"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Wednesday, 27 June 2012

አርባ አምስት ኢትዮጵያውያን ታንዛንያ ውስጥ ሞተው ተገኙ


በታንዛንያ አቋርጠው ማላዊ ለመግባት በኮንቴይነር ታጭቀው ይጓዙ ከነበሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ውስጥ ቢያንስ አርባ አምስቱ ጫካ ውስጥ ሞተው መገኘታቸው ተነገረ፡፡
72 የሚሆኑት ደግሞ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡

የታንዛኒያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ፔሬራ አሚ ሲልማ፣ ሟቾቹ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውንና በሕይወት ያሉትም መዳከማቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በኮንቴይነር ጭኖ ድንበር ሊያሻግራቸው የነበረውና ለጊዜው ማንነቱ ያልታወቀው የከባድ መኪና አሽከርካሪ፣ ኢትዮጵያዊያኑ መሞታቸውን ሲረዳ ከታጨቁበት ኮንቴይነር እያወጣ ጫካ ውስጥ እንደወረወራቸው ምክትል ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ አሽከርካሪው የት እንደገባና መኪናውን የት እንዳደረሰው ሊታወቅ እንዳልተቻለ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል፡፡

አሰቃቂውን የስደተኞች ሞት ሰምተው አስከሬናቸው የተጣለበት አካባቢ በአካል ሄደው እንደጐበኙ የገለጹት ሚስተር ፔሬራ፣ ሟቾቹ በአካባቢው ወደሚገኝ ሆስፒታል መወሰዳቸውንና የኢትዮጵያ ኤምባሲን ስለጉዳዩ ለማነጋገር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያን በኮንቴይነር ታጭቀው በታንዛኒያዊያን እገዛ ድንበር ለማቋረጥ ሲሞክሩ ለሞት እንደሚዳረጉ ተጠቁሞ፣ የጉዟቸውን መነሻ በኬንያ ናይሮቢ በኩል በማድረግ የታንዛኒያዋን አሩሻ ከተማን፣ ፓንያ በምትባለው ሕገወጥ መተላለፊያ በኩል አቋርጠው ወደ ማላዊ ለመግባት ሲሞክሩ በተደጋጋሚ እንደሚታዩ በዘገባው ተመልክቷል፡፡

ሟቾቹ ይገኙበታል በተባለው የዶዶማ ሆስፒታል ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ኢዝቅኤል ሞፑያ፣ ሟቾችንና በጣር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን እየተቀበሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችም በረሃብና በውኃ ጥማት በአሰቃቂ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ለሰባ ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን ከካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንና ከታንዛንያ መንግሥት ምግብና መጠለያ የቀረበላቸው እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡ ከሟቾቹ ጋር በተያያዘ እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋለ አካል እንደሌለም ታውቋል፡፡

No comments:

Post a Comment