በሰሎሞን ተሰማ ጂ.
(semnaworeq.blogspot.com)
ባለፈው ሐሙስ በተደረገው የኢህአዴግ/ወያኔ የካቢኔ ሹም-ሽር ላይ በርካታ አስተያየቶች በመደመጥ ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም የበርካቶቹ አስተያየትና ትንተና እዚህ ግባ የማይባልና፣ በወያኔዎች አማርኛም “ውኃ የማይቋጥር” ሆኖ ስላገኘሁት፣ የኔን አስተውህሎት ላቀርብ ወደድኩ፡፡ በቅድሚያ ግን፣ በሀገር ውስጥ ያሉት የተቃዋሚ ፖለቲካ ማኅበሮች/ፓርቲዎች መሪዎች እየተቀባበሉ የሚደጋግሙት ነገር ያው የተለመደውን ነው፤ “ሹመቱ ሕገ መንግሥቱን የተከተለ አይደለም!” ምናምን የሚል ወቀሳ አይሉት ትችት፣ እንዲያው የንፉግና የፈሪ ጩኸት ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን መሪዎች ወያኔ ደጋግሞ አጥጋቢ አማራጭ የላችሁም የሚላቸው ለምን እንደሆነ፣ ብዙዎቹ አሁንም አልተገለጠላቸውም፡፡ መቼ “ተገለጠ/ቡድሀ!” ብለው እንደሚጮሁ አላውቅም፤ በተስፋ ግን እንጠባበቃለን፡፡
ወደዋናው ጉዳያችን እንመለስ፡፡ ኢሕአዴግ/ወያኔ የሰሞኑን ሹም-ሽር ሲያደርግ ለሕዝቡ አዲስ ነገር አልሆነበትም፡፡ አዲስ ነገር የሆነባቸው ካሉም ኢሳት ቴሌቪዥን በነሐሴ 2004 ዓ.ም ያወጣውን መረጃ ያላነበቡትና ወቅታዊ የፖለቲካ ጥንቅሮችን የማይከታተሉት ወገኖች ብቻ ናቸው፡፡ በሀገር ጉዳይ (በወል ቤታችን ጉዳይ ላይ እስከመቼ ድረስ ቸልተኛና ገለልተኛ ሆነው እንደሚቀጥሉ ባይገባኝም) ላይ ቸለል የሚሉት ወገኖች ናቸው፡፡ ከዚያ ወጭ ያሉትና የወቅቱን የሕወሀት-ወያኔን መቅነዝነዝ ሰበብ ያልተረዱት ብቻ ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ነፍስ ፖለቲከኛ ሆና በመገኘት ፈንታ “መሲሐዊት” ለመሆን እየተንደፋደፈች መሆኗን ወያኔዎች መረዳታቸው ነው፡፡ በመሆኑም ከነበሯቸው ብዙ ብዙ አማራጮች መካከል የሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ሹመት አጸደቁ፡፡
የፓርላማውን ስርጭት ለተመለከተው ሰው ሁለት የሚደንቁ አልቦ-ቋንቋ እንቅስቃሳችን ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን አሳይተዋል፡፡ የተሹዋሚዎቹን ስም ዝርዝር ሲያነብ የነበረው ኃይለ ማርያም ደሳለኝ (The
Mimic Man)፣ መለሰ ዜናዊኛ ማስኩ/ጭንብሉ ጠፍቶበት ሲኮለታተፍ ነበር፡፡ ምናልባትም በሥራ ብዛት ሰበብ ይህንን የሚያህል
ድርጅታዊ ውሳኔ ሲወሰን በስብሰባ ላይ አልተገኘም ነበር ይሆናል፡፡ ጎበዞቹ የወያኔ አርክቴክቶች ውሳኔያቸውን እንዲያነብ አዳራሹ
ውስጥ ከገባ በኋላ ነው የሰጡት፡፡ የተሹዋሚዎቹን ስም ዝርዝር ሲያነብ ከፍተኛ የሆነ ቃና-ቢስነት ይታይበት
ነበር፡፡