"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Saturday, 28 November 2015

የ“ሞጋቾቹ” ድራማ ደራሲና ፕሮዱዩሰሯ ባለመግባባት ተለያዩ


Written by  ማህሌት ኪዳነወል
የ“ሞጋቾቹ” ድራማ ደራሲና ፕሮዱዩሰሯ ባለመግባባት ተለያዩ
ድራማው በደራሲ ውድነህ ክፍሌ ሊቀጥል ነው

  በየሳምንቱ ረቡዕ ምሽት በኢቢኤስ ቴሌቭዥን የሚቀርበው የ“ሞጋቾቹ” ተከታታይ ድራማ ደራሲ በሆነው ኃይሉ ፀጋዬና በፕሮዱዩሰሯ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የተለያዩ ሲሆን ድራማው በታዋቂው ፀሐፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ ይቀጥላል ተብሏል፡፡ 

የድራማው ደራሲ አንጋፋው የተውኔት ፀሐፊ ኃይሉ ፀጋዬ ለአዲስ አድማስ እንደተናገረው፤ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንያቶች ከመቅዲ ፕሮዳክሽን ባለቤትና ዶክተር ኮከብን ሆና በድራማው ላይ ከምትተውነው መቅደስ ፀጋዬ ጋር አለመግባባቶች ይፈጠሩ ነበር፡፡
“አሁን ግን በዋናነት ያጋጨን መቅደስ የታሪኩ አቅጣጫ በሆስፒታሉ ዙሪያ ብቻ እንዲሆን ፈለገች፤ እኔ ደግሞ ሌሎቹም ታሪኮች አስፈላጊ በመሆናቸው በጀመርኩት መቀጠል እንደሚገባኝ ተናገርኩ፡፡ በተጨማሪም የተዋንያን መረጣ (casting) ውስጥ አንተን አይመለከትህም ተባልኩ፡፡ እኔ ደግሞ እስካሁንም ለስራዎቼ ተዋንያን የምመርጠው እራሴ ነኝ፡፡ ሌላው መጠባበቂያ ስራዎች አትስጠኝም ትላለች፤ እኔ ደግሞ ባለው መስራት ይቻላል በቂ ነው እላለሁ፡፡ በነዚህና መሰል ጉዳዮች መግባባት ስላልቻልን በሽማግሌ ተነጋግረን ተለያይተናል፡፡” ብሏል፤ ደራሲ ኃይሉ ፀጋዬ፡፡ ፕሮዲዩሰሯ ከዚህ በኋላ የድራማውን ርዕስና ገፀባህርያቱን መጠቀም ትችል እንደሆነ ጠይቀነው ኃይሉ ሲመልስ፤ ተገቢውንና በቂ ክፍያ ስለፈፀመች መጠቀም እንደምትችል ገልጿል፡፡
መቅደስ ፀጋዬ በበኩሏ፤ “የድራማው ፕሮዱዩሰር እኔ አይደለሁም፤ ሆኜም አላውቅም፤ ሰዎች “መቅዲ ፕሮዳክሽን” ስለሚል እኔ እመስላቸዋለሁ፤ ትልቁ ድርሻ የኔ ቢሆንም ባለቤትነቱ የሦስት ሰዎች ነው፡፡ ፕሮዱዩሰሩ በኃይሉ ነው፤ ለበኃይሉ ደውሉለት” በማለት ከአለመግባባቱ ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ተቆጥባለች፡፡
መቅደስ እንዲህ ትበል እንጂ ደራሲ ኃይሉ ፀጋዬ ያለ እሷ ሌላ ሰው እንደማያውቅ ነው የተናገረው፡፡ “የትኛውንም አይነት ውል የተዋዋልኩትና ስራዎችን ስሰራ የነበረው ከሷ ጋር ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ፕሮዱዩሰሯ እሷ ነች፤ ሽማግሌዎች በመሃል ገብተው ያነጋገሩንም ከሷ ጋር ነው” ብሏል ደራሲው፡፡ መቅደስ የጠቆመችን አቶ በኃይሉ ማሞ በበኩሉ፤ በድራማው ላይ በፕሮዱዩሰርነት የሰራው የመጨረሻዎቹን ሦስት ክፍሎች ብቻ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ሆኖም አለመግባባቱ በተከሰተበት ወቅት ሽምግልና ውስጥ ነበርኩበት በማለት ስለሁኔታው ለአዲስ አድማስ አስረድቷል፡፡
“ዋናው የአለመግባባቱ መነሻ የነበረው የስክሪፕት መዘግየት ነው፤ የታሪክና የካስቲንግ ጉዳይ ትልቅ ችግሮች አልነበሩም፤ ዋናው ችግር የስክሪፕት በጊዜ አለመድረስ ነው” ያለው አቶ በኃይሉ፤ አለመግባባቱ የተፈታበት መንገድ ያስደሰተው ይመስላል፡፡ “ሰው አብሮ ከሚሰራው ጋር በብዙ ነገር ይጋጫል፤ ሆኖም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሽምግልና በሰላም ተለያይተናል፡፡” ብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር መምህርና አንደኛው አሸማጋይ የነበሩት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ጀዋሬ በበኩላቸው፤ “ዋናው ፀብ ፕሮዱዩሰሯ እንዲፅፍ የፈለገችውና እሱ የፈለገው መጣጣም አለመቻሉ ነው፤ በትእዛዝ መፃፍ ደግሞ ይከብዳል፡፡” ብለዋል፡፡
የደራሲ መለወጥ በታሪኩ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ አይኖርም ወይ በሚል ተጠይቀውም፤ “በብሎኬት የተጀመረን በጭቃ መጨረስ አይሆንም፤ በጭቃ የተጀመረንም በብሎኬት መጨረሱ እንደዛው ከባድ ነው፤ መሰረቱ ያለው በጀመረው ሰው እጅ ነው፡፡ ይሄ እንዴት ይታረቃል የሚለውን አብረን የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ ተመልካች ላይ ተፅእኖ የማሳደሩ ጉዳይ ግን ጥያቄ የለውም” ብለዋል፤ ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ጀዋሬ፡፡ 

No comments:

Post a Comment