ዋናዎቹ በቴዲ አፍሮ ውስጥ የተከሰቱት ስህተቶች የሚያጠነጥኑት
በደጃዝማች ባልቻ እና ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ዙሪያ ነው።
ሁለቱም ጀግኖች በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና በመጫወታቸው፤
በ’ያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ልዩ ስፍራ አላቸው። ነገር ግን ምንም
ያህል ብንወዳቸው የሌላውን ታሪክ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ መስጠት
የለብንም። ቴዲ አፍሮም አውቆት ሳይሆን ባላወቀው መንገድ ይመስለናል
ስህተቱን የሰራው። እንዲህ ነው ነገሩ
።
በዚህ አልበም ውስጥ በተለይም የፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራው
እና ራስ አባተ ቧያለው አባ ይትረፍ ታሪክ ወይም ስራ ሸርተት ብሎ ለነ
አባ ነፍሶ እና አባ መላ ሄዷልናከዚህ በመቀጠል እርማቱን እየሰጠን፤
በዚያውም ተጨማሪ የታሪክ ዳሰሳ እናደርጋለን።
ምኒልክ ወደ አድዋ ሲሄድ ምናለ፤
አረ አይቀርም በማርያም ስለማለ።
ወይ ሳልለው ብቀር ያኔ
እኔን አልሆንም ነበር እኔ።
ካለ በኋላ... ገና በዘፈኑ ማለዳ ላይ፤ “ባልቻ አባቱ ነፍሶ
መድፉን ጣለው ተኩሶ” ይለናል።
ከላይ ያለውን ስንኝ በህሊናችሁ እንደያዛችሁ ጥቂት ስለ ባልቻ
አባ ነፍሶ ላውጋ። - ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ። (ባልቻ አባነፍሶ) በአባታቸው
ኦሮሞ፣ በናታቸው የጉራጌ ተወላጅ ናችው። በ1888 ዓ.ም. በአድዋ ጦርነት
ወቅት በአጼ ምኒልክ ስር ሆነው በመድፍ አስተኳሽነት ተሰልፈዋል። ቴዲ
በዘፈኑ ውስጥ “ባልቻ አባቱ ነፍሶ” በማለት በተደጋጋሚ ገልጿቸዋል።
ሆኖም ነፍሶ የፈረሳቸው እንጂ የአባታቸው ስም አለመሆኑን እዚህ ላይ
አስምረን እንለፍ። ይህ እንደጉልህ ስህተት ላይታይ ይችላል። ውሎ ሲያድርግን ለመጪው ትውልድ የተሳሳተ መልዕክት እንዳያስተላልፍ ነው
እርምት የሚያሻው። እናም ቴዲ ይሄን ዘፈን መድረክ ላይ እንደገና
ሲጫወተው… ባልቻ አባቱ ነፍሶ ሳይሆን “አባቱ ሳፎ” ብሎ
እንደሚያቀነቅን ተስፋ አናድርግ።
እዚሁ ላይ አንድ ነገር ልጨምር። በዚሁ የቴዲ ዘፈን ውስጥ
ባልቻ አባ ነፍሶ “መድፉን ጣለው ተኩሶ” የሚል ስንኝ እንሰማለን።
ባልቻ አባነፍሶ በወቅቱ በምኒልክ ስር በነበረው ጦር ውስጥ የመድፍ
አስተኳሽ እንደነበሩ ገልጫለሁ። በ’ርግጥ መድፉን ተኩሶ የሰበረው ባልቻ አባ ነፍሶ ነበር?
አይደለም። ሊቀ መኳስ አባተ ቧያለው እንጂ።
ነገሩ እንዲህ ነው። ገና ጦርነቱ በህዳር ወር አምባላጌ ላይ
ሲጀመር ከጣልያን የተማረከ መድፍ ነበር። ይህንን መድፍ በኣጼ ምኒልክ
ቤተመንግስት ውስጥ ያደገው ሊቀመኳስ አባተ ይረከበዋል። በኋላ ላይ
የካቲት 23 ቀን አድዋ ላይ ጦርነት ሲደረግ፤ በዚያው በጣሊያን መድፍ፤
ከማዶ የሚተኩሰውን የጣሊያን መድፍ፤ አፉን መትቶ ተኩሱ እንዲቋረጥ
አደረገ። ታዲያ በዚያን ጊዜ እንዲህ ተባለ።
“አባተ ቧ ያለው ነገረኛ ሰው፣ አባተ አባ ይትረፍ አወሻካች ነው፤
ይህን መድፍ ከዚያኛው አቆራረጠው።” ተብሎ ተገጠመላቸው።በመሆኑም በአድዋ ጦርነት ዘመን መድፍን በመድፍ ተኩሶ
የጣለው፤ ሊቀ መኳስ አባተ ቧያለው (አባ ይትረፍ) መሆኑን እንደገና
እናስምርበት። በዚህ አጋጣሚ ስለአባተ (በኋላ ራስ ሆነዋል) ይቺን
እንጨምርና ጀግናውን እንሰናበት።
ራስ አባተ በሚንሊክ ቤተመንግስት ውስጥ ያደጉ፤
በጀግንነታቸው የታወቁ፤ በአገር ውስጥ ሁከት ሲነሳ መጀመሪያ ከምኒልክ
ቤተ መንግስት እየተላኩ፤ እሺ ያለውን በሰላም እምቢ ያለውን በጦርነት
እየቀጡ አገር የሚያረጋጉ ሰው ነበሩ። በኋላ ላይ ልጅ እያሱ ራስ አባተ
አስረዋቸው የነበረውን ታሪክ እንዝለለውና ከዚያ በኋላ ተፈትተው
ንግሥት ዘውዲቱና አልጋ ወራሽ ተፈሪን ማገልገላቸውን መስክረን
እንለፍ።
ሊቀ መኳስ አባተ ቧያለው (በኋላ ራስ ተብለዋል)… ቀልጠፍ
ያሉ ጦር አዋቂ ሰው ነበሩ። በተለይም ለማዕከላዊ መንግስት አልገዛም
የሚለውን፤ ሲሆን በፍቅር ካልሆነም በጦር ክፉኛ ይመቱት ነበር።
ለዚህም ነው… በፈረሳቸው ስም (በአባ ይትረፍ) ይህ ቅኔ የተዘረፈው።
“ወንጌል ተምሯል እንዴ፣ ያባተ ፈረስ፤
ይትረፍ ለነገ አይል፣ ምንም ቢደገስ” ተብሏል። የቅኔው ወርቅ ምንም
ጦርነት ቢደገስ፤ “አባ ይትረፍ” ለነገ ሳይል ይመታዋል ለማለት ነው።
እንደው ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ፤ የ’ነዚህን ጀግኖችመጨረሻ እናውጋችሁ። አባተ ቧያለው በኋላ ላይ ራስ ተሰኝተው፤ ወሎ
ላይ ተሹመው ነበር። ሆኖም ብዙ ሳይቆዩ ጥቅምት 6፣ 1910 ዓ.ም.
ሞተው ደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ። ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶም ጣሊያን
በ1928 ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት አዲስ አበባ ድረስ
ጦራቸውን ይዘው መጥተው፤ ረጲ ጋራ ላይ ሰፍረው ትልቅ ጦርነትአድርገው ነበር። ሆኖም የጣሊያን ኃይል እየበረታ በመምጣቱ ወደ በቾ
ቢመለሱም፤ ጦራቸው በመመናመኑ እና ተበትኖ በጣሊያን ተማረኩ።
ሆኖም “እጄን ለጣልያን አልሰጥም” ብለው በራሳቸው ሽጉጥ ጥቅምት 27
ቀን፣ 1929 ዓ.ም. መስዋዕት ሆኑ። በኋላ ላይ ስለክብራቸው ደጃዝማች
ባልቻ ሆስፒታል ተገነባ።
ወደሌላው የታሪክ ምዕራፍ እንሸጋገር። በቴዲ አፍሮ ዘፈን ውስጥ
ለፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ በቂ ስፍራ ተሰጥቷቸው፤ አስፈላጊውን
ሙገሳ አግኝተዋል። ከብዙ ትውልድ በኋላ ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ አባ
መላ ሲወደሱ መስማት እጅግ ደስ ያሰኛል። እንዲህ ይላል ቴዲ በዘፈኑ…
“ዳኘው ያሉት አባ መላ ፊት ሀብቴ ዲነግዴ፤
ሰልፉን በጦር አሰመረው ፊት ሆኖ በዘዴ።”
ሆኖም የአድዋን ጦርነት በመላ ከፊት ሆነው እንደመሩ ተደርጎ
በቴዲ አፍሮ ዘፈን ውስጥ እንሰማለን። በ’ርግጥ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ
ምርጥና የተከበሩ ጀግና ይሁኑ እንጂ፤ የአድዋን ጦር ፊታውራሪ ሆነው
የመሩት እሳቸው ነበሩ? አይደሉም፤ ፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራው እንጂ።
በአድዋ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ጦር ዋና አበጋዝ ፊታውራሪ
ገበየሁ እንጂ ሀብተጊዮርጊስ አልነበሩም። በወቅቱ በእድሜም ሆነ በማዕረግ
የሚበልጡት ፊታውራሪ ገበየሁ ነበሩ። የፈረሳቸውም ስም “አባ ጎራው”
ይባላል። በዘመኑ የነበረ ወታደር ፉከራ ሲጀምር፤ “ከነፍጥ ጎበዝ አየሁ፤
ከጀግና ገበየሁ!” ይል ነበር። ቀረርቶውም ሲቀጥል… በፈረሳቸው ስም “አረ
ጎራው” ይባላል። በፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራው ስም የተገነባ ቅርስ
ባይኖርም… ሁሌም “አረ ጎራው፣ አረ ጀግናው!” የሚለውም እንጉርጉሮ
ስንሰማ ልባችን ደስ ይለዋል። ምናልባት ብዙ ሰዎች “አረ ጎራው” የሚለውን
ዜማ እንጂ፤ የዜማውን ምክንያት ገበየሁ አባ ጎራውን አያውቋቸውም። ድሮ
ድሮ ኢትዮጵያዊው ጀግና ለመዝመት ሲነሳ… “አረ ጎራው!” እያለ
የሚያቅራራው፤ መነሻውም ሆነ መድረሻው ፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራውን
ለማስታወስ ነበር። ዛሬ በርግጥ ታሪኩን ባያውቁትም፤ “አረ ጎራው” መባሉ
አልቀረም። (በ’ርግጥ አሁን ታሪኩ ተረስቷል መሰል)
የፊታውራሪ ገበየሁን ጀግንነት እዚህ ላይ ዘርዝረን
አንጨርሰውም። ሆኖም አንድ ነገር እንጨምር። በታሪክ ወደ ኋላ መልሰን
ፊታውራሪ ገበየሁ አባጎራውን ልናስታውሳችሁ ነው።
ከአድዋ ጦርነት በፊት የሸዋ ፈረሰኞ... “አረ ጎራው!” ብለው በጌታቸው ፈረስ
ስም ከፎከሩ በኋላ... የአባ ጎራው ፈረስ፣ ምናለ ምናለ፤
መረብን ተሻግረን እንዋጋ አለ።
የአባ ጎራው ፈረስ፣ ምናለ ምናለ፤
መረብ ተሻግሬ፣ ባህር ልያዝ አለ።
አባሮ ገዳይ፣ ቆንጥር ለቆንጥር፤
ጥቂት ለነፍሱ፣ የማይጠረጥር… እየተባለ ሲፎከር
የካቲት 23 ቀን፣ 1888 ዓ.ም. የአድዋ ጥሮነት ፈነዳ።
የአድዋ ጦርነት ሊጀመር ነው። ሆኖም ጦርነቱን ለመጀመር
የሚንሊክ ትዕዛዝ ይጠበቅ ነበር። በወቅቱ፣ የአድዋ ስላሴን ጣሊያን ይዞት
ነበር፤ ሰራዊቱ ጦርነቱ የሚጀመርበትን ቀን መናፈቅ ጀምሮ ፊታውራሪ
ገበየሁን በግጥም ሸነጥ ያደርጓቸው ነበር። እነሆ የአምባላጌውን ጦርነት
የጀመሩት ፊታውራሪ ገበየሁ በእጃቸው ላይ የመቁሰል አደጋ ቢደርስም
እያገገሙ ነበር። እናም… ሰራዊቱ በግጥም…
“የአድዋ ስላሴን፣ ጠላት አረከሰው፤
ገበየሁ በሞቴ፣ ግባና ቀድሰው።” ይላቸው ጀመር።
ጦርነቱ የካቲት 23 ቀን፣ ጠዋት ተጀመረ። የካቲት 23 ቀን
ጠዋት፣ ከጄነራል አልቤርቶኒ ጋር በተደረገው ውጊያ የጣሊያኖቹ መድፍ
ክፉኛ አስቸገረ። ወታደሩም ወደፊት ከመሄድ ይልቅ ወደኋላ አፈገፈገ።
በዚህን ጊዜ ፊታውራሪ ገበየሁ ፈረሳቸው ላይ እንደተቀመጡ፤ “ወደ ሸዋ
የምትመለሱ ሰዎች፤ የአምባላጌው ጀግና እንዴት እንደሞቱ ለንጉሡና ላገሬ
ሰው ንገሩ” ብለው ጮኸው ተናገሩና ፈረሳቸውን በአለንጋ በትር
አስነስተው፤ እንዳንበሳ ወደ’ሚተኮሰው መድፍ ጋለቡ። ሲያፈገፍጉ የነበሩ
ሌሎች ፈረሰኞችም ተከተሏቸው። ፊታውራሪ ገበየሁ ግን በመድፍ
ተመትተው 3፡00 ላይ ወደቁ።
ይህንን የተመለከቱ የሸዋ ፈረሰኞች እንደዝናብ የሚወርደውን
የመድፍ ጥይት ሳይፈሩ ፊት ለፊት ገቡበት። ከመድፈኞቹም ጋር
ተጨፋጭፈው ፊት ለፊት ተሰልፎ የነበረው የጄኔራል አልቤርቶኒ
ሰራዊት ተበተነ። ለዚህም የፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራው ውለታ
የሚጠቀስ ነው።
የአባ ጎራው መሞት ሲሰማ ምኒልክ በጣም አዝነው
ማእንግዲህ በአድዋ ጦርነት ወቅር የጦሩ ከፊታውራሪ ገበየሁ አባ
ጎራው ሞት በኋላ በአመቱ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የኢትዮጵያ
የጦር አበጋዝ ሆነው ተሾሙ። እንግዲህ የታሪኩ እውነት ይሄ ነው።
ምንም እንኳ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ በአድዋ ጦርነት ቢሳተፉም፤
የጦሩ አበጋዝና ፊት ቀደም መሪ ገበየሁ አባ ጎራው በመሆናቸው… በቴዲ
አፍሮ ዘፈን ውስጥ የተገለጸው አባባል፤ እውነት ይስተካከል ዘንድ በአባ
ይትረፍ እና በአባ ጎራው ስም አደራ እላለሁ።
በአጠቃላይ ሁለቱም በቴዲ አፍሮ ዘፈን ውስጥ የተካተቱት
ባልቻ አባ ነፍሶ እና ሀብተጊዮርጊስ አባ መላ ቢያንስ በስማቸው
ሆስፒታል እና ድልድይ ተሰይሞላቸው ስማቸው ከመቃብር በላይ ነው።
አሁን ደግሞ በዘፈን ተወደሱ… ይህ ሁሉ ደስ ይላል። ነገር ግን እነራስ
አባተ እና ፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራው ታሪክ የማይዘነጋቸው ጀግኖች
በመሆናቸው፤ የአድዋ ድል ሲነሳ ሁሌም አብረው ይወሳሉ። ሆኖም
የነሱን ታሪክ ለሌላው መስጠት አግባብ ባለመሆኑ፤ ይህም ሆን ተብሎ
የተፈጸመ እንዳልሆነ በማመን፤ ሲቻል ተከርክሞ እና ታርሞ ቢቀርብ
ደስታችን ወሰን አይኖረውም። ስራውንም ሙሉ ያደርገዋል።
ከዋናው ርዕስ እንዳንወጣ ስጋት ቢያድርብንም፤ ይህቺን የታሪክ
መስመር መርቀን እንሰነባበት።
የአድዋ ድል መታሰቢያ አንደኛ አመት ሲከበር፤ ሁሉም
ከየጎራው ፈንቅሎ መጥቶ ጃን ሜዳ ላይ ሰፈረ። አጼ ምኒልክም
በተዘጋጀላቸው ድንኳን ውስጥ ሆነው ሰልፈኛውን ይመለከታሉ። በግራና
በቀኝ ታላላቅ ሹማምንቶች፤ የፈረንሳይ፣ የእንግሊዝ፤ የሩሲያ
ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል። ጦረኞች “ዘራፍ” እያሉ አለፉ። የሸዋ ፈረሰኞች
ግን ፈረሶቻቸውን ዳንገላሳ እያስመቱ ዝግ ብለው በምኒልክ ፊት ለማለፍ
ተዘጋጁ። ከነዚህ ፈረሰኞች ፊት ግን ማንም ሰው ያልተቀመጠባት፤ በብር
እና በወርቅ መጣብር ያሸበረቀች አይነ-ግቡ በቅሎ አለች። አጼ ምኒልክን
ጨምሮ ሌሎች መኳንንት ያውቋታል። ከምኒልክ ዙፋን በቀር ሁሉም
ከተቀመጠበት ተነሳ።
በዚህች በኮርቻዋ ላይ ማንም ባልተቀመጠባት በቅሎ ላይ አንድ
ሌላ ጀግና ይቀመጥባት ነበር። አሁን ከጃንሜዳው አውዳመት በህይወት
ቆሞ አልታደመም። ነገር ግን በኮርቻው ላይ በእውቅ በተሰፋ አረንጓዴ
ቢጫ ቀይ ባንዲራ ይታያል። ይህች በቅሎ የፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራው
ነበረች። በቅሎዋን እየጎተተ ከፊት ሆኖ ሲያልፍ የሚታየው የፊታውራሪ
ገበየሁ አባ ጎራው የመጀመሪያ ልጅ ነበር።
ንጉሠ ነገሥቱም ፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራን በማሰብ እንደገና
አለቀሱ። ሌሎች የሸዋ ፈረሰኞች በቅሎዋን ተከትለው ሲያልፉ፤ የጃንሜዳ
አቧራ በመጠኑ ቦነነ። የጀግኖች ታሪክ ግን በአቧራ አይሸፈንም፤
ፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራውም ከመሰዋታቸው በፊት፤ “ወደ ሸዋ
የምትመለሱ ሰዎች፤ የአምባላጌው ጀግና እንዴት እንደሞቱ ለንጉሡና
ላገሬ ሰው ንገሩ” ብለው ነበር የወደቁት። እኛም ይህንኑ ተናገርን፤
እነሆም የታሪክ መዝገባችንን ዘጋን።
No comments:
Post a Comment