"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Tuesday, 3 June 2014

የእናቶች ቀን እና ቅድስት ድንግል ማርያም ፀሐፊ፡- ፍቅር ለይኩን፡፡ በእናቶች ቀን የመስቀል ላይ የፍቅር ስጦታ የሆነች እናታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልንዘክራት ይገባናል!!!



ሰማይ ሰማያት፣ ምድርና ሞላዋ፣ አለቆች፣ ሥልጣናት፣ መናብርት፣ አጋእዝት፣ መኳንት፣ የሰማይ ሠራዊት መላእክት፡- ምሕረትንና ይቅርታን ለሰው ልጆች ሁሉ ባወጀው በእግዚአብሔር ቅዱስና ሕያው ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ የፍቅር ትእይንት እጅግ በተደመሙበትና በተመሰጡበት፣ በዚህ ሕያው ፍቅር ምድርና ሰማይ በደመቁበትና ባሸበረቁበት፣ የፍቅር ዜማ፣ የፍቅር ልዩ ቅኔ ነፍስን በሚመስጥ ቅላጼ፣ በውብ ስርቅርቅታ፣ በታላቅ ድምጽ ከአድማስ አድማስ፣ በተራሮች፣ በባሕሮችና በውቅያኖሶች ዳርቻ ሁሉ በተሰማበት፣ ጸሐይና ከዋክብት ለዚህ ፍቅር በልባቸው ጉልበት በፍቅር እግር ስር በቀራኒዮ በተንበረከኩበት፣ ጨረቃም በፍቅር ትሕትና፣ በፍቅር ቸርነትና ትእግስት ተመስጣ ደም በለበሰችበት፣ በደም በተነከረችበት፣ ምድርና ሞላዋ፣ ሰማይ ሰማያት በፍቅር መሳጭና ልዩ ትእይንት በደመቁበት ፍቅር እንዲህ ሲል በትሑት ድምጽ፣ በፍቅር ጩኸት ቃሉን አሰማ፡-
እነኋት እናትህ . . . ተፈጸመ!
የእሾህ አክሊል ዘውድን ተቀዳጅቶ በጎልጎታ በመስቀል ላይ የነገሰው ፍቅር ጌታችን ኢየሱስ ኢየሱስ ስለ ሰው ልጅ ፍቅር እና መዳን በደም የተነከሩ፣ በደም የተጋረዱ ዓይኖቹን በእንባ ጎርፍ ወደምትታጠበው እናቱ ዞር አደረጋና አያት፤ አንገቱንም ዘንበል አድርጎ በመከራና በሐዘን የጎበጠች እናቱን በፍቅር ዓይን በአንክሮ ተመለከታት… በዛ ጭንቅ ውስጥ በመስቀል ጣር ላይ ሆኖ እንኳን ጌታችን ቅድስት እናቱን አልዘነጋትም፣ አልተዋትም፡፡ አዎ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን እናቱን ይቅርና ለሚሳለቁበት፣ ለሚሰድቡትና በጦር ለወጉት እንኳን በመጨረሻ የመስቀል ላይ መከራው ሰዓት፡- ‹‹አባት ሆይ የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!›› ሲል ይቅርታንና ምሕረትን ነበር የማለደላቸው፡፡

በጎልጎታ በመስቀሉ ዘንድ ከልጇ ስር እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ከልጇ ሳትለይ የቆየችው ይህች ምስኪን እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም አስቀድሞ በአረጋዊው ስምዖን እንደተተነበየላትና እንደተነገረላት፡- ‹‹ከክርስቶስ ኢየሱስ የተነሳ በነፍሷ የመከራ፣ የስደትና የጭንቀት ሰይፍ ያለፈባት ናት፡፡›› (ሉቃ ፪፣፴፭) በሄሮድስ ዘመን ገና በጌታ በሕጻንነቱ ወራት ከሄሮድስ የቁጣ ሰይፍ ለመሸሽ በግብጽ በረሃ የተሰደደች፣ የሕይወትን ራስ፣ የእስራኤልንና የአሕዛብ ሁሉ ተስፋ የሆነውን ጌታን ታቅፋ በሲና በረሃ የተንከራተተች፣ የተጠማች ፣ የተራበች፣ የተገፋች፣ የተጎሳቆለችና በብዙ ጭንቀት ውስጥ ያለፈች… እናም ገና ጌታን ከወለደችበት ወራት ጀምሮ በነፍሷ ባለፈው የሐዘን ሰይፍ የተነሳ በመከራ ደቃ፣ ሰውነቷ ገርጥቶ፣ አይኗ በእንባ ጎርፍ እየታጠበ ነፈሷ ተጨንቃ የሐዘን ከል ለብሳ በመስቀሉ ስር የተገኘቸውን እናቱን ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ በፍቅር ዓይን አያት፣ በፍቅር ዓይኑ ቃኛት፡፡
በዛ ሁሉ ጭንቀትና እንደ መርግ በከበደ መከራ ውስጥ በሐዘን የተጎሳቆለች በጌታችን እናት በቅድስት ድንግል ማርያም ታላቅ ሰብእና ውስጥ በእግዚአብሔር ምሕረት፣ በእግዚአብሔር ፍቅር የተዋበና የደመቀ ንጽሕና፣ ብርቱ ትእግስትና የጸና ተሰፋ ይታይባት ነበር፡፡ በመጽሐፍ እንደተነገረላት‹‹ነገርን ሁሉ በልቧ ትጠብቅ›› ለነበረች ለድንግል ማርያም ነፍስን በሚመትር፣ ልብን በሚሰብር ጥልቅ ሐዘኗ ውስጥ በእግዚአብሔር ፍቅር፣ በእግዚአብሔር አሳብና በጎ ፈቃድ የደመቀና የተዋበ ንጽህናዋ ሐዘኗን አልፎ፣ መከራዋን ድል ነስቶ የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የእግዚአብሔር ውበት በሁለተናዋና በዓይኖቿ ውስጥ ደምቆ ይታይ፣ ጎልቶ ይነበብ ነበር፡፡ ይህችን የፍቅር እናት ይህችን የንጽህናና የፍቅር ተምሳሌት ጌታ በመስቀሉ ላይ ሆኖ እጅግ ይወደው ለነበረው ደቀ መዝሙሩ ለዮሐንስ ‹‹እነኋት እናትህ!›› ሲል የመስቀል ላይ የፍቅር ስጦታውን አበረከተለት፡፡ በእርግጥም ፍቅርን ለሚሰብከው፣ ሁለተናው በጌታውና በመምህሩ ፍቅር ለነደደና ለተዋበ፣  ለፍቅር ደቀ መዝሙር ለቅዱስ ዮሐንስ የተገባች ስጦታ ነበረች ድንግል ማርያም፡፡ በእዚህ ደቀ መዝሙርም በኩል ቅድስት ድንግል ማርያም ለሁላችን እናት ትሆነን ዘንድም በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ለሚያምኑ ሁሉ ተሰጠች፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ ለቅድስት ድንግል ማርያም ያለው ልዩ ፍቅርና ክብር ውሉ የሚመዘዘው ከዚሁ ከቤተልሔም እስከ ጎልጎታ ድንግል ማርያም ከልጇ፣ ከወዳጇ ሳትለይ ባሳየችው ትልቅ ጽናትና የፍቅር ተጋድሎ ነው፡፡ ስለዚህም የቤተ ክርስቲያን ልጆች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መውደዳችን የመስቀል ላይ ፍቅር ስጦታ በመሆኗ ነው፡፡ እርሷ በእግዚአብሔር የተመረጠች፣ የተከበረች፣ የተወደደች ብጽእት ናትና እንከብራታለን፣ እንወዳታለንም፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን አባት አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው፡- ‹‹. . . ስለዚህ ማርያም ሆይ እንወድሻለን እውነተኛ የጽድቅ መብልንና እውነተኛ የሕይወት መጠጥ የሆነውን ክርስቶስ ኢየሱስን ወልደልሽልናልና፡፡›› ብሎ እንዳመሰገነው፡፡
ለእኛ  ለኢትዮጵያውያን እናት ሁሉንም ነገር ነች፡፡ እናት ሀገር፣ እናት ማረፊያ፣ እናት ዘመድ፣ እናት ወዳጅ፣ እናት መምህር፣ እናት አባትም እናት ሁሉንም ነች፡፡ በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ ስለ እናቶቻችን ስናስብ ወይንም ስንጠየቅ ልባችን በፍቅር ይሞላል፣ ዓይናችንም የስስትና የናፍቆት እንባ ይሞላዋል፡፡ በተለይም ደግሞ ልጆችን የማሳደግ፣ የመንከባከብና በመልካም ሥርዓት ቀርፆ የማሳደግ ከባድ ቀንበር በአብዛኛው በሴቶች ጫንቃ ላይ በሚወድቅበት በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ እናት በብዙ ውጣ ውረድ በብዙ ችግርና መከራ፣ ቃላት ሊገልጸው በማይችል ሰቆቃና ስቃይ ውስጥ በማለፍ የጓዳዋን ገመና የውስጧን ጭንቅትና ብሶት በውስጧ አምቃ፣ ልቧ በፍቅርና ሁሉም ነገ ያልፋል በሚል ተስፋ ገጽታዋ ደምቆ በጽናቷና በብርታቷ ሰብእናችንና ማንነታችንን ለቀረጸች ለእኛ ኢትዮጵያውያን እናታችን ልዩ ትርጉም፣ ልዩ ስፍራ፣ ልዩ ክብር አላት፡፡
አንድ ወዳጄ በሞት የተለዩትን የእናቱን አስመልክቶ ያለኝ ንግግሩ እስከዛሬም ድረስ ስለ እናት ሳስብ በኅሊናዬ ውስጥ ይደውላል፡፡ ይህ ወዳጄ በሞት ስለተለዩት ስለ እናቱ እንባን ባቆረዘዙ ዓይኖቹ እንዲህ ነበር ያለኝ፡-‹‹እናቴ መካሪዬ፣ እናቴ ምስጢሬ፣ እናቴ የልቤ ወዳጅ፣ እናቴ ገመናዬን ከታች፣ እናቴ ሁሉም ነገሬ ነበረች… እናም የእናቴ ፍቅር በዘመናት ርዝመት፣ በጊዜዎች ማለፍ ውበቱና ድምቀቱ ሳይደበዝዝ እስከ መቃብር ድርስ አብሮኝ ይወርዳል…፡፡›› በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ ስለ እናታችን ስናስብና ስናስታውስ ልባችን በሐዘን ስሜት ይዋጣል፣ መከራዋ ጭንቀቷ ውጣ ውረዷ፣ ለነገ ማንነታችን በልቧ የሰነቀችው መልካም ምኞቷና ራእይዋ ትዝ ይለንና ነፍሳችን በናፍቆት ስስት፣ በናፍቆት ትዝታ ይዋጣል፡፡ በምንም ሊመለስ የማይችል ውለታዋን ለማሰብ ስንልም ለፍቅሯ ዋጋ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በጊዜያችን፣ በገንዘባችን፣ በጉልበታችን መስዋእትነት ለእናቶቻችን መባንና ስጦታን እናቀርባለን፡፡ ይሄ የሚገባ የሚመሰገን በጎ ምግባርም ነው!
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ትልቅ ስፍራና ስም ያለው፣ በርካታ የሃይማኖት መጻሕፍትን በመጻፍ የሚታወቀውና ቤተ ክርስቲያንን ከመናፍቃን ሐሰተኛ ትምህርት በመከላለክል ስሙ የገነነው፣ የወንጌል አስተማሪና ሰባኪ የሂፖው ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ አጉስቲን በብዙ እንባና ጸሎት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ስላደረሰቸው እናቱ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፡-
‹‹ኦ! አምላኬ ሆይ የአንተ ልጅ ለመሆን የበቃሁት በእናቴ ብርቱ ጸሎት ነው!››ቅዱስ አጉስቲን እድሜ ዘመኗኑ ሁሉ ስለ እርሱ መዳን በጽኑ ፍቅር፣ በታላቅ ተስፋና በብርቱ ጸሎት የተጋደለችለት እናቱ ባረፈችበት ቀን የመዝሙርን101ኛውን ዳዊት፡- ‹‹አቤቱ ምሕረትንና ፍርድን እቀኝልሃለሁ!›› የሚለውን መዝሙር በበገናው በመደርድር በእንባ ሆኖ ካዜማ በኋላ ከሐዘኑ ሊያጽናኑት ለመጡ ወዳጆቹ እንዲህ አላቸው፡- ‹‹…ሃምሳ ዓመት ሁሉ ስለ እኔ መዳን በጥልቅ ፍቅር ላለቀሰችልኝ ውድ እናቴ ስለ ውለታዋና ፍቅሯ የማፈሰውን እንባዬን እንደ ግብዝነት እንዳትቆጥሩብኝ አደራ፤ ማለቱ በሕይወት ታሪኩ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ የአሜሪካው የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆርጅ ዋሽንግተንም ስል እናታቸው ሲናገሩ፡- ‹‹እናቴ በሕይወቴ ዘመን ካየኋቸው ሴቶች ሁሉ እጅግ የተዋበች ናት፡፡ መላው እኔነቴ ሁሉ ለእናቴ የተሰጠ ነው፡፡ በሕይወት ዘመኔ ያገኘሁትን ስኬት ሁሉ ከእናቴ በተቀበልሁት ሞራላዊ፣ ስነ ልቦናዊና አካላዊ ትምሕርት የተነሳ ነው፡፡›› በማለት ለእናታቸው ያላቸውን አድናቆት፣ ልዩ ፍቅርና ክብር ገልጸዋል፡፡
በእናቶች ቀን ልትዘከር በተገባት የክርስቲያኖች ሁሉ የፍቅር የመስቀል ስጦታ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወት ውስጥ ከቤተልሔም ግርግም እስከ ቀራኒዮ የታየውና የተገለጸው የእመቤታችን ታላቅ ጽናት፣ ፍጹም ፍቅር፣ ብርቱ ትእግስትና ጭምትነት በእኛም በክርስቲያኖች የመስቀል ጉዞ ውስጥ ይታይ ዘንድ ይገባል፡፡ በእናቶች ቀን በብዙ ፍቅር፣ በጸና መስዋእትነት ሰብእናችን ለቀረጹ፣ ለእናቶቻችን በምስጋና ቃል በፍቅር ስጦታ እናቶቻችን ልናስባቸውም ይገባናል፡፡

የእመቤታችን በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን!
ሰላም! ሻሎም!

No comments:

Post a Comment