"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Wednesday 27 March 2013

ማልዶ የወጣ Maldo Yewta


 የዲያቆን አሸናፊ መንን ገጽ

ማንም ሰው ለእግዚአብሔር ኢትዮጵያ ወይም ኬንያ ልወለድ ብሎ አሳብ አላቀረበም፡፡ ሙሉ በሙሉ ፈቃዱ የእግዚአብሔር ሆኖ ራሳችንን በዚህ አገርና በዚህ ቤተሰብ ውስጥ አግኝተነዋል፡፡ የምንኖርበትን አገር፣ የምንወለድበትን ቤተሰብ የመረጠልን ምርጫ አዋቂው እግዚአብሔር ነው፡፡ በእግዚአብሔር የሆነልን ነገር መልካም ነው፡፡ ሰው ሆነን መፈጠራችን፣ መዳናችን፣ ክርስቲያን መሆናችን.. የሆኑልን መልካም ነገሮች ናቸው፡፡ በእግዚአብሔር ወደፊት የሚሆነውም መልካም ነው፡፡ ከእግዚአብሔር እጅ የምንቀበለው ነውር፣ ነቀፋ፣ እንከን፣ ነቁጥ የሌለበት ነው፡፡

ልጆቻችን የወደዱን በብዙ መልካምነታችን ነው፡፡ የትዳር ጓደኞቻችን የመረጡን በቁምነገራችን ነው፡፡ መሥሪያ ቤታችን የተቀበለን በሙያችን ነው፡፡ ወዳጆቻችን የወደዱን በማረካቸው ነገራችን ነው፡፡ ወላጆቻችን የወደዱን የእነርሱ ስለሆንን ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን የወደደን ስለ እኛነታችን ነው፡፡

እኛን ለቤተሰባችን፣ ቤተሰባችንን ለእኛ የሰጠ እግዚአብሔር ነው፡፡ ወላጆቻችን ያዩንና የወደዱን ከተወለድን በኋላ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ዓለም ሳይፈጠር በአንድ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ዓይቶናል /ኤፌ. 1÷4/፡፡ በማኅፀን ደም አርግቶ፣ አጥንት ሰክቶ ፣ ጅማት አዙሮ፣ ሥጋ አልብሶ፣ እስትንፋስ ዘርቶ ሠርቶናል፡፡ በማኅፀን በስውር የመገበንም እርሱ ነው፡፡ ወላጆቻችን የሚያውቁን ስንወለድ ነው፣ እግዚአብሔር ግን የሚያውቀን ዓለም ሳይፈጠር ነው፡፡ ነቢዩ፡- “ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ” ያለው ለዚህ ነው (መዝ. 138÷ 15-16)፡፡




ወላጆቻችን በእኛ ላይ ካላቸው ዓላማ ይልቅ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለው ዓላማ ይልቃል፡፡ ዓላማው የሚጠፋ ሳይሆን የሚኖር፣ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ፣ ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላለማዊ፣ ነው፡፡ አዎ ጠራርገው ካሳደጉን ወላጆቻችን፣ ለትዳር ካጩን ጓደኞቻችን፣ አባቴ እናቴ ካሉን ልጆቻችን በፊት ማልዶ የፈለገን እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ እንደ ወላጆቻችን የልደት ወዳጃችን አይደለም፣ የማኅፀን ወዳጃችን ነው፡፡ ከዚያም በፊት ዓለም ሳይፈጠር ዘመን ሳይቆጠር፣ ታሪክ ሳይቀመር ያየንና የወደደን ነው፡፡ ልጅነታችንን ዓይተው ወላጆቻችን ወደዱን፣ እግዚአብሔር ግን ያልተሠራ አካላችንን ዓይቶ መረጠው፡፡ መልካችንን ዓይተው ወዳጆች አፈቀሩን፣ ሊያዩት የሚዘገንነውን ሽል በማኅፀን ውስጥ እግዚአብሔር ወደደው፡፡ ሙያችንን ዓይተው አለቆች አቀረቡን፣ ሊሠራን እግዚአብሔር ጠራን፡፡ እኛን በማፍቀር እኛን በመምረጥ ቀዳሚው እግዚአብሔር ነው፡፡ ገና ሳንወለድ የወደደን፣ ገና በማንኖርበት ዘመን የሚወደን ለዘላለም ያፈቀረን እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡



ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአብዛኛው ትምህርቱ በምሳሌ ነበር፡፡ ምሳሌ ረቂቁን የሚያጎላ፣ የማይታየውን የሚያሳይ ነው፡፡ ጌታችን ከሰጠው ምሳሌዎች አንዱ ከማለዳ እስከ ማታ የወደደንን እግዚአብሔር የሚተርክ ነው፡፡ በማቴ. 20÷1-16 ላይ ይህን ምሳሌ እናገኛለን፡፡

በምሳሌዉ ውስጥ የመንግሥተ ሰማያት ባለቤት ሆኖ የተጠቀሰው ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ መንግሥተ ሰማያት ወይም ወንጌል በወይን እርሻ ትመሰላለች፡፡ ለወይኑ ሠራተኞች ወይም ለወንጌል አገልግሎት ባለቤቱ ተቀጣሪዎችን ፈለገ፡፡ ከማለዳ እስከ ጠዋት ለአምስት ጊዜ ያህል ሠራተኛ ፍለጋ ወጣ፡፡ የመጀመሪያው ማልዶ ነው፡፡ የቀኑ ሰዓት ሳይጀምር አንድ ሳይባል ማልዶ ፍለጋ ወጣ፡፡ ሁለተኛ በሦስት ሰዓት ሠራተኞችን ፈልጎ ቀጠራቸው፡፡ ሦስተኛ በስድስትና በዘጠኝ ሰዓት ወጥቶ ሠራተኞችን ፈልጎ ቀጠራቸው፡፡ የሥራ ሰዓቱ ሊፈጸም አንድ ሰዓት ሲቀረው በአሥራ አንደኛው ሰዓት ሠራተኞች አገኘ፡፡ የሚቀጥራቸው አጥተው ሲንከላወሱ አግኝቶ ቀጠራቸው፡፡ በመጨረሻ ለሁሉም እኩል ደመወዝ ሲከፍል ቀኑን በሙሉ ሲሠሩ የዋሉት አጉረመረሙ፡፡ ያጉረመረሙት ደመወዛቸው ተቀንሶ ሳይሆን ከሌሎቹ እኩል ስለተከፈላቸው ተበሳጭተው ነው፡፡ ባለቤቱ ግን በገንዘቡ የወደደውን የማድረግ መብት ነበረውና ብስጭታቸውን አላደመጠም፡፡ ጌታችን ምሳሌውን ሲዘጋ፡- “እንዲሁ ኋለኞች ፊተኞች ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ የተጠሩ ብዙዎች የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸው” አለ (ማቴ. 20÷16)፡፡

የወይኑ ቦታ ሠራተኞች እንድንሆን ሁላችንም ተጠርተናል፡፡ የወንጌል ሠራዊት፣ የክርስቶስ ወታደር እንድንሆን ባለቤቱ ጋብዞናል፡፡ አንዳንዶች በማለዳ ተጠርተዋል፡፡ ዘመናቸው አንድ ተብሎ ሳይቆጠር ገና በማኅፀን ጥሪው ደርሶአቸዋል፡፡ እነ ይስሐቅ፣ እነያዕቆብ፣ እነኤርምያስ፣ እነ ዮሐንስ መጥምቅ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡ አንዳንዶችም በልጅነት ወራታቸው ጨዋታቸውን ጥለው፣ ሕጻንነታቸውን ረስተው ለእግዚአብሔር ለመዘመር፣ ለመቀደስ ተጠርተዋል፡፡ ሌሎችም በቀትሩ ሰዓት በወጣት ዘመናቸው ሲንከራተቱ ጥላ ወዳለበት ወደ ወይኑ እርሻ ተጠርተዋል፡፡ ሌሎችም በዘጠኝ ሰዓት ቀትሩ አለፈ ሲሉ ሠርኩ ሲቃረብ በጎልማሳነት ጥሪው ደርሶአቸዋል፡፡ የቀሩት ዓለም ጡረታ ስታወጣቸው ጡረታ የማያወጣው ጌታ ወደ ቤቱ ሰብስቧቸዋል፡፡ ዘመናቸውን በሙሉ በእግዚአብሔር ቤት የኖሩ፣ ከሕጻንነት እስከ ሽበት ያገለገሉ በእነዚህ የሠርክ ገቢዎች ላይ ቅሬታ አላቸው፡፡ “እኛ ትክለኞች ነን፤ ባቀናነው ቤት ማንም ዛሬ መጥቶ እንዴት ይፈነጭበታል. . .” ይላሉ፡፡ የወይኑ ባለቤት ግን ጠርቷቸዋል፡፡ አታስፈልጉም ተብለው ሁሉም በጣላቸው ሰዓት ታስፈልጉኛላችሁ ብሎ ሰብስቧቸዋል፡፡ በአዋጅ ጡረታ ወጥተው በሰማያዊ አዋጅ ለሥራ ተጠርተዋል፡፡ አብርሃም ቢጠራ በሠርክ ነው፡፡ በ75 ዓመት ጥሪ ሰምቶ ወጣ፡፡ በዛሬ አሠራር አብርሃም ጡረታ ከወጣ ድፍን ሃያ ዓመቱ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ሠርክን ማለዳ፣ ምሽትን ብርሃን፣ ፍጻሜን ጅማሬ ማድረግ ይችላል፡፡ የሠርክ ገቢዎች ሆይ የጠራችሁን እንጂ የሠራተኞችን ድምፅ አትስሙ፡፡ ደመወዝ ከፋዩ ባለቤቱ ብቻ ነው፡፡ እርሱ ከወደዳችሁ የሚጥላችሁ፣ እርሱ ከቀጠራችሁ የሚሰርዛችሁ የለም፡፡ እናንተም ምንም ቢሆን በቤቱ የኖሩትን አክብሩ፡፡ ዛሬ ሕይወታቸው ቢወድቅም የአንድ ቀንን መታመን የማይረሳው ጌታ እንደሚያስባቸው አትዘንጉ፡፡

ጌታ አንዳንዶችን በዘመናቸው ሁሉ ይፈልጋቸዋል፡፡ ማልዶ ወጥቶ ፈለጋቸው፡፡ እነርሱ ግን ዓለምን ገና እንወቃት አሉ፡፡ ቤተሰቦቻቸውም ትምህርታቸው ይሻላቸዋል፣ ሃይማኖትን መጠጋት የፍርሃት ምልክት ነው ብለው አከላከሏቸው፡፡ በልጅነት ወራት በሰንበት ት/ቤት፣ በሠርክ ጉባዔ ጠራቸው፡፡ ነገር ግን የልጅነት ስስ ልባቸው ለጌታ ጠንካራ ሆነ፡፡ ተስፋ ሳይቆርጥ በወጣትነት ዘመናቸው ጠራቸው እነርሱ ግን በሱስና በዝሙት፣ በወረተኛዋ ዓለም ፍቅር ተይዘው እምቢ አሉ፡፡ እንደውም እግዚአብሔር የለም አሉ፡፡ እንደገና ወጣትነቱ ሲሰክን ጎልማሳነቱ ሲመጣ ፈልጋቸው፡፡ ዕውቀትና ጉልበት የተባበረበት ዕድሜ ላይ ነን ማን ይችለናል? ብለው ገፉት፡፡ ተስፋ ሳይቆርጥ በሽምግልና ጠራቸው፡፡ አሁንማ እግዚአብሔር ማለት መቀለድ ነው፣ ድሮ ይሻል ነበር፡፡ ስሸነፍማ አማኝ አልሆንም፣ የመጣውን እንቀበላለን አሉት፡፡ ሌሎችም እያጣጣሩ ወደ ሞት እየሄዱ እንኳ ሊያምኑት እምቢ አሉ፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ በዘመናችን ሁሉ የሚፈልገን እግዚአብሔር ነው፡፡

ይህንን ጌታ በእናንተ ደጃፍ ላይ ስንት ዘመን አቆማችሁት? በራችሁን ለሚያንኳኳ እንግዳ ፈጥናችሁ እየከፈታችሁ ልባችሁን ለሚያንኳኳ ጌታ ምነው አስቻላችሁ? ዛሬ ዕረፍት እንድታጡ፣ ልባችሁን እስክትከፍቱ ትዕግሥት እንድታጡ መንፈስ ቅዱስ ያግዛችሁ!

ዛሬ ጥሪውን ብትቀበሉም ጥሪው ግን ዓለም ሳይፈጠር ማልዶ የመጣ ጥሪ ነው፣ የሚፈለገው ጌታ ብዙ ዘመን ፈልጎናል፡፡ አሁን ግን በተራችን ልንፈልገው ይገባል፡፡ እርሱን ማመንም ሆነ አለማመን ዘላለማዊ ውጤት አለውና ልናስብበት ይገባል፡፡ ማልዶ የወጣ፣ ማልዶ የፈለገን፣ ማልዶ የወደደን ጌታ ስሙ ቡሩክ ይሁን!

No comments:

Post a Comment