"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Saturday 15 September 2012

እኔ የምለው …እዚህ አገር ዘመናዊ ወህኒ ቤቶች የመገንባት እቅድ አለ እንዴ?



 አይገርምም… አንዱ ካድሬ ወዳጄ እኮ ነው ሹክ ያለኝ፡፡ ዘመናዊ ስላችሁ ታዲያ ፍላት ስክሪን ቲቪ ምናምን ያለው
ማለቴ አይደለም፡፡ እንደሱ ከሆነማ እንደ ኮንደሚኒየመ በዕጣ ተከፋፍለነው የወህኒ ቤት እጥረት ተፈጠረ የሚል
ዓለም አቀፍ ዘገባ መሰራጨቱ አይቀርም፡ እናላችሁ … ዘመናዊ ሲባልም “አንፃራዊ” መሆኑ ልብ ይባልልኝ፡፡
እኔን የሚገርመኝ ምን መሰላችሁ? ፈጣሪ ለእነጃፓን ማለቂያ የሌለው የቴክኖሎጂ ፈጠራና ተሰጥኦ ሲያድላቸው ለምንድነው ለእኛ ክፋት፣ መጠላለፍ፣ ጥላቻና ሃሜት ከድርሻችን በላይ ያሻረን? ቀላል ጥያቄ እንዳይመስላችሁ፡መሬት ይቅለላቸውና በምንም ጥያቄ አይበገሩም የሚባሉት ጠ/ሚኒስትራችን እንኳን አቅቷቸው ትተውታል አሉ፡፡
ወደ ቁምነገሩ ስንመጣ… አሁን ጃፓን የሰራችው አዲስ መነፅር የሚበሉትን ምግብ መመጠን እያቃታቸው ከልክ
በላይ ለሆነ ውፍረት (obesity) ለሚጋለጡ ሰዎች ሁነኛ መፍትሄ ነው ተብሏል፡ እንዴት መሰላችሁ? መነፅሩ ትንሿን ምግብ ቆልሎ የሚያሳይ ነው … ስለዚህም ተመጋቢዎቹ ገና ሲያዩት የምግብ ፍላጐታቸው ይቆለፋል፡፡ እንደድሮው
እያግበሰበሱ የስጋ ክምር መስራት ቀረ ማለት ነው፡፡ ችግር ፈቺ መሆን ማለት እንግዲህ ይሄው ነው!
ባይገርማችሁ… ስለዚህ መነፅር ገና እንደሰማሁ ነው ለአገራችን የተመኘሁት፡፡
ለእኛ የሚያስፈልገን መነፅር ግን ትንሽ ለየት ይላል፡፡ ገና በምግብ ራሳችንን ስላልቻልን ከልክ በላይ ውፍረት ለጊዜው
ችግራችን አይደለም፡፡ እኛ የሚያስፈልገን እርስ በርስ የምንተያይበት መነፅር ነው፡፡ እኛ የሚያስፈልገን ዲሞክራሲያችንን አጋንኖ የሚያሳየን መነፅር ነው፡፡ እኛ የሚያስፈልገን የፖለቲካ ምህዳሩን አገር አሳክሎ (ለጥጦ) የሚያሳየን መነፅር
ነው፡፡

አንድ ባለፈረስ ምን አደረገ መሰላችሁ? ፈረሱ ያገኘውን ሁሉ ሳር ነው ብሎ እንዲግጥ መላ ሲዘይድ ቆየና አረንጓዴ
መነፅር በትእዛዝ አሰራለት አሉ፡፡ ከዛ በኋላ ስለ ቀለብ መጨነቅ ቀረለት፡፡ ፈረስ ሆዬ ካርቶኑንም፣
ጫማውንም፣ ቡትቶውንም ሳር እየመሰለው ይጐሰጉሳላ! በእርግጥ ለእኛ የሚሰራው መነፅር ከዚህ ፍፁም ይለያል፡፡ (እኛ ፈረስ አይደለንማ!) አያችሁ … የእኛ ችግር ሌላ ሳይሆን የአተያይ ነው፡፡
ኢህአዴግ ኢኮኖሚው 11 በመቶ ዓመታዊ እድገት እያሳየ ነው ይላል፤ ተቃዋሚዎች ሃሰት ብለው ይሟገታሉ፡፡ ማነው ሃቀኛ ካላችሁኝ… መልሴ ሁለቱም የሚል ነው፡፡ (አዋቂ ይዋሻል እንዴ?) ተቃዋሚዎች የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል
ይላሉ፤ ኢህአዴግ የጠበበ ነገር የለም ባይ ነው፡፡ ማንን እንመን? ሁለቱንም፡፡ ለምን ብትሉ? የሁለቱም አመራሮች ነጭ ፀጉር ያበቀሉ አዛውንቶች ስለሆኑ ይዋሻሉ ልንል አንችልም፡፡ (በአገራችን ባህል ሽማግሌ አይዋሽማ!) ደሞስ ለፖለቲካ
ምህዳር ብለው ነው የሚዋሹት! እኛ ግን ትክክለኛውን እይታ ማግኘት እንድንችል በልዩ ትእዛዝ መነፅሩ ይሰራልን፡፡ ጃፓን ስሪት ቢሆን ደግሞ ይመረጣል፡፡ (የቻይናው ችግር አያጣውም ብዬ እኮ ነው!)

No comments:

Post a Comment