"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Thursday 28 June 2012

እዛ እየታሰርን እዚህ እየሞትን… “የት ሄጄ ልፈንዳ አለ አብዮቱ!” (አቤ ቶኪቻው)


ትላንት ሁለት አሳዛኝ ዜናዎች ሰምቼ ደብቶኝ ነበር የዋልኩት። ሲጠበቅ የነበረው የእነ አንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ “አሸባሪ ናችሁ!” በሚል ፍርድ መደምደሚያ አግኝቷል። ቀጣዩ ምን ይፈረድባቸው ይሆን? የሚለው ነው። ጊዜውን ጠብቆ አብሮ የምናየው ነው። ነገር ግን አንድ ጥይት እንኳ ተኩሰው የማያውቁ ግለሰቦች “አሸባሪ” ተብለው በይፋ ሲፈረድባቸው ስናይ ድብርት ሲያንሰን ነው!
ሌላው አሳዛኝ ዜና ደግሞ ወደ ደቡብ አፍሪካ በኮንቴይነር ውስጥ ታጭቀው እየኮበለሉ ከነበሩ መቶ ምናምን ስደተኞች መካከል ወደ አርባ አምስት የሚጠጉት ህይወት ማለፉ ነው። እኔ የምለው መከራችን  አልበዛም ትላላችሁ!? እዛ እስር እዚህ ሞት… የት ሄደን እንፈንዳ…!?
ልብ አድርጉልን ከኛ የባሱ ካድሬዎች ሀገራችን እድገት በእድገት ናት ጥጋብ በጥጋብ ናት በሚሉበት በዚህ ወቅት ነው ይሄ ሁሉ ሰው በስደት ላይ የሚያልቀው! ውድ ካድሬዎቻችን አነዚህ ሰዎች ለሞት ያበቃቸው ስደት ከምን የመጣ ይመስላችኋል!? ወይስ ደልቶናል ጠግበናል የሚለው መግለጫ የፓርላማ አባላቱን ብቻ የሚመለከት ነው?
ወዳጄ በእውነቱ አሁንም ቢሆን ድብርት ላይ ነኝ! ለማንኛውም የአንዷለም አራጌን የመጨረሻ ንግግር እና የበዓሉ ግርማን አንዲት ግጥም እንደሚከተለው ልጋብዝዎ…
ለራሴ፣ ለልጆቼ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ !
ያሳለፍነው ግማሽ ምዕተ ዓመት የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰብአዊ ክብሩና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የታገለበት ዘመን ነው፡፡ ይሁንእንጂ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ባለቤት ለመሆን እስካሁን አልታደለም፡፡ እኔም በተፈጠርኩበት በዚህ ዘመን ለራሴ፣ለልጆቼና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ዴሞክራሲና ነፃነት እንደሚገባን በማመን አቅሜ በፈቀደው መጠን ታግያለሁ፡፡ ይኼንበማድረጌ በማንም ላይ በክፋት አልተነሳሁም፤ ይኼን በማድረጌ ህግ ጥሼ አላውቅም፤ ይኼን በማድረጌ በደሃዋ ሃገሬ ጥቅምላይ አልተነሳሁም፤ ይሄን በማድረጌ ፈጣሪዬን፣ የኢትዮጵያን ህዝብም ሆነ ህሊናዬን የሚያሳዝን አንዳች ነገር ፈፅሜያለሁ ብዬአላምንም፡፡ ፍፁም ሰላም ይሰማኛል፡፡ እኔን እዚህ ያቆመኝ የነፃነት ናፍቆት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶችም ፍትህን ለምኜስነፈግ ይኼ የመጀርያዬ አይደለም፡፡ ከሳሾቼ እንድጠጣው የሚፈልጉትን የግፍ ፅዋ በፀጋ ከመጠጣት ውጪ ባልፈረፀምኩትወንጀል ማቅለያ የመጠየቅን አማራጭ ህሊናዬ ስላልተወልኝ አዝናለሁ፡፡
ነፍሱን ይማረውና ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ በኦሮማይ መፅሐፉ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር።
እንባ እንባ ይለኛል
ይተናነቀኛል
እንባ ከየት አባቱ
ደርቋል ከረጢቱ
ሳቅ ሳቅም ይለኛል
ስቆ ላይስቅ ጥርሴ
ስቃ ‘ያለቀሰች
መከረኛ ነፍሴ
መከራዎቻችንን ኦሮማይ የምንልበትን ጊዜ ያቅርብለን!!

No comments:

Post a Comment