"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Thursday 14 April 2016


በዶ/ር አለማየሁ ዋሴ እሸቴ ከታተመው እመኋ ከሚለው መጽሐፍ ላይ የተወሰደ።

ለእኛ ዘመን የተሰጠ የማንቂያ ተግሳጽ!!!፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨

" በአፍላ ትጀምራላችሁ በወረት ትተውታላችሁ። ያወቃችሁትን ትረሳላችሁ ፣ ያላወቃችሁትን ለማወቅ ትጥራላችሁ ፣ የያዛችሁትን ትረግጣላችሁ ፣ ያረገጣችሁትን ትይዛላችሁ። ምኞታችሁ ልክ የለውም፣ አእምሮአችሁ ብዙ ነው። ያማራችሁን ስታገኙ ወዲያው ይሰለቻችኋል። ተው የተባላችሁትን ትሽራላችሁ፣ የተከለከላችሁትን ትደፍራላችሁ ፣ የተፈቀደላችሁን ችላ ትሉታላችሁ። ቤተ መቅደስ እንዳትገቡ ብትከለከሉ ወደፊት ቤተ መቅደሱን በመስታወት ሠርታችሁ መቅደስ ባትገቡም እንኳን ሁሉን ከውጪ ሆናችሁ ማየት ትፈልጋላችሁ። ሁሉን ማወቅ ትፈልጋላችሁ በአንዱም ግን አትጠቀሙበትም። ሁሉ አላችሁ ፣ ግን ባዷችሁን ናችሁ። ሃይማኖት እንጂ እምነት የላችሁም!!
......ጥበብን "ሀ ግእዝ" ብዬ ላስተምርህ ብሞክር መንደር ውስጥ በቃረምካት ዕውቀት ተመክተህ በመሰልቸት "ሆ ሳብዕ" ብለህ ቀድመህ ትዘጋዋለህ። የግል ታሪካችሁ ቢታይ ወጥነት የጎደለው ከዚህም ከዚያም የተለከፈከፈ የተማሪ ኩፋዳ ውስጥ ያለ እህል ይመስላል። ተምራችሁ እውቀት ስታገኙ፣ ሠርታችሁ ሀብት ስታፈሩ ከላይ የሆናችሁበትን ሀገር ለቃችሁ ሰፋ ወዳለው እንሂድ ብላችሁ እንደገና ከታች ትጀምራላችሁ። ትቀጥላላችሁ በመጨረሻ ከጀመራችሁበት ትገኛላችሁ። ትቸኩላላችሁ ትወስናላችሁ ወዲያው ትጸጸታላችሁ። በጽኑ ታማችኋል!"
ከታሪክ ፍቅርንና ልማትን ሳይሆን ጥላቻንና ጥፋትን ለይታችሁ ትቆፍራላችሁ። ከዚያም ቀጥላችሁ የከበረ ማዕድን እንዳወጣችሁ ሁሉ በኩራት ደረታችሁን ነፍታችሁ ሳትመርጡ ሁሉን በአደባባይ ትዘሩታላችሁ፣ እናም ወደ ኋላ ስለ ታሪካችሁና ስለ ቅርሳችሁ ባሰባችሁ ቁጥር ፍርሃትና ሃፍረት ይሰማችኋል። ስለሆነን ከኋላ ታሪካችሁና ክብራችሁ እየራቃችሁ መጣችሁ። .......
ቅቤ ላይወጣችሁ ትናጣላችሁ። በዚህ አለም ጥድፊያ ታማችኋል። ሀገራችሁን ትንቃላችሁ፣ ጥላችሁ ለመሄድ ትፈልጋላችሁ፣ ከሄዳችሁ በኋላ ደግሞ አፍታ ሳትቆዩ አገሬ ናፈቀኝ ትላላችሁ። በቁማችሁ የናቃችሁትን የሃገራችሁን አፈር በሞታችሁ ልትለብሱት ትናፍቃላችሁ። ለሀገሬ አፈር አብቃኝ ብላችሁ በድናችሁን ልካችሁ የወገኖቻችሁን ልብ ትሰብራላችሁ። ግብዝነታችሁ መጠን የለውም። ሁለት ሀገር እንዲኖራችሁ ትፈልጋላችሁ፣ አንዱን በደም ሌላኛውን በመታወቂያ ታስባላችሁ። ከአንዱም ግን በአግባቡ አትኖሩም። ዘመናችሁም በምልልስና በመዋተት ያልቃል። ምን እንደምትፈልጉ አታውቁም እናም ፍለጋችሁ አያልቅም።
.... እኛ አባቶቻችንን እናምናለን። በእነርሱም ደስ ይለናል። የነገሩንን ተቀብለን ቃል ኪዳናቸውን ጠብቀን እንኖራለን።
"ጽላተ ሙሴ አክሱም ጽዮን እንዳለች ሲነግሩን መጋረጃ ገልጠን ሳጥን ከፍተን እንይ አላልንም፣
ጌታ የተሰቀለበት የግማደ መስቀሉ ክፋይ ግሼን ማርያም አለ ሲሉን ቆፍረን አውጥተን እንመልከት አላልንም ፣
ቅዱስ ጽዋው ወንዝ ውስጥ አለ ሲሉንም አውጥተን እንመልከት አላልንም"።
" አባቶቻችንን አምነን ሀገራችን የበረከት ምድር መሆኗን ተረድተን የጌታችንን የጸጋ ስጦታ ተቀብለን በእምነት እንኖራለን። ምንም የለንም ሁሉ ግን የእኛ ነው። ድሆች ብንባልም ባለጸጎችም ነን። የተራቆትን ብንመስልም የጸጋ ልብስ አለን። ሐዘንተኞች ብንመስልም ደስተኞች ነን። ስለ ሀገራችን መባረክ ፣ ቅድስት ሀገር መሆን፣ ቅዱስ ቅርስ በእጃችን እንዳለ አለም እንዲያረጋግጥልን አንፈልግም። የሌለንን አለን፣ ያልተሰጠንን ተቀበልን ብለን የምንኮፈስ ግብዞችም አይደለንምና። የሌለን ነገር ለመጠበቅና ለመታመን ስንል ሥጋችንን እየጎሰምን በገዳም ለመኖር የምንወስን ጅሎችም አይደለንምና"።