"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Saturday 23 March 2013

የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ - ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን

 



የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ

ተስፋ ባጣ ምድረ በዳ
ያንድ እውነት ይሆናል ዕዳ፡፡
እና ትንፋሼ አልሆነሽም፥ ሆኜብሽ መራር መካሪ
“ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ፣”
እውነት ላንቺ መች ተስፋ ናት፥ ጉስቁል ልሳንሽን ነክሳሽ
ክንድሽን ካዘለ ቅርስሽ፥ መጠላለፍ ሲሆን እጣሽ
ከእንግሊዝ የሞት አማልክት፥ መተናነቅ ሲሆን ድርሻሽ
መልመጥመጡ፥ መሽቆጥቆጡ፥ መስሎሽ ድንገት የሚያዋጣሽ
የኔ እውነት ሆነብሽ ዕዳሽ ፡፡ …..
ወራሪም ፈጣሪን ላያቅ
የጣለውን በስሏል እንጂ፥ ወድቋል ብሎ ግፉ ላያልቅ
መች ትተርፊያለሽ ኢትዮጵያ፥ ሕዋስሽ አብሮኝ ካልሠራ
አንገትሽ ብቻ መቅደላ፥ አፋፍ ወጥታ ብታበራ
የቀረው ሠራ-አከላትሽ፥ በየጥሻው ተዘርሮ
ከአባት በወረሽው ንፍገት፥ ነብዞ ደንዝዞ ተቀብሮ
ባጉል ወጌሻ ታጅሎ
እጅና እግርሽ ታሽቶ ዝሎ
እኔን ለጥንብ አንሳ ጥሎ፤
ከደቀቀ ከደከመ፥ ክንድሽ አልነሣ ካለ
ሞት እንጂ ለኔስ ምን አለ?.....
ሆኖም ጐስቋላ አልምሰልሽ፥ የሚያዝንልኝ አልፈልግም
ጠላትሽን በክንድሽ እንጂ፥ በእንባሽ ወዝ ባላሸንፍም
የልቤን ፍቅር በሰተቀር፥ እማወርስሽም ውል የለኝ
የኮሶ ሻጭ ልጅ ደሃ ነኝ፡፡ …..

ደሞም ያላንቺ የለኝና
ድሌም የተሰፋ ጐሕ ባይሆን፥ ከሞት ጋር ትግል ነውና
ከዚህ ሌላ ትእዝብት ውረሽ፥ ሳይነጋ እንዳስመሸሽብኝ
ጊዜና ትውልድ ይፍረደን፥ ሳልነቃ እንዳስረፈድሽብኝ፡፡
ያም ሆኖ ለራስሽ እንጂ ለኔ ከቶም አታልቅሺ
አንቺ ነሽ እንባ እምትሺ፤ …..
የእምነትሽ መተሣሰሪያ፤ ውልሽ ለተላቀቀብሽ ላንቺ ነው እንባ እሚያሰፈልግሽ፡፡
አዎን፥ ይኽን እወቁልኝ፥ ምስክር ሁኑኝ ሰማዕታት
ለሷ ነው እንባ የሚያስፈልጋት፡፡
ከጠላቶቹ ጭብጥ ውስጥ፥ ትንፋሼን በጄ ስነጥቃት
ሞቴን ከመንጋጋቸው ውስጥ፥ መንጭቄ እኔው ስሞታት
ላገሬ ብድር ልከፍላት
የነፈገቺኝን ፍቅር፥ በራሴ ሞት ልለግሳት!.....ያኔ ነው እንባዋ የሚያጥራት፡፡
ሰለዚህ ለራስሽ እንጂ፥ ልቅሶሽ ለኔ ምን ሊረባ
ብቸኛ ምሬት ነው ኃይሉ፥ ወኔ መሰለቢያው ነው እንባ፡፡
እና ለራስሽ እዘኚ
እንጂ ከቶ ለኔ እትባክኚ፡፡ …..ይልቅስ ተረት ልንገረሽ፥ የተላከ ከእንግሊዝ ዘንድ
እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ፥ እጅ ተይዞ ሊወሰድ፥
ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ?አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ፡፡ …..ዳዊት እንዲያ በበገናው፥ ማልቀስ ማላዘን መያዙ
ይኽ የጐልያድ ውላጅ፥ ቢበዛበት ነው መዘዙ
ምንጩ እንደአሽን እየፈላ፥ አገሩን ምድሩን ማንቀዙ
ቸግሮት ነው፥ መጋፈጡ፥ ከስንቱ መወናጨፉ
በባላንጣው ሳቢያ ምክንያት፥ የራሱን ወገን ማርገፉ፡፡ …..ታድያ እንግዲህ አንቺ ኢትዮጵያ፥ እኛስ ልጆችሽ ምንድነን
አመንኩሽ ማለት የማንችል፥ ፍቅራችን የሚያስነውረን
ዕዳችን የሚያስፎክረን
ግፋችን የሚያስከብረን
ቅነነት የሚያሳፍረን፥ ቂማችን የሚያስደስተን
ኧረ ምንድነን? ምንድነን?አሜከላ እሚያብብብን፥
ፍግ እሚለመልምብን፥
ከአረም ጋር ያፈራን ጊንጦች፥ ከእንክርዳድ ያልተለየን ዘር
ግርዱ ከምርቱ ተማጥቆ፥ ከቶ ያልተበራየን መከር
ምንድነን? ምንድነን እኮ?አረጋዊውን ባንቀልባ፥ ከምንሽከም እንኮኮ
ጐልማሳውን ከወኔ ጣር፥ ካልፈታን ከፍርሃት ምርኮ
እንደ ወዶ ገባ ወደል፥ መጠለሉን ከሴት ታኮ …..ካቃተን፥ ምንድነን እኮ?.....አየሽ እንቺ እማማ ኢትዮጵያ፥ አየሽ አንቺ እናት ዓለም
ቃል የእምነት ዕዳ ነው እንጂ፥ ያባት የናት እኮ አይደለም፡፡ …..

ያም ይቅርና መርዶ ላርዳሽ፥ ስሚው እኔ እንደሰማሁት
እርም በልተሽ ከምትቀሪ፥ ስሚው ገብርዬንም ጣሉት፡፡ …..እስቲ እንግዲህ በይ ፍረጂኝ፥ ከእንግዲህ እኔ ፍሬ አላይም?
ዘርቶ መቃም ወልዶ መሳምአባባል ለኔ አይባልም?እስቲ ገብርዬን መሰል ዘር፥ ፍሬው ከቶ አይለመልምም?እኔስ ዘር ዘራሁ አልልም? …..ምነው ፍንጭትክን ገብርዬ፥ ያን ፍንጭትክን አጨለሙት
እንደ ሬት ልግ አከሰሉት
እንደ ኮሶ አስመረሩት? ......ከጡቶችሽ እቅፍ ነጥቀው፥ ከማኅፀንሽ ፍቅር ቆርጠው
እውነትን ሲገሉ እንዲህ ነው፥ ፈገግታውን አጨልመው፡፡
እስቲ እባክህን ገብርዬ፥ የዛሬን እንኳ ስቀህ ሙት
በዕድል ጥቀርሻ እንደአጀሉት
እንደ ወላድ ጣውንት ጡት
አርማ ጉሳ እንደቀለሙት
ፈገግታህን አያጥቁሩት፡፡
እምቢ በላቸው ገብርዬ፥ በአባት ሤራ እንዳስገዘቱት
በመሃላ እንዳሳገዱት
የነፍሰህን ጮራ ብርሃን፥ ከገጽህ እንደቀበሩት
ዘለዓለም ላያጨልሙት
ወንድምዬ እምቢ በላቸው፥ የዛሬን እንኳ ስቀህ ሙት፡፡ …..ያለፈ ጥረታችንን፥ ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ፥ ያልሞከረነው ነው እሚቆጨኝ፡፡
እና በኔ ይሁንብህ፥ መጣሁ፥ ስቀህ ተቀበለኝ
እኔም ላዋይህ አድምጠኝ …..እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ፥ እጅ ተይዞ ሊወሰድ
ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ?አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ፡፡ …..


ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን
እሳት ወይ አበባ

1 comment:

  1. የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
    እነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.

    ReplyDelete