"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Monday 1 September 2014

ቴዲ አፍሮ – በሁለት ጽንፎች

ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጽሞ ሊተቹ የማይችሉ ሶስት ግዝፍ ነገሮች አሉ። እነዚህም
1ኛ – ሃይማኖት
2ኛ – መንግስት
3ኛ – ቴዲ አፍሮ
ናቸው።
ከእንግዲህ ቴዲ አፍሮ ዘፋኝ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ መቆራቆዣ ተቋም ሆኗል። ይህን አስመልክቶ ወዳጃችን Girmabbaacabsaa Guutamaa እንዲህ ይላል….
“ቴውድሮስ ካሳሁን aka ቴዲ ኣፍሮ ዘፋኝ ብቻ ኣይደለም። በሃገሪቱ ውስጥ ካሉት ይልቁንም ባብዛኛው ሊታረቁ የማይችሉ (divergent) ማህበረ-ፖለቲካዊ እሳቤዎችን በሚያራምዱ ኤሊቶች ከሚመሩት የተለያዩ ቡድኖች መካከል የኣንዱ ግሩፕ political ideologue ነው ቴዲ።”
ይህ ብያኔ (Definition) የተለጠጠ ቢሆንም ውሸት ግን አይደለም። ቴዲ በሁለት ጽንፍ የቆሙ የፖለቲካ ወገኖች መቆራቆዣ አእማድ (Pillar) ሆኗል።
የቴዲን ዘፈኖች መተቸት ችግር ያስከትላል። የቴዲ ስራ ላይ ሂስ ማቅረብ “ሃራም” ሆኗል። ለምን ቢባል — ቴዲ ለደጋፊዎቹ የማይሳሳት እና ሁሉን አወቅ ነው። የቴዲን ስራዎች መንካት ያሰድባል፤ ያስዘልፋል፤ ባስ ሲል ደግሞ የኢትዮጵያን አንድነት እና “ኢትዮጵያዊነትን” እንደመካድ ያስቆጥራል። የቴዲን አዲሱ ነጠላ ዜማ የተቹ ሰዎች ብዙ ስድብ ሲቀምሱ ታዝቤያለሁ።
በተመሳሳይም የቴዲን ዘፈኖች ማድነቅ ችግር ያስከትላል። ቴዲ በነቃፊዎቹ ዘንድ ሁሌ ስህተት ነው። ስለዚህ የቴዲን ስራዎች ማድነቅ ብሄር ብሄረሰቦችን እንደ መጨቆን፤ የቀድሞ ስርዓትን እንደመናፈቅ እና ገፋ ሲል ደግሞ መንግስትን በ17 መርፌ እንደ መውጋት ተደርጎ ይቆጠራል። “ጥቁር ሰው” የወጣ ጊዜ የኦሮሞ ልሂቃን እና የመንግስት ደጋፊዎች ለምን የአጼ ምኒልክ ስም ተጠራ በሚል የስድብ መዓት ሲያወርዱ አስተውያለሁ።
የሆነው ሆኖ ቴዲ ከእንግዲህ ተራ ዘፋኝ ብቻ አይደለም።
በሰባ ደረጃ
“በሰባ ደረጃ የተባለው ነጠላ ዜማ ቴዲን የሚመጥን ነው ወይስ አይደለም?” የሚለው ክርክር መቋጫ አልባ ይመስላል። ይሄን ዘፈን ሌላ ዘፋኝ ቢጫወተው እንዲህ አይነት አቧራ ያስነሳ ነበር? መልሱ ግልጽ ነው። በእርግጥ ሙዚቃ የስሜት ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን በእውቀት የሚተች ጥበብም ነው።
— ለምሳሌ
አስቴር አወቀ በአንዱ ዘፍኗ ውስጥ እንዲህ የሚል ስንኝ አላት።
አዳራሽ
በብዛት ይገኛል
ሽንኩርት እና ፍራሽ
ይሄ ግጥም በሁለት መልኩ እጅግ ደካማ ነው።
1ኛ አዳራሽ ውስጥ ሽንኩርት እና ፍራሽ በጭራሽ አይሸጥም።
2ኛ ከአጠቃላይ የዘፈኑ አውድ (Context) አንጻር ይሄ ስንኝ ምንም ግንኙነት የለውም።
ይሄ አዝማሪዎች የሚታወቁበት የግጥም አይነት ሲሆን የላይኛው እና የታችኛው ሃሳብ ፍጹም አይገጥምም። በዚህ ዘመን እንዲህ አይነት የዘፈን ግጥም ከትችት አያመልጥም።
የቴዲ አፍሮ “በሰባ ደረጃ” ሃሳቡ በጣም ግሩም ነው። ሆኖም ግን ግጥሙ ውስጥ ልክ በድሮ ጊዜ አዝማሪዎች እንደሚያደርጉት የላይኛውና የታችኛው ስታንዛ የማይገናኝ እና ከአውዱ ውጪ የሆነ ግጥሞች መኖራቸው ዘፈኑን እንዲተች ምክኒያት ሆኗል። ይሄን ሃሳብ ለማጠናከር ብዙዎች የሚከተለውን አንጓ ከግጥሙ ውስጥ ይመዛሉ።
“አምጧት ከጎኔ ትቀመጥ
እንጀራ አይቀርብም ካለ ወጥ”
ጋዜጠኛና ገጣሚ Demeke Kebede ይሄ አይነት ግጥም ለቴዲ አፍሮ አይመጥንም በማለት ይከራከራል። ከዚህም በተጨማሪ “አርምዴ ሜሪ” ብሎ ስሟን ማዟዟሩ ተገቢ እንዳልሆነ ያሰምርበታል።
ታዋቂው ገጣሚና የወግ ጸሃፊ Bewketu Seyoum ግን በዚህ ሃሳብ አይስማማም። እንዲያውም ቴዲ አፍሮ ከዳግማዊ አጼ ቴውድሮስ ቀጥሎ የተነሳ “ሳልሳዊ ቴዎድሮስ” ነው በማለት አሞካሽቶት ሲያበቃ “አርምዴ መሪ ብሎ መጥራት የገጣሚነት ነጻነቱ ይፈቅድለታል” በማለት በተለየ መንገድ ተንትኖታል።
እርግጥ በእወቀቱ እንዳለው ቴዲ የባህል ዘፈን ለመዝፈን ግዴታ በእንኮዬ መስክ እና በኳሊ በር ወይም በጃን ተከል ዋርካ ስር እያለ መዝፈን አይጠበቅበትም። ሆኖም ግን “አርምዴ ሜሪ” ተብሎ ለትውልድ ሲተላለፍ የሚያመጣውን ጉዳት እንዴት እንደተመለከተው አልገለጸም። እስኪ አስቡት አስቴር አወቀ በአንድ ዘፈን ውስጥ “አወቀ አስቴር” ተብላ ብትጠቀስ የወደፊቱ ትውልድ አወቀ የሚባል ወንድ ዘፋኝ ነበር ብሎ ሊተረጉመው ቢችልስ? ቴዲ በጥቁር ሰው ውስጥ “ባልቻ አባቱ ነፍሶ” ያልኩት አውቄ ነው ማለቱ ብዙዎችን አሳዝኗል። የሚስራ ሰው መሳሳቱ የሚጠበቅ ስለሆነ ማመኑ አይከፋም ነበር።
የሜሪን ስም ጉዳይ ብንቀበለው እንኳን እነዚህን ግን ማለፍ አይቻልም። ሴይቼንቶ የሚለውን አጠራር ቴዲ “ሴሼንቶ” ብሎ ገድፎታል። ሴሼንቶ የሚባል መኪና አልነበረም። መውዜር የተባለውን ጠመንጃም መውዜሬ እንደማለት “መውዘሬ” ሲል አንሻፎታል።
በሰባ ደረጃ እነዚህ አይነት ህጸጾች ቢኖሩበትም በርካታ የጠፉ ቃላትን በማምጣት አዲሱን ትውልድ ታሪክ በማስተማሩ ቴዲያችን ሊመሰገን ይገባዋል።
መግቢያው ላይ ያለው የክራር ድምጽ ከሜሪ አርምዴ አገራረፍ ጋር የሚመሳል መሆኑ ጥሩ ቢሆንም በኪቦርድ ተከትፎ መሰራቱ ጥራቱን ደካማ አድርጎታል። የሙዚቃው ምት 6 በ 8 (በተለምዶ ችክችካ የሚባለው) ሲሆን ማስጨፈሪያ አይነት ስለሆነ ቴዲ ከፊታችን ላለበት የአሜሪካ ኮንሰርት ጥሩ መሳቢያ ይሆንለታል።
ቅኔ የመፈለግ በሽታ
በሰባ ደረጃ ቅኔ አለው በማለት በርካታ ሰዎች የተለያየ ትርጉም ሰጥተውታል።
– ግርማ “ቴዲ ኣፍሮና እሱ የሚወክለው ኤሊት የፒያሳውን ሰባ ደረጃ እንደመውጣት ኣድካሚ ነው ያለውን ኢትዮጵያን የማዳን ሃላፊነት በፍቃደኝነት ወስደዋል” በማለት ተንትኖታል።
– ሌላኛው አስተያየት ሰጪ “ቴዲ ለፍቅር እንጂ ለብር እንደማይንበረከክ “ብርም አይገዛሽ – ኬረዳሽ” በማለት ኮንሰርቱ ላሰረዙበት ሰዎች ነገራቸው” ብሏል።
“አቅፎ ገልዋን አልጠግብ ያለው
ማነው ካላችሁ ማነው ማነው?”
– “ያለው እኮ ለወያኔዎች ልክ ልካቸው ሲነግራቸው ነው” ብሎ የጻፈም አለ።
ጋዜጠኛ ደመቀ ግን “ሰባ ደረጃን ደግሜ ደጋግሜ ብሰማውም አንዳችም የፖለቲካ ሰበዝ ተሰብዞበት አላገኘሁትም” በማለት ዘፈኑ የፍቅር እንጂ የፖለቲካ እንዳልሆነ ተከራክሯል።
እኔም ከደመቀ ጋር በብዙ መልኩ እስማማለሁ። ለምን ከተባለ አንዲት ምሳሌ ሰጥቼ ልሰናበት።
ሶስቱ አልማዞች
በደርግ መጀመሪያ ዘመን ህዝቡ ዘፈኖችን እና ስነጽሁፍን ሁሉ ቅኔ ማላበስ ፋሽን አድርጎት ነበር። አፈና ሲኖር እንዲህ አይነት የህዝብ አስተያየት (Public opinion) የተለመደ ነው። የሆነው ሆነ ጥላሁን ገሰሰ ሶስቱ አልማዞች የሚል አንድ ሸክላ አሳተመ። የዘፈኑ አዝማች እንዲህ የሚል ነው
አልማዝን አይቼ አልማዝን ባያት
ሶስተኛዋ አልማዝ ብትመጣ ድንገት
ሁለቱን አልማዞች ስላስረሳችኝ
ምርጫዬ ከምርጫ ተበላሸብኝ
ይሄ ዘፈን የተዘፈነው በወቅቱ የደርጉ ሊቀመናብርት ለሆኑት ለብ/ጄነራል ተፈሪ በንቲ፤ ለሻለቃ መንግስቱ ኃይለማሪያም እና ለሻለቃ አጥናፉ አባተ ነው ተብሎ ተወራ። ልክ ልካቸውን ነገራቸው እያለ ሕዝቡ ወሬውን አስተጋባው። ይሄ ወሬ እነ መንጌ ጆሮ ሲደርስ ወዲያው ሸክላው ታገደ። ደራሲው ተስፋዬ ለማ በቁጥጥር ስር ዋለ። ጥሌም ሁለት ጥፊ ቀምሶ ሁለት ቀን ታስረ።
ደራሲ ተስፋዬ ለማ ከረጅም ጊዜ እስር በኋላ ሲፈታ ወደ ውጪ አገር ተሰደደ። በቅርቡ ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት እንዴት እንደጻፈው ተረከ። እንዲህ በማለት….
አንድ ቀን ከሰዓት ላይ ማኪያቶ ለመጠጣት ጆሊ ባር ገባሁ። የታዘዘችን አሻሻጭ (ባር ሌዲ) በጣም ውብ ነበረች። ታዛኝ ስትሄድ እንዴት ቆንጆ ነች … ይህቺስ አልማዝ ነች ብዬ ከጀልኳት። ማኪያቶውን ይዛ የመጣችው ግን ሌላ አስተናጋጅ ነበረች። የሚገርመው ይህቺኛዋም በጣም ውብ ሆና ታየችኝ። መጨረሻ ሂሳብ ስጠይቅ ደግሞ ሌላ ሞንዳላ አልማዝ ስትመጣ ወዲያው ከሁለቱ የበለጠ ውብ ሆና ታየችኝ። ወዲያው እስክሪብቶ አውጥቼ ማስታወሻዬ ላይ “ሶስቱ አልማዞች” ብዬ ጻፍኩ። ግጥሙን እዛው ቁጭ ብዬ ጨርሼው ጥላሁን ዘፈነው።
አይገርምም?
**ማሳሰቢያ
——————
የስድብ (አስተያየት) ፈጽሞ የተከለከለ ነው። ቴዲ እራሱ እንኳን በፍቅር እንጂ መች በስድብ ያምናል?

No comments:

Post a Comment