"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Wednesday 31 October 2012

መለስ እና የባነር ላይ ታሪኮቹ


የኢትዮጵያ ብዕሮች ህብረት
ፀሐፊ፦ ጥበበ አቢዮት
አዲስ አበባ አዲሱን ዓመትና መስቀልን የተቀበለቸው በአበቦች አጊጣና በችቦ ደምቃ ሳይሆን የአቶ መለስን ፎቶዎች በያዙ ሰፋፊ ባነሮች ተከፍና ነው፡፡ በመሆኑም 2005 ዓ.ምን ዘመነ ባነር ብየዋለሁ፡፡
ሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከአቶ መለስ ፎቶ ስር ልዩ ልዩ ጥቅሶች የሰፈሩባቸው ባነሮችን ከየመግቢያና መውጫ በሮቻቸው ላይ ማንጠልጠላቸው ግዴታ የተጣለባቸው ይመስላል፡፡ አንዳንዶቹማ የብረት አጥሮችን በሙሉ ባነር ዘርረውባቸው መስሪያ ቤታቸውን የልብስ ማስጫ አስመስለውታል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በህንፃዎቹ ግድግዳ ፖስተሮችን ለጣጥፈው ጭራሽ ፎቶ ቤት ለመሆን ጥቂት ቀርቷቸዋል፡፡ ኧረ ጋለሪ ሆነዋል ብል ይቀላል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አንስተን ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ስንወያይ “አንደ አጀማመራቸው ከሆነ ከምንበላው እንጀራ ላይም ሳይለጥፉበት አይቀሩም!” ብሎኛል እየተንገሸገሸ፡፡
በዚህ ዘመን የፕሮፓጋንዳ ዛር ከላዩ ላይ ተሰቅሎ እየጋለበው የሚይዘውንና የሚጨብጠውን ያሳጣው የወያኔ-ኢህአዴግ አይነት የፖለቲካ ድርጅት የለም፡፡ ወያኔ-ኢህአዴግ ኢትዮጵያን በወሬ ብቻ ለማበልፀግ ፖሊሲና ስትራቴጅ ነድፎ የተነሳ ድርጅት ነው፡፡ የበሬ ወለደ ወሬዎችን በመፈብረክ በዓለም ላይ የሚስተካከለው አልተገኘም፡፡ በየጊዜው ቃላትን በማምረትም እንዲሁ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ጠባቂነት፣ ኢንተርሃሞይ፣ ነፍጠኛ፣ ሽብርተኛ፣ ፀረ-ሰላም ኃይል፣ አኬልዳማ፣ ሙስና፣ ልማታዊ ምንትስ፣ ጠባብ፣ ትምክህተኛ… መች ተዘርዝሮ ያልቅና፡፡
ታድያ ይህንን ሁሉ ፕሮፓጋንዳውን የሚጠቀምበት ‘ተው ታገስ! ከጥፋትህ ተመለስ!’ የሚሉትን የአገርና የወገን ተቆርቋሪ የሆኑትን ሰላማዊ ዜጎች ለማጥቃት ነው፡፡ የፕሮፓጋንዳውን እሳት ለማራገብ የሚጠቀምበት ወናፉ ኢቲቪ ሲሆን ወናፉን በሁለት እጆቹ ጨብጦ የሚነፋው ደግሞ “የሁለት ምርጫዎች ወግ” መፅሃፍ ደራሲ ኮሚኩ በረከት ስምኦን ነው፡፡ “የኮሚኬሽን” ጉዳዮች ሚኒስትር እሱ አይደል በቃ ስራው ይህን ገራገር ህዝብ መኮመክ ብቻ ነው፡፡ ዓይኖቹን እያስጨፈነ ማሞኘት፡፡
እናም አዲስ አበባችን ከዋና ከተማነት ወደ አቶ መለስ የፎቶ አልበምነት ተቀይራ አሸብርቃ አምሮባት ከረመቻታ፡፡ ስለሆነም በዋና ዋና ጎዳናዎቿ ዳርና በህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋሞቿ አጥር ላይ ከተሰቀሉት የመለስን ፎቶ ከያዙ ግዙፍ ግዙፍ ባነሮች ላይ ተፅፈው ካነበብኳቸው ህልቆ መሳፍርት ጥቅሶች መካከል እጅግ በጣም ጥቂቶችን በማንሳት እውነታነታቸውን ለመመርመር ፈለግሁ፡፡

1. “ታሪክ ሰሪው መሪ”
ወያኔ-ኢህአዴግ የታሪክን ትርጉ፣ ምንነትና ዋጋ ገና በውል የተረዳ አልመሰለኝም፡፡ አይ…ይ! ታሪክ መስራት ረክሷል ለካ፡፡ ታሪክ መስራት እኮ እንዲህ በባነር ላይ እንደሚፅፉት ቀላል አይደለም፡፡ ደግሞም የቃላት ጋጋታ ጊዜ ሲያልፍበት ከንቱ ውዳሴ ከመሆን አያልፍም፡፡ ለመሆኑ እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ መለስ የትኛውን ለህዝብ የሚበጅ ጉልህ ተግባር አከናውኖ ነው “ታሪክ ሰሪ” ለመባል የበቃው፡፡ መለስ እኮ ርዕደ መሬት ሆኖ የኢትዮጵያን የቆየ ታላቅና ገናና የታሪክ ግንብ የናደ እንጅ ታሪክ የሰራ መሪ አይደለም፡፡ አገር ማስገንጠል፣ የባህር በር አልባ ማስቀረት፣ በዘርና በጎጥ መከፋፈል፣ ህዝብን በመጨፍጨፍ የግፍ ደም ማፍሰስ፣ ምርጫ ማጭበርበር፣ የህዝብን ሀብት መዝረፍና ማዘረፍ፣ በቴሌቪዥን መደስኮር፣ በአደባባይ ህዝብን መዝለፍ… ታሪክ መስራት ነው ተብሎ ከታመነ እንግዲህ ያው እንደለመድነው እንደበቆሎ እያረርን ስቀን ዝም ነው እንጅ ሌላ ምን እንላለን፡፡ ጊዜ ስታገኝ ተናገር ወንዝ ሲጎልልህ ተሻገር አይደል የሚባለው፡፡ የኋላ ኋላ ጊዜ የሚፈርደው ጉዳይ በመሆኑ ዳኝነቱን ለእሱ ሰጥቸዋለሁ፡፡
ይልቅስ መለስ “ታሪክ ሰሪው መሪ” ከሚባል ብዙ አንፀባራቂ ታሪኮች የመስራት አጋጣሚዎች ተመቻችተውለት ሳይጠቀምባቸው በመቅረቱ የተሸወደ መሪ ቢባል ነው ትክክል የሚሆነው፡፡ ታሪክ ለመስራት ከተመቻቹለትና ከተሸወደባቸው ጥሩ አጋጣሚዎች መካከል የ1997 ዓ.ምን ምርጫ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
2. “የነፃነታችን ፋና እና ለህዝብ ሻማ ሆኖ ቀልጦ ያለቀ…”
ይሄ ጥቅስ ሳነብባቸው እጅግ በጣም ካሸማቀቁኝ መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ “ሞኝ ባያፍር የሞኝ ዘመዱ ያፍር፡፡”
እርግጥ ነው መለስ ታጋይ ነበር፡፡ ነገር ግን በትግሉ የኢትዮጵያን ህዝብ በሙሉ ነፃ አውጥቷል የሚል እምነት ፈፅሞ የለኝም፡፡ ነፃ አውጭ ነው ከተባለም ነፃ ያወጣው እሱንና ቤሰቦቹን ብቻ ነው፡፡ /ቤተሰቦቹን ስል መላውን የትግራይ ህዝብ እያልኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡/ እሳቱን ከዳር ሆኖ ሲሞቅና ሻርታ እየዞረ ሲመለከት የነበርው መለስ ሻማ ከተባለ እነኛ ከእሳቱ ውስጥ ተማግደው በመንደድ ከስለው በየበረሃው፣ ጋራና ሸንተረሩ የቀሩት እልፍ አላፍ ኢትዮጵያውያን ምን ይባሉ፡፡
ነፃ የወጣችሁ የመሰላችሁ ሰዎች ካላችሁ “በረጅም ገመድ ታስራ የተለቀቀች ዶሮ የተፈታች ይመስላታል፡፡” ስል ተርቸባችኋለሁ፡፡
መለስ ለገዛ ስልጣኑ፣ ለቤተሰቦቹና ለስርወ መንግስቱ ሻማ ሆኖ በመብራት ቀልጦ አልቆ ሊሆን ይችላል እንጅ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ለ21 ዓመታት በአስፈሪ ጎጎኖ ጨለማ ውስጥ ሲኖር አንኳንስ የሻማ ብርሃን ቀርቶ የአንዲት ፍሬ ክብሪት ብልጭታ በዓይኖቹ አላየም፡፡
3. “አባይን የደፈረ ጀግና”
ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ አባይን የፈሩ መሪዎች ነበሯትን? እንኳንስ አይደለም አረቦችን በጦር ቴክኖሎጅ እጅግ ስልጡን የሚባሉትን አውሮፓዊያንንም የጤፍ ያህል አይመለከቷቸውም ነበር፡፡ ኧረ በጀብደኝነትስ የሚታማ ማንም መሪ በታሪካችን የለንም፡፡ አጋጣሚና ሁኔታው አልመቻችላቸው ብሎ እንጅ አባይን ለመገደብ ያልወጠኑ መሪዎች አልነበሩም፡፡
አንድ ጥያቄ ብቻ ልጠይቅ የአንዲትን በዘመኑ በግዛቷ ፀሀይ አትጠልቅም የተባለላት ኃያል አገር ዲፐሎማቶችና ዜጎች ከማሰር፣ ጦርነት ውስጥ ገብቶ አንገትን ለሰይፍ ከመስጠት እና ከዚሁ ከምድራችን መንጭቶ ወደ ውጭ የሚፈስስን ጅረት ለመገደብ ከማቀድ የትኛው የበለጠ ድፍረትን ይጠይቃል?
ደግሞ ኢትዮጵያ አባይን ለመገደብ ከሚያስችላት አቅም ላይ እንዳልደረሰች በገለልተኛ አጥኝዎች መረጋገጡ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ከድሃ የህዝብ አገልጋዮች ደመወዝ ላይ ሳይፈልጉ በግድ እየቆረጡ ልጆቻቸውን ጦም በማሳደር ልማት ብሎ ነገር የለም፡፡
ባጠቃላይ የአባይ ጉዳይ የለመደበት ወያኔ-ኢህአዴግ ለፕሮፓጋንዳ መሳሪያነት የሚጠቀምበት የህልም እንጀራ ነው፡፡ አይቻልም እንጅ ቢቻል እንኳን ግድቡ ከኤሌክትሪክ ፍጆታችን ያለፈ ለሌላ ለምንም ሊጠቅመን አይችልም፡፡ 85 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ገና ከኩራዝ ባልወጣባት አገር እንሸጣለን፣ እናበድራለን፣ እንቀበጥራለን፣ ጂኒጃንካ… ቧልት ብቻ ነው ሆኖ የሚቀረው፡፡ ይልቅስ ከምድጃ የሚወራውን ወደ አደባባይ ባናወጣውና ዓለም ባይስቅብን ጥሩ ነው፡፡
4. “የአፍሪካ መሪና አባት”
አገሩን በወጉ ማስተዳደር ባለመቻሉ ዘወትር ሲወቀስና ሲነቀስ የኖረ መሪ በምን ሂሳብ ታስቦ ነው የአፍሪካ መሪ ለመባል የሚበቃው፡፡ በእርግጥ መለስ ራሱን የአፍሪካ ወኪል አድርጎ ለመከራከር አንድ አንድ እንቅስቃሴዎችን መሞከር መጀመሩ የማይካድ ነው፡፡ ነገር ግን ተግባሩ የራስን ድስት እያሳረሩ የጎረቤትን ማማሰል ነው የነበረ፡፡ በተጨማሪም መለስ የግል ስብዕናውን ለመገንባትና በመጠኑም ቢሆን ዝና ለማግኘት ተጠቀመበት እንጅ ለዚህ የድህነትና የጉስቁልና ተራራ ከላዩ ላይ ተከምሮበት እያቃሰት በሰቆቃ ለሚኖር ህዝብ ምንም የፈየደለት ነገር የለም፡፡
መለስ እኮ ምዕራባዊያን በቅኝ ግዛት ዘመን ባደረሱት ጥፋት ለቅኝ ተገዥ የአፍሪካ አገሮች ካሳ እንዲከፍሏቸው ሲጠይቅ በግራዚያኒ ስለተጨፈጨፉት ሰላሣ ሺህ ኢትዮጵያዊያን ንፁህ ደም አንዲትም ቃል አልተነፈሰም፡፡
ስለዚህ መለስ እንኳንስ የአፍሪካ የኢትዮጵያ አባትም ለመሆን ያልቻለ መሪ ስለነበር ጥቅሱ የልጆች አባትና የህወሓት ስርወ መንግስት ንጉስ በሚል ቢስተካከል ሊመጥን ይችላል፡፡
5. “ታላቅ የህዝብ ፍቅር የነበርው መሪ”
እኩልነት፣ ፍትህ፣ አንድነት፣ ችግርን አብሮ መጋራት፣ ልማት፣ ዕድገት፣ ብልፅግና… የሚሉት የህዝብ ፍቅር መገለጫዎች ዘረኝነት፣ አድሎ፣ ጭቆና፣ መከፋፈል፣ ጉስቁልና፣ ድህነት፣ ኋላ ቀርነት፣ ጨፍጫፊነት፣ ደም አፍሳሽነት፣ ዘራፊነት፣ ራስ ወዳድነት፣ ባንዳነት… በሚሉት የጥላቻ መገለጫዎች ቦታ ተተክተው ከሆነ ትክክል ነው፡፡ አለበለዚያ ግን መለስ የስልጣን ፍቅር እንጅ የህዝብ ፍቅር ኖሮት አንድም ቀን በተግባር አይተነው አናውቅም፡፡
6. “ታላቅ የህዝብ ፍቅርን ያገኘ ብቸኛው መሪ”
አቤት! የእኛ ማንዴላ¡ የእኛ ጋንዲ…¡ ቆይ እኔ ምለው መለስን የኢትዮጵያ ህዝብ በጠቅላላ የሚያፈቅረው ከሆነ ለምን ሲባል መቃብሩ በኮማንዶ ይጠበቃል? ከማን ነው የሚጠበቀው? ነው ወይስ ቅድስት ስላሴ ግቢ ውስጥ ጅብ አለ? የመለስ አስከሬን ከእነ ጥላሁን ገሰሰ እስከሬን በምን ይለያል? በዚህ ብቻ መለስ በህዝብ ምንያክል የተጠላ አምባገነን እንደነበረ መረዳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም አስከሬኑ ዛሬም ከኢትዮጵያ ህዝብ ስጋት ነፃ ሆኖ አልታየምና፡፡ ወያኔዎች ሁሉም ነገር የውሸት እንደሆነ ግጥም አድርገው ስለሚያውቁት ከመስጋታቸው የተነሳ ነው አስከሬኑ በጥብቅ እንዲጠበቅ ያዘዙት፡፡ “ሌባ እናት ልጇን አታምንም፡፡”
7. “እራዕይህን እውን አናደርጋለን”
ይህ ጥቅስ እጅግ በጣም አስደንግጦኛል፡፡ ምክንያቱም የመለስ ታላቁ ራዕይ ታላቁን የህወሓት ስርወ መንገስት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ዘላለማዊ አድርጎ መገንባት ስለነበር፡፡
በተጨማሪም የመለስ ምስል በጉዞ ላይ ካለ አንድ ዘመናዊ የቻይና ባቡር ስዕል ጋር ሆኖ የተቀነባበረ ፎቶ የታተመበት ሰፊ ባነር ስቴዲየም አካባቢ ተሰቅሎ ተመልክቻለሁ፡፡ በመሰረቱ ፖሊሲን ከቻይና ቀድቶ “የህዳሴ መሀንዲስ መባል” ይቻላል፡፡ ነገር ግን ታሪክን ቀድቶ የራስ ማድረግ በፍፁም አይቻልም፡፡ መለስ የቀደሙት መሪዎች ገንብተውት ያለፉትን ሲያፈርስ እንጅ የባቡር መስመር ገንብቶ አይተነው አናውቅምና፡፡
ሌላው አስገራሚና አስቂኝ ትዕይንት ደግሞ መለስ 21 ዓመታት ሙሉ ወደ ውጭ አገር ሊበርር የተንደላቀቀ ህይወት ከሚመራበት ቤተ-መንግስት ወጥቶ ወደ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲሄድም ሆነ ሲመለስ አሱ በሚያልፍበት አካባቢ አይደለም ሰው ወፍ አንኳን ዝር አትልም ነበር፡፡ በኋላ ግን ህይወቱ አልፋ በሳጥን ታሽጎ ሲመጣ ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኖ እርፍ አለ…
በተጨማሪም በደም መንኩሶ ቀይ ቆብ ከአናቱ ላይ በደፋው፣ እሳት ያረገዘ ክላሽን ኮቭ በወደረው፣ ሳንጃና ገመድ በወገቡ ባንጠለጠለው ቅልብ የአጋዚ ኮማንዶ ጦር የሚጠበቀው ታላቁ ቤተ-መንግስት ለረጅም ዘመናት የተዘጉት ደጆቹ ተከፍተው ሰዎች እንደልብ ሲገቡባቸውና ሲወጡባቸው ታይተዋል፡፡ መለስ በህይወት እያለ እነኛ የግፈኞች መመሸጊያ የሆነው ዋሻ በሮች ተከፍተው የህዝብን ብሶትና ለቅሶ ቢያስተናግዱ ነበር ታሪኩ በወርቅ ዓምድ ላይ ተፅፎ አልፋና ኦሜጋ ሆኖ የሚቀረው፡፡
እኔን ያወዛገበኝ ጉዳይ ደግሞ የአቶ መለስ እድሜ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታቶች በፊት አንድ ቀን ባጋጣሚ የግንቦት 20 በዓልን አከባበር በወናፉ ኢቲቪ ተመልክቼ ነበር፡፡ ታድያ በኢቲቪ የተመለከትኩት ዋና ኩዳይ የሽግግር መንግስቱን አመሰራረት ትውስታ ነው፡፡ በዚያ የትውስታ ዝግጅት ላይ “የ43 ዓመቱ መለስ ዜናዊ የሽግግር መንግስቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ ታምራት ላይኔ ደግሞ…” የሚል ዓረፍተ ነገር በእርግጠኝነት ሰምቻለሁ፡፡ በመሆኑም ኢቲቪ ያኔ በተናገረው መሰረት ከ43 ላይ 21 ስንደምርበት 64 ይሆናል፡፡ እናም መለስ 57 ሳይሆን 64 ዓመቱ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ወያኔዎች ልክ አንደምርጫው ውጤት የጣኦታቸውን እድሜም ማጭበርበር ጀመሩ ወይንስ ኢቲቪ ተሳሳተ?
በመጨረሻም ሀሳቤን ሳጠቃልለው የሞተ አይነሳም እንጅ የወያኔ-ኢህአዴጎች ኢየሱስ የሆነው የትግራዩ መለስ ልክ እንደክርስቲያኖች የናዝሬቱ ኢየሱስ ሙስና መቃብርን ድል ነስቶ ቢነሳና በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ዳርና በየመንግስት መስሪያቤቱ አጥር ከፍ ብለው የተሰቀሉትን የባነር ላይ ታሪኮቹን ቢመለከት በእጅጉ ተበሳጭቶ ያን ያደረጉትን ወያኔዎች በሙሉ በደም ፍላት የሚረሽናቸው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እሱን ትክክለኛውን መለስ ዜናዊ ትተው ሌላ መለስ ዜናዊ የተባለ በገሀዱ ዓለም ያልነበረ አዲስ የህወሓት ገፀ ባህሪ ፈጥረዋልና፡፡

No comments:

Post a Comment