"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Friday 18 May 2012

ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት


ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት

ተላከ፤ ከአራዳ ልጆች
                              አቅራቢ፤ መስፍን ማሞ ተሰማ
ቀዳሚ፤ ይድረስ ለዲበኩሉ!
ወዳጃችን ዲበ! ለጤናህ እንደምን አለህልን? እንዲያው ለመሆኑ እንዲያው ለነገሩ፤ ምነው
ድምፅህ ጠፋ ከቀዬው ካገሩ? ምነዋ ራቀን የደብዳቤህ ትሩፋቱ፤ የፈረንጅ ሀገር ሁሉ ወጉ?
እዚህ በጦቢያችን እዚህ በቀያችን ወዳጅ ሲጠፋ፤ ድምፁ አልሰማ ሲል - ምነው የበላው
ጅብ አልጮህ አለ? ይባል ነበር። እንግዲህ ነበር ነው። ድሮ።
  ዛሬ ዘመንማ እንኳን ጅብ የሚኖርበት ጫካ እንኳን የሚመሽግበት ጎሬ ኖሮት ሰው ሊበላ
ቀርቶ እኛም መኖሪያ አጥተናል፤ ወንድምአለም። እና ይኸውልህ ዛሬ ዘመን ወዳጅ ጓደኛ
ዘመድ አዝማድ ድንገት ድምፁ እልም ድርግም ካለ፤ ሲጠሩት ካልሰማ፤ ሲፈልጉት
ካልተገኘ - ወይ ቃሊቲ ወርዷል፤ ወይ ሰፈራ ተጭኗል፤ ወይ ‘በድንገተኛ አደጋ’ በመኪና
አስገጭተው አልያም በዱርዬ አስደብድበው ተቀጥፏል፤ ካልሆነም ተሰዷል።
  እና ዲበ! ሰው ሲጠፋ ዛሬ ዘመን - ሰው በልቶታል - እንላለን፤ አዲስ ቅኔ ተቀኝተን።
ታዲያ መቼም ‘ሰው በልቶታል’ ማለታችን በዘይቤ መግለጣችን፤ ዕውነትም ‘ሰው በላ’ ዘመን
ውስጥ መኖራችን፤ ነውና ምክንያቱ፤ ሌላም አይደል ዲበኩሉ - የቅኔያችን ትርጉሙ።
  አየህ ዲበ፤ የኛ ኑሮ የኛ ህይወት፤ የኛ ነገር የኛ ሀገር፤ ፖለቲካው ኢኮኖሚው፤ አኗኗሩ
የማህበሩ ቢተነተን ቢዘረዘር፤ ልብ ያደማል፤ ልብ ያደክማል - ዋዛም አይደል። እና ይህን
ያንን አዘግይተን ለሌላ ቀን፤ ሠላም ጤና መሆንህን ሰምተናልና በዚያ ሰሞን በርግብ
መልዕክት ካንተው ቀዬ ካንተው ሀገር፤ እንግዲህስ እንጀምር የደብዳቤያችንን ፍሬ ነገር።
 *             *  *
ወዳጃችን ዲበ፤ ለዚህ መልዕክታችን ጉባኤያችን የተሰየመው ከአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ
ወዲህ ማዶ ከሚገኙት መኖሪያ ቤቶች ባንደኛው ነው። እና የእለቱ ውሎ ይኸውልህ
ተዘርዝሮ።

*             * *
  የቤቱ በር ሁለት ጊዜ በማከታተል ተንኳኳ። ቀጥሎ ፀጥታ። የአምስት ሴኮንድ ፀጥታ።
በድጋሚ አንዴ ኳ! በድጋሚ የአምስት ሴኮንድ ፀጥታ። እትዬ አቻሜ ከተቀመጡበት
ሳይንቀሳቀሱ “ማን ልበል?” አሉ ድምፃቸውን ዘለግ አርገው ሰአታቸውን እየተመለከቱ።
  “ሽኩር ሽቅርቅር” አለ ከውጪ በር አንኳኪው።
  ኒቂሴ በሩን ከፈተች። ሽኩር ገባ። የመጨረሻው ጉባኤተኛ ነበር። ሌሎቻችን ከግማሽ
ሰዓት በፊት ጀምሮ በተለያዩ ደቂቃዎች በተመሳሳይ የበር ማንካኳት ሥነሥርዐት እና
በተለያዩ የመታወቂያ ኮድ ቅጥያዎች ራሳችንን እየገለፅን ተጠናቀን ገብተን ነበር - ከጉባ
ኤው አዳራሽ። እና ሽኩር - የመጨረሻው ዕድምተኛ - ሠላምታ ሰጥቶን ተሰየመ።


እንደዕውነቱ ከሆነና አንተም ያኔ እንደምታውቀው ሽኩር ሽቅርቅር አይደለም።
መሽቀርቀርን አያውቃትም። ልሽቀርቀርም ቢል መሽቀርቀሪያ የለውም። መሽቀርቀሪያ
ቢያገኝም መሽቀርቀር  ለሱ አትሆንም። መሽቀርቀር እሱ ላይ አታምርም። ግን ‘ሽኩር
ሽቅርቅር’ የሚለው መለያው ወደ ጉባኤዎች አዳራሽ የመግቢያ ኮዱ ነው። ሙሉ ስሙንማ
ታውቀዋለህ። እና ለማንኛውም እንደ ያኔው እንደ ድሮው፤ የአራዳ ልጆች አዱ ገነት ላይ
ከያሉበት ተጠራርተው ተገናኝተው ተሰባስበው፤ በነፃነት መወያየት መጨዋወት
አክትማለችና፤ ‘ያልጠረጠረ ተመነጠረ’ ሆኗልና ዘመኑ - ዘመነ ህወሃቱ - ለዚህ ነው
መጠንቀቃችን፤ ምስጢር መግባቢያ መዘየዳችን።
  እና ይኸውልህ ሽኩር ሽቅርቅር እግሮቹን እንደለመደው አጣጥፎ ከእማማ ድንቡሎ ጎን
እንደተቀመጠ ፈረንጅ አምላኩ በሣቅ ታፍኖ አይኑ ፈጦ አፉን በሁለት እጆቹ ግጥም አርጎ፤
ይማፀናል በዐይኑ - እትዬ አቻሜን።
  እኛማ ለምደነዋል። በፊት ነበር፤ ገና ያኔ የኮድ መለያ ስንጀምር፤ “ሽኩር ሽቅርቅር”
የሚለው ኮድ በሽኩር አንደበት ሲነገር፤ በሳቅ ፍርስ ፍርስርስ እንል የነበር። አሁን ግን
ታርቀናል፤ ሽኩር ሽቅርቅርን ለምደናል - ከፈረንጅ አምላኩ በቀር።
  እና ሁኔታውን ያጤኑት እትዬ አቻሜ ፈረንጅ አምላኩን እያስተዋሉ - “ፊትህ አብጧል፤
አይኖችህ ተጎልጉለዋል፤ የታነቅህ ትመስላለህ፤ ተንፍስና ይውጣልህ” አሉት ፈገግ እያሉ።
  የፈረንጅ አምላኩ የታፈነ ሳቅ ፈነዳ። ፍንዳታው ለኛም ተረፈን። ጧ! ብለን ሳቅን
የፈረንጅ አምላኩ ሳቅ እያሳቀን። ሽኩር ሽቅርቅርም ሳቀ - ያቺን ሌባ ጣቱን - እንደ
ኢህአዴጉ መሪ - ፈረንጅ አምላኩ ላይ እየቀሰረ፤ እየወዛወዘ። መቼም ዘንድሮ ሌባ ጣትን
በሆነ ባልሆነው መቀሰር ማወዛወዝ ልማድ ሆኗል። ማጅራት መቺው፤ ኪስ አውላቂው፤ ቁጭ
በሉው…የሀገር መሪው፤ ሰላዩ፤ ካድሬው… ሁሉም ሌባ ጣቱን ይቀስራል ያወዛውዛል
በሌሎች ላይ። ሥራው እያባነነው፤ ሥራው እያስበረገገው። ዛቻ መሆኑ ነው ማስፈራሪያ፤
የሌባ ጣት መለያ። ታዲያ ሌላው ‘ለመለስ ነው እምነግረው፤ ሌባ ጣቱን እማስይዘው’
ይላል ዞር ብሎ፤ ጆሮ ቆራጭ እንዳይቆርጠው ተጠንቅቆ። ይቺ እንግዲህ ሾርኒ ናት።
ዘንድሮ ሾርኒ ሽር ብትን እያለች… ከተማ ገጠሩን ሞልታለች።
  “አንተ መቼም ዕድሜ ጠግበህም አመልህ አይሰክንም” አለ ሽኩር በምናውቃት ቅላፄ -
ፈረንጅ አምላኩን የጎን እያየ።
  “ሽኩር ነፍሴ! ዕድሜ የጠገቡ እነማንን አይተኻል? የኖህ አያት ማቱሳለ እንኳን 969
(ዘጠን መቶ ስልሳ ዘጠኝ) ዓመት ኖሮ እንዴት በጎረምሳነቴ ልሙት? እንዴት በእሳት
ዘመኔ ልቀጠፍ? ብሎ ነበር አሉ። አጋፋሪ እንደሻው ዘ ብሄረ አዲስአባ ይኸው እሰከ ዛሬ
ከአገር አገር እሚንከራተቱት ሞትን ለማምለጥ አይደል? እንግዲህ ሞትን መሸሽ የጀመሩት
በ66 ዓመታቸው ነበር - ያኔ ድሮ። እስቲ አስቡት ዘመኑን፤ ስንትና ስንት ዓመታቸው
ይሆናል አሁን? እና ወንድሜ ሽኩር - ሽኩር ሽቅርቅር - ገና በለጋነቴ በለግላጋነቴ ገና
በአፍላነቴ ዕድሜ ጠግበኻል አትበለኝ፤ አታሟርትብኝ። ይቺ ሌባ ጣትህንም ያዝልኝ።
እምቢ ካልክ ለምነግረው እነግራ” አለ ፈረንጅ አምላኩ እያበራ ፊቱ።
  እትዬ አቻሜ ሳይቀሩ ከልባችን ሳቅን፤ የፈረንጅ አምላኩ ለጋነት ለግላጋነት ፊት
ለፊታችን ተቀምጦ እየታየን።
  ጋብ እንዳለ ሳቃችን፤ ትንፋሻችንን ስንሰበስብ ዙሪያችንን ቃኝቶ “ኮረም ተሟልቷል” አለ
አስተማሪ አለሙ እትዬ አቻሜን እየተመለከተ።  እርግጥ ነው ሁላችንም ተገኝተናል። ኒቂሴ፤ ድንብላል፤ እማማ ድንቡሎ፤ ሽኩር፤
ፈረንጅ አምላኩ፤ ቮልቮ ሳተናው፤ አስተማሪ አለሙ፤ ኢንጂነር ዋቅጅራ እና አድባራችን
አቻሜ። ዘበርጋ ግን አልተገኘም። ቦንድ ሊገዛ ናዝሬት ወርዷል። ታዲያ ቦንዱ ነጋዴው
ኢህአዴግ የሚሸጠው ቦንድ እንዳይመስልህ። ይህኛው ቦንድ ሌላ ነው። የኛ ነው። የኛ
ቦንድ ህብረት ነው። እና ዘበርጋ ቦንድ ሊዘረጋ ነው የወረደው። ሌሎችም አብረውት
ወርደዋል፤ በየአቅጣጫው።
  “እንግዲህማ እንጀምር” አሉ እትዬ አቻሜ የጉባኤያችን አድባር።
በግማሽ ክብ ቅርፅ ከተቀመጥንበት
ሁላችንም ተነሳን። ከፊት ለፊታችን ባለው
                                                                            ግርግዳ ላይ ዕድሜ በጠገበ የነሀስ ክፈፍ ባለው
መስታወት ውስጥ የብፁዕ አባታችን አቡነ
ጴጥሮስ ፎቶ በትልቁ ሆኖ ተሰቅሏል። ከብፁዕ
አባታችን ምስል አናት እመቤታችን ድንግል
ማርያም አንድ ልጇን አማኑኤልን
እንደታቀፈች የያዘው ምስሏ ይገኛል። በብፁዕ
አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ግራና ቀኝ
የመላዕክት አለቃ ሠይፈ ነበልባል ቅዱስ
ገብርኤልና ፈረሰኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ
ከነግርማ ሞገሳቸው ይገኛሉ።
ከፎቶዎቹ ግርጌ አነስተኛ ጠረጴዛ አለ።
ጠረጴዛው የቤተክህነት አልባሳትን ዐይነት
የደመቀ ህብረ ቀለም ያለው ልባስ
ተደርጎበታል። በዚህ ጠረጴዛ ላይ እማማ
ድንቡሎና ኢንጂነር ዋቅጅራ በከፍተኛ
ጥንቃቄና ሥነሥርዐት ሁለት መፃህፍት
አምጥተው አራርቀው አስቀምጠው ወደ
ቦታቸው ተመለሱ። አንደኛው መፅሀፍ
በሰማያዊ ሁለተኛው መፅሀፍ በቢጫ የሀር
ልባሳት ተሸፍነዋል።
  አስተማሪ አለሙና የቴሌኮሙኒኬሽኗ
ኤክስፐርት ኒቂሴ ደግሞ ወርቃማ መልክነት
ባላቸው የዋንጫዎች ቅርፅ ላይ የቆሙ ሁለት ሻማዎችን አምጥተው እንዲሁ በከፍተኛ
ሥነሥርዐት ከብፁዕ አባታችን ግርጌ ከመፃህፍቱ ግራና ቀኝ አስቀምጠው ተመለሱ።
  ሽኩር ነጭ ዳንቴል ከለበሰ አነስተኛ ሙዳይ ውስጥ የተቀመጠ ክብሪት አውጥቶ ሁለቱን
ሻማዎች በርጋታ ለኮሳቸው። ቀጥሎ የክፍሉ መብራት ጠፋ። እትዬ አቻሜ በዝግታ
ተራምደው ከጠረጴዛው ፊት ለፊት ፊታቸውን ወደ አቡነጴጥሮስና ምስሎቹ አድርገው
ተንበረከኩ። እሳቸውን ተከትለን እኛም በያለንበት ተንበረከክን።  እነሆ የመፃህፍቱንም ልባሳት
እትዬ አቻሜ በከፍተኛ ጥንቃቄ ተራ
በተራ ገለጡዋቸው። በመጀመሪያ
የገለጡት በሰማያዊ ሀር የተሸፈነውን
ነው። እሱም ታላቁ መፅሀፍ - መፅሀፍ
ቅዱስ - ነው። ሁለተኛው በቢጫ ሀር
የተሸፈነው ሲሆን እሱም “ታሪካዊ
ተውኔቶች” ፀጋዬ ገብረመድህን
ይላል። በሽፋኑ ላይ የአራት
ኢትዮጵያውያን ምስሎች ይገኛሉ።
አንዱ የብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ
ነው።
  እትዬ አቻሜ አንድ እጃቸውን
በፀጋዬ መፅሀፍ ላይ አሳረፉና
“ባለህበት ካብናቶችህ ጋር አይለይህ”
አሉ በሚተናነቅ ድምፅ። “አሜን”
ስንል ተቀበልናቸው። ቀጠሉና
ታላቁን መፅሀፍ - መፅሀፍ ቅዱስ -
በሁለት እጆቻቸው በዝግታ አንስተው
ተሳለሙ። አሁን ወደ እኛ ዞሩና
መፅሀፉን እንደያዙ በአየር ላይ
የመስቀል ምልክት ሰሩ። በያለንበት
አንገቶቻችንን ደፍተን ተሳለምን። በመቀጠል ፊታቸውን ወደ ብፁዕ አባታችን አቡነ
ጴጥሮስ አዙረው መፅሀፍ ቅዱሱን ከነበረበት በዝግታ መልሰው አስቀመጡ። ቀጥሎ ሁለት
እጆቻቸውን ደረታቸው ላይ አነባበሩና “ልጆቼ ፀሎታችንን እንጀምር” አሉን።
  እነሆ ፀሎተ ጴጥሮስን በአንድ ህብረ ድምፅ በዝግታ ጀመርን።
ፀሎተ ጴጥሮስ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን!
ብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ሆይ!
ስለ እኛ ስለበደለኛና ሀጢያተኛ ልጆችህ፤ ስለ እኛ ወኔያችን ስለከዳን ሀሞታችን ስለፈሰሰ
ለሥጋችን ስላደርን በነፃነታችን ስለነገድን ለሃይማኖታችን ስለታበይን፤ ስለ እኛ ድኩማን
ወገኖችህ ስትል ከኢትዮጵያ አምላክ ታማልደን ዘንዳ እንማፀንሃለን።
አቤቱ ሃዘናችንም ከፍቷል። ሞታችንም በርክቷልና።
አቤቱ በመንፈስ ሁለቴ በሥጋም ደጋግመን ሞተናልና።መስቀሉን በደረታቸው ያንጠለጠሉ መፅሀፉንም በጣቶቻቸው የገለጡ አባቶቻችን
ክደውናልና። ስለ ቃሉ ስለ መስቀሉ ስለ ህዝበ ክርስትያኑ ሳይሆን፤ ስለ ሥጋቸው ያደሩ
ፈልተዋልና።
ስለ ዕውነት ቆመው ስለ እውነት መስክረው ስለ አረጋውያን ስለ ህፃናት ስለ ሴቶችም ስለ
ጉብሎችም ስለ ድውያንም ሲሉ - ግፈኞችን ከመገዘት ግፍንም ከማውገዝ ይልቅ
መስቀላቸውን እንዳንጠለጠሉ መፅሀፉንም እንደያዙ ቤተክህነቷን ህዝቡንና ጦቢያን
ያለተከላካይ እረኛ ጥለው ሥጋዊ መከራና ፍዳን በመንፈሳዊ ዕምነትና ፅናት ከመቋቋም
ከሥጋዊ መከራ ሥጋቸውን ለማዳን የሸሹ ስደተኛ አባቶች በዝተውብናልና።
አቤቱ ብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ሆይ!
ደግሞም በምድረ ኢትዮጵያ በቤተክርስትያኗ መንበር ላይ የተቀመጡት ጠባቂዎቿ ስለ
ወንጌሉ ስለቃሉ ስለመስቀሉ ማስተማርና መፅናት ሳይሆን፤ ስለ ህዝቡም ረሃብ ድህነት
ዋይታ ሰቆቃና ፍረደ ገምድል እስርና ፍጅት - አቤቱ ማለት! እግዚዞ ማለት! ለፈጣሪም
ማመላከት ሳይሆን፤ በህይወት እያሉ ሃውልታቸውን የሚያንፁና የሚያሳንፁ፤ ቃለ እግዚ
አብሄርንም ያዛቡ የኦርቶዶክስ ቀኖናንም የረገጡ በፍቅረ ንዋይ የተጠመዱ፤
በቤተመቅደሱም ውስጥ ክፋት የሚሸርቡ፤ ተንኮልንም የሚፈፅሙ፤ ህዝበ ክርስቲያኑንም
የሚናውጡ ግብዞች ሆነውብናልና።
ደግሞም እነሆ ዝርያቸውና መልካቸው እንዳንተውና እንደኛ ባህላቸውም ተፈጥሯቸውም
ቋንቋቸውም እንዳንተውና እንደኛ የኢትዮጵያ፤ ግና ልቦናቸውና ምግባራቸው የጣሊያኑን
ግራዚያኒ የሆኑ ጦቢያን ማንቁርቷን አንቀዋታልና፤ ህዝቧንም ምርኮኛ አርገዋልና።
አቤቱ በዚያን የፋሽስት የሰቆቃና የጨለማ ዘመን አዛኝቱ ማርያም ፅናትን ትሰጥህ ዘንዳ
እንደተማለድካት፤ እነሆ ስለኢትዮጵያ ነፃነት ስትል ስለህዝቦቿም አርነት ስትል
ስለመስቀሉም ቃል ስትል፤ እግሮችህና እጆችህ በሰንሰለት ታስረው አካልህ በሹምባሾች
ጅራፍ ተተልትሎ ደረትህ በፋሽስት ጥይት ተነድሎ በሞትህ ቤዛ እንደሆንከን፤ አቤቱ
እኛንም ከጭንቅ አማላጇ ከድንግል ማርያም አማልደን። አቤቱ የኢትዮጵያችንን ሞቷን
ሞተን በሞታችን ህይወት እንድንሆናት የመንፈ ፅናት የአካል ብርታት ይኖረን ዘንዳ
ከኢትዮጵያ አምላክ ከፈጣሪያችን ከቸሩ መድሓኔዓለም አማልደን።
አቤቱ ብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ሆይ! እነሆ የዕምነት ፅናት መንፈስህ በእኛም
በልጆችህ ውስጥ ይኖር ዘንዳ እንማልድሃለን - በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ
ስም አሜን!እነሆ ፀሎታችንን ፈፀምን። ሻማዎቹም ጠፉ። መብራት በራ። ሁላችንም ዘና ብለን
በየቦታችን ተቀመጥን። የተዘጋጀውን ቡና እና ሻይ ኒቂሴና ድንብላል አደሉን። ዘይትና
በርበሬ ተለውሶ የተቀባውን ቂጣ ቆራርሰውም አዞሩልን።
  ወዳጃችን ዲበ! እነሆ ይህ እንግዲህ ዘወትር መደበኛ ጉባኤያችንን ስንጀምርና ስናሳርግ
የምንፀልየው ፀሎታችን ነው። ፀሎተ ታሪኩ እንዲህ ነው። ካለፉት ዓመታት በአንደኛው
ዓመት - ለጠላት ፍንጭ ላለመስጠት ነው ዓመተ ምህረቱን መሸሸጋችን - እትዬ አቻሜ ወደ
አንድ - ስሙን መጥቀስ ወደማንፈልገው - ክፍለ ሃገር ጥንተ ጥንታዊ ገዳም ተጉዘው ነበር።
በዚያ ገዳም ውስጥ አባ ዠንበሩ ይገኛሉ። አቻሜ ስለ አባ ዠንበሩ ብዙ አውግተውናል።
እኛም ከደብዳቤዎቻችን በአንዱ ወይም በሁለቱ ከየህ ቀደም ስለ አባ ዠንበሩ እንዳወጋንህ
ትዝ ይለናል። እና ይኸውልህ አቻሜ - አቻምየለሽ ጎበና - የጎበና ዳጬ የዘር ዘር ከዛ ገዳም ሲመጡ -
ፀሎተ ጴጥሮስን አመጡ። እኛም ተቀብለን ፀሎተ ጴጥሮስን ከልባችን ማህደር አኖርነው።
እና እንግዲህ ፀሎተ ጴጥሮስ አመጣጡ፤ ሥርወ ታሪክ አወጣጡ፤ ከገዳም ነው ፍልሰቱ።
የገዳም ነው ህይወቱ። የኢትዮጵያ ነው መልዕክቱ።
ታዲያ ከቡናችን እና ከሻያችን ፉት እያልን ቂጣችንን ጨርግደን ትንሽ እንዳረፍን
“ሁላችሁም ፀጋችንን ይዛችዃል?” አሉን እትዬ አቻሜ።
  “አዎን” አልናቸው በአንድ
ድምፅ ከየጎናችን ፀጋችንን
እያወጣን። እትዬ አቻሜ
ፀጋችን የሚሉት ፀጋዬን ነው -
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህንን።
ስምን ማን ያወጣል ቢሉ -
መላዕክት አሉ። ዕውነትም
ፀጋዬ። የኛ ፀጋ፤ የአገር ፀጋ፤
የኢትዮጵያ ፀጋ - ፀጋችን ነው
ፀጋዬ፤ ይላሉ አቻሜ ዘወትር
ፀጋዬን ሲያነሱ።
  የአባቶቹ መንፈስ በላዩ
ያደረ፤ በአባቶቹ መንፈስ የኖረ፤
በአባቶቹ ልሳን የተናገረ፤ -
የአብናቶቹ መልዕክተኛ
መንፈሳቸው ነው ፀጋዬ። ለኛም
ድምቀታችን፤ ታሪካችን ፀጋዬ
ነው ፀጋችን - ይላሉ በብርቱ
ተመስጦ ስለፀጋዬ ከጀመሩ።
ታዲያን አንዳንዴ  የእንባ ሳግ
ይተናነቃቸውና በሃሳብ ጭልጥ
እልም ይላሉ - አቻምየለሽ
ጎበና።
  አስተማሪ አለሙም ከእትዬ
አቻሜ ቢብስ እንጂ አያንስም - ለፀጋችን ያለው ፍቅር፤ ለፀጋችን ያለው ክብር። ዋቅጅራም
እንዲሁ ነው። “ነጋቲካ ያ ጋሼኮ” /ደህና ሰንብት ጋሼ ሆይ/ ይላል አይኖቹ በእንባ እየተሞሉ
የጋሽ አበራ ለማን የፀጋዬ ሞት ስንብት ሥነ ቃል ግጥም በቃሉ እየተወጣ። አቤት በዚህ
የጋሼ አበራ የፀጋችን ስንብት ሥነ ቃል ስንትና ስንት እንባ አፍስሰናል? ገጣሚያችን ጋሽ
አበራ “ያ! ጋሼኮ” -  ብሎ የሲቃ ምጥ አስምጦናል። በእንባ ጅረት አሳጥቦን፤ በሀዘን ብርድ
አኮማትሮን፤ በሀዘን ውርጭ ጨብጦናል። እና ዛሬም በየአመቱ የፀጋዬን ሙት አመቱን
ስንዘክር ተሰባስበን - እንሰማለን በሀዘን ድባብ በእንባ ጅረት “ነጋቲካ ያ ጋሼኮ”ን ጋሼ
አበራ በእንጉርጉሮ ሲያዜምልን። እና ለአንተ ለወዳጃችን ድንገት እንኳን “ነጋቲካ ያ
ጋሼኮ”ን ካልሰማኸው ካላየኽው፤ ይኸውልህ ለአብነት ቀንጨብ አርገን፤ በዚህ መልዕክት
ያካተትነው።ቀለሙ ፈሰሰ ቀንዲል ተሰበረ
ብዕሩ ለገመ ብራናው ጠቆረ
ዋርካው ተቆረጠ አድባር ተሸነፈ
አገር አኮረፈ ሰንኪኑ አረጠ
…አረ ሞረሽ በሉ…አረ ዳኛ ጥሩ…
አገር እርቃን ቀረ ገበናው ተገልጦ
ጋሼ ሳይነጋጋ በድንገት አምልጦ…
ምሶሶው ወደቀ አዳራሽ ፈረሰ
ጣሪያው ተነደለ ቤቱ ተጠረሰ
አገር ጦም አደረ መሶቡ ደረቀ
ምልክቱ ጠፋ ፀጋው ተሰረቀ
…አረ ሞረሽ በሉ…አረ ጴጥሮስ በሉ…
ታሪክን ማን ይንገር ባህልን ማን ያውጋ
የትመጣው የጠፋው የት ይሂድ ፍለጋ?
ቆሌው ለሸሸበት እኔነት ላጠጠው
ትውፊቱ ለራቀው በንትሱ ለጠፋው
አንት ነበርክ የኔታው አንት ነበርክ ፋናው
ወገን ፍኖት ጠፋው እንግዲህ ማን ይምራው?
አረ ሞረሽ በሉ አረ በልግን ጥሩ
የከርሞ ሰው ጠፋ እናት አለም ጠኑ
መች እንዲህ ነበረ ውላችን ቃላችን
ሽልማት ሆነ እንዴ ላንተ መጮኻችን?
ሽልማት ሆነ እንዴ ከል መልበሳችን
ሽልማት ሆነ እንዴ ቱቢት ስፌታችን?
የቀለሙ ቀንዲል ፈሰህ ማንባታችን…
እሪ በይ ሀገሬ እሪ በይ ኢትዮጵያ
ኢልመ አባ ገዳ ጠፋ ከገበያ
እሪ በይ ሀገሬ…
ኢልመ ኦቦ ቀዌሳ የአምቦ የቱለሙ
የሜጫው ጃዊሳ
ነጋቲካ አለ ቆረጠ ተነሳ
ያንኮበሩ ዲያቆን የጦቢያው አንበሳ…
አንተ ጋሼ…
ለካስ ወንድ ልጅ እሚያለቅሰው ብቻውን ነው
ያልከው እንዲህ ነው?
ለካስ ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት ማለት ይህ ነው?... ወዳጃችን ዲበ! ይኸውልህ ቀደም ሲል እንደጀመርንልህ እትዬ አቻሜ “ፀጋችንን
ይዛችዃል?” ባሉን ጊዜ ሁላችንም ከጎናችን ያወጣነው የፀጋዬን ታሪካዊ ተውኔቶች መፅሀፍነው፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታተመው። እንግዲህ “ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት”ን፤ እነሆን
ተቋደሰን ።
ተከታይ፤ ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት
ብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ የጣሊያን ፋሽስት ወራሪ እስረኛ ነበሩ። የቀድሞ
መጠሪያቸው ሃይለማርያም ይባል ነበር። ብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ
አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሥላሴና የወሎ ጳጳስ ናቸው። የታሰሩትም አዲስ አበባ
ቀድሞ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ዛሬ ቀዳማዊ ሃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ /አአዩ/ ያኔ
የኤልማርሻሉ ሮዴልፎ ግራሲያኒ የኢጣሊያ መንግሥት እንደራሴ መኖሪያ ግቢ ነው -
ይለናል ፀጋችን ስለ ብፁዕ አባታችን ሲያስተዋውቀን በጴጥሮስ ያቺን ሰዓት ታሪካዊ
ተውኔት።
  እነሆ የታሪክ አስገራሚ ጥልፍልፎሽ፤ አስገራሚ እንቆቅልሽ።
  “እኔን የሚገርመኝ ሁሌም የሚደንቀኝ ለዛሬይቷ ኢትዮጵያ የፖለቲካ የአኮኖሚና
ማህበራዊ ምህዳር ለውጥ እንብርት በሆነው የቀዳማዊ ሃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ - በ
አንድ ወገን ግራዚያኒ - የቅኝ ገዢነት፤ የአምባገነንነት፤ የፀረ ኢትዮጵያነት ተምሳሌ
የሆነው የፋሽስት መሪ መኖሪያ፤ በሌላ ወገን ስለ ኢትዮጵያ ነፃነት ስለህዝቧም ህልውና
ስለባንዲራዋም ክብር ‘እምቢኝ ለፋሽስት እምቢኝ ለአምባገነን እምቢኝ ለጦቢያ ጠላት’
ያሉት የነፃነት ቀንዲል ተምሳሌያችን የብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ እስር ቤት የመሆኑ
የታሪክ ተቃርኖ እንቆቅልሽ ነው” አለች ድንብላል - ስመ ጥሩዋ አካውንታንት።
  አዎ! ይህ ሀቅ ነው ዲበኩሉ። የቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከዛን ዘመን ወዲህ
የብፁዕ አባታችንን ቀንዲል የተረከቡ ለባንዲራዋ ክብር ለዳርድንበሯ መታፈር ለህዝቦቿም
እኩልነት ሠላምና ብልፅግና ለመልካም አስተዳደር ግንባታም ለለውጥ ነውጥ ክብሪት የሆኑ
አያሌ ስመጥር ትንታግ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን አፍርቷል። ብዙዎቹም በለውጥ
ነበልባል ለሌሎቻችን ብርሃን ለመሆን ነደው አልቀዋል።
  ግና ትውልድ አያልቅምና ሌሎች ቀንዲሉን ተረክበዋል። በብፁዕነታቸው ፋና
እየተመሩም ‘እንቢኝ ለዘረኞች እንቢኝ ለአፋኞች እንቢኝ ለአምባገነኖች ለኢትዮጵያ
ጠላቶች’ እያሉ ናቸው። ነገ ሌላ ቀን ነው። ነገ በጦቢያ ምድር ፀሐይ ይወጣል። ከዛ በፊት
ግን ይጨልማል። ሊነጋ ሲል ይጨልማል - ይላሉ አባ ዠንበሩ ሲያስተምሩ።
  “እስቲ ሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻን አቅርቡት” አለች ኒቂሴ የፀጋችንን መፅሀፍ እየገለጠች።
እነሆ ሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻ፤ ከፀጋችን ብዕር ለቅምሻ።
“…ሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻ የሰላሳ ሶስት ዓመት ጎልማሳ ቀጠን ረዘም ያለ አቋቋመ
መልካም ሾጤ የጮሌ ጭራቅ የጋኔል ልዝብ የጊዜ ብልጥ ንቁ አንደበተ ምዝን ወገኑን ናቂ
ለራሱ አዋቂ እማይነደው እማይበርደው ዓይነ ግትር ልበ ጥጥር ጨልሂ አበሻ ነው።…ልቡ
ወዶ አያውቅም። ልዝብነቱንና ንፉግ ራስ ወዳድነቱን በቁጠባ ስለሚጠቀምበት የተመዘነ
አስተያየት አለው ብለው በስህተት የሚያምኑበት ስለሚበዙ ያያሌ ሰው ልብ አኮላሽቶ
አባክኗል።…ጊዜን በጊዜ ዕድልን በዕድል አመዛዝኖ አመጣጥኖ ይገዛል ይሸጣል። ይነግዳል
እንጂ አያምንም አይታመንም።…በሥልጣን እንጂ በዕውነት አያምንም። ወዳጅነቱ አደጋ
ነው። መሣሪያነቱ ፍቱን ነው። በጎነትን በከንቱነት የሚያዛምድ…የቅንነት ገፊ የመቅሰፍት
ሊቅ ነው። ሮዴልፎ እንኳን መሣሪያነቱን ቢያደንቅም ባህርዩ ይዘገንነዋል።…አመጣጡጴጥሮስን በማግባባት፤ በማሳሳት ወይም በመሸጥም ቢሆን ለግራዚያኒ ፖለቲካ መሣሪያ
ለማስደረግ ነው። የሱ ድልና ትግል የአእምሮ እንጂ የደምና የልብ ህዋስነት የለውም።” እንግዲህ ሹምባሽ ባሻ ይህ ነው አባ ግርሻ - አለ ዋቅጅራ ከመፅሀፉ ገፅ ላይ ቀና ብሎ።
  “ያንተ ያለህ!” አሉ አቻሜ። “አሁን የግርሻን የልቡን ልብ መርምሮ ማን ሊነግረን ይችል
ነበር? ከፀጋችን በቀር። በአባቶቹ መንፈስ በአባቶቹ ዘመን መኖርን የኖረ ደግሞም የጊዜን
ሠንጠረዥ በጊዜ ተሻግሮ በአካል በእኛ ውስጥ ከእኛው ጋር ሥጋ ወደሙ ተላብሶ ኖሮ -
የቀድሞውን የድሮውን ከዛሬው ጋር ከምናየው በሠንሠለት አያይዞ አቆራኝቶ ማን እንደ
ፀጋችን ማንነታችንን የፈተነ? ውስጣችንን የመረመረ? ድንቅም አይደል ፀጋችን
መስታወታችን?” አሉ አቻሜ እኒያ የሚያማምሩ ትልልቅ ዓይኖቻቸው ይበልጥ እየተለቁ።
አየህ ዲበ! እንግዲህ ሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻ ለጣሊያን ያደረ ለግራዚያኒ ያጎበደደ
ለግራዚያኒ የነገደ በክህደት ያበደ ብፁዕ አባታችንን የፈተነ እንደ ጲላጦስ የከዳ የዲያቢሎስ
መልዕክተኛ መፃጉ ልበ ጣሊያን አበሻ ነው - ግርሻ ማለት።
  “ዕውነት ብለዋል አቻሜ” ሲል ቀጠለ አስተማሪ አለሙ። “የሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻ ባህሪ
ሁሌም የሚያስደምም ሁሌም የሚቆነጥጥ መሆኑ ፀጋችን የትላንቱን የጣሊያን ዘመኑን
የክህደቱን የጲላጦስ ዘመንነቱን ማሳቀመጡ ብቻም ሳይሆን - ዘመንን ተራምዶ ዛሬንም
የሚያሳየን መሆኑም እንጂ!
 “ልብ በሉ! ፀጋችን ሲነግረን - የጊዜ ብልጥ ንቁ አንደበተ ምዝን ወገኑን ናቂ ለራሱ
አዋቂ…ነው - ይለናል ሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻ። ታዲያስ?! የዚያን ዘመኑን ሹምባሽ ባሻ
የዚያን ዘመኑን ግርሻ ዛሬስ እዚህ በእኛው ዘመን በእኛው ህይወት እያየነው አይደለምን?
ወገኖቹን የናቀ ለራሱ ያወቀ የጊዜ ብልጥ - ሞልቶ ተትረፍርፎ ስንቱን ንፁህ ረፍርፎ፤
በስንቱ ደም ነግዶ የደለበው የፋፋው ሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻ ስንትና ስንቱ ነው? ዛሬ ዘመን
ሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻ ነው ሀገራችንን ያጠፋው። ለይቶላቸው የግራዚያኒን ልብ ልባቸው
ተግባሩን ቆዳቸው ያደረጉት ህወሃታውያኑማ አንደኛውን ጠላት ናቸው - ያው እንደ
ጥልያን።
  “ያጠፋን ባሻ ነው፤ ሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻ የህወሃት መቆስቆሻ!!! ፀጋችን እንደነገረን -
ጊዜን በጊዜ ዕድልን በዕድል አመዛዝኖ አመጣጥኖ ይገዛል ይሸጣል…አያምንም
አይታመንም…በሥልጣን እንጂ በዕውነት አያምንም…ብሎናልና ስለ ባሻ አባ ግርሻ፤
እኛንም ያሰቃየን ይኸው ተፈጥሮ ነው የዛሬ ዘመን የአባ ግርሻ ውልዶች የሥልጣን አባዜ
ፍሎች። ወዳጅነታቸው አደጋ መሣሪያነታቸውም ፍቱን ነው ለህወሃት ጌቶቻቸው - እንደ
ባሻ አባ ግርሻ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ እንዳደረው ነጭ አበሻ።” አለና አስተማሪ አለሙ
በረጅሙ ተነፈሰ።
“እዚህ ላይ” አለች ኒቂሴ ረዥሙን የሐረሪን ጀለቢያዋን በተጣጠፉት እግሮቿ መኻል
እያስተካከለች። “እዚህ ላይ ልብ ብላችሁ ካልሆነ እንጂ ሌላም አለ አስደማሚ እንቆቅልሽ
በቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ።”
  “እንስማዋ ታዲያ” አላት ቮልቮ ሳተናው ታክሲ ሾፋሪው።
  እና ቀጠለች ኒቂሴ።
  “ዩኒቨርሲቲው መንፈስ አለው። የአባታችን መንፈስ በግቢው ይኖራል። የግራዚያኒ ልብ
በግቢው ውስጥ አለ። የሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻ ጣዕረ ሞት መንፈስ በግቢው ውስጥ አለ።የብዙ ጦቢያ ልጆች ንፁህ ደም በግቢው ውስጥ አለ። እና እኒህ አልሚና አጥፊ መንፈሶች
በግቢው ውስጥ ሁሌም እንደተናነቁ ሁሌም እንደተፋለሙ ሁሌም ማደሪያቸውን ነፍስ
እንዳደኑ አሉ። እኒህ መንፈሶች በየትውልዱ ወደ ግቢው በገቡ ወጣቶች ውስጥ ይኖራሉ፤
እያደቡ። ልበ ጥጥር የጮሌ ጭራቅ የጋኔል ልዝብ ዓይነ ግትር ወገኑን ናቂ ለራሱ አዋቂ
ይፈልጉና - ጥልቅ ይላሉ ከልቡ፤ ይመቻቸዋልና።
  “እና ቤታቸውን ይሰራሉ ይገነባሉ፤ ልቡ ልባቸው ገላው ቤታቸው ይሆናል። እና
ይኸውላችሁ ግራዚያኒና ባሻ ልቦቻቸውን አቀናጅተው ከምርኮኛቸው ልብ ጋር አንድ
አምሳል አንድ አካል አድርገው ይኖራሉ ተመቻችተው። ልባቸው ማደሪያቸው ይሆናል -
የኒህ ልበ ጥጥር ጨልሂ አበሻዎች የዘመኑ ሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻዎች። አለ ልቡ
የግራዚያኒ በልባቸው ከግርሻ ጋር ጡት ተጣብቶ በኢትዮጵያውያን ደም ፋፍቶ። ታዲያ፤
ቼ! ፈረሴ….ሲሏቸው…ስልጣን ነብሴ….ይላሉ ሹምባሽ ወግራዚያኒን የሆኑ
ቼ! ፈረሴ….ደም ነው ምሴ!
ቼ! ፈረሴ…..ዘረኝነት ኮርቻዬ!
ቼ! ፈረሴ….ኢትዮጵያዊነት ደመኛዬ!
ቼ! ፈረሴ.....ዘረዘፍ ሻዕቢያ ዘራፍ ወያኔ…ስልጣን ነብሴ ደም ነው ምሴ፤ ዘረኝነት ኮርቻዬ
ኢትዮጵያዊነት ደመኛዬ…ዘራፍ ሻዕቢያ ዘራፍ ወያኔ…ዘራፍ ወዲ ግርሻዚያኒ…ይላሉ
እንደ ቁራ ሲያንቋርሩ።
  “እነሆ መለስ ዜናዊ አንዱ ወዲ ግርሻዚያኒ ነው። ኢሳያስ አፈወርቂ ሌላው ግርሻዚያኒ።
ስብሃት ነጋ ስዩም መስፍን እኒህና ሌሎች ሁሉ ግርሻዚያኒያን ቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ ግቢ
የተማሩ፤ ነበር እዛው ሳሉ በግርሻና ግራዚያኒ መንፈስ የነሆለሉ ለዕኩይ ግብ የተመለመሉ።
የአባታችንን የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን መንፈስ አልቀርብ ብለው፤ እርሳቸው ሊያቅፏቸው
ሲቀርቧቸው ግና በላያቸው የሰፈረው የግርሻዚያን መንፈስ እንደዛር እያንዘፈዘፋቸው
ሲሸሹዋቸው ሲርቁዋቸው፤ ታዲያ ይህን የአባ ግርሻ ጣዕረ መንፈስ ተመልክቶ እየፈነደቀ
እየጨፈረ አጢኖ፤ የግራዚያን ብኩን ርኩስ ልብ በጭራቅ ልቡ አስልቶ በጭራቅ ልቡ ከበሮ
ደልቆ…ደልቆ…ተያይዘው ተቃቅፈው ግርሻዚያኒ አንድ አምሳል አንድ አካል  ሆነው
ጥልቅ አሉባቸው መለስ ወኢሳያስን ስብሃት ወስዩምን እንዲሁም ሌሎቹን ከሌሎቹ
መርጠዋቸው፤ ፈቅደዋቸው። እና ወገኖቼ ይህ ነው እንቆቅልሹ፤ የዩኒቨርሲቲው ታሪክ
ምፀታዊ ጥልፍልፎሹ።” አለችና ኒቂሴ ውሃ ከብርጭቆ ግጥም አርጋ ጠጥታ በረዥሙ
ተነፈሰች ከቅምጧ ተመቻችታ።
  “ለመሆኑ” አሉ እማማ ድንቡሎ ወደ ኒቂሴ እየተመለከቱ “ለመሆኑ ግርሻዚያኒ ማን ነው?”
  “ስም ከማርዘም ብዬ ግርሻንና ግራዚያኒን አጣምሬ” አለች ኒቂሴ ፈገግ እያለች።
“ድንቅ እንጂ ነው ኒቂሴ፤ ማለፊያ ስም አውጥተሻል” ካሉ በዃላ እማማ ድንቡሎ ጥቂት
እንደመተከዝ ብለው ቀጠሉ። “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር አሉ እኒያ አያቶች ነገር በምሳሌ
ሲያስተምሩ። ዕውን አሁን እኒህ ሁሉ በጦቢያ ላይ ይጨክኑ? እንደው ምን አይነቱ
ጋንጩር ቢሰፍርባቸው ነው እንዲህ ለሀገርና ለወገን መቅሰፍት ያደረጋቸው? መቼም
ጃንሆይ በዘመናቸው ብዙ መልካም ነገር ለሀገራቸው ሰርተዋል። ስህተትም የአዳም ተፈጥሮ
ሆኖ መሳሳታቸው አልቀረም። በእግዚአብሄር መንግሥት ብቻ ነው ስህተት የማይኖረው።
ታዲያ ትምህርት ቤት ከፍተው ባስተማሩ፤ የዓለሙን ሁሉ ዕውቀት ወጣቱ እንዲገበይ
ባደረጉ፤ እሳቸው በከፈቱት ኮሌጅ ተምረው ምነው በእሳቸው ላይ መጨከናቸው? አረመኔው
መንግሥቱ ሃይለማርያም ነብሱ ነብሷን ስታጣ በገሃነም ብረት ምጣድ ትንቸስቸስና
በነፍሳቸው እያሉ አሰቃይቶ ገደላቸው። እኒህ ደግሞ በአፍሪካ አዳራሽ እንኳን ሀውልታቸውአይቁም ብለው ከእሳቸው ይልቅ ንኩሩማን አምጥተው መትከላቸው ዕውነትም
ግርሻዚያኒነታቸው ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን? ፍረደን ጴጥሮስ! ፍረደን የኢትዮጵያ አምላክ!
እኛማ ብቻችንን ነን…አማልደን ጴጥሮስ አማልደን ከእመቤታችን…ብቻችንን ነን አላንተ
ማን አለን!” አሉ የብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስን ምስል እየተማፀኑ።
  አዎ ዕውነት ተናግረዋል እማማ ድንቡሎ። እኒህ የዛሬዎቹ ህወሃቱ አራት ኪሎ የከተሙቱ
ወይንም አስመራ የነገሱት ሻዕቢያኑ - ፀረ ኢትዮጵያ የሆኑቱ ዛሬ የሚራቀቁቱ ሁሉም
የተማሩቱ ያኔ ነበሩ ከግቢው፤ ከቀዳማዊ ሃይለሥላሴ የዕውቀት ማዕድ ተቋድሰው። አዎ
ዕውነት ነው። ዛሬ በጃንሆይ ቤተመንግሥት ተንሰራፍተው ተኮፍሰው ጃንሆይን ያወግወዛሉ
ነፍጠኛ ነው እያሉ። ዛሬ ጃንሆይን በንኩሩማ የተኩቱ…ከዚህ ወዲያ ግራዚያኒነት ከዚህ
ወዲያ ሹምባሽነት ከወዴት ሊመጣ ከወዴት ሊከሰት - ከዘመኑ ግርሻዚያኒ ውልዶች በቀር
ከህወሃት?
ወዳጃችን ዲበ! ፀጋችን ያነጠበልን በጣሊያን ዘመን የተፈፀመ የክህደት ምግባርና ሠብዕና
እንደምን ዘመንን ተራምዶ የዛሬውን ያለንበትን የሀገራችንን ዕውነታ በጴጥሮስ ያቺን ሰዓት
እንደመስታወት እንዳሳየን ለአብነት ይሆን ዘንዳ የሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻንና የብፁዕ
አባታችንን ጥቂት ምልልሶች ነቅሰናልና - እነሆን ግርሻን አስቀድመን፤
“…በምሳሌ ተማፅኜዎት ችግር ዘዴ ይወልዳል ብዬዎት አባቴ ተዘነጋዎት?...እዩት እኔ
ለችግሩ ዘዴ ሆኜ ለምሥጢሩ ከሽማግሌዎቹ ጋር ያው ከምትቸጋገሩ፤ እነሱም በትዕዛዝ
ምክንያት ግዝትዎን ሳይሰብሩ በቅድስት ቤተክርስቲያን መዛግብት ሳይሰረዙ አጉል
ባይወገዙ፤…እርስዎም ከክቡር እምክቡራን ማርሻል ግራዚያኒ ጋር እንዲያው ከንቱ
ከመጣረር ላያዛልቅ ከመካረር፤ ባንድ በኩል ኢትዮጵያዊ በሌላ በኩል ሹምባሽ ነኝ፤
እና…ችግር ላልነው ምክንያት እኔን ካረገኝ ዘዴው እኔን ከፈጠረኝ፤ ምናለ ያው በኔ ሳቢያ
እንዳማካይ መወያያ ብጠቀም እንደመሳሪያ ለችግራችን መግባቢያ…”ይላቸዋል ግርሻ
አባታችንን ቀርቦ ሲፈትናቸው። ታዲያ፤ አንዴ በቤተክህነት አባቶች ስማቸው ከመዛግብት
ተፍቆ እንዳይወገዙ፤ አንዴ ማርሻል ግራዚያኒንና የጣሊያንን የበላይነት መቃወም ትርፉ
በራስ ላይ ነው መዘዙ… እያለ ቢወተውት …አባታችን እንዲህ አሉት በምሳሌ ሲነግሩት፤
“ይቺን ጨረቃ አየሃት ልጄ?...ጨረቃዋ በእኩለ ሌሊት ድንገት በሌለባት ጣጣ የሰራ
አካላትዋን ተግጣ፤ ባንዳች ዱብ ዕዳ ጋሬጣ፤ በደረቀ ሌሊት ተኩላ፤ የደም ሥሯን
ተዘንጥላ፤ ሲዋኝባት ሲፎክርባት ሲጠጣ ዲደነፋባት፤ አንጀቷን ማህፀኗን አርዶ፤ እንዲህ
የደም ድግስ ለምዶ፤ ተንፈራግጦ ባኖ አብዶ፤…እኛ አሁን ጩኸት ብናግድ መለማመጡን
ብናቅድ እንዲያው በገዛ እጁ በውድ፤ ወተትና እርጎ ለምዶ ጥፍሩን ጥርሱን ጎርዶ? ቡራኬ
ሠላም ሊያወርድ? በልምምጥ ነው እሚሄድ፤ በደም መስከር የለመደ እብድ?”ይሉታል
ዐይን አውጣውን ግርሻ ይጠይቁታል። አያይዘውም፤
“…እኔን ማግባባትህ ቀርቶ ይልቅስ አንተ ተመከር፤ አንዴ እንደ ኢትዮጵያዊ አንዴ
እንደ ሹምባሽ መናገር፤ ችግር ካልከው እሱ ይበልጣል ከችግር ሁሉ መቸገር”አሉት ብፁዕ
አባታችን እንደው ለምናልባት ይገባው እንደሁ፤ እንደው ለምናልባት ይመከር እንደሁ
አስበው።
  ግና ባሻ አባ ግርሻ ሹምባሽነቱ በደሙ ናኝቶ ከልቡ ልብ ገብቶ እሱነቱን አስክዶ
ለጣሊያን አድሮ..እንዲህ አላቸው አባታችንን በቀቢፀ ተስፋ ተወጥሮ፤
“…ጊዜው አሁን ሌላ ዓለም ነው፤ ምነው ዐይንዎን አይከፍቱትም? እንኳንና ኢትዮጵያዊ
ኢትዮጵያ እሚሏት የለችም።…ዕውነት ማየት ካቃትዎ ይፋ ማየት ካቃትዎ፤ ዐይንዎንመክፈት ከተሳነዎ…አመንኩባት የሚሏትን ኢትዮጵያ እኔ ላሳይዎ…ባደባባይ ከቴቲኪንትና
ከኮማንዳቶሪዎች ጋር በችሎት፤ ከኮሚሳሪዎች ጋር በገጠር በከተማና በመንደር ከኔ ቢጤው
አበሻ ጋር ሳነፈንፍ እምውል እኔ ነኝና የዛሬዬቱን ኢትዮጵያ አውቃታለሁ።…ለምርመራ
ተወስዶ የተመለሰን ወንድ አጥንቱ ተሰብሮ ቅስሙ ምድር ነክሶ ናላው ተበዝብዞ ወኔው
ተመዝብሮ አይቼዋለሁ። ለምርመራ ተወስዳ የተመለሰች ሴት ሴትነትዋን ተለክፋ ክብሯን
ተቆሽሳ…ህሊናዋ ዳሽቆ የእናትነት አለኝታዋ ተደፍጥጦ አይቻለሁ። አባታቸው ጫካ ለብሶ
በረሀብ ሲደናበርና ሲደናቀፍ ለጦርና ለስደት ለገደልና ለጋሬጣ የተሰዋባቸው ህፃናት ጊዜ
ከድቶ አራቁቶ ሰብሳቢ እያሳጣቸው የትውልድ ጠፍ ሲሆኑ አይቻለሁ። የሕዝብ ፈቃድና
ወኔ ተሰልባል፤ ያንድነቱ ሙላ ተላቆ ተገነጣትሏል፤ ሀሞቱ ደርቋል፤ ወንድነቱ ከስሯል፤
ተስፋው ባክኗል፤ ከ እንግዲህ እንደ መርገምት ተልከስክሶ፤ ማለት አንዴ መመለሻ የሌለው
ብኩን ሕዝብ ነውና ኢትዮጵያዊ እሚሉት ለራሰዎ ህይወት ቢጠነቀቁ ይሻላል።” “እግዚኦ ድፍረት፤ እግዚኦ ትእቢት!” አሉ እማማ ድንቡሎ ጉንጮቻቸውን በሁለት
እጆቻቸው ይዘው የግርሻን ንግግር ማመን እያቃታቸው።
  አዎ ግርሻ አስደናቂ ነው። የተናገረው ሁሉ ዛሬም በዐይናችን የምናየውን ነው። እንደ
ጣሊያን ዘመን ሁሉ ዛሬም በየቀኑ ቃሊቲ ለምርመራ ገብቶ አጥንቱ ተሰብሮ ቅስሙ ምድር
ነክሶ፤ በዱርዬዎች እንዲደበደብ ተደርጎ ወኔው ተመዝብሮ…ያየነው የምናየው ብዙ ነው።
ዛሬም እንደ ጣሊያን ዘመን ቃሊቲ ገብታ ህሊናዋ ዳሽቆ የእናትነት አለኝታዋ ተደፍጥጦ
ያየናት የምናያት ኢትዮጵያዊት ሞልታለች። ስንት መቶ ሺህ የኢትዮጵያ ሠራዊት የደርግ
ሠራዊት ተብሎ ዛሬም እንደ ጣሊያን ዘመኑ ልጆቹ ጊዜ ከድቶ አራቁቶ ሰብሳቢ አጥተው
የትውልድ ጠፍ ሆነው አይተናል። ሶማሌ ዘምቶ የሞተ ሠራዊት ህፃናት ልጆቹ ባዶ ሜዳ
ቀርተው በረሀብና በችግር ሲቆሉ አይተናል። ባድመ ሄዶ ያለቀው ሠራዊት ቤተሰብ ለማኝ
ሆኖ አይተናል። ታዲያ ግርሻ አከርካሪ የለውም። ለጠላት አድሮ በወገን ቁስል እንጨት
መስደድ እንጂ ለሀገርና ለወገን መቆም ለእሱ ትርጉም የለውም። ግርሻ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ
አይበቀል ነው። ግርሻ የኢትዮጵያ ጠላት መሳሪያ ነው። ግርሻ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት
ነው።
ግርሻ በኢትዮጵያዊነቱ አያምንም። ግርሻ በኢትዮጵያም አያምንም። ግን ግርሻ
በጣሊያን ያምናል። ግርሻ ወዳጅነቱ አደጋ መሳሪያነቱ ግን ፍቱን ነው። ግርሻ ከ1928 ዓ/ም
እስከ 1933 ዓ/ም ኢትዮጵያን ለመዘበረው ጣልያን አድሮ ጣሊያንኛ እየተናገረ ለጣሊያን
እያስተረጎመ ለጣሊያን አድሮ ኖረ። እነሆ ከ1983ዓ/ም እስካለንበት ዘመነ ዓመት ድረስ
እንግሊዝኛ የሚናገሩ ለህወሃት ያደሩ በህወሃት የሚያምኑ ኢትዮጵያዊነታቸውን የካዱ
በዘረኝነት የተካኑ ለራሳቸው ያወቁ ወገንን የናቁ የዘመኑ ግርሻዎች ስንትና ስንት ናቸው?
መቼም ፀጋችን ስለግርሻ የፃፈው በዘመነ ህወሃት አይደለም። ታዲያ እንዴት ቢሆን ነው
በጣሊያን ዘመን ግርሻ ውስጥ የዛሬ ዘመን ህይወታችንንና ግርሻዎችን እያየን ያለነው?!
አንድ ሰሞን አንድ አዛውንት የኢህአዴግ አገዛዝ ያስመረራቸው ሌት ተቀን የሚያዩት
ሰቆቃና ግፍ ያንገፈገፋቸው “ለመሆኑ እኛን የሚገዛን ጣሊያን ነው ወይ?” ማለታቸው
እንደምን ያለ ዕውነት ነው?! ይህ የአዛውንቱ ታሪክ ፈጠራ ሳይሆን በርግጥም በአደባባይ
የተናገሩት ነው፤ ከእንግዲህ ባለው ህይወቴ የሚመጣውን እቀበላለሁ ብለው።
  እነሆ የግርሻን በዚሁ ሸብ አርገን ለመሆኑ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ለግርሻ ምልጃ ምን
መልስ ሰጥተውት ይሆን? የሚለውን ቀንጨብ አርገን እናቀርባለን፤
“…አዎን አንተ ውስጥ /ኢትዮጵያ/ የለችም ምክንያቱም አታምንባትም፤ ወይም በራስህ
አታምንም ወይም ባገርህ አታምንም፤ ስለዚህ  የዕምነት ምስኪን ነህ መተማመኛ የሌለህ፤
እና ለኔ አትቸገር ቀድሞ ለራስህ አታውቅም፤ እኔ በኢትዮጵያ ስለማምን እኔ እስካመንኩእሷ አትሞትም።…ልጄ፤ ልጄ አንተ የዚህ ሕዝብ ግብርና ክብሩ የት
ይታይኻል?...መጠንቀቅስ ለኔ ህይወት ሳይሆን ባለታሪኩን ሕዝብ እንደ ጥጃ ያያሌ ምዕተ
ዓመታት ታሪኩን እንዳሻንጉሊት፤ ጀግንነቱን እንደ እንቆቅልሽ፤ ሃይማኖቱን እንደ አምልኮ
ጣዖት እንድታፍርበት ከገራህና ካስተጣጠቀህ ባላንጣ ነው ልጄ፤… አንተ ታየኝ የምትለው
አንገታቸው ለባዕድ ተደፍቶ ከጎህ ፈለግ ወደ ምሽግ ፈለግ መንፏቀቃቸውን እንጂ ለዚህ
ባበቃቸው ወራሪ ተኩላ ጥላቻ በየእለቱ ጥርሳቸውን ማፋጨታቸውንና በምሬታቸው
መተባበራቸውን አይደለም። የባላንጣውን ጭቆና ባጤነ ቁጥር የሕዝቡም የአርበኛውም
የስደተኛውም የመንፈስ ትብብር እንደሚያጤን አላየህም? ማወቅስ ልጄ የወገኖቻችሁን
ስንኩልነትና ከንቱነት ለማስተጋባትና በታሪኩ ላይ ያለውን መተማመን ለመስለብ
የማታመጡት ተንኮል ወለድ ፈጠራ አለመኖሩን ነው። ማየትስ ልጄ ከትላንት የተማርነው
ለነገ የምናተርፈው ተስፋ እንዳይኖረን በልማድ ብቻ በደመ ነፍስ እየተንገዋለልን፤
ከወራሪዎቻችን ተስፋና ዓላማ የተትረፈረፈ ቅንጣቢ እየቃረምን፤ በሀገራችን ስደተኞች
በቤታችን ባይተዋር በንብረታችን ደጀ-ጠኝ በማዕዳችን ቀላዋጭ ሆነን ከመቅረት ሞት
መምረጣችንን ነው። ላንተ የታየህ የጅል የሰነፍ አሟማት፤ ጥርስና ትርጉም በሌለው
የህይወት ድል መኻል ተሻሽቶ መጣሉ እንጅ፤ የንቁ የልባም አሟማት በሞት መንጋጋ
መኻል ተግ ብሎ ነቅቶ የገዛ ሞቱን ከባላንጣው ጥፍር መኻል ገንጥሎ ወስዶ ራሱ
ሲሞታት፤ የህይወት ባለቤት ራሱ እንደነበር የሞቱም ባለቤት ራሱ እንደነበር የሞቱም
ባለቤት ራሱ መሆኑን ማስመስከሩ አደለም። ስለዚህ ልጄ ካንተም ሆነ ያገር አዛውንት
ካልካቸው ጋር፤ ያው እንደ ግራዚያኒ መቸጋገር እንጂ መመካከር አይኖርምና ፈቃድህ ሆኖ
የመጨረሻ ሰዓቴን በግል እንዳሳልፋት…ብቻዬን ተወኝ።”  እነሆ የአባታችን የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ አልፋና ኦሜጋ መልስ። ለትላንቱ እኛነታችን
ለባሻ አባ ግርሻ፤ ለዛሬም ህይወታችን ለግርሻዚያኒ ውልዶች ይሆን ዘንዳ እነሆ አልፋና
ኦሜጋ ቃል - እኔ በኢትዮጵያ ስለማምን እኔ እስካመንኩ እሷ አትሞትም!! ቃል ለምድር
ቃል ለሰማይ!
  ብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ሆይ፤
  አዎን ኢትዮጵያ አትሞትም! አዎን እኛ ልጆችዋ ለህያው ቃልህ ቃል ገብተን፤ እኛ
በኢትዮጵያ ስለምናምን እኛ እስካመንባት ኢትዮጵያ አትሞትም! መስዋዕትነትህም ከንቱ
ቃልህም መና አይሆንም። ለቃልህ ቃል ገብተን ቃል ለምድር ቃል ለሰማይ ብለናል።
ወዳጃችን ዲበ! አባታችን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በአንድ ወገን ሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻ፤
በሌላ ወገን የመስቀሉን ቃል ለፈራሽ ገላቸው ደህንነት የለወጡ ለግራዚያኒ ያጎበደዱ ህዝበ
ክርስቲያኑን የካዱ መስቀል አማትበው መፅሀፍ ቅዱስ ስመው፤ በሽምግልና ካባ
ተጠቅልለው ‘እባክዎ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ሆይ፤ ለጣሊያን ይደሩ፤ ባንዲራችንን
ይርገጡ፤ አርበኞችን ያውግዙ፤ ስለታላቋ ጣሊያን ንጉሥና መንግሥትም በየአድባራቱ
ያስተምሩ፤ ለስጋዎ ይወቁበት እኛ ለስጋችን አውቀንበታልና” እያሉ ቢያስጨንቋቸው በሥጋ
ለባሽነታቸው በስጋዊ ህይወት ቢፈትኗቸው ጊዜና፤ የሞትን ፅዋ ከመጨለጣቸው
አስቀድመው እንዲህ አሉ አባታችን በፀጋችን መንፈስ አድረው፤
አዬ፤ ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከ መቼ ድረስ እንዲህ፤ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን ሰቀቀንዋን፤ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺእኮ ማንም የላት…እና ፈርቼ እንዳልባክን፤ ሲርቀኝ የሃይልሽ ውጋጋን
አንቺ ካጠገቤ አትራቂ፤ በርታ በይኝ እመ ብርሃን
ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት፤ እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን።
አዎን ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ
እማማ ኢትዮጵያን መንፈሴ ተፈትቶ እንዳልከዳት ሰጋሁ…
ታዲያ ዛሬ ኢትዮጵያ ስትወድቅ፤ ከምትሰጪኝ ለፍርሃት ጦስ
ምነው በረኝነት ዕድሜ፤ ዓይኔን በጓጎጣት የሎስ
የጋኔል ጥንብ አንሳ ከንፎ፤ ወርዶ በጭለማ በርኖስ
ባክሽ እመ ብርሃን ይብቃሽ፤ ባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ
ፅናት ስጪኝ እንድካፈል፤ የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ፤
ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ፤ ከነደደችበት እቶን
የሷን ሞት እኔ እንድሞታት፤ ገላዋ ገላዬ እንዲሆን።…
አዎን ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ።…  አቤቱ ብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ሆይ!
  እነሆ ኢትዮጵያና እኛም ልጆችህ ዳግም በጠላት እጅ በጠላትም አገዛዝ ወድቀናልና።
አርሰን ማምረት ነግደን መኖር አልቻልንምና። በገዛ ቀያችን በገዛ ሀገራችን ባይተዋር
ተደርገናልና። ጎረቤትን በጎረቤት ወንድምን በወንድም ዘርን በዘር ላይ የሚያነሳሳ
የሚያናክስ የሚያጫርስ መቅሰፍት ወሮናልና። ደግሞም ለዘመናት በሃይማኖቶቻችን
ዕምነት ልዩነት ሳይሆን በአንዲት ሀገር ልጅነታችን በኢትዮጵያዊነት ዜግነታችን ተከባብረን
ጠላትን በጋራ መክተን ባንዲራችንን በጋራ ከፍ አርገን ተሳስበን ተፈቃቅረን በኖርንባት
ኢትዮጵያችን እነሆ እስላምና ክርስቲያን እያሉ አበጣብጠው ሊያጫርሱን፤ ከፋፍለው
ሊበትኑን ሌት ተቀን እንቅልፍ ያጡ የጥፋት ሳጥናኤሎች ከበውናልና።
አቤቱ ጨለማ ዘመን ውስጥ ገብተን ጨለማ ውጦናልና ጴጥሮስ ሆይ እኛንም ብርታት
ስጠን። እንሸሸግበት ጥላ እንፀናበት ልብ አማልደን። እነሆ ከምስራቅም ከምዕራብም አጋር
የለን። ብቻችንን ነን፤ ኢትዮጵያም ያለኛ ማንም የላት። የኢትዮጵያችንን ሞቷን እኛ
ሞተን በሞታችን ህይወት እንድንሆናት እርዳን፤ አዎ! ብቻችንን ነን ጴጥሮስ አንዳች አጋር
የሌለን።
  አዎ! የኛ ዘመን የከፋ ሆኗልና ኢትዮጵያም ጠባቂ የላትምና። እነሆ በጎቹን ወደ መስክ
ያሰማራ እረኛ ከግራና ቀኝ ኮረብቶች ተኩላና ቀበሮ እያደቡ ቢመጡበት ምን ያደርጋል?
መልካም እረኛ፤ ስለ በጎቹ የኖረ እረኛ በጎቹን ሰብስቦ ከቀበሮና ተኩላ ያሸሻቸዋል። በጎቹን
ከጥፋት ያድናቸዋል፤ ከቀበሮና ተኩላ መንጋጋ ይከላከላቸዋል።
 እንግዲህስ በኛ ዘመን ኢትዮጵያ ጠባቂ እረኛ አጥታለችና። ቀበሮና ተኩላ ሆድዕቃዋነንና
ማንቁርቷን ነክሰዋታልና። ግራዚያኒያዊ አገዛዝ ግፍና ሰቆቃ ማጅራቷን ቁልቁል
ረግጧታልና። የልጆቿ ዋይታ የእናቶች እንባ የአረጋውያንም ሀዘን በርክቷልና።  እነሆ ደግሞም አባታችን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሆይ! ኢትዮጵያ የመንፈስ እረኛም
አጥታለችና። የሃዋርያቱን ስም የያዙ፤ በሃዋርያቱ ህይወት ያልኖሩ ስለ ቃሉ ስለ መስቀሉ
እንደ ሃዋርያቱ የሥጋን ፍዳና ስቃይ ይቀበሉ ዘንዳ ያልወደዱ አንድም በመኻላችን ያሉ
አንድም ጥለውን የተሰደዱ አዎን እነርሱ ያንተን የአባታችንን ፈለግ ያልተከተሉ ህዝቡን
ለቀበሮና ተኩላ ኢትዮጵያንም ለደመኛ ጠላቷ አጋልጠዋልና።
  አቤቱ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ሆይ! የኢትዮጵያ መከራ የኛም የልጆችህ ፈተና
በዝቶብናልና፤ ፅናትና ብርታትን  ከቸሩ መድሃኔዓለም አማልደን። የቁም ሞት ከመሞት
ታደገን። ከኢትዮጵያ አምላክ አስታርቀን…አዎ! ብቻችንን ነን፤ ከምስራቅም ከምዕራብም
አጋር የለን።
ወዳጃችን ዲበ! እነሆ ደግሞ በማስከተል ማርሻል ሮዴልፎ ግራዚያኒን እናቀርባለን፤
ፀጋችን በታሪካዊ ተውኔቱ ካነጠበልን ቀንጭበን።
“…’የሊቢያው ጅብ የአዲስ አበባው ቄራ አራጅ’ በሚል ቅጥል የተሰየመው ሮዴልፎ እሳት
የላሰ የጦር ዘዴኛም ነው ይባላል። የመንፈስ ንፍገት ቁጣ ድምፀ አጋኖና ጭካኔ ያነፀው
ሮዴልፎ በስድስት ጫማ ከአራት ኢንች ቁመት ላይ አካለ ጥጥርና ደንደሳም ግልፍተኛና
ችኩል ነው። መጠቅ ያለ የሲቃ ሳቅ የሳቀው የሊቢያን አርበኞች መሪ ኦማር ኡሉ
ሙክታርን ሰማኒያ ሺህ ወታደሮች ተሽከርካሪ ገሃነም ይሰኙ በነበሩ በትሬንታ ኳትሮዎች
መኻል የኤሌክትሪክ ሽቦ አቀጣጥሎ እያጠመደ በፈጃቸው ጊዜ የተቀሩትን በጆንያ ከትቶ
ከየካፋ በሰቀላቸው ጊዜ፤ እንዲሁም የካቲት 12 1929 ዓ/ም የአዲስ አበባን ህዝብ በእሳት በ
አካፋና በጦር መሳሪያ ባስፈጀው ጊዜ ነው ይባላል።…አልፎ አልፎ የበረሃው አሳማ በሚል
ስም የሚጠራው ሮዴልፎ፤ ሙሶሎኒ ኢትየዮጵያን ከነገሌ በኩል ሊወር
ሲያስታጥቀው…የጦርና የመርዝ ጢስ ወታደሩ መሪ ነህ ብሎ ሲሾመው፤ ‘የኢትየዮጵያን
ምድር የምትፈልጋት ከነህዝቧ ነው ወይስ ያለህዝቧ?’ ብሎ አፌዘ ይባላል።…”እነሆ
በፀጋችን ብፅር የተነደፈው ሮዴልፎ ግራዚያኒ ይህን ይመስላል።
“እግዚኦ! ማህረነ ክርስቶስ’ አሉ እትዬ አቻሜ እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ዘርግተው።
“ኪራላይሶ” ሁላችንም በአንድነት።
“እግዚኦ! ኢትዮጵያን በቃሽ በላት”
“ኪራላይሶ”
“እግዚኦ! ልጆቿን ከመበታተን አድን”
“ኪራላይሶ”
ቀጥሎ ዝምታ። እንደ መቃብር የከበደ ዝምታ ለጥቂት ጊዜ በመኻከላችን ሰፈነ።
ወዳጃችን ዲበ!
ግራዚያኒ ከአረመኔ ቁንጮዎች አንዱ አረመኔ ነበር። ቂመኛ። ሙሶሎኒ ግራዚያኒን ወደ
ኢትዮጵያ ያዘመተው ለበቀል ነበር። አድዋ ላይ ጣልያን ተዋርዳለች። አድዋ ላይ ድፍን
አውሮፓ ተዋርዷል። በአድዋ ድል ድፍን ቅኝ ገዢ ሁላ ነጭ ላብ አልቦታል። የአድዋ ድል
ደወል ከተራራ ተራራ እየተላተመ በደንና በጉድባው እያስተጋባ ከውቅያኖስ ውቅያኖስእያቆራረጠ በግፍ ቀንበር በቅኝ ገዢዎች አገዛዝ ስር በወደቁት ህዝቦች ሁሉ ዘንድ ተሰማ።
የአድዋ ደወል ጥሪ በአፍሪካ ተራራዎች አስተጋባ። በላቲን አሜሪካና በካሬቢያን ሸለቆዎች
ሁሉ ተናኘ። ኢትዮጵያ ገዘፈች። ያፄ ምኒልክ ስም ምድረ ኮሎኒያሊስትን አርበደበደ።
አንዘፈዘፈ። ለሶስት ሺህ ዘመን  ዓለምን ረስታና በዓለም ተረስታ  ኖረች - የተባለችው
ኢትዮጵያ፤ በአባ ዳኘው እምዩ ምኒልክ በዓለም ዳርቻዎች ሁሉ ስሟ በክብርና በፍርሃት
አስተጋባ። አነሆ ኢትዮጵያ ስሟ ለነፃነት ናፋቂዎች ቀንዲል ብርሃን፤ ለኮሎኒያሊስቶች
ደግሞ ነበልባላዊ እቶን ሆነ። እነሆ በምሥራቅ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተብለው
በሚታወቁ ጥቁር ህዝቦች የአውሮፓ መንግሥት አካል የሆነ የፈረንጅ መንግሥት በምድረ
ኢትዮጵያ በአድዋ የጦር አውድማ ላይ ድል ሆኗልና!! ይህ ታሪክ የተሰራው በ1888 ዓ/ም
በወርሃ የካቲት ነው።
  “አዎ!” አለ አስተማሪ አለሙ ዓይኖቹን ከፊት ለፊት ግርግዳ ላይ ከሚገኘው የብፁዕ
አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ፎቶግራፍ ተክሎ። “አዎ! ታላቋ ሮማ እያለች ራሷን ስታሞካሽ
የኖረቸው ጣሊያን ከአድዋ በዃላ የሀፍረትና የሀዘን ማቅ ለበሰች። ማቋን ሳታወልቅ ለአርባ
ዓመታት ማቀቀች። ለአርባ ዓመታት የመርዝ ጋዝ ስትቀምም፤ ቦንብ ሰርታ ስታከማች፤
የባሩድ ዘር ስታመርት፤ መትረየስ ስትወለውል ቆየች፤ ኢትዮጵያን በመውረር ቂሟን
ልትወጣ እያደባች።
“በ1928 ዓ/ም ጣሊያን አወጀች፤ ማቃችንን የምናወልቅበት ኢትዮጵያን የምንበቀልበት
እነሆ ወቅቱ አሁን ነውና የጣሊያን ህዝብ ሆይ ክተት! - አለች። እነሆ ሮዴልፎ ግራዚያኒን
ከነመርዝ ጋዙ ከነቦንቡ ከነመትረየሱ ከነአጋሰስ ግሳንግሱ ሁሉ ጋር…ኢትዮጵያን አቃጥላት
ደማችንን ተበቀላት ብላ ላከችው። እና ግራዚያኒም ለአለቃው ለቤኒቶ ሙሶሎኒ
‘ኢትዮጵያን የምትፈልጋት ከነህዝቧ ነው ወይስ ያለህዝቧ?’ አለው፤ በደም ጎርፍ ሲያዋጃት
እየታየው።
  “አዎ! የውርደት ማቃቸውን ያላወለቁ ጥቁር ሸሚዝ የለበሱ ቄራ አራጅ ፋሽስት
ወታደሮች በሊቢያው ጅብ በአዲስ አበባው ቄራ አራጅ እየተመሩ ኢትዮጵያን አቃጠሉ።
ህዝቡን ፈጁ። ኢትዮጵያ ግን ነዳ አልከሰመችም። ኢትዮጵያውያንም አላለቁም። ከምድረ
ገፅ አልጠፉም። ፋሽስቶች አዲስ አበባን እንደተቆጣጠሩ የዛኑ ቀን የጣሊያኑ ፋሽስት
መንግሥት መሪ ቤኒቶ ሙሶሎኒ በሮማ አደባባይ “ኢትዮጵያ የጣሊያን ሆናለች” ሲል
አወጀ። ወዲያውም አዲስ አበባ ባስተላለፈው ቀጥተኛ ትእዛዝ ‘በዓለም ፊት ለታላቋ ሮማ
መዋረድ ተጠያቂ የሆነው ምኒሊክ አራዳ ላይ የሚገኘው ሀውልቱ በአስቸኳይ ተነስቶ
ወደፊት ተጨማሪ ትእዛዝ እስከሚተላለፍ ሰው በማያየው ስውር ቦታ ተቀምጦ ብረቱ ጥበቃ
እንዲደረግ” አለ።
  “እነሆ ፋሽስቶች አባ ዳኘውን በህይወት ባያገኙ ሀውልታቸውን በውድቅት ሌሊት ከአራዳ
ላይ አንስተው ሀውልት አሰሩ፤ ሀውልት ማረኩ። የአዲስ አበባ ሕዝብ በማግስቱ የእምዬ
ምኒሊክን ሀውልት አራዳ ላይ ቢያጣ ሀገር ለገር ተጠራርቶ እሪ ብሎ አለቀሰ፤ የደም እንባ
የቁጭት እንባ አነባ። ምኒሊክ ያረፈበትን ሀውልት አፈር ዘግኖ አፈር በትኖ ማለ።
ለፋሽስቶች ብገዛ ይህ አፈር እሾህ ቆንጥር ሆኖ ይጓጉጠኝ፤ እቶን እሳት ሆኖ ይለብልበኝ
አለ፤ እና አቅም ያለው ጉልበት ያለው ጫካ ገባ። አርበኛ ሆነ። አቅም ያጣው ደካማው
የአርበኖች ዓይንና ጆሮ ሆነ። እና ፋሽስቶችን የቁም ስቅል ያሳይ ገባ።
  “ፋሽስቶች አርበኞችን በመርዝ ጋዝ ቢለበልቧቸውም፤ በመትረየስ ቢቆሉዋቸውም፤
በቦንብ ቢያቃጥሏቸውም፤ ለመቀጣጫ እያሉ በየዛፉ ቢሰቅሉዋቸውም…ግና ሌሎች
አርበኞች ተተኩ። የኢትዮጵያን ሠንደቅዓላማ ከፍ አርገው እያውለበለቡ ‘እንቢ ለጣሊያንእንቢ ለፋሽስት፤ ጥራኝ ጫካው ጥራኝ ዱሩ…’ ብለው የነፃነት ፋኖ ሆኑ።” አለና አስተማሪ
አለሙ በረጅሙ ተንፍሶ ዙሪያ ገባውን ቃኘ።
  “ያም ሆኖ” ሲል ቀጠለ ኢንጂነር ዋቅጅራ “ያም ሆኖ የግራዚያኒ የበቀል ደም ጥማት
በቀላሉ ሊቆርጥለት አልቻለም፤ ቅዠቱ አልሰመረለትምና። ኢትዮጵያን ቢይዝም
ሊቆጣጠራት ግን አልቻለም። ባንዲራዋን ቢያወርድም፤ ባንዲራዋን ቢያዋርድም ግና
በየሸለቆው በየጉድባው በየተራራው በአርበኞች ከመውለብለብ ማገድ አልሆነለትም።
ሹምባሽ ቢያግተለትልም የአርበኞችን ቅስም መስበር ወይም የአርበኞችን እንደ ንብ
ሠራዊት ማመም ማቆም አልቻለም። መርዝ ጋዙ ኢትዮጵያውያንን ከምድረ ገፅ
አላጠፋም። እንደ ሀምሌ ዝናብ የወረደው ቦንብ የአርበኞችን መትረየስ ላንቃ አልዘጋም።
  “በኢትዮጵያ መደፈር የበገኑ በባንዲራዋ መዋረድ የቆሰሉ የነፃነት ቀናዒ የሆኑ
የኢትዮጵያዊነታቸው ፍቅር ያነደዳቸው የኤርትራ ተወላጅ ወጣት ኢትዮጵያውያን አብረሃ
ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የካቲት 12 ሺ ዘጠኝ መቶ ሃያ ዘጠኝ ዓ/ም ግራዚያኒና ግብረ
አበሮቹ በተሰበሰቡበት አድፍጠው በመጠጋት አስር የእጅ ቦንቦች ጆሮ ግንዳቸው ላይ
አከታትለው ቢለቁባቸው ግራዚያኒ በ365 የቦንብ ፍንጥርጣሪዎች ቆስሎ እንደ አይጥ
ተጠቅልሎ ወደቀ። የፋሽስት አየር ሃይል ጄኔራል ሊኦታ እግሩ ተቆረጠ። ሌሎችም ቆሰሉ።
ግራዚያኒ ይቁሰል እንጂ አልሞተም፤ መላከ ሞትን ግን ተመለከተ። ይህ ታላቅ ታሪክ
የተፈፀመውም በገነተ ልዑል ቤተመንግሥት ዃላ ቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ
ነበር። እነሆ ደመ ፍሉው የሊቢያው ጅብ የፋሽት ቤኒቶ ሙሶሎኒ ቀኝ እጅ ፋሽስቱ
ሩዶልፎ ግራዚያኒ አበደ። የውሻ እብደት አበደ።
  “ፋሽስቶችም አወጁ። ጥቁር ለባሽ ወታደሮቻቸውን ሰብስበው ለሶስት ማዕልትና ለሶስት
ሌሊት አዲስ አበባን አቃጥሏት ህዝቡንም ፍጁት አሏቸው። እነሆ አዲስ አበባ ለሶስት
ማዕልት ለሶስት ሌሊት ነደደች። አዛውንት ህፃናት እመጫት እርጉዝ አካለ ስንኩል አይነ
ስውር ሴት ወንድ በሽተኛ ጤነኛ ማንንም ከማንም ሳያማርጡ ኢትዮጵያዊን ሁሉ ባገኙበት
በቆንጨራ በአካፋ በሳንጃ በመትረየስ ፈጁት። በየጎጆዎች የተጠለሉትን ድፍን ቤተሰብ በር
እየዘጉ ከነነፍሳቸው አቃጠሏቸው።
  “ሰላሳ ሺህ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ላይ ረገፉ። ሰንበት ብለው ፋሽስቶች አብረሃና
ሞገስን አፈላልገው ቢያጧቸው ሹምባሾች ሹክ ቢሏቸው ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም ዘልቀው
አብረሃና ሞገስ የተሸሸጉት እዚህ ገዳም ነውና አቅርቧቸው ብለው መነኮሳቱን ቢወጥሯቸው
‘አናውቅም’ አሏቸው መነኮሳቱ ረጋ ብለው። እና በዛኑ ቀን በዛው ዓመት በወርሃ ግንቦት
በዋለው በአቡነ ተክለሃይማኖት ቀን መነኮሳቱ የተክልዬን ቀን ሊያከብሩ እንደታደሙ ለወሬ
ነጋሪ ሳያስቀሩ 297 መነኮሳትንና 23 አገልጋዮችን በሙሉ ፋሽስቶች በመትረየስ
ፈጁዋቸው።…እና እንግዲህ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ፋሽስት ወራሪን በየአድባራቱ
ማውገዛቸው ለፋሽስት አትንበርከኩ፤ ለፋሽት አትደሩ፤ ለፋሽስት አትገዙ እያሉ
ማስተማራቸው፤ የዃላ ዃላም እንደ ሠማዕታቱ እንደ አርበኞቹ ሁሉ መስዋዕት መሆናቸው
ሌላም አይደል ትርጉሙ ለነፃነት ለባንዲራ ለኢትዮጵያ ትንሳዔ ነው።” አለ ዋቅጅራ
በተሰበረ ድምፅ ሠማዕታቱን እያስታወሰ።
  ዝምታ። የሀዘን ዝምታ። የትውስታ ዝምታ። ሠማዕታቱን፤ አርበኞችን፤ የደብረሊባኖስ
ገዳም መነኮሳቱን አቡነ ጴጥሮስን በዝምታችን አሰብናቸው።…
አየህ ዲበኩሉ፤ ይህ ታሪካችን ነው። ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ካደረጓት የሶስት ሺህ ዘመን
ታሪኮች መኻል አንዱ ታሪካችን። እኛ ኢትዮጵያውያን በታሪካችን አናፍርም። ታሪካችንንበታሪክነቱ ከነሰንኮፉ ከነፍሬው፤ ከነድክመቱ ከነብርታቱ፤ ከነውበቱ ከነምትሃቱ፤ ከነድቀቱ
ከነግዝፈቱ የኛ የኢትዮጵያውያን ታሪክ ነው እንላለን።
  እነሆ ዛሬ ዘመን የገነኑ ግርሻዚያኒያን ግና ታሪክ የላችሁም ይሉናላ! ጉድ ነው።
የኢትዮጵያ ዕንብርት መዲና አዲስ አበባ ላይ ተቀምጠው፤ እምዬ ምኒልክ የቆረቆሩዋት
አዱ ገነት ላይ ቂብ ብለው፤ ሩዶልፎ ግራዚያኒ ያነደዳት ሸገር ላይ በሊመዚን ሽር ብትን
እያሉብን - አድዋ ለኢትዮጵያውያን ምናችሁ ነው? አሉን። አድዋ የእናንተ አይደለችም
አሉን! አፋቸውን ሞልተው አይናቸውን አፍጠው። አዎ፤ የግርሻዚያኒዎች አለቃ መለስ
ዜናዊ - አድዋ ለኢትዮጵያ አድዋ ለእናንተ ለኢትዮጵያውያን ምናችሁ ነው? ሲል ጠየቀን፤
ጣሊያን እንኳን ያልካደውን።
በ1888 ዓ/ም ጣሊያን አድዋ ላይ ጦርነት ገጥሞን ብንደቁስው፤ በድፍን ዓለም ዜናው
ሲዛመት “በንጉሥ ምኒልክ የተመራው የኢትዮጵያ ጦር በኢትዮጵያ ግዛት አድዋ ላይ
የአውሮፓን ሀገር የጣሊያንን ጦር ድል አደረገው” ብለው ነው ፈረንጆቹ ራሳቸው ታሪኩን
የዘገቡት። በምድረ ጣሊያንም ቢሆን በራሷ ቋንቋ የራሷን ታሪክ የራሷ ዜጎች ሲፅፉ፤ “ታላቅ
ውርደት በኢትዮጵያ ተዋረድን። የሃያሏ ጣሊያን ጦር በምድረ ኢትዮጵያ አድዋ ላይ
በንጉስ ምኒልክ ከተመራው ያልሰለጠነ ዃላ ቀር ህዝብ ጋር ጦርነት ገጥሞ ተሸነፈ። ሮማ
በታሪኳ እንደዚህ ተዋርዳ በፍፁም አታውቅም።” ብለው ነበር የሀዘን እንጉርጉሮ የሀዘን ሙሾ
ያወረዱት፤ ለአርባ ዓመታት የሀዘን ማቅ ያጠለቁት። ታዲያ እንዴት ቢሆን በየትኛውስ
የታሪክ መዝገብ ምንስ ቢታሰብ ነው አድዋ ለእናንተ ለኢትዮጵያውያን ምናችሁ ነው?
ያሉን - ህዋሃታውያን ሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻ ወግራዚያኒያውያን?
  እኒህ ልበ ጥጥር አፈ ጮሌ ለራሱ አዋቂ ወገኑን ናቂ መልኩ የኢትዮጵያ ልቡና ግብሩ
የጣሊያን የሆኑ ጨልሂ ህወሃት ወባሻ ግርሻዎች - አዋጅ አስነገሩ በሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና
ዓ/ም - እንዲህ ሲሉ፤
  “የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! ጠላት ሲመጣብህ ጨርቄን ማቄን ሳትል ለሀገርህ ዳር ድንበር
መከበር ቀፎው እንደተነካ ንብ መትመምህ ከ አባቶችህ በደም የወረስከው ነውና እነሆ
ሻዕቢያ የሀገርህን ዳር ድንበር አቋርጦ ትግራይ ገብቶ ባድመ ላይ መሽጓልና ዛሬ ነገ ሳትል
ተነስ” አሉን።
  የህወሃቱ ሜዠር ግርሻዚያኒ መለስ ዜናዊ በለመደው ያልተገራ አንደበቱ እንደ አድዋ
ሁሉ ‘ባድመ ለእናንተ ለኢትዮጵያውያን ምናችሁ ናት?’ ስለምን አላለንም?
  ይልቁንም “ድረሱላት ለትግራይ ድረሱላት ለባድመ ያለ እናቷ ኢትዮጵያ ያለወገኗ
ኢትዮጵያውያን ትግራይስ ማንም የላት። እና ለባድመ ኢትዮጵያውያን ሆይ
ድረሱላት…ክተቱላት” ነበር ያሉን ህወሃታውያኑ በሬዲዮ በጋዜጣ ሲጠሩን።
  ግና እኛ እንደነሱ አይደለንምና በሀገራችን ዳር ድንበር ጉዳይ ለመጣብን ግራና ቀኝ
አንልም። ሀገር ሲወረር መልካው ሲናጋ የኢትዮጵያ ህዝብ ንብ ነው። ተርብ። በበደሉት
ላይ አቂሞ ለሀገሩ ዳር ድንበር ከመሰዋት አያፈገፍግም።
  አድዋ ለእናንተ ምናችሁ ነው? ስላሉን የአካላችን ክፋይ በሆነችው ትግራይ አቂመን
አኩርፈን ባድመ ላይ ከመሰዋት አልታቀብንም። ሰው በራሱ ላይ ያቄም ሰው በራሱ ላይ
ያኮርፍ ዘንዳ ይቻለዋልን? እና ከተትን። ከደቡብና ከምስራቅ ከምዕራብና ከመሃል ሀገር
እንዲሁም ከሰሜን (እነሱ ህወሃታውያኑ ግን ነፍጠኞች ነው እሚሉን) ከያለንበት
ኢትዮጵያውያን ተጠራርተን ወደ ትግራይ ክፍለሀገራችን አቀናን። ባድመ ዘመትን።
ሻዕቢያን ገጠምን። ወራሪን መከትን።  “አጨራረሳችን ግን ያሳዝናል” ሲል ጀመረ ፈረንጅ አምላኩ ያቆጠቆጠ ጉንጩን እያሸ።
“ደማችን ደመ ከልብ መስዋዕትነታችንም ከንቱ ሆነ። በኢትዮጵያውያን ታሪክ ውስጥ ወደር
ከማይገኝላቸው የህወሃት የአገዛዝ ዘመን ወንጀሎች አንዱ የዚህ ጦርነት ውጤት ነው።
የፈሰሰው ደም የተከሰከሰው አጥንት የከሰረው ኢኮኖሚ ውጤቱ ምንድን ነው? ህወሃትና
ሻዕቢያ እንደለመዱት ከመጋረጃ በስተጀርባ ተገናኝተው ተስማሙ። የኢትዮጵያ ጦር በዚህ
ጦርነት ሻዕቢያን አሳምሮ መቅጣት ብቻ ሳይሆን ያለፍትህ ያለፈቃዳችን በፊርማ
የተነጠቅነውንም ግዛታችንን የአሰብ ወደብን ማስመለስና መጠበቅ ይችል ነበር።
  “ዕድሜ ለግርሻዚያኒ መለስ ዜናዊ ሻዕቢያ በደማችን ይበልጥ ካበተ። በመስዋዕትነታችን
ይበልጥ አተረፈ። የዚያ ሁሉ ሺህ ኢትዮጵያዊ ወታደር የፈሰሰው ደም ሳይደርቅ የወደቀው
ሬሳ ሳይሰበሰብ የቆሰለው ሳይታከም ህወሃት ኢትዮጵያን አልጀርስ ላይ በይፋ ለሻዕቢያ
ደግሞ ሸጠ። በሰላሙም በጦርነቱም ኢትዮጵያን እንደጲላጦስ ደጋግሞ ካደ። ለሻዕቢያም
ደግሞ ደጋግሞ ሸጠ አሻሻጠ” አለ ፈረንጅ አምላኩ በቁጭትና በብግነት።
ወዳጃችን ዲበ! ይህ መቼም አሳዛኙና አሳፋሪው ያለንበት ዘመን እውነታ ነው። በአንድ
ወገን አባ ዳኘው እምዩ ምኒልክ ዕድሜያቸውን ሙሉ ከላይ እታች ደክመው ዳር ድንበሯን
አስምረው አስከብረው በገነቧት ኢትዮጵያና በቆረቆሩዋት መዲና ተቀምጠው ‘የኢትዮጵያ
መንግሥት ነን’ እያሉ፤ በሌላ ወገን አፄ ምኒሊክን ቅኝ ገዢ ነፍጠኛና አረመኔ ነው እያሉ
ይከሳሉ፤ ይወነጅላሉ፤ ታሪክ ያጎድፋሉ እነሱና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ሹምባሽ ባሻ አባ ድርሻ
ፀሀፍቶቻቸው ሁሉ። ‘ማን ላይ ተቀምጠሽ ማንን ታሚያለሽ?’ አሉ ጥንታውያኑ ሲተርቱ?!
  በአንድ ወገን ‘አድዋ ለናንተ ምናችሁ ነው?’ እያሉ፤ በአንድ ወገን ባድመ ዝመቱ እያሉ፤
በአንድ ወገን የሀገሪቱን ለም መሬት ሊዝ እያሉ ለአረቡ ለህንዱ ለቻይናው ለሃምሳ ዓመት
ለመቶ ዓመት እየቸበቸቡ፤ በአንድ ወገን የአኝዋክን ህዝብ የወልቃይት ጠገዴን ህዝብ
የአፋርን ህዝብ የደቡቡን ህዝብ የኦሮሞን ህዝብ በዘረኝነት ዘር የማፅዳት ዘመቻቸው ለጆሮ
ዘግናኝ ኢሰብአዊ ግፍና እልቂት እየፈፀሙ…በደም ፋፍተው በደም ከብረው …የኸው አሉ
ህወሃታውያኑ ከዘመን ዘመን ጫንቃችን ላይ ተንፈራጠው።
  ሲያሻቸው በሬዲዮ ቴሌቪዥን ቀርበው ሲያሻቸውም አደባባይ አቁመውን ከፍ ዝቅ
አርገው ባልተገራ አንደበታቸው እያዋረዱን እየሰደቡን፤ ሲያሻቸው ቅራቅንቦ ሰርተው ህዳሴ
እንቶ ፈንቶ ብለው ሲጫወቱብን ሲሳለቁብን፤ ሲያሻቸው ሰብስበው ቃሊቲ ወስደው
ሲያጉሩን፤ ደግሞ ቅልልቦሽ ሲሉብን ሽማግሌዎች እየላኩብን እንደ ልጅ እንደ ማሙሽ
እንደ ማሚት ‘…ሁለተኛ አይለምደኝም..’ አስፈርመው አፈራርመው ገበጣ ሲገብጡብን፤
ሲያሻቸው ምረጡ እያሉ በእንቁልልጭ ጨዋታ ሲያጃጅሉን በጢቢ ጢቢ ሲያጎኑን ሰቅለው
ሲያወርዱን…ይኸው አሉ ዘመንን በዘመን አስቆጥረው…ይኸው እኛም አለን እንላለን
ከዘመን ዘመን ግርሻዚያኒዎችን ተሸክመን።
  “ይህ ሁሉ እርግጥ ነው” አለ ሽኩር ከፔርሙዝ ሻይ በፊንጃል ቀድቶ ከተጎነጨ በዃላ
“ይሁሉ ሀቅ ነው። የትላንት የዛሬ ትዕይንት ድራማ ነው። ወንድሞቼ፤ እኔን የሚያሳስበኝ
አንድ ነገር አለ ዘወትር የሚረብሸኝ። መቼም እኒህ አራት ኪሎ ቤተመንግሥት የገቡት
ሰዎች ደንቆሮ መሃይምናን አይደሉም። እነርሱ ሳያውቁ በስህተት የሰሩት ወይም የሚሰሩት
ነገር ፈፅሞ የለም። አድዋ ለእናንተ ምናችሁ ነው? ሲሉ መቼም ስለአድዋ ገድልና ታሪክ
ሳያውቁ ቀርተው አይደለም። እንኳንና እነርሱ ዛፍ ሳር ቅጠሉ ኢትዮጵያ የበቀሉ አንደበት
ቢኖራቸው ይመሰክራሉ። አሠብ የእናንተ አይደለችም፤ አሠብ የኢትዮጵያ ሆና አታውቅም
ሲሉንም መቼም የታሪክና የኢኮኖሚ መሃይምናን ሆነው አይደለም። እነዚህ እንደጣሊያንየሚያስቡ፤ እንደ ጣሊያን የሚሠሩ፤ እንደ ጣሊያን ያቄሙ እንደ ጣሊያን የሚበቀሉ
በመሆናቸው እንጂ።
  “ወንድሞቼ ኢትዮጵያ ወደር አልባ ቀውስ ውስጥ ወድቃለች። እንደ ዘመነ መሳፍንት
ሁሉም በየክልሉ በየጎጡ ልንገስ ነፃ ልውጣ ይላል። ሁሉም የየጎጡን ፓርቲ ግንባር ህብረት
ምናምን እያለ ፈጥሯል። ይህን የፈጠሩት የኔ ቢጤ ነግዶ ሠርቶ አርሶ…አዳሪዎቹ ብዙሃኑ
የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለንም። ተማሩ ተመራመሩ የተባሉት ናቸው። ከገዢዎቻችን ጋር
አፍ ለአፍ ገጥመው ሲመክሩ ሲያማክሩ አብረው ሲቆርሱ አብረው ሲጠጡ በየዘመኑ
ኢህአዴግን ያጀቡት ናቸው የልብ ልብ የሰጡት ያተበቱት። የተማሩት ናቸው እንደ
እንጉዳይ ድርጅት አፍልተው ህብረት ያሳጡን፤ የበጠበጡን፤ ግራ እሚያጋቡን። እንጂማ
እኛ ያው ህዝብ ነን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ።
  “እንግዲህ በዚህ አያያዛችን ነገ ደግሞ ሌላው ‘ጊዜ የሰጠው ቅል” ሲነግስ መቅደላ ለናንተ
ምናችሁ ነው ሊለን ነው? መቼም እንደ ምኒሊክ ሁሉ ቴዎድሮስንም እንዘክራለን።
እናከብራለን። ስለ መይሳው አፄ ቴዎድሮስ እናስተምራለን። እንፅፋለን። ቴዎድሮስ
የኢትዮጵያ መቅደላም እንደ አድዋ የኢትዮጵያ እንደ ባድመም የኢትዮጵያ ናቸውና።
  “እስቲ አስቡት በተያዘው አካሄድ ነገ ደግሞ ሌላው ተነስቶ ላሊበላ ለናንተ ምናችሁ ነው
ቢለንስ? እርግጥ ነው በእድሜያችን ‘አዲስ አበባ የእናንተ አይደለችምና ጊዜያችን ሲመጣ
እያንዳንድሽ ተመንጥረሽ ትወጫለሽ’ የሚሉ መኖራቸውን ሰምተናል በዓይናችንም
አይተናቸዋል። ወንድሞቼ ሀገራችን በተማሩ ህመምተኞች መርፌ በተጠቀጠቀችው መርዝ
ተመናምና ተጎሳቁላ አጓጉል ሆና እንዳትቀር ነው ስጋቴ፤ ፍርሃቴ፤ የዘወትር ጭንቀቴ።
“እንጂማ እኛ ህዝብ ነን። የኢትዮጵያ ህዝብ። ለሀገራችን ነፃነት ቀናዒ። ለጠላትም
መቅሰፍት። የምንፈልገው በተፈጥሮ ባገኘነው በኢትዮጵአዊነት የዜግነት መብታችን
በሀገራችን በሠላም በፍቅር ተከባብረን በየክልሉም በነፃነት ተዘዋውረን አርሰን ነግደን
መኖር ነው። የሁሉም ዜጎቿ የሆነች ከማዕዷም ሁላችንም የምንካፈልባትን ኢትዮጵያን
መገንባት እንፈልጋለን። ግን እንዴት? አውራ የለንም።
“እኛ ለሀገራችን ሠላምና ዕድገት መስዋዕትነት ከመክፈል ወዳ ዃላ አንልም። ግን መሪ
የለንም፤ ለኢትዮጵያና ለኛ የቆመ መሪ። በታሪካችን ሁሌም ከመሪያችን ጎን ቆመን ነው
ታሪክ ስንሰራ የኖርነው። ዛሬ ታሪክ ለመስራት ጥላ የለንም። ዛሬ ታሪክ ለመስራት ታሪክ
የሚያሰራ አውራ ኢትዮጵያ አጥታለች። ወንድሞቼ ሀገራችን እንደ አባታችን ብፁዕ አቡነ
ጴጥሮስ ግፈኞችን አውግዞ ግፈኞችን ገዝቶ፤ ህዝቡንም ለኢትዮጵያ ጠላት አትገዙ የሚል
የመንፈስ አባት የላትም። ሀገራችን የመንፈስም የሥጋም መሪ አጥታለች።” አለና
የቀዘቀዘውን የፊንጃል ሻይ አንስቶ በአንድ ትንፋሽ ጨለጠ። ለጥቂት ሴኮንዶችም ዝምታ
ሰፈነ። ቀጥሎ፤
  “እግዚኦ ማሀረነ ክርስቶስ” አሉ እትዬ አቻሜ።
  “ክራላይሶ” እኛ።
  “አቤቱ ኢትዮጵያ ዛሬም እጆቿን ወዳንተ ዘርግታ ትማለድሃለችና የኢትዮጵያ አምላክ
ሆይ ተማለዳት”
  “አቤቱ ተማለደን”  “አቤቱ ኢትዮጵያ ግፍና መከራ በዝቶባታልና ብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ሆይ
ህዝቧንና ኢትዮጵያን በቃ ይል ዘንድ ከፈጣሪያችን አማልደን”
  “አቤቱ አማልደን”
  “አቤቱ ሠላምና ፍቅር ርቀውናልና፤ አቤቱ መቻቻልና ህብረት ሸሽተውናልና፤ አቤቱ
ሠላምና ፍቅር መቻቻልና ህብረትም ከኢትዮጵያውያን ልብ ይኖሩ ዘንዳ የሠማዩ አባታችን
ሆይ እንማልድሃለን”
  “አቤቱ እንማልዳለን”
  ደግሞ ከጥቂት ጊዜ ፋታ በዃላ፤
  “ልጆቼ!” አሉን እትዬ አቻሜ ሁላችንንም በየተራ ተመልክተውን ዓይናቸው ኒቂሴ ላይ
ቀርቶ። “ልጆቼ፤ እንግዲህ ጉባኤያችንን ከማሳረጋችን አስቀድሞ ብፁዕ አባታችን አቡነ
ጴጥሮስ ሐምሌ 22 ቀን 1929 ዓ/ም ከቀኑ በአምስት ሰዓት ላይ አራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ቤተክርስቲያን አጠገብ በፋሽስቶች ጥይት ተደብድበው ከመገደላቸው በፊት የተናገሩትን
የአደራና የውግዘት ቃል ብንሰማውስ?” አሉ ጥልቅ ሀዘን ባጀበው ድምፀ ቅላፄ።
  እነሆ ኒቂሴ የፀጋችንን ታሪካዊ ተውኔቶች መፅሀፍ ገልጣ ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት ከሚለው
የመጨረሻውን ትዕይንተ አንቀፅ በዝግታ ነገር ግን ጥልቀት ባለው የሀዘን ድምፀት ዐይኖቿ
በእንባ ተሞልተው አነበበች…
“እግዚአብሄር ይፍታችሁ፤ እግዚአብሄር ይፍታችሁ ልጆቼ፤ ለጠላቶቻችሁ ለፋሽስት
አትገዙ ልጆቼ፤…እንኳን እናንተ መሬቷም እንዳትገዛ ገዝቻለሁ፤ /በፀሎት/…እመብርሃን
ብቻዬን ነኝ ትዕዛዝሽን ተቆራኝኝ…ምላሴን የቃልኪዳኔ ምንጭ
አርጊየት፤…/በአደራ/…ልጆቼ በመንፈስ ጀምራችሁ በሥጋ እንዳታልቁ፤ ለሀገራችሁ
በመልካም ፍሬ ፈንታ አሜከላ እንዳትሆኗት፤…ለጠላታችሁ…አትገዙ…እንኳን እናንተ
መሬቷም እንዳትገዛ ገዝቻለሁ፤…ልጆቼ እግዚአብሄር ይፍታችሁ…” ሁላችንም በቅፅበት ከተቀመጥንበት ተንበርክከን፤ “አሜን አባታችን፤ እግዚአብሄር
ይፍታን፤ እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይማለዳት!…” አልን ግንባራችንን ከወለሉ አሳስመን
የብፁዕ አባታችን የአደራ ቃል በጆሯችን ዘልቆ በህሊናችን ጓዳ እያስተጋባ። …በኒቂሴ
ዐይኖች ሞልቶ የነበረው እንባ በተንበረከከችበት በፀጥታ እየወረደ ከወለሉ ላይ ይንጠባጠብ
ነበር…
  “እንግዲህስ ጉባኤያችንን እናሳርግ” አሉን እትዬ አቻሜ ቀጠሉና።
  እነሆ የጉባኤያችን መዝጊያ ሥነሥርዐቱና ፀሎቱ /ፀሎተ ጴጥሮስ/ አስቀድሞ
በመግቢያችን እንደገለፅንልህ ነው ሂደቱ። እና ፀሎተ ጴጥሮስ እንዳለቀ ሻማዎቹም
እንደጠፉ መብራት ከበራ በዃላ አቻምየለሽ ጎበና አሰናበቱን - እንዲህ ብለው፤
“ልጆቼ የኢትዮጵያ አምላክ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ የብፁዕ አባታችን አደራ ከናንተ ጋር
ይሁን፤ ለኢትዮጵያ ጠላት ከቶም አትገዙ፤ ለኢትዮጵያ ትንሳኤ በትግላችሁ ሁሉ የብፁዕ
አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ዕምነትና ፅናት ከናንተ ጋር ይሁን! በሚደርስባችሁ መከራና ስቃይ
እንግልትና እስር ሁሉ ብፁዕ አባታችንን አስቡ፤ የጭንቅ አማላጇን ድንግል ማርያምን
ተማለዱ፤ ብርታትና ሃይልን ታማልዳችዃለችና! ልጆቼ ከቀን ተኩላ ከሌሊት ጅብ ቅዱስገብርኤል ይጠብቃችሁ፤ እንግዲህ የኢትዮጵያ አምላክ ይከተላችሁ፤ በሠላም ወደየቤታችሁ
ግቡ!’
  “አሜን!”ወዳጃችን ዲበ! እነሆ ጉባኤያችን ተጠናቀቀ። አሁን የቀን ብርሃን ለምሽት ጊዜውን
አስረክቧል። የቤት ውስጥ መብራት ቢኖርም መንገዱን ጨለማ ውጦታል። እናም እትዬ
አቻሜንና እማማ ድንቡሎን እየተሰናበትን ተራ በተራ ጨለማው ውስጥ ገብተን ጉዞ
ጀመርን…ከመንገዳችን መጨረሻ ብርሃን እንዳለ እናውቃለንና…
  ይህንን መልዕክታችንን ፈረንጅ ሀገር ለሚገኙ ወገኖቻችን ታቀርብላቸው ዘንዳ
ፈቅደናል።
  የኢትዮጵያ አምላክ በሠላምና በጤና ጠብቆህ በዐይነ ሥጋ ለመገናኘት ያብቃን፤
ባለህበት ሠላምና ጤና ሁንልን! ናፋቂዎችህ የአራዳ ልጆች።
መጋቢት 2004 ዓ/ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ለአስተያየትዎ የመልዕክት አድራሻ ይኸውልዎ፤ mmtessema@gmail.com
ማስታወሻ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕረስ የፀጋችንን ታሪካዊ ሥራዎች በማሰባሰብ ‘ታሪካዊ
ተውኔቶች’ በሚል ርዕስ በአንድ ጥራዝ በማሳተም ለታሪክና ለተውልድ የሚዘልቅ ቅርስ በማቆየቱ
ሀገራዊና ዜጋዊ ምሥጋናችንን ከአክብሮት ጋር እናቀርባለን።

No comments:

Post a Comment