ከቅርብ ዓመታት በፊት ነው! በግብፅ ይኖር የነበረው ወጣት ምንም እንኳን ገና በወጣትነቱ በትምህርት፣ ሃብትና ትዳር "የተሳካለት ሰው" የሚባል ቢሆንም ከጥቂት ቀናት በፊት ግን ይመካበት የነበረውን ትዳሩን ጥያቄ ውስጥ ገብቶበታል:: ባላወቀው ምክንያት የሚወዳት ባለቤቱ ከወገብ በታች ፓራላያዝ ትሆናለች:: እርስዋን ለማሳከም ያልሄደበት ሆስፒታል ባይኖርም የሚሄድበት ሆስፒታል እንደሌለ ግን ተነግሮታል:: "የያዛት በሽታ አይድንም!" የሚል መራራ ሐዘንን ሰምትዋል! ብዙ ያሰበለት የልቡ ፍቅር ሲጠወልግ፣ የወደፊት ሕልሙ ሲጨልም፣ የልጅ አምሮቱም እንዲሁ ላይመጣ ሲቀር አስቀድሞ አውቋል! ባለቤቱ አልጋዋ ላይ ትበላለች አልጋዋ ላይ ትፀዳዳለች! ለጥቂት ጊዜ እዛው አልጋዋ ላይ ሳምንታትንና ወራትን ስታሳልፍ ከራሱ ጋር እየታገለ በትዕግስት ቢያስታምማትም ከዚህ በላይ መቆየት ግን በአካል ሲኦል የመግባት ያህል ሁኖ ተሰማው:: ስለዚህ በፍቺ ከርስዋ ጋር መለያየትን መረጠ:: ነገር ግን ፍርድ ቤት ከመሄዱ በፊት አስቀድሞ የንስሃ አባቱን ማማከር እንዳለበት አመነና ወደሳቸው ሄዶ ያሰበውን ይነግራቸዋል! እሳቸው ግን በፍፁም እንደማይሆን፣ ጌታ ያጣመረውን እርሱ መፍታት እንደማይገባ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሱ ያስረዱታል:: ከዚያም ሁለቱም በጸሎት እንዲተጉና ወደ እመቤታችን እንዲያመለክቱ ተነጋግረው ይለያይሉ:: የንስሃ አባቱም የወጣቱንና የባለቤቱን የክርስትና ስማቸውን ፅፈው በመቅደሱ መንበር ላይ አስቀምጠው ለ 3 ቀና ያህል በፅኑ ፆምና ጸሎት እየተጉ ቆዩ::
ከ3 ቀን ብኋላ ወጣቱ በሕልሙ እርሱ ከሚሰራው ፎቅ ተወርውሮ ወድቆ ሲሰባብረ፣ ሰዎችም መጥተው ሲያለቅሱለት፣ ባለቤቱ ግን መጥታ ለሰዎቹ "ምንም እንዲህ ተሰብሮ ቢጎዳም ከልቤ አፈቅረዋለሁና አልለየውም! ባለቤቴ ነውና አልለየውም! እስከ ሞት ድረስ አስታምመዋለሁ" ስትላቸው ያያል:: ይሄ የጌታ መልዕክት ይሆን እንዴ? ይልና ያየውን ለንስሃ አባቱ ይነግራቸዋል! እሳቸውም የእግዚአብሔር እጅ በድንግል ማርያም ምልጃ ስራውን እንደሚሰራ፣ ምንም እንኳን ሚስቱ በሞት አፋፍ ላይ ብትሆንም ሞትን የሚገድል ክርስቶስ ግን እንደሚፈውሳት፣ ፍቺዉንም መሰረዝ እንዳለበት የሚናገር ሕልም እንደሆነ ይተረጉሙለታል:: እርሱም "ያሰብኩትን ሳይሆን ጌታዬ ያሰበው ይሁን" ብሎ ፍቺውን ሰርዞ ለሚወዳት ባለቤቱ በፀሎት ፈውስን ይለምን ጀመረ::
ከጥቂት ሳምንታት ብኋላ የተወደደው ጾመ ፍልሰታ ይገባና እርሱም 14 ቀናት በተመስጦ በጾምና በጸሎትና ቆይቶ ነሐሴ 16 ቀን የእመቤታችንን የዕርገትዋን በዓል ያከብር ዘንድ ወደ ቤ/ክ ሲሄድ ባል ከሚስቱ ልጆችም ከወላጆቻቸው ጋራ ጧፍ አብርተው ሲዘምሩ ተመልክቶ ልቡ በሐዘን ይመታል! ልጅም ሚስትም በማጣቱም በማዘን በቤ/ክኑ በነበረው የእመቤታችን ስዕለ አድኅኖ ተደፍቶ <እመቤቴ ሆይ የወጣትነት ዕድሜዬን በደስታ ያልፈፀምኩበት፣ የልቤን ጓደኛ በበሽታ ያጣሁበትስ ምን ዓይነት ቀን ነው? እርስዋ በአልጋ ታስራ የምትቆይበት እኔ ደግሞ በእርስዋ ስቃይ የምሰቃይበት እስከመቼ ነው? እባክሽን ጽንሱን ያዘለለ ድምፅሽን አሰሚኝና እኔም ለክብርሽ ልዝለል! እባክሽን ለቶማስ የሰጠሽውን ሰበንሽን በሚስቴ ላይ ጣይ!> እያለ ምርር ብሎ ያለቅሳል::
ከቤ/ክ መልስ ወደ ቤቱ ሲገባ ግን ሚስቱ ከአልጋዋ የለችም! ፍርሃት ፍርሃት አለው! ምናልባት ሞታ ሊቀብርዋት ሂደው ይሆን? ብሎ አሰበ:: ደግሞ ቆይቶ "አይ! አይደለም! በፍፁም አይሆንም" ይላል! ወደ ኩሽና ቤቱ ሲገባ ፍፁም ለማመን በማይቻል መልኩ ሚስቱ በ2 እግርዋ ቆማ ስትሰራ ያያታል:: አንደበቱ መናግር ቢያቅተውም ዓይኖቹ ግን የዕንባን ዘለላ እያፈለቁ ይናገሩለት ጀመር:: ሚስቱም ስታየው እየሮጠች መጣችን ተጠመጠመችበት:: <አንተ ወደ ቤ/ክ ከሄድክ ብኋላ ቤታችን ባለው የእመቤቴ ስዕለ አድህኖ ላይ ተንበርክኬ አለቀስኩ! "እመቤት ሆይ ችግሬን ታውቂያለሽና አማልጂኝ! ለተጠማ ውሻ የራራው ልብሽ እባክሽ ለኔም ይራራልኝ! ቆሜ የትንሳኤሽንና የዕርገትሽን በዓል አክበር ዘንድ እግዚአብሔርንም አመሰግነው ዘንድ ፈውሺኝ" አልኳት:: ከዚያም አንዲት ብርሃን የለበሰች ሴት መጣችና "ተነስተሽ ቁሚ" አለችኝ! እኔም "መቆምኮ አልችልም" አልኳት:: እርስዋም "ልጄ ሆይ አይዞሽ! ጌታ ፈውሶሻልና አቆምሽ ዘንድ መጥቻለሁ" አለችኝ! ከዚያም ሁለት እጄን ይዛ አስነሳችኝ! ከዚህ በፊት ተሰምቶኝ የማያውቅ ስሜትም ተሰማኝ! ኃይልም በእግሮቼ መሃል አልፈና እግሮቼም ፀንተው ቆሙልኝ! ከዚያም ባርካኝ ከዓይኔ ተሰወረች!> ብላ ለባልዋ ትነግረዋለች! እርሱም ከሚሰማው ነገር የተነሳ ዲዳ ሆነ! በእግርዋም ተንበርክኮም ሊፈታት እንዳሰበና ተስፋ ቆርጦ እንደነበረ ይቅርታ ይጠይቃታል:: እርስዋም ይቅር ብላው ተቃቅፈው ጌታን አመሰገኑ! ተያይዘውም ትንሳኤዋንና እርገትዋን ለማክበር በጋራ ወደ ቤተክርስቲያን አመሩ!
ፍቅርዋ በልባችን ጣዕሟም በአንደበታችን ያሳድርብን! ጸጋውን ክብሩን ትሳልብን ታሳድርብን! ምልጃ በረከትዋ ለሁላችን ይሁን!!
via Biniyam Aregawi
No comments:
Post a Comment