"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Tuesday, 26 June 2012

ሙላቱ አስታጥቄ ከበረ፤ ኢትዮጵያም ተደሰተች




Monday, June 25th, 2012 | Posted by zehabesha
ሙላቱ አስታጥቄ ከበረ፤ ኢትዮጵያም ተደሰተች
Share

የጃዝ ሙዚቃው ንጉስ ሙላቱ አስታጥቄ ሰሞኑን እዚሁ ሰሜን አሜሪካ ቦስተን ውስጥ በሥራው የክብር ዶትሬቱን አግኝቶ በዓለም ደረጃ የሃገራችንን ስም አስጠርቷል። እርሱ ከብሮ ሃገራችንም እንድትደሰትበት አድርጓልና የሚከተለውን ይህን ታላቅ አርቲስት የሚዘክረውን የእንግዳወርቅ ባዬን ልዩ ጽሁፍ አስተናግደናል። ይታደሙ።
ኢትዮ -ጃዝ የተባለውን የሙዚቃ ስልት በመፍጠር የኢትዮጵያን የጃዝ ሙዚቃ እድገት ከፍተኛ ደረጃ ላይ አድርሷል። አንጋፋ ሙዚቀኛና የሙዚቃ አቀናባሪ በመሆንም ይታወቃል። በአሁኑ ጊዜ ላሉት የጃዝ አፍቃሪያን መበራከት መሠረት የጣለ አንጋፋ የኪነጥበብ ሰው እንደሆነም ይነገርለታል- አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ።
ከአርባ ዓመት በላይ በሙዚቃው ዓለም የቆየው አርቲስቱ፣ በእነዚህ ዓመታት እራሱንም ሆነ ሀገሩን የሚያስጠሩ በርካታ ሥራዎችን ያበረከተ ታላቅ የሀገራችን የጥበብ ሰው ነው።

ለበርካታ ዓመታት ሕይወቱን ለሙዚቃ ጥበብ የሰጠው ሙላቱ ፊደል መቁጠር የጀመረው በቄስ ትምህርት ቤት ነው። ቀጥሎም በአዲስ ከተማና በእንግሊዝ የማኅበረሰብ ትምህርት ቤት አስራ ስድስት ዓመት እስኪሞላው ድረስ ዘመናዊ ትምህርቱን ተከታትሏል። ከዚያም በእንግሊዝ አገር ወደሚገኘው ላንድስ ፊም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሄዶ ትምህርቱን እንደቀጠለ መረጃዎች ያስረዳሉ።
በወቅቱ የአውሮፕላን ምህንድስና እንዲያጠና በሚል በቤተሰቦቹ ግፊት ወደ እንግሊዝ ያመራው አርቲስት ሙላቱ፣ በውስጡ የተቀበረው የሙዚቃ ጥበብ ሌት ተቀን እረፍት ይነሳው ጀመር። ከቀለም ትምህርቱ ጐን ለጐን በትምህርት ቤቱ በሚገኘው የሙዚቃ ጓድ ውስጥ በመጫወት የነበረውን ልዩ ተሰጥኦ ለማግኘት የበቃውም ገና በወጣትነቱ ነበር።
ለምህንድስና ትምህርት ተልኮ ጥበብ ወደ ሙዚቃ ያመጣችው አርቲስት ሙላቱ፣ በወቅቱ እንደ ፊዚክስና ኬሚስትሪ በመሳሰሉት የሣይንስ ትምህርቶች የተሻለ ውጤት የነበረው ተማሪ ቢሆንም በእንግሊዝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በወቅቱ ስመጥር በነበረው የትሪኒት ኮሌጅ ኦፍ ሚውዚክ በመግባት የክላርኔትና የፒያኖ ትምህርቱን በክላሲካል የሙዚቃ ዘርፍ ለሁለት ዓመታት ተከታትሏል።
በሃያዎቹ የዕድሜው አጋማሽ ወደ ሰሜን አሜሪካ በመጓዝ በቦስተን በሚገኘው በርክሌይ ኮሌጅ የሙዚቃ ትምህርቱን በመቀጠል ሁለገብ የሙዚቃ ፈጠራ፣ ቅንብርና የምርምር ሥራ ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን ለአራት ዓመታት ያህል ተከታተለ። ይህም በወቅቱ በኮሌጁ ይሰጥ የነበረ ከፍተኛ ሥልጠና ሲሆን፤ አርቲስቱንም የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተማሪ ለመሆን አብቅቶታል።
አርቲስት ሙላቱ በዚህ ሳይገታ በዚያው በአሜሪካ በሚገኘው ኸርትኔት ሞደርን ሚውዚክ ኮሌጅ ውስጥ ተጨማሪ የአራት ዓመታት ትምህርቱን አጠናቅቋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የካልቸራል ስተዲስ መምህር የሆኑት አቶ ስሜነህ በትረየስ « ሙላቱ አስታጥቄ ማነው?» በሚል ርዕስ ስለ አርቲስቱ ሕይወት ያካሄዱት የዳሰሳ ጥናት እንደሚያስረዳው አርቲስት ሙላቱ በለንደን ቆይታው ኤድሞንዶሮስ ከተሰኘው የሙዚቃ ቀማሪና የላቲን ጃዝ ባንድ መሪ ጋር በርካታ ሙዚቃዎችን ተጫውቷል።
አርቲስት ሙላቱ በተለያዩ የምሽት ክበቦችና የቴሌቪዥን ሥርጭቶች ዝግጅቱን በማቅረብ የነበረውን የሙዚቃ ተሰጥኦ በተደጋጋሚ አስመስክሯል። ከዚህም አልፎ «ነፍስ ነሽ» የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሙን «ፋራንክ ሆልዳና ኒያዝ አልሸሪፍ» ከተሰኙ አሳታሚዎች ጋር በመተባበር አቅርቧል።
ይኸው ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚያስረዳው አርቲስቱ ወደ ሰሜን አሜሪካ ከተጓዘ በኋላ በ1958 ዓ.ም አፍሮ -ላቲን ሶል (Afro -Latin Soul) ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት አልበሞቹን ለማሳተም በቅቷል። በመጀመሪያው አልበም «አይፈራም ጋሜ አይፈራም»፣ «አልማዝ» እና «አክሱም» የተሰኙትን ኢትዮጵያዊ ሙዚቃዎችን ሲያካትት በሁለተኛው «ቆንጂት» እና «ከረዩ» የተሰኙትን አክሎበታል። ይህ አጋጣሚ ነበር ሙላቱ « ኢትዮ ጃዝ» የተሰኘውን የሙያ ልጁን ለመጠንሰስ የበቃው።
በአርቲስቱ የተፈጠረው ኢትዮ ጃዝ ዛሬ በዓለማችን እንደ አንድ የሙዚቃ ስልት ተቀባይነት አግኝቷል። የኢትዮ ጃዝ ማዕከላዊ ሃሳብ የጃዝ ሙዚቃን ባህርያት ከአገር በቀል የኢትዮጵያ ሙዚቃና የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር ማንነታቸውን ሳይለቁ ማዋሃድ ነው። ሙላቱ እንዲህ አይነቱን የሙዚቃ ዘይቤና ስያሜ ለዓለም ካስተዋወቀበት ጀምሮ ከአራት አሥርት ዓመታት በላይ አፍሪካ ለዓለም የሙዚቃ ባህል ያበረከተችውን አስተዋፅኦ ያለመሰልቸት ሲያስረዳና በሥራዎቹም ሲያረጋግጥ ኖሯል።
ጥናቱ እንዳሰፈረው በአሁኑ ወቅት በደርዘን የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ቡድኖች የሙላቱን ፈር ተከትለዋል። በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ በርካታ የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ አቀንቃኞችን ያፈራ ሲሆን፤ የእዚህ ሙዚቃ ስልት አቀናባሪ፣ ተጫዋችና አድናቂዎችንም ሊፈጥር ችሏል።
ሙላቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀውን የጃዝ ሙዚቃ አላባውያን እንዳለ ከመገልበጥ ይልቅ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ያልተቋረጠ ጥናት በማካሄድና ግኝቶቹን በሥራዎቹ ውስጥ በማካተት የተለያዩ ሥራዎችን አቅርቧል። አቶ ስሜነህ በጥናታቸው ላይ ለእዚህ እንደ ምሳሌ ያቀረቡት በአብዛኛው ባለ አምስት ድምጽ (ፔንታቶኒክ) ስኬል የሆነውን የኢትዮጵያ ሙዚቃ አርቲስቱ ከባለ አሥራ ሁለት (የጃዝ ሙዚቃ) ጋር በማዳቀል ለበርካታ ዓመታት ሲመራ መር ቆይቶ ውጤታማ ሥራ መሥራ ቱንና የሀገሩን ሙዚቃ በዓለም ላይ እንዲደመጥ ማድረጉን ነው።
የኢትዮጵያው ሙላቱ (Mulatu of Ethiopia) የተሰኘውን ሦስተ ኛውን አልበም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ድጋፍ ወደ አሜሪካ በማቅናት አበርክቷል። በመቀጠል በአገር ውስጥ የመጀመሪያ የሆነውን አልበም « ኩሉን ማንኳለሽ» በሚል ርዕስ ከፊሊፕስ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ማሳተሙን ይኸው መረጃ ያስረዳል።
ሙላቱ ኢትዮ ጃዝ በማለት ካቋቋማቸው የሙዚቃ ባንዶች በተጨማሪ ከኢትዮ ስታር፣ ራስ፣ ዳህላክ፣ ኦልስታር እና ዋልያስ ጋር በርካታ ሥራዎችን ያቀረበ ቢሆንም ቀልቡን በእጅጉ ከሳቡት መካከል በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ትልቅ አሻራ የጣሉት ሶል ኤክስ የተባሉት የሙዚቃ ቡድኖች ነበሩ።
አርቲስቱ ለድምፃውያን ሙዚቃ በማቀናበር ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ሥራዎችን በመቀመርና በመሣሪያ ብቻ የተዘጋጁ ሙዚቃዎችን በአገር ውስጥና በውጭ አገር አስቀርጿል። ለዚህም ለኢትዮጵያ አየር መንገድ በተከታታይ የተቀረጹትን « ኢትዮ ጃዝ» እና «አስዮ ቤሌማ» የተሰኙትን በምሣሌነት መጥቀስ በቂ ነው።በጥናቱ ላይ እንደተገለጸው፤ ሙላቱን ልዩ የሚያደርገው የተዋጣለት የመድረክና የስቱዲዮ ሙዚቀኛ መሆኑ ብቻ አይደለም። በተለያዩ የአገራችን ብሔረሰቦች ሙዚ ቃዎ ችና አገር በቀል የሙዚቃ መሣሪያዎች ላይ የሚያደርጋቸው ዘርፈ ብዙ የምርምር ሥራዎችም ጭምር እንጂ። ከሰሜኑና ከመካከለኛው የአገራችን የሙዚቃ ባህል ባለፈ በኮንሶ፣ በወላይታ፣ በከፋ፣ በደራሼ፣ ጋሞ፣ አኙዋክ፣ በሱርማና በሌሎችም ብሔረሰቦች ሙዚቃ ላይ ምርምር አድርጓል።
ለሀገራችን ባህላዊ ሙዚቃ ከፍተኛ አክብሮት ያለው አርቲስቱ ፤ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ለማሻሻል የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ከዚህ በፊት ተሠርቶባቸው የማያውቁትን አዳዲስ ሥራዎች እንዲሠራባቸው አድርጓል። ለአብነት ያህል ባለስድስት ክር የነበረውን ክራር በማሻሻል የክሮቹን ብዛት ወደ ስምንት በማሳደግ የተለያዩ ሙዚቃዎችን ተጫውቶባቸዋል። አርቲስቱ ከዚህም አልፎ እነዚህን የክራር ክሮች ወደ አሥራ ሁለት የማሳደግ ዓላማ አለው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሙዚቃና የሙዚቃ መሣሪያዎች ሙላቱ በርካታ ምርምር ካደረገባቸው መካከል ሌላው ተጠቃሽ ናቸው። አቶ ስሜነህ በጥናታቸው ላይ እንደገለጹት፤ አርቲስቱ ይህን ቱባ የቤተክርስቲያን ባህል መሠረት በማድረግ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ካቀናበረው «ደወል» ከሚሰኝ ሥራ ጀምሮ «ቤተክርስቲያን» እንዲሁም በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ቆይታው በ2000 ዓ.ም ተደርሶ ለተመልካች ያቀረበው « የያሬድ ኦፔራ» ይጠቀሳሉ። በክራርና በከበሮ ላይ ያደረገው የሙከራ ሥራዎችም እንዲሁ።
አርቲስቱ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በመድረክ የሙዚቃ ተጫዋችነት፣ ሙዚቃ በመድረስና በማቀናበር ለጥበቡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርግ ቆይቷል። ሙያዊ ተጋድሎም አድርጓል ማለት ይቻላል። እ.ኤ.አ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ያደረጋቸው የረጅም ዓመታት ሙያዊ ተጋድሎ በዓለም አቀፍ መድረክ ይበልጥ እውቅና አስገኝቶለታል። በተለይ ፓሪስ የሚገኘው ቡዳ ሚውዚክ የተሰኘው ሪከርድ ሌብል «ኢትዮ ጃዝና ኢንስትሩመንታል» በሚል ርዕስ በሙላቱ ከተቀነባበሩት ቀደምት ሥራዎች የተወሰኑትን ለዓለም አቀፍ አድማጭ ማድረሱ በስፋት እንዲታወቅ አድርጐታል።
ሙላቱ ከዚህ ቀደም ሲልም በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም አቀፍ የሙዚቃ መማክርት ሽልማት ዕጩ ፣የኢንተርናሽናል ጃዝ ፌዴሬሽን የቦርድ አባል እንዲሁም የፖላንድ የጃዝ ማኅበርና የብሔራዊ ጃዝ ኤዱኬተርስ አባል ወዘተ የነበረ መሆኑ ዕውቅናው ከዚያ በፊት እንደነበረ ያስረዳል።
ለሰባት ዓመታት ያህል የሙላቱን ሙዚቃ በመጫወት ይታወቅ የነበረውና በአሜሪካ እጅግ ገናና የሆነው አሥር አባላት ያሉት ኦርኬስትራ በ1996 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከሙላቱ ጋር ተጫውቷል። በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ላይም የሙዚቃ ኮንሰርቶችንም አቅርበዋል። ኮንሰርቶች በሬድዮ በቀጥታ እስከመተላለፍ የደረሱ በመሆናቸው ታዋቂነትና ተወዳጅነትን አትርፈዋል።
በሆሊውድ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው የፊልም ፕሮፌሰር ጂም ጃርሙሽ « የግሌ ትዝታ»፣«የከርሞ ሰው» እና «ጉብልዬ» የተሰኙትን የሙላቱ ሙዚቃዎች « ብሮክን ፍላወር» ለተሰኘው ፊልሙ ማጀቢያነት ለመጠቀም መጠየቁንም መረጃው ጠቁሟል። ይህ በርካታ ሽልማቶችን ያገኘው ፊልም የሙላቱን የዓለም አቀፍ ዝናን አሳድጐታል።
በ2000 ዓ.ም ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የራድክሊፍ ኢንስቲትዩት ፌሎሺፕ በማግኘቱ በዚያ በማስተማርና በምርምር ሥራዎች ለአንድ ዓመት ያህል ቆይቷል። በዩኒቨርሲቲው ካቀረባቸው በርካታ ሌክቸሮች ባሻገር የኢትዮጵያን የባህል ሙዚቃ መሣሪያዎች የማዘመን ምርምሮች አካሂዷል። «የያሬድ ኦፔራ» የተሰኘውን አዲስ የሲንፎኒ ሙዚቃ በማቀናበር ለበርካታ የአሜሪካና ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በማቅረብ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱን መረጃው ያሳያል።
በጥበብ ውስጥ ከአራት አሥርት ዓመታት በላይ የዘለቀው አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ የኢትዮጵያን ጃዝ ሙዚቃ ለማስተዋወቅ ዓለምን ዞሯል። ከታዋቂ ሰዎች ጋርም ኮንሰርቶችን አዘጋጅቷል። የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችንም አግኝቷል።ከአገራችንም አልፎ የዓለማችን ብርቅዬ አርቲስት በመሆኑ በጀርመን አገር በስሙ መንገድ ተሰይሟል። በተለያዩ ኢንሳይክሎፒዲያዎች ታሪኩ መመዝገቡንም ነው የአቶ ስሜነህ ጥናታዊ ጽሑፍ የሚያስረዳው።
ሙላቱ ከአሜሪካው የበርክሌይ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ኮሌጅ የክብር ዶክትሬት ያገኘ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት እዚሁ ሰሜን አሜሪካ በቦስተን ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ታላቅ የሽልማት ሥነ ሥርዓት የክብር ዶክትሬቱን ተቀብሎ ኢትዮጵያን ከፍ አድርጓታል። በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይህ የክብር ዶክትሬት ሊሰጠው ችሏል።S
የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ አባት የሆነው አርቲስት ሙላቱ ለበርካታ ዓመታት የሙዚቃውን ጥበብ ለማሳደግ ባከናወናቸው ሥራዎች የክብር ዶክትሬቱን በሚቀበልበት ዋዜማም በመዲናችን አዲስ አበባ አርቲስቱንና የአርቲስቱን ሥራዎች ለመዘከር አንድ መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። ከሰሞኑ በአዲስ አበባ «ዝክረ የአርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ የኪነ ጥበብ ሥራዎች» በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን መድረክ ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ነው። በማዕከሉ አዳራሽ በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ከሙዚቃ፣ ከተውኔት፣ ከፊልምና ከተለያዩ የኪነጥበብ ማኅበራት የተውጣጡ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ታዋቂ ሰዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። በአርቲስቱ ሕይወትና ሥራዎች ላይ ያጠነጠነ ጥናታዊ ጽሑፍም ቀርቦ ውይይት ተደርጐበታል።
ከአርቲስቱ የሙዚቃ ሥራዎች ውስጥ ለዝግጅቱ የተመረጡ ጥቂት ሙዚቃዎች በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተመራቂ ተማሪዎች (በያሬድ ግሩቭ ባንድ) ቀርበዋል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እልፍነሽ ኃይሌ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ የኪነ ጥበብ ሰው ብቻ ሳይሆን በሀገሩ ጥበብ የሚኮራና አገሩን ለውጭው ዓለም ያስተዋወቀ ታላቅ ሰው ነው ብለዋል።
ለተሰማራበት ሙያ ማደግ ባበረከተው አስተዋፅኦ እና በተለይ ኢትዮ- ጃዝን በዓለም ላይ ለማስተዋወቅ ያደረገውን ጥረት ለመዘከር ሲባልም መድረኩ መዘጋጀቱን ነው የገለጹት። እንዲህ ያለው መድረክ አንጋፋ አርቲስቶች ሥራቸውንና የሥራ ልምዳቸውን ለተተኪው ትውልድ እንዲያስተላልፉም ዕድል ይከፍታል ብለዋል።
የጥበቡን ሰው ከማበረታታት ባለፈ ኪነ ጥበብ በተጠናከረ መንገድ እንዲቀጥልና ተተኪው የጥበብ ሰው ለሙያው የተለየ ትኩረትና ክብር እንዲሰጥ በማድረግ በኩልም ጠቀሜታው ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይ ተመሳሳይ ዝክረ ኪነጥበብ መድረኮችን የማዘጋጀት ሥራው እንደሚቀጥል ገልጸዋል። የባህል ማዕከሉ በአገራችን ብዙም ያልተለመደውን ሰው ካልሞተ ወይም ካልሄደ በቀር የማይታወስበትንና የማይዘከርበትን አሠራር በመስበር የጥበቡ ሰዎች በሕይወት እያሉ በሠሯቸው ሥራዎች የሚመሰገኑበትና የሚዘከሩበትን መንገድ ማዘጋጀቱ ያስመሰግነዋል።
ኢትዮጵያም በረሃብና በድርቅ የሚታወቀው ስሟ በነሙላቱ አስታጥቄ ከፍ ማለቱ ለኛ ትልቅ ሞራል ነው። እንኳን ደስ ያለህ ሙላቱ አስታጥቄ።እኛም!S

No comments:

Post a Comment