"Food is nothing without freedom! We Need Freedom
”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!
Tuesday, 26 June 2012
ሰዎቻችን ቋንቋቸው የተደበላለቀው ምን ተንኮል ቢያሴሩ ነው!?
ድሮ ድሮ አሉ የሰው ልጆች ቋንቋ ሁሉ አንድ ነበር። ታድያ ከእለታት በአንዱ ቀን ትልቅ ግንብ ገንብተው ፈጣሪያቸው ያለበት ሰባተኛው ሰማይ ላይ ደርሰው ምን እያደረገ እንደሆን ሊሰልሉት አሴሩ።
የሀሳባቸውን ለመሙላትም፤ አንድም የሰው ልጅ ሳይቀር ተሰባስበው በዚህ እኩይ ስራ ላይ ተጠመዱ። እግዜርም ይህ የማይሆን የቂል ሀሳባቸው እንደማይሳካ ያውቃልና፤ በሌሎች መልካም ስራዎች ላይ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ፣ እንዲሁም በዚህ የተነሳ የሚደርስባቸውን አደጋ ለመታደግ ብሎ ይህንን ስራ ሊያቋርጥባቸው ፈለገ። ከዛም ቋንቋቸውን ደበላለቀው። ከዛስ…? ከዛማ አንዱ ብሎኬት አምጣ ሲል ውሃ ሲያቀብለው፣ ሙገር ሲሚንቶን አቀብለኝ ሲል የቀበና አሸዋ ሲያመጣ ግንቡ በየት በኩል ይግባቡ በየት በኩልስ ይገንቡ!? ሀሳባቸው ከንቱ ሆኖ ቀረ።
ይህ ታሪክ አፈታሪክ ይሁን ሀይማኖታዊ ታሪክ እንጃ፤ ግና ከድሮም ጀምሮ ስንሰማው ኖረናል። ንግግራችን እና ቋንቋችን ለመልካም ካልሆነ ቢደበላለቅ በስንት ጣዕሙ! የሚል አንኳር ሃሳብም ይዟል። እውነትም አለው።
በዛ ሰሞን “ስካይፕ እና የመሳሰሉት የኢንተርኔት ቴክኖሎጂዎች በኢትዮጵያ ምድር መጠቀም ሊያስቀጣ ነው።” ተብለን፤ “አይይይ… እንግዲህማ ምን ቀረ…? ከዚህ ቀጥሎ ህልማችንንም ቁዘማችንንም ፀሎታችንንም በአዋጅ የምንቀማበት ጊዜ ደረሰ አይደለምን!?” ብለን እጅግ አድርገን ስናማርር ድንገት ከመንግስት ባለስልጣናት አንዱ ቤቴሌቪዥናችን ብቅ ብለው “ስካይፕም ሆነ ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በአዋጅ ሊከለክሉ ነው የተባለው በሬ ወለደ ወሬ ነው” ብለው ተስፋ ሰጥተውን ነበር።
በነጋታው ደግሞ ሌላው ባለስልጣን ተነስተው፤ “ስካይፕም ሆነ ሌሎች የቴሌን ገቢ የሚቀንሱ እና በደህንነት ስጋት የእኛን ኪሎ የሚቀንሱ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ጥርቅም አድርገን እንዘጋለን ምን ታመጣላችሁ!?” አይነት ንግግር መናገራቸውን ሰማን!
እኔ የምለው አቶ ሽመልስ፤ የመንግስት ቃል አቃባይ ሆነው ሳለ ለምን ቃላባይ ሲያደርጉዎት ዝም ይላሉ!? እርሶ ያቀበሉት ቃል በነጋታው “ውሸቱን ነው አትስሙት!” ሲባሉ ጎረቤትዎስ፣ ለቤተሰብዎስ፣ ለባንኮኒ ጓደኞችዎስ ምን ስም ያሰጥዎታል? እንዴ ምንም ቢሆን ሁለት ፀጉር አብቀለዋልኮ… የማንም ማላገጫ ሲሆኑማ ዝም አይበሉ!? እውነቴን ነው የምልዎ እኔ ለርሶ በመቆርቆር ነው የምናገረው…! ከዚህ በኋላ፤ “ይህንን ቃል አቀብል” ሲባሉ “መጀመሪያ እውነት መሆኑን ማሉልኝና” በሉዋቸው እንጂ ዝም ብለውማ አይመኑ! እንዴነችና ስልጣኑ ባፍንጫዎ ይውጣ እንጂ የማንም መጫወቻማ አይሆኑም…!
እኔ የምለው አቶ በረከት፤ እኛማ እኮ እርሳቸውን አምነን ለስንት ወዳጆቻችን “ስካይፕ አልተከለከለም!” ብለን ነገርን መሰልዎ…!? ለወደፊቱም ቢሆን አቶ ሽመልስ የሚናገሩትን ለማረጋገጥ እርስዎ ጋር እንድንደውል ስልክዎን ቢሰጡን ደስ ይለኛል።
እዝችው ጋ ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎትማ… አቶ ሽመልስ ባለፈው ጊዜ “ስካይፕ አይከለከልም” ብለው የዋሹን እለት አያይዘውም ስለ አቶ መለስ ጤና ነግረውን ነበር። “እኛ በአደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ክስት ግርጥት ብለው ተመልክተናቸው እግዜር ይማራቸው እያልን እየፀለይን ነው አሁንስ ሻል አላቸው ወይ?” ብለን ብንጠይቃቸው፤ እርሳቸው ሆዬ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሙሉ ጤንነት ላይ ናቸው!” ብለው ነግረውናል። አሁን ሳስበው ግን ስካይፕ አይከለከልም ብለው እንደዋሹን ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩንም ጤና አስመልክቶ የነገሩንን ለማመን ተቸግረናል። እና እርስዎ ቢነግሩን ደስ ይለናል! አለበለዛ ግን ህዝቡ፤ የአቶ ሽመልስን ንግግር ተቃራኒ ትርጉም በመውስድ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣር ተይዘዋል በቅርቡም ቀብር ሊሆን ይችላል!” ብሎ ቢያስብ እኔ የለሁበትም።
እኔ የምለው ወዳጄ፤ ባለስልጣኖቻችን እንደምን ያለ ተንኮል አስበው ይሆን ቋንቋቸው እንዲህ የተደበላለቀባቸው!?
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment