"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Friday, 11 May 2012

ሲብላላ ቆይቶ የፈነዳው የቴዲና የአዲካ ውዝግብ



ሲብላላ ቆይቶ የፈነዳው የቴዲና የአዲካ ውዝግብ [Addis Admas]
“እውነት ነፃ ያወጣል፤ ቴዲም የሚለው ነው” – አዲካ
በሽምግልና ስለተያዘ መናገር አንፈልግም - የቴዲ አፍሮ ተወካይ
ቅሬታ እስካልቀረበ አዲካ ህጋዊ ነው – ኦዲዮ ቪዥዋል
ቴዲ ኢትዮጵያዊ ወንድሜ ነው፤ መልካሙን ይግጠመው – አዲስ ገሰሰ

በቴዲ አፍሮ እና በአልበሙ
አሳታሚ በአዲካ መካከል፤ እልባት ያላገኙና በሽምግልና እየታዩ የሚገኙ ሶስት አወዛጋቢ ጉዳዮች የተፈጠሩ ሲሆን፤ ከእነዚህም አንዱ የማስታወቂያና የስፖንሰር ጉዳይ ነው። የአልበሙ ህትመትና ሽያጭ በተመለከተ ሁለቱ ወገኖች የተፈረመው ውል፤ የማስታወቂያና የስፖንሰር ጉዳዮችን ያካትታል። አዲካ፤ አልበሙን ለማስተዋወቅ የተለያዩ ስፖንሰሮችን በማፈላለግና በማስታወቂያ ሥራ እንዲያግዝ ውል ገብቷል። ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች፤ አርማቸውን በቴዲ ሲዲ፤ በካሴት፤ በቢልቦርድ፤ በፖስተር፤ በፍላየር እና በሌሎችም ላይ ያስተዋውቃሉ በሚል ሁለቱም ወገኖች እንደተስማሙ የውል ሰነዱ ያሳያል፡፡ ከስፖንሰሮቹ አንዱ በሆነው በሜታ አቦ ዙሪያ ነው ውዝግብ የተነሳው።

የሜታ አቦ – የቢራ ማስታወቂያ
ከውል ውጭ የሰራነው ነገር የለም የሚለው አዲካ፤ በውሉ መሰረት ከሜታ አቦ እና ከሌሎች ስፖንሰሮች ጋር በትብብር ሰርተናል ይላል። አዲካና ሜታ አቦ በትብብር ለመስራት የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ፤ የሜታ አቦ ማስታወቂያዎች እንዴት እንደሚስተናገዱ ይዘረዝራል። ሰዎች በመጠጥ ሰክረው ያልተገባ ነገር ሲፈፅሙ ከማሳየት በመለስ፤ ማናቸውም የሜታ ማስታወቂያዎች እንደሚስተናገዱ የመግባቢያ ሰነዱን በመጥቀስ የቢራ ፋብሪካው ገልጿል።
የሜታአቦ ማስታወቂያዎች በቢልቦርዶችና በፖስተሮች ላይ ታትሞ የተሰራጨ ሲሆን፤ ሲዲ ላይ መታተም ከጀመረ በኋላ ቴዲ አፍሮ ቅሬታ እንዳቀረበ የሜታ አቦ ዋና ሃላፊ ተናግረዋል። ፖስተሮችና ቢልቦርዶች ላይ የተካተተው የሜታ አቦ አርማ፤ በሲዲውም ላይ መታተሙ ምንም ችግር የለውም በማለት ምላሽ ሰጥተን ነበር ይላሉ የቢራ ፋብሪካውን በበላይነት የሚያስተዳድሩ ሃላፊ። የሜታ አቦ አርማ በሲዲ ላይ መታተሙ እንዳላስደሰተው የገለፀው ቴዲ አፍሮ፤ ሲዲውን በስጦታ የሚያበክትላቸው ህፃናት የቢራ አርማ እንዲሰያዩ አልፈልግም በማለት ምክንያቱን እንዳቀረበ የቢራ ፋብሪካው ሃላፊ ተናግረዋል። ቢራ ፋብሪካው የአርቲስቱን አቋም በመስማት፤ አርማው ከሲዲዎች ላይ እንዲሰረዝ መፍቀዱን የገለፁት የፋብሪካው ሃላፊ፤ አዲካ ሶስት መቶ ሰራተኞችን በመቅጠር የሜታ አቦ አርማ ከሲዲው ላይ በፓርከር እንዲጠፋ ማድረጉን ተናግረዋል።
ስንት ታተመ? ስንት ተሰራጨ?
በእያንዳንዱ ሲዲ ላይ መለያ ቁጥር እንዲሰፍር የተደረገው፤ ስንት ሲዲ እንደታተመ ለመቆጣጠር ታስቦ ነው የሚለው ቴዲ አፍሮ፤ በሲዲው ላይ መስፈር የነበረበት መለያ ቁጥር 120ሺ ሲዲ ላይ ታትሞ መቋረጡን ተቃውሟል።የመለያ ቁጥር በሲዲው ላይ እንዲሰፍር የተደረገው፤ የህትመት ብዛት ለመቆጣጠር ሳይሆን፤ ኦርጂናል ሲዲ ለሚገዙ ደንበኞች በእጣ ለመሸለም ታስቦ እንደሆነ አዲካ ገልጿል። ከተወሰነ ህትመት በኋላ የመለያው ቁጥር ለምን እንደተተወ ተጠይቆም፤ በጊዜ መጣበብ የተነሳ ከብሄራዊ ሎተሪ ፈቃድ ማግኘት ባለመቻሉ፤ የእጣ ሽልማቱ ስለቀረ ነው ብሏል – አዲካ። የማስተር ሲዲ ርክክብ እንደተጓተተ የገለፀው አዲካ፤ 500ሺ ኮፒ በስምንት ቀን ውስጥ አሳትሞ ለገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ ችግር ገጥሞት እንደነበር ይጠቅሳል።
የሲዲውን ሽፋን ካተሙት ድርጅቶች አንዱ ሀምራዊ ፕሪንተርስ ሲሆን፤ የድርጅቱ ባለቤት አቶ ተከስተ አብርሃ፤ የሲዲ ሽፋን፣ የግጥሞች፤ የፍላየር እንዲሁም የፖስተር ህትመት እንዳከናወኑ ገልፀው፤ መለያ ቁጥር የሰፈረበት የሲዲ ሽፋን እኛ ጋ ታትሟል ብለዋል። ከአከፋፋዮች አንዱ የሆነው ጣና ኢንተርቴይመንት በበኩል፤ ሲዲው በተባለለት ቀን ለአከፋፋዮች አለመድረሱ ችግር እንደፈጠረበትና ከተገመተው በታች እንደተሸጠ ተናግሯል። ቢሆንም ግን፤ የቴዲ አፍሮ ሲዲ በአገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ገበያ እንዳገኘ ጣና ኢንተርቴይመንት ገልፆ፤ ከ116ሺ በላይ ካሴትና ሲዲ ከአዲካ እንደተረከበ አስታውቋል፡፡
100ሺህ ሲዲና ካሴት ከአዲካ እንደወሰደ የሚገልፀው አምባሰል ሙዚቃ ቤት፤በአዲካ ከተጠቀሰው የካሴትና የሲዲ ህትመት ወጪ ሌላ አለመታተሙንና አለመሠራጨቱን ተናግሯል፡፡
ጣናንና አምባሰልን ጨምሮ ሶስት ሙዚቃ ቤቶች አልበሙን በአከፋፋይነት እንደተረከቡ የታወቀ ሲሆን፤ ከእነዚህ አንዱ የሆነው ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት 70ሺህ ካሴትና ሲዲ መውሰዱን ምንጮች ይናገራሉ፡፡
የኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሃይላይ ታደሰ በበኩላቸው፤ህገወጥ ሲዲ ሲባዛም ሆነ ወደ አገር ሲገባ ቅሬታና ሪፖርት እንደሚደርሳቸው ገልፀው፤ ሆኖም እስካሁን የደረሰን መረጃና ቅሬታ የለም ብለዋል። የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዕቁባይ በርሄ፤ ማህበሩ የደረሰው ቅሬታ ባለመኖሩ አዲካ ህጋዊ ነው ብለን እንቀበላለን ብለዋል።
ቴዲ አፍሮና ማናጀሩ የአዲስ ገሠሠ
አዲስ ገሰሰ የቴዲ አፍሮ ማናጀር በመሆን ለዘጠኝ አመታት እንደሰራ የሚታወቅ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት ከአርቲስቱ ጋር ተለያይተዋል። ጃኖ ባንድ በሚል ስያሜ አዲስ የወጣቶች የሙዚቃ ቡድን ለማቋቋም ለአመት ያህል ሲጥር የቆየው አዲስ ገሰሰ፤ ከቴዲ አፍሮ ቅሬታ እንደቀረበበት ምንጮች የገለፁ ሲሆን፤ ለጃኖ ባንድ እንጂ ለኔ በቂ ትኩረት አትሰጥም በሚል አሰናብቶታል ብለዋል።
አዲስ ገሠሠ በበኩሉ ስለ ጉዳዩ ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፤ ስለ ችግሩ መናገር ቢቻልም፤ ዋናው ነገር ኢትዮጵያዊው ወንድሜ ቴዲ፣ ልጄም በመሆኑ መልካሙን ሁሉ እንዲገጥመው በሙሉ ልቤ ሁሌም እመኛለሁ
ብሏል፡
ሽምግልና
የሁለቱ ወገኖች የአዲካና የቴዲ አፍሮ ጉዳይ፤ ወደ ሽምግልና እንዳመራ ታውቋል። በሽምግልናው እየጣርኩ ነው የሚለው አዲካ፤ እስካሁን ግን የተገኘ ውጤት የለም
ብሏል። “እውነት ነፃ ያወጣል፤ ቴዲም የሚለው ነው” በማለት የገለፀው አዲካ፤ ለመስማማትና ለመነጋገር ፍቃደኞች ነን፤ የተቻለንን
ያህል ጊዜ እንጠብቃለን ብሏል፡፡
ጉዳዩ በሽምግልና እንደተያዘ የገለፁት የቴዲ አፍሮ ተወካይ፤ በሽምግልና ላይ ስለሆንን ለጊዜው ምንም መልስ መስጠት አንችልም ብለዋል።
Filed in: Amharic Posts

No comments:

Post a Comment