"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Wednesday 10 October 2012

በለገጣፎ ገሃነምና ገነት አየሁ! “በኔ ዘመን የኦሮሞ ልጆች እንዳይታሰሩ አድርጌያለሁ” ጁነዲን

legetafo 7


“የኦሮሞ እንግዴ ልጅ” በሚል ስያሜ የሚጠራው ኦህዴድ በ1997 መስቀለኛ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። ጥያቄውን ያቀረቡት አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ አዛውንት ነበሩ። ጥያቄው የቀረበው አዳማ /ናዝሬት/ ቀበሌ 11 አዳራሽ ውስጥ ነበር። ተጠያቂው የወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ሳዶ ሲሆኑ ስብሰባው የተጠራው “ለምን አልመረጣችሁንም” በሚል ኦህዴድ ከህዝብ ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት ታስቦ ነበር።
“ኦነግ ኦሮሞ ነው። እናንተም ኦሮሞ ከሆናችሁ ለምን አንድ አትሆኑም? እናንተ አንድ ብትሆኑ ልጆቻችን አይታሰሩም፣ አይገረፉም፣ አይሰቀሉም፣ የደረሱበት እየጠፋ ሃዘን አንቀመጥም፣ ኦሮሞ እስከመቼ ይታሰራል?” የሚል ጥያቄ ያቀረቡት አባት ንግግራቸውን መጨረስ አልቻሉም ቤቱ በጭብጨባ ተናወጠ።
“በኔ ዘመን የኦሮሞ ልጆች እንዳይታሰሩ አድርጌያለሁ። በድሬዳዋና በቦረና በኩል የገቡትን ኦነጎች ድጎማ በመስጠት አርሰው እንዲበሉ አድርጌያለሁ። አሁን የምትናገሩትን በሙሉ አላውቅም” የሚል መልስ ሲሰጡ ቤቱን ሁከት ሞላው። ስም እየጠቀሱ የታሰሩ፣ የተሰወሩና የተገደሉትን ተሰብሳቢዎቹ በየተራ ተናገሩ። “በሌሊት የማናውቃቸው ሰዎች በራሳችን ወንድሞች እየተመሩ ይበረብሩናል። አሁን እናንተ ለኦሮሞ ትቆረቆራላችሁ?” ጥያቄው ዘነበ። እንደፈለጉ እንዲናገሩ ክፍት በሆነው መድረክ ሙስናም ተነሳ። የአርሶ አደሩ መሬት መቸብቸቡ ተጋለጠ። ለሶላት አንሄድም በማለት አዳራሽ ውስጥ ጸሎታቸውን አድርሰው ጁነዲንን ሞገቱ። ሰሞኑን ይፋ የሆነውን ግምገማና ውሳኔ አስመልክቶ የጎልጉልየአዲስ አበባ ዘጋቢዎች ያነጋገሩዋቸው ወደኋላ ተመልሰው ያነሱት አስተያየት ነበር። “መሬታችሁ አይነካም። ፊንፊኔ መቼም ቢሆን የኛ ናት። ነፍጠኛ የጫነ ሌጣ ፈረስ አትመልከቱ። ሌጣ ሌጣ ነው” ያሉት አቶ ጁነዲን ቀጣዩ እጣቸው ምን ይሆን?

አቶ ጁነዲን ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የኦህዴድ አመራሮች መራገፋቸው እንደማይቀር የሚገልጹት አስተያየት ሰጪዎች የኦህዴድ ካድሬዎችና አመራሮች በወገኖቻቸው ላይ እየፈጸሙ ያለው ወንጀል ባዕድ ከሚፈጽመው በላይ እንደሆነ ይናገራሉ። ስርዓቱ ተጠቅሞባቸው እንደሚጥላቸው እያወቁ ስለምን ወገናቸው ላይ እንዲህ አይነት አስከፊ የተላላኪነት ተግባር ይፈጽማሉ ሲሉ ይጠይቃሉ።
ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ ወጣት የለገጣፎ ነዋሪ አንድ አብይ ማስረጃ ላሳይህ ሲል የጎልጉልን ሪፖርተር እየመራ ወደ ካንትሪ ክለብ ግቢ ወሰደው። ካንትሪ ክለብ በግፍ፣ በሚገርም ክፍያ፣ ያለ በቂ ዝግጅት ከአርሶ አደሩ ላይ የተነጠቀ ሰፊ መሬት ነው።
የካንትሪ ክለብ ዴቨሎፐርስ (COUNTRY CLUB DEVELOPERS P.L.C. – CCD) ድረገጽ እንደሚመሰክረው ሥፍራው ከ160 ሄክታር ወይም 16 ሚሊዮን ካሬ ሜትር አካሎ ይዟል። እያንዳንዱ ቪላ 1000 ካሬ ሜትር ይዞታ ሲኖረው፣ ከ282 እስከ 513 ካሬ ስፋት ባለው ቦታ ላይ ቪላዎቹ ተኝተው ይታያሉ።
ዋናውን መግቢያ እንዳለፉ ኢትዮጵያ ለገጣፎ ውስጥ ስለመገኘትዎ ማረጋገጫ የለዎትም። ቪላዎቹ ከመሬት ብዙም ከፍ ሳይሉ ተንጣለው ሲያዩዋቸው የተሽኮረመሙ ይመስላሉ። እየቀረቡ ሲሄዱ የቤቶቹ ድርድርና አሰራር ያስገርማል። ብዙ ሪል ስቴቶች ቢኖሩም እንደ ካንትሪ ክለብ ያለ አለ ማለት አይቻልም። ፎቅና ምድር ሆነው የተሰሩት ህንጻዎች የሲሚንቶና የድንጋይ ክምር አይመስሉም። መሬቱ የተዋበት ጡብ፣ በየመንገዱ ያሉት መብራቶች፣ የመዳመቂያ እጽዋቶቹ፣ ሳርና የተመረጠ አበባ የለበሰው መስክ ቀልብ ይሰልባል። ያለማገነን በለገጣፎ ገሃነምና ገነትን አይቻለሁ። አገርቤት መሆንዎን የሚያውቁት ባሬላ ተሸክመው ከወዲያ ወዲህ የሚሉትን “ምስኪኖች” ሲመለከቱ ነው።
ወጣቱ በቀስታ እያመለከተ እነዚህ ሁሉ የምታያቸው የቀን ሰራተኞች አብዛኞቹ የመሬቱ ባለቤቶች ነበሩ። አባት፣ እናት፣ ልጅ ቤተሰቦች ንብረታቸው ላይ ተፈርዶባቸው የቀን ሰራተኛ ሆነዋል። ለንብረታቸው የተከፈላቸው ካሳ ተመጣጣኝ ቢሆን ኖሮ እዚህ ጭቃ አያቦኩም ነበር። ወጣቱ አለቀሰ። ቤቶቹ የሚሸጡት ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ነው። እንግዲህ አንድ አባወራ አራት ጥማድ መሬት ከተወሰደበት አራት ቪላ ይሰራበታል ማለት ነው። በአምስት ሚሊዮን ብር ሂሳብ ከሃያ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ግብይት ባንድ አባወራ መሬት ላይ ተፈጽሟል። እንደ ወጣቱ ገለጻ አራት ሄክታር የተወሰደበት አባወራ 120ሺህ የማይሞላ ብር ወስዶ ከጨዋታ ውጪ ይሆናል። እናም ኩሊ ለመሆን ይገደዳል። ይህንን ወንጀል ህዝባቸው ላይ የሚፈጽሙትና “ለምን” ብሎ ሲጠይቅ አስረው የሚገርፉት ኦሮሞዎች ናቸው። እንዲህ ያለው ግፍ የት አገር ተፈጽሟል?
ሶስት ወጣቶች ሆነው ሮፓክ ሪል ስቴት ግቢ ውስጥ ገቡ። ሮፓክ “ያለ እረፍት ለአገርና ለህዝብ ሲባትቱ ኖረው ተሰው የሚባሉት ሟቹ ጠ/ሚኒስትር” ወንድም ንብረት እንደሆነ ከወሬ በላይ ነው። ወጣቶቹ ይህም ቦታ በግፍ ያለ ተመጣጣኝ ክፍያ የተወሰደ የአርሶ አደር አባቶቻቸው ንብረት ነው። አንደኛው “ልማት መልካም ነገር ነው። ቦታው ለምቶ ከተማዋ ማደጓ ደስ ይላል። እድገቱ አንዱን እየገደለ መሆኑ ግን ትርጉሙ ሌላ ነው። አንዱ ደጅ እያደረ፣ ሌላው በሞቀ ቪላ የሚኖረው እስከመቼ ነው?” ሲል በንዴት ጠየቀ። አያይዞም ሰሞኑን በለገጣፎ የተነሳው ተቃውሞና እስር የአንድ ቀን ሳይሆን የቆየ ችግርና ብሶት ውጤት መሆኑንን አስረዳ።
ለገጣፎ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ከተሞች አርሶ አደሩ በሳንቲም ቤት የሚሰላ ካሳ እየተከፈለው ለልመና ተዳርጓል። ከከንቲባዎችና ከኦሮሚያ ባለስልጣናት ጋር በመሻረክ መሬት ንግድ ውስጥ የዋኙ ወደፊት የሚመጣው ችግር ሊታያቸው አልቻለም። ወጣቶቹ እንደሚሉት ከመሬት ንጥቂያና በቂ ካሳ ካለማግኘት ጋር በተያያዘ ገምጋሚም ተገምጋሚም የለም። ስለዚህ ህዝብ ፍርድ የሚሰጥበት ቀን ተቃርቧል። የሚያሳዝኑት የለፉበትን ሃብት አሟጠው “ማረፊያና መጦሪያ ገዛን” የሚሉት ናቸው።
በካንትሪ ክለብ መግቢያ ዋና የጥበቃ ማማ በር ፊትለፊት በተሰሩ የሳጠራ ታዛዎች ውስጥ ሽልጦ እየገመጡ የሚታዩት የቀን ሰራተኞች ዛሬ ርስት የላቸውም። አርሶ መሰብሰብ አቁመዋል። የተሰጣቸውን ገንዘብ አራግፈው በቀን ስራ መተዳደር እድላቸው ሆኗል። የጎልጉል ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ አዛውንት “ሲያልቅ አያምር አሉና” ዝም አሉ።
ዋናው ጉዳይ ይህንን ውሳኔ ማን ወሰነ የሚለው ነው። አቶ ጁነዲን በቀጥታ ትዕዛዝ ካላይ የተጠቀሰው መጠን ያለው መሬት ለካንትሪ ክለብ እንዲሰጥ ማዘዛቸውን ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። ማዘዛቸው ብቻ ሳይሆን ለመሬቱ እንዲሰጥ የወሰኑት ካሳ በሳንቲም ቤት በካሬ መሆኑ ባለንብረቶቹን እስካሁን የሚያቃጥል ጉዳይ ነው። ከሁሉም በላይ የሚያንገበግበው ደግሞ አቶ ጁነዲን በስጦታ መልክ አንድ ቪላ ተበርክቶላቸዋል መባሉና “መነ ሞቲ” የሚል ቅጽል ስም የተሰጠውን ቪላ ሁሉም ማወቃቸው ነው። የጎልጉል ዘጋቢ ቤቱን ቢመለከተውም ቤቱ የአቶ ጁነዲን ስለመሆኑ በማስረጃ የቀረበ ማረጋገጫ አላየም።
ክሊኒክ፣ ሱፐር ማርኬት፣ መዋዕለ ህጻናት፣ ትምህርት ቤት፣ ቤተ መጽሃፍት፣ ጅምናዚየም፣ የጎልፍ ሜዳ፣ መዋኛ፣ የቴኒስ መጫወቻ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የጤና ማዕከል፣ የተለያዩ የህዝብ መገልገያዎች ያሉት የካንትሪ ክለብ መኖሪያ መንደር ማዳበሪያ የማይነካው አትክልት ማዘጋጃ ቦታም አለው። በአዲስ አበባና በክልል የተመረጡ ባላብቶችና ታዋቂ አትሌቶች፣ባለስልጣናትና የዘመኑ ነገስታቶች የተሰገሰጉበት የካንትሪ ክለብ በዋና ባለቤትነት የሚያንቀሳቅሱት የአቶ መለስ አማካሪ መሃንዲስ ናቸው። ሸሪካቸው አንድ በመንገድ ስራ የተሰማራ መሬት ደላላና ኮንትራክተር እንደሆነም ለማወቅ ተችላል።
ለነዋሪዎቹ ሁሉን አሟልቶ ለማቅረብ በ1998 ዓም የተቋቋመው ካንትሪ ክለብ ለወሰደው መሬት በአግባቡ ካሳ ተከፍሎ የተሰራ ከተማ ቢሆን ኖሮ ያሰኛል። አንድ ሺህ የተለያዩ ቅርጽ ያላቸው ቪላዎችና ዘመናዊ ህንጻዎች የያዘው የመኖሪያ መንደር በርካታ የራባቸው በየቀኑ ጥርስ ይነክሱበታል። በመሬት ንግድ የጠገቡ ባለስልጣናት መጨረሻ ላይ የመደብ ትግል ውስጥ ገብተዋል። በመደብ ትግሉ ጅማሬ ለጊዜው አቶ ጁነዲን ግንባር ይሁኑ እንጂ የሚከተሉዋቸው እንዳሉ አንዳንድ መረጃዎች እየወጡ ነው።

ጁነዲን ሳዶ
በሃይማኖት ጣጣ፣ በሙስናና፣ በፖለቲካ የሃይል አሰላለፍ እየተናጠ ያለው ኦህዴድና አመራሮቹ ህወሓት ከጀመረው የማጥራት ዘመቻ አስመልክቶ ሪፖርተር ጋዜጣ አቶ ጁነዲን ከኦህዴድ ድርጅት አባልነታቸው ስለመባረራቸው ምንጮቹን ጠቅሶ ከመዘገቡ ውጪ በይፋ የገለጸ መንግስታዊ ተቋም የለም። ጎልጉል ኦህዴድ በመደብ ትግል መጫረስ ጀምሯል በሚል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ክፍል አነጋግሮ ባስነበበው ዜና የኦህዴድ ግምገማ ሲጠናቀቅ ከሃይማኖትና ከሙስና ጋር በተያያዘ የተገመገሙ ስለመኖራቸው፣ አቶ ጁነዲን በግምገማው ቀዳሚ እንደሚሆኑ ጠቅሰን ዘግበን ነበር።
መሬታቸው ያለ በቂ ካሳ ክፍያ መወሰዱ ሲብስባቸው ተቃውሞ ካሰሙት መካካል ታስረው የነበሩት ሰባት የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ዋስ ጠርተው እንዲለቀቁ መደረጋቸውን ፖሊስ “ህዝብን ለጸረ ልማት በማነሳሳት” ወንጀል ክስ መስርቶባቸው እንደነበር የአሜሪካ ሬዲዮ አማርኛ ክፍል ሰኞ መስከረም 28 ቀን ተናግሯል።
በተያያዘ ዜና በህመም ምክንያት የሥራ መልቀቂያ አስገብተዋል የሚባሉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳ

አለማየሁ አቶምሳ
ኦህዴድን አስመለክተው ማስተባበያ ሰጥተዋል። በቴሌቪዥን ባርኔጣ ለብሰው የቀረቡት አቶ አለማየሁ፣ ኦህዴድ እንደተዳከመ የሚናፈሰው አሉባልታ ከእውነት የራቀ መሆኑንን ካስታወቁ በኋላ “ከድርጅታችን ዓላማ ውጪ ሲንቀሳቀስ የነበረ አንድ አባል አግደናል” ብለዋል። አሉባልታ ስላሉት ግን ማብራሪያ አልሰጡም። ኦህዴድ ራሱን መገምገሙን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ የቀጣዩን ዓመት በጀት በማጽደቅ በቆራጥነት ለመስራት ከስምምነት መደረሱን ተናግረዋል። እሳቸው ይህንን ይበሉ እንጂ ኦህዴድ ውስጥ የተፈጠረው አለመግባባት እታች ቀበሌ ድረስ መዝለቁን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ።

No comments:

Post a Comment