"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Wednesday 5 December 2012

ኢህአዴግ ህገመንግስቱን መቼ መቼ ነው የሚጠቀምበት… ለአመትባሉ ይሆንን!?


ኢህአዴግ ህገመንግስቱን መቼ መቼ ነው የሚጠቀምበት… ለአመትባሉ ይሆንን!?
ይሄንን ጥያቄ ልጠይቃችሁ ጀመርኩና አንድ ሁለት አንቀፅ ከወረድኩት በኋላ፤ ሀሰብም ለማሰባሰብ ወዳጆቼም እንዴት አደሩ…? የሚለውን ለማወቅ እንዲሁም ምን አዲስ ወሬስ አለ? የሚለውንም ላማጣራት፤ ፌስ ቡክ ሰፈር ጎራ አልኩ። ልክ ይሄኔ እጅግ የተከበሩ የአዲሳባ ጦማሪያን ወዳጆቼ “ህገ መንግስቱ ይከበር” የሚል መፈክር ለጥፈው ተመለከትኩ። ዘለቅ ስለውም፤
“ህገ መንግስቱ በመንግስት መከበር ካልቻለ በስተቀር ዜጎች በጋደለ ሜዳ ተጫውተው ለመሸነፍ ይገደዳሉ። በአመለካከታቸው እኩል እድል ይነፈጋሉ ይህንን ተግባር ለመቃወምና መንግስት ህገመንግስቱን እንዲያከብር በመጠየቅ ህገመንግስታዊ መብታችሁን ማስጠበቅ የምትፈልጉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከህዳር 27 ጀምሮ ህገመንግስቱ እስከጠደቀበት ቀን ህዳር 29 ድረስ፤ በፌስ ቡክ፣ ቲዊተር እና ጡመራ መድረኮቻችሁ ላይ ማስታወሻችሁን እና ሀሳባችሁን በማስፈር የዘመቻው ተካፋይ እንድትሆኑ ተጋብዛችኋል። ይላል።
በእውነቱ ልባችን እና ቀልባችን በአንድ ጉዳይ ላይ ማንሰላሰሉ፤ የተሳሰርንበት ገመድ ምን ያህል ረጅም እና ጠንካራ መሆኑን ድጋሚ እንዳውቅ አደረገኝ። ስለዚህ ለወዳጅነታችን እና ለተሳሰርንበት ገመድ ስል ከሁለቱ አንቀፅ ቀጥሎ ያሉትን ስቀጥል፤ ዘላለማዊ ክብር ለዞን 9 ወዳጆቼ እና “የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል” ለሚሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንዲሆን በመመኘት ነው…!
ቀጠልኩ፤
መድረክ፤ “ኢህአዴግ ህገመንግስቱን ጥሷል” ብሎ ፍርድ ቤት ሊገትረው እንደሆነ ሰምተናል። ጥሩ ሀሳብ ነው። እስቲ “ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ” የሚለው ብሂል መቅረት እና አለመቅረቱንም በዛው “ቼክ” እናድርገው።
መንግስታችን ህገመንግስቱን “ፍሩ እንጂ አትድፈሩ” እያለ በተደጋጋሚ ሲነግረን ሰምተን በማስታወሻችን መዝግበናል። ግን ይቺ ህገ መንግስት ምንድናት? እኛ እኛ የምናከብራት፣ የምንፈራት፣ የምንታሰርባት፣ የምንሰደድባት፤ መንግስት መንግስት እንዳሻው የሚያገላብጣት፣ የሚዘቀዝቃት፣ የሚያራቁታት፣ ብሎም የሚደፍራት ይቺ ህገ መንግስት እኮ ለመንግስት ምኑ ናት?
የምሬን እኮ ነው፤ ለስሙ ህጊቱ የምትጠራው በመንግስት አባትነት ነው። “ህገ መንግስት” እንዲሉ። ነገር ግን መንግስታችን እንደርሷ እና እንደእኛ ያጎሳቆለው አለ ለማለት አያስደፍርም።
በእውነቱ በቅርቡ እንኳ መንግስታችን፤ ህገመንግስቱን በጣም በሚያስታውቅ እና ግልፅ በሆነ ሁኔታ ሲደፍር እጅ ከፍንጅ ተይዟል። አረ በህግ አምላክ…! ቢሉትም የሚሰማ አልሆነም። በነገራችን ላይ፤ ከዚህ በፊት ሟች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከተናገሩት ንግግር በሙሉ በእጅጉ የሚያስገርመኝ፤ (በቅንፍም ለእርሳቸው ክብር ስል የሚያስገርመኝ አልኩ እንጂ ነገሩ እንኳ ደሜን የሚያፈላው ማለቴ ነው።)  እና ደሜን የሚያፈላው ንግግር “ህገመንግስታዊ ስርአቱን እያብጠለጠላችሁ በምንም ተዓምር ህገመንግስታዊ ከለላ ልታገኙ አትችሉም” ሲሉ የተናገሩት ነው። ይሄ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በቅርቡ የሚሞት ባለስልጣን ካለ አልያም በሀዘን ከፎቅ የሚፈጠፈጥ አንድ ወዳጃቸው ከተገኘ ቢጠይቅልኝ ደስ ይለኛል።
አንዳንድ ግለሰቦች ህገመንግስቱ ላይ ተቃውሞ አላቸው። ተቃውሟቸውም ለምን ህገመንግሰት ኖረ ሳይሆን፤ በህገመንግስቱ ውስጥ የተቀመጡ አንዳንድ አንቀፆች ለሀገራችን ጠቀሜታ የላቸውም ብለው ያስባሉ። ይሄንን ማሰብ በምንም ተዓምር ሀጥያት ሊሆን አይችልም። ሀሳቡን በሌላ ሀሳብ ለማስረዳት መሞከር የመንግስት ፋንታ ነው። ነገር ግን እንዚህ ሰዎች በህገመንግስቱ ውስጥ የማይስማሟሙባቸው አንቀፆች አሉ ማለት የህገመንግስቱን ከለላ አያገኙም ወይም ህገመንግስቱ ሲደፈር ዝም ይላሉ ማለት አይደለም። ጠቅላዩ ግን “በምንም ተአምር የህገመንግስቱን ጥበቃ አታገኙም” ይላሉ። ውይ… ይሄንን ነገር ስሰማው እኚህ ሰው ባይሞቱም ኖሮ በሰው እጅ ሰበብ ይሆኑ ነበር ብዬ ሁሉ አስባያለሁ። እናም እንኳን በሰው እጅ ሰበብ አልሆኑ…
ለማንኛውም ትክክለኛው ሀሳብ ግን ማንም ሰው ህገመንግስቱን ቢቀበልም ባይቀበልም የሀገሪቱ ህግ ሆኖ እስከፀደቀ ድረስ ከለላም ክልክላም እንደየአስፈላጊነቱ ያገኘዋል። በዛውም ደግሞ ማንናውም ግለሰብ ህገመንግስቱ ቢመቸውም ባይመቸውም በአደባባይ ሲደፈር ግን “አረ ሼ!” ብሎ ነውር መሆኑን መናገር አለበት።
ሳስበው ሳስበው መንግስታችን ህገመንግስቱን የራሱ የክት ዕቃ አድርጎታል። ሲያሻው ይደርበዋል ሳያሻው ደግሞ ቁምሳጥኑ ውስጥ ይቆልፍበታል።
አሁን በቅርቡ ደግሞ በተደጋጋሚ ከህገመንግስቱ ውጪ የሆኑ ምግባሮችን ሲፈፅም ስናየው ህገመንግስቱ ላይ መቆለፍ ብቻ ሳይሆን ቁልፉም “አደሮቢ” ወንዝ ውስጥ ገብቶበታል እያልን እንድናስብ አድርጎናል።
በሀገሪቱ ውስጥ የሚወጡ በርካታ አዋጆች መመሪያዎች እና ደንቦች ህገመንግስቱን የሚቃወሙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የፕሬስ አዋጁን እና የሽብርተኝነት ህጉን ብቻ ማየት በቂ ነው። ነገረ ግን መንግስታችን እነዚህን ህጎች ከውጪ ሀገር ምርጡን ህግ ነው ያስመጣሁት! ይለናል። ሲጀመር ህግ የክለብ እግር ኳስ ተጫዋች አይደለም ዝም ብሎ በአለም ላይ ምርጥ ስለሆነ አምጥቶ ማስፈረም አይጠቅምም። እንደሀገሪቱ ባህልና ወግ እንዲሁም አኗኗር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከህገ መንግስቱ ጋር መጣጣም አለበት።
የሆነው ሆኖ ደፋሩ መንግስታችን ህገመንግስቱን በተደጋጋሚ እየደፈረ ነው። ይኸው አሁን በቅርቡ እንኳ ከህገ መንግስቱ ጋር በፍፁም በሚጣረስ መልኩ የሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሹመት አፅድቋል። እንዲሁም በእስልምና እና ክርስትና እምነቶች ላይ “በስመ አብም…ም” ሳይል “ቢስሚላሂም” ሳይል እጁን እያስገባ እንደሆነ ክፉኛ እየተወቀሰ ነው።
በየቤታችን አንድ የሆነ ዕቃ አይጠፋም። በሳጥን ውስጥ የሚቆለፍበት። የሚወጣው ለአውዳመት ብቻ የሆነ ዕቃ። ከዛ በፊትም ከዛ በኋላም ተቆልፎበት ይቀመጣል እንጂ ማንም እንዲጠቀምበት የማይፈቀድ ዕቃ።
ጥያቄያችንን ደግመን እናንሳት መንግስት ህገ መንግስቱን መቼ መቼ ነው የሚጠቀምበት…? ለአመት በዓል ለዓመት በዓል ይሆንን!?  ደግሞስ ለህዳር 29 “ዓመትባል” ሰሞን እንኳ ጥቅም ላይ ያልዋለ ህገመንግስት ለመሆኑ መቼ ነው ጥቅም ላይ የሚውለው!?
መልስ ያለው መልሱን፤ መልስ የሌለው ደግሞ ጥያቄ ምልክት እንጨምርና “እነርሳቸውን” እንጠይቃለን! እርሳቸውማ አወሳስበውን ሄዱ!

No comments:

Post a Comment