የወላዲተ አምላክ ድንቅ ተአም
)፡- ዛሬ ፃድቃኔ ማርያም ሄጄ በአይኔ ያየሁትን ተአምር ልፅፍላችሁ ወደድኩኝ፡፡ ቀኑ ቅዳሜ ነው ፤ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ወደ ፃድቃኔ ለመሄድ የሚነሱበት ቀን ስለሆነ መጀመሪያ የሚወጣው አውቶቡስ እንዳያመልጠን ከባለቤቴ ጋር በጠዋት ነበር አውቶቡስ ተራ የደረስነው ፤ ነገር ግን ሰው እዛ ያደረ ይመስል 12፡00 ላይ አውቶቡሱ ሞልቶ መንቀሳቀስ ጀምሮ ነበር፡፡ ባለቤቴም ‹‹አይ በዚህም ሰዓት ደርሰን አመለጠን ይገርማል ተወው ባክህ እመቤቴ እንደፈቀደች››አለችኝና ሁለተኛው አውቶቡስ ላይ ገባን፡፡ ይህኛው ደግሞ ቀጥታ ዘላቂ ሰው ስላጣ የመንገድ ሰዎችንም በመጫን ነበር የሞላው፡፡ ጉዞ ወደ ፃድቃኔ ማርያም ፤ ውዳሴዋን ደግመን ጉዞ ጀመርን፡፡ መኪናው ሲያወርድ ፤ ሲጭን 9፡00 አካባቢ ደብረ ምጥማቅ ደረስን ፤ እዚህ እንውረድና በአቋራጭ እንሂድ ተባብለን ሰላ ድንጋይ ሳንደርስ ወረድን ፡፡ እቃችንን ለአንድ የሀገሬው ሰው አሸክመን አቋራጩን ተያያዝነው ፡፡ ልጁ እንዲህ አለን ‹‹ ዛሬ ግን ማደሪያ የምታገኙ አይመስለኝም በጣም ብዙ ሰው ነው የመጣው አለን›› :: ‹‹ችግር የለውም ውጪ አንጥፈን እናርፋለን ለመተኛት መች መጣን››አልነው፡፡
ደጇን ስንረግጥ ልጁ ያለው አልቀረ የወንዶች ማረፊያ ሁለቱም አዳራሽ ከአፍ እስከ ገደቡ ሞልቷል ፤ በረንዳውን ላይ ብናይ የበረንዳው ይብሳል ፡፡ የኔን ማረፊያ ውጭ አነንጠፍንና የእሷን ለማየት ወደ ሴቶች ማረፊያ እያቀናን ሳለ ፤ አንዲት መንፈስ ያደረባት ሴት ፤ እጇም እግሯም በሰንሰለት ታስራ እንዲ እያለች የእመቤታችንን ማዳን ትመሰክራለች ‹‹ ዛሬ ደግሞ ኪዳነምህረት ድንቅ ነገር ሰርታለች ሂዱነና እዩ›› እያለች ለሰዎች ስትናገር እንደ አጋጣሚ እኔም ሰማሁ፡፡ እሷ የጠቆመችን ቦታ ላይ ስንሄድ አንዲት የ12 ዓመት ህፃን ልጅ እና እህትየዋ አንድ ላይ ቆመው ተመለከትን ፡፡ ጠጋ ብለን ምን ተደርጎላቸው ነው ስል ስጠይቅ ‹‹ የዚች ህፃን አይኗ በራላት›› ሲሉ ነገሩን፡፡ ለኔ የተደረገልኝን ያህል ደነገጥኩኝ፤ በጣምም ደስ አኘኝ፡፡ እህትየዋ የምትይዘውን የምትጨብጠውን ነገር አጥታ ነበር ፡፡ ታናሽ እህቷ የተደረገላትን ነገር እያየች ከአእምሮዋ በላይ ስለሆነ እና ደስታው ፈንቅሏት ታለቅሳለች ፤ እኛም ገርሞን ማደሪያችንን ትተን ልጅቷ ጋር ረዥም ደቂቃዎች ስለሁኔታ ለመስማት እዛው አረፍ አልን ፡፡ እህትየዋም ሰዎች ጥያቄዎችን ሲጠይቋት እንዲህ አለች ፡-
‹‹ ቤት ውስጥ ከእኩያዎቿ ጋር ስትጫወት የበረንዳ ብረት አይኗን መታት ፤ ለጊዜው ከማበጥ ውጪ ምንም አልሆነም ነበር ፤ ነገር ግን በጊዜ ሂደት አይኗ እያበጠ መጣ ፤ እይታዋንም ጋረዳት ፤ ትምህርቷንም አቋርጣ ለ6ወር ያህል ህክምና ፍለጋ አሉ የተባሉ የአይን ስፔሻሊስቶች ጋር ብራችንን አውጥተን ሄድን ፤ መፍትሄ ግን ሊመጣ የልጅቷም አይን ማየት ግን አልቻለም ፤ ቤተሰባችን ጭንቅ ውስጥ ገባ ፤ በመጨረሻ እመቤቴ እንዳደረገች ታድርጋት ብይ እዚህ ይዣት መጣሁ ዛሬ ሶስተኛ ቀናችን ነው ፤ ለሶስት ቀን ያህል ፤ ጠዋት ተሸክሜአት ጸበል እወስዳታለሁ ፤ እምነቱን ከፀበል ጋር ደባልቄ አይኗ ዙሪያው ላይ እቀባታለሁ ፤ ይህው እናንተ እንደምታዩት እግዚአብሄር ፈቅዶ ዛሬ አይኗ ሊያይ ችሏል›› ብላ ለቅሶ፡፡
‹‹ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው›› ዮሀንስ ራዕይ 15 3-4 ፤ ‹‹ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነች፥ ለዓይናችንም ድንቅ ናት።›› መዝሙረ ዳዊት118፥23 ከማለት ውጪ ሌላ ምን ይባላል፡፡አምኖ የመጣ እንዲህ ይደረግለታል ፤ ብዙዎቻችን ግን እግዚአብሔር ቤት ስንሄድ በሁለት ልብ ሆነን ነው ፤ ስንመለስም ከሁለት ያጣ የምንሆነው ለዚህ ይመስለኛል፡፡
ያየነውን ነገር ማመን እስኪያቅተን ድረስ እየተገረምን ማረፊያ ፍለጋ ስንንቀሳቀስ ሰዎች ተሰብስበው አየን ፡፡ ሁሌ ማታ 11፡00 ላይ በወንዶች ማረፊያ አካባቢ እና በሴቶች ማረፊያ አካባቢ አዲስ ለመጡ ሰዎች የቦታውን ስርዓት ፤ ምን እንደሚደረግ ፤ ምንስ እንደማይደረግ አባቶች ለ30 ደቂቃ ያህል ያስረዳሉ፡፡ ጠጋ ስንል ተረኛው አባት እንዲህ ሲሉ ነገሩን፡-
እኛ እንኳን ለ3 ቀን ነው የመጣነው ገዳም ውስጥ የሚኖሩ መነኮሳት ይህን ሁሉ ችለው ነው የሚኖሩት? ይገርማል ፤ እግዚአብሔርም አለምን ትተው እሱን ብለው የመጡትን ያስችላቸዋል:: በመጨረሻም ፀሎት አድርገውልን ወደ ማደሪያችን ሸኙን፡፡ ይህን ስመለከት ብዙ ቦታዎች ስንሄድ የቦታውን ስርዓት ሳናውቅ የምናጠፋ ሰዎች እንበዛለን ፤ ልክ እንደ ፃድቃኔ ማርያም ገዳም ቀን በቀን ሳይሰለቹ እንደዚህ አይነት ነገሮች ሁሉም ቦታ ቢለመድ ጥሩ የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡
‹‹ ይህውላችሁ ልጆች ሀገር አቋርጣችሁ ከተለያየ ቦታ እዚ የመጣችሁት እናንተ ፈልጋችሁ ብቻ አይደለም ፤ እግዚአብሔርም ፈቅዶላችሁ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ እሱ ፈቅዶ እና ወዶ እስካመጣችሁ ድረስ የመጣችሁበትን አላማ የሚያስተጓጉል አንዳች ነገር ማድረግ የለባችሁም ፤ ይህ ቦታ የምህላ ፤ የፀሎት ፤ የሱባኤ ቦታ ነው ፤ እዚህ ቦታ ላይ ከእናንተ የሚጠበቅባችሁ ነገር አለ እርሱም ፡- ወደ ገዳም ስትወርዱ ጫማችሁን አድርጋችሁ መግባት አይቻልም ፤ ሴቶችም ወንዶችም በገዳም ውስጥ ስትመላለሱ ክርስትያናዊ አለባበስ መልበስ አለባችሁ ፤ በማደሪያችሁም ሆነ ገዳም ስትወርዱ ጮክ ብሎ መነጋገር አይቻልም ፤ ብዙ ሰዎች አርምሞ ስለሚይዙ እነሱንም መረበሽ ስለሆነ ይህ አጥብቆ የተከለከለ ነው ፤ የቻለ በቀን ሰባት ጊዜ ፀሎት ማድረስ አለበት፤ ካልቻለህ ግን ሶስቱን ጸሎት ማስተጓጎል የለበትም ፤ ከሰኞ እስከ አርብ ድረስ በሽተኛ ካልሆነ በቀር ምግብ 12 ሰዓት ላይ ነው መብላት የሚቻለው እስከዚያ ሁሌ ጾም ነው(ከበዓለ 50 በቀረ) ፤ የተፈቀዱት ምግቦች ቆሎ ፤ባቄላ ፤ ጥጥሬዎች እና በሶ ከሰኞ እስከ አርብ ሲሆን ቅዳሜ እና እሁድ ዳቦ መብላት ይፈቀዳል ፤ እንጀራ እና ወጥ ገዳም ውስጥ ባላችሁበት ጊዜ መብላት አይቻልም ፤ ጸበል ጠዋ በ11 ይከፈታል ከዚያ በፊት ጸበል መውረድ አይቻልም እስከ ሰባትም ስንትም ሰዓት ይቆያል ፤ እዚህ ቦታ ላይ በዓመት 1ጊዜ ብቻ ነው ቅዳሴ ያለው ፤ ጠዋት ሊነጋ ሲል 11 ሰዓት ላይ ኪዳን ማድረስ ፤ ሲነጋ ትምህርተ ወንጌል መሳተፍ ፤ከ ሰዓት ከ9፡40 ጀምሮ ምህላ ማድረስ አለባችሁ የዛኔ ነው የመጣችሁበትን አላማ እና እናንተ የምትገናኙት ›› እያሉ ብዙ ነገር ነገሩን መከሩን፡፡
እኛ እንኳን ለ3 ቀን ነው የመጣነው ገዳም ውስጥ የሚኖሩ መነኮሳት ይህን ሁሉ ችለው ነው የሚኖሩት? ይገርማል ፤ እግዚአብሔርም አለምን ትተው እሱን ብለው የመጡትን ያስችላቸዋል:: በመጨረሻም ፀሎት አድርገውልን ወደ ማደሪያችን ሸኙን፡፡ ይህን ስመለከት ብዙ ቦታዎች ስንሄድ የቦታውን ስርዓት ሳናውቅ የምናጠፋ ሰዎች እንበዛለን ፤ ልክ እንደ ፃድቃኔ ማርያም ገዳም ቀን በቀን ሳይሰለቹ እንደዚህ አይነት ነገሮች ሁሉም ቦታ ቢለመድ ጥሩ የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡
የሚቀጥለው ቀን ጠዋት
ለሊት ኪዳን አድርሰን ወረፋው እንዳይበዛ ፀበል ወረድን ፤ ፀበል ተጠምቀን ስናበቃ ለመጠጣት አንዱ ልጅ ጋር ጠጋ ብዬ ቁጭ አልኩ ፤ ጎንበስ ብዬ ሳየው አንዳች ነገር ጉልበቱ ላይ ትልቅ እጢ ቋጥሮ ተመለከትኩኝ ፤‹‹ወንድሜ ምን ሆነህ ነው›› አልኩት፡፡ እሱም ‹‹ ተወኝ ባክህ ልቤ ደንድኖ አልሰማ ብዬ ነው እንዲ የሆንኩት አለኝ››፡፡ አልገባኝም አልኩት ‹‹ሰው ንስሀ ገብቶ ወደ በፊቱ ምግባሩ ከተመለሰ የባሰውን ነው የሚሸከመው አለኝ›› ይባስ ግራ አጋባኝ፡፡ ቀስ ብለህ ልታስረዳኝ ትችላለህ አልኩት፡፡ እርሱም፡-
‹‹ ትውልዴ አዲስ አበባ ነው የ22 አካባቢ ልጅ ነኝ ፡፡ይህውልህ የዛሬ 2 ዓመት በፊት እጠጣለሁ ፤አጨሳለሁ ፤ እጨፍራለሁ ብቻ ምንም ከሀጢያት የቀረኝ ነገር የለም ሁሉን አደርጋለሁ ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለሁ የዚያን ጊዜ ጉልበቴ ላይ ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ በልክ ትልቅ እጢ ወጣብኝ ፤ ብዙ ቦታ ብሄድ ኦፕራሲዮን መሆንን ነበር እንደ መፍትሄ ያስቀመጡልኝ ፤ እሱን ደግሞ እኔ አልፈልገውም ፡፡ እናቴ እስኪ ፃድቃኔ ሂድ አለችኝ ፤ ‹‹ምን ማለትሽ ነው ዶክተሮች ኦፕራሲዮን እያሉ እዛ ምን ልሰራ ነው የምሄደው›› ብዬ ከእሷ ጋር ተጣላን ፤ ውዬ አድሬ ሳስበው መሄድ እንዳለብኝ ውስጤ ነገረኝ ፡፡ ከአዲስ አበባ ተነስቼ በሶ እና ቆሎ ብቻ በመያዘ ቀጥታ እዚህ ቦታ መጣሁ ፤ አንድን አባት አግኝቼ ችግሬን ስነግራቸው በደንብ አደመጡኝና ‹‹በል አሁን ጸበል እንዳትጀምር ፤ ንስሀ ግባ፤ ቀኖናህን ስትጨርስ መጠመቅ ትችላለህ›› አሉኝ፡፡ እሺ ብዬ ንስሀዬን ከራሴ ላይ አወረድኩኝ ፤ ቀኖናዬን ጨረስኩ ፤ከዚያ ጸበል መጠመቅ ስጀምር ሰዎች እምነት ሲቀቡ ተመለከትኩኝ ፤ ለምን እኔስ አልቀባም ብዬ ጸበሉን ከእምነት ጋር እየደባለኩ ቁስሉን መቀባት በጀመርኩኝ በሶስተኛው ቀን ተሸክሜ የመጣሁትን እጢ በመግል መልክ ከሰውነቴ ወጥቶ አለቀ ፤ ተሸሎኝ ወደቤቴ ስመለስ እማዬ ስታየኝ ማመን አልቻለችም ነበር ፤ አለቀሰች ፤ እመቤቴን ወላዲተ አምላክን ማመስገኛ ቃላት አጣች ፤ እኔም ለአንድ ዓመት ያህል ከቤተክርስትያን አልራኩም ነበር ፡፡ የሆነ ጊዜ ላይ ግን ከቤቱ ጠፋሁ ፤ ወደ ቀደመ ምግባሬ ቀስ እያልኩ ገባሁበት ፤ የተደረገልኝን ነገር ዘነጋሁ ፤ ይህው አሁን ደግሜ የዛሬ ሁለት ዓመት ይዥው የመጣሁትን እጢ አሁን ተመልሶ መጣብኝ ›› ብሎ ሲነግረኝ ሰውነቴን አንዳች ነገር አራደኝ፡፡
ስንቶቻችን ነን ገብተን የወጣን ፤ ውለታውን የዘነጋን ፤ የተደረገልንን ነገር የረሳን ፤ ከሞት አፋፍ ከጠላት ወጥመድ ጠብቆ አሳልፎን ዛሬ ላይ ከቤቱ ሸርተት ያልን? ቤት ይቁጠረው ፡፡ እኔ አይኔ የልጁ እጢ ላይ ነው ፤ ልጁ ደግሞ አይኑ እኔ ላይ ነው ፡፡ ‹‹ አሁን አኮ ቀንሶ ነው ያየህው›› አለኝ ፡፡ ‹‹ሳይቀንስ ባየው የቱን ያህል ነበር?›› ብዬ ራሴን ጠየኩኝ፡፡እንዲህ ሲል ቀጠለልኝ ‹‹ ትላንት ምልክት አይቻለሁ በጥቂት ቀናት ውስጥ አፍስሳ ትጨርስልኛለች ፤ በአውራ ጣቴ በኩል በቢጫ ፈሳሽ መልክ ትንሽ ትንሽ ሲወጣ ተመልክቻለሁ ፤ ከአሁን በኋላ ግን ወደ በፊቱ ማንነቴ እንዳልመለስ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ ፤ እርግጠኛ ነኝ አሁን እድናለሁ አለኝ፡፡›› የልጁ እምነት ገረመኝ፡፡ ስንቶቻችን ነን አፋችንን ሞልተን በእምነት ‹‹እድናለሁ›› ማለት የምንችል ፤ እንዲህ ለማለትም ፍጹም እምነት ያስፈልጋል፡፡ የመጣሁበትን ጉዳዬ እረስቼ ቁጭ ብለን ስለራሱ ፤ አዛው ቦታ ላይ ስላየው ተዓምር ሲነግረኝ ሰዓቱ መዝለቁን አላስተዋልኩም ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ‹‹በል እመብርሀን ወላዲተ አምላክ ትርዳህ ፤እግዚአብሔር በምህረቱ ይጎብኝህ››ብዬው ወደ ማረፊያየ ለመሄድ ብድግ አልኩ ፡፡መሬት መሬት አቀርቅሬ ፤ የነገረኝን ታሪክ ከራሴ ጋር እያቆራኝውት እንደ ውሻ የተፋሁትን ነገር ደግሜ የላስኩበትን ሁኔታዎች ሳወጣ ሳወርድ ምንም ሳላውቀው ማረፊያዬ ጋር ደረስኩኝ፡፡
ኡራኤል ቤተክርስትያ
ከወራት በፊት ነው አዲስ አበባ ኡራኤል እለቱ እሁድ ፤ ቀኑ ደግሞ 22 ላይ ውሎ ለማስቀደስ ወደዚያው አቀናሁ፡፡ ሁሉም ነገር ደስ በሚል ሁኔታ ተጠናቅቆ ወደ ቤት ለመሄድ እግሬን ሳነሳ ፤ ቆይ አንድ ጊዜ ዛሬ ድንቅ ተዓምር ትሰማላችሁ ትንሽ ቆዩ አሉን ፡፡ ለመሄድ የተነሳሁት ልጅ ደግሜ ቁጭ አልኩ፡፡
ልጅቷ ከሲሜሲ አካባቢ ሰው እየመራት ነበር ቅዳሴ ለማቀደስ ኡራኤል የተገኝችው ፡፡ ቅዳሴ አልቆ ጸሎት አድርሳ የቅዳሴ ፀበል ለመጠጣት ትፈልግና ትሄዳለች ፤ እግዚአብሔር ፈቅዶ የቅዳሴ ጸበል በጠጣች ፤ ፊቷን አይኗን በደባበሰች ፤ በጥቂት ደቂቃ ውስጥ የአይን ብርሀኗ መመለሱን ሲነግሩን ‹‹ ስራህ ድንቅ ነው›› ከማለት ውጪ አሁንም ዝምታን ነበር የመረጥኩት፡፡ ሰው እየመራ የመጣችው ልጅ እያየች ወደቤቷ ልትመለስ ችላለች ፤ በማታው ጉባኤ ላይ አንደምትገኝ እና ተዓምራቱን ለሰዎች እንደምትመሰክር ቃል ገብታ ወደ ቤቷ እያየች ተመልሳለች፡፡ለካ ይህ ልታሰማኝ ኖሯል 4 ታክሲ አቋርጠር ያመጣህኝ ብዬ እኔም ወደቤቴ ሄድኩኝ፡፡
ሌሎችን ያየሁትን ተአምራት በሌላ ጊዜ እናንተ ጋር ለማድረስ ቃል እገባለሁ
‹‹ስራህ ድንቅ ነው በሉት››
ቸር ሰንብቱ
‹‹እግዚአብሔር ቤተክርስትያናችንን ይጠብቅ››
No comments:
Post a Comment