እስክንድር ነጋ ያለበትን ማወቅ እንፈልጋለን?
ከአንድ ሰአት በፊት የእስክንድር ነጋ ባለቤት አለም አቀፍ ተሸላሚዋ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል በአስቸኳይ እንደምትፈልገኝ ደውላልኝ ተገናኘን፡፡ እናም ስቅስቅ ብላ እያለቀሰች እንዲህ አለችኝ ‹‹ዛሬ ጠዋት ለእስክንድር ስንቅና ለክረምት የሚሆን ልብሰ ይዤለት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሄድኩኝ፡፡ ልጃችንንም እያመመው ከኣባቱ ጋር ላገናኘው ይዜው ነበር የሄድኩት፡፡ ሆኖም ባልተለመደ ሁኔታ ፖሊሶቹ ከአንድ ሰአት በላይ ካስጠበቁኝ በኋላ ሃላፊያቸው መጥቶ ‹እስክንድርን አናገናኝሽም፣ ምግቡም አይገባለትም› አለና ከግቢ እንድወጣ አደረገኝ›› አለችኝ፡፡ በሁኔታው በጣም ተቆጥታ ስለነበር ይዛው የነበረውን ዕቃ በሙሉ ጠባቂዎቹ አጠገብ ጥላ ወጣች፡፡ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ተመልሳ ለመሰብሰብ ስትሄድ ዕቃዎቹን አጣች፡፡ ከፖሊሶቹ ፊት ትታው ስለወጣችው ዕቃና ምግብ እንዲህ የሚል መልስ አግኝታለች ‹‹እኛ አላየንም፡፡ ምናአልባት ሌባ ወስዶት ይሆናል››
ለጥቂት ደቂቃ ካረጋጋኋት በኋላ ስለሁኔታው ማረሚያ ቤቱ አካባቢ ካሉ ወዳጆቼ ለማጣራት ሙከራ አደረኩ፡፡ እናም እስክንድርና ናትናኤል ዛሬ ሌሊት ከነበሩበት ክፍል ወጥተው ተወስደዋል የሚል መረጃ አገኘው፡፡ ነገር ግን የት እንደወሰዷቸው ለማወቅ ያደረኩት ጥረት እስካሁን አልተሳካም፡፡ ስለዚህ እባካችሁ የት እንዳደረሳችኋቸው ንገሩን?