"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Saturday 15 September 2012

የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም!


አሲምባ ርዕሰ አንቀጽ
                                                            ጳጉሜ 3 ቀን 2004 ዓ.ም
የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም!
                                       ፯ኛው ዓመት የቀይ ሽብር ዝክረ ሰማዕታት በአሲምባ የውይይት መድረክ
                                      አሲምባዎች ለምንደር ነው በየዓመቱ የቀይ ሽብርን የሰማዕታት ቀን የምንዘክረው?
ለኢትዮጵያ ህዝብና ለሀገራቸው ባላቸው ፍቅር፤ የጥቂቶች መንደላቀቂያ መንግሥተ ሰማዕት 
ለብዙሃኑ ግን አሣር መቁጠሪያ እሥር ቤት የነበረችውን ኢትዮጵያ የብዙሃኑ ለማድረግ፤ ሕዝባችንን
ከዘመናት የመከራ ማቅ ለአንዴም ለሁሌም ለማላቀቅ፤ የስልጣን ሱስ ካሰከራቸው የሀገር ሀፍረቶች፤
ፋሺሽቶችና ጠባብ ብሔረተኞች ጋር ተናንቀው ሕይወታቸውን በድፍረት መስዋዕትነት ለከፈሉ፤
ሕይወታቸውን ሰጥተው ሕይወት ለሰጡን፤ የጀመሩት ዕውነተኛ የሕዝባዊ ሥርዓት ምሥረታ ትግል
ባግባቡ እንዲቋጭ፤ በአደራም የተቀበልነውና ለሌላም ትውልድ የማንለጋው ኃላፊነት እንደሆነ
በመገንዘብ፤ እኛም ከመቼውም የበለጠ ለመታገል ቃላችንን መልሰን የምናድስበት፣ ታግለው ያታገሉንን
እኒያ የቁርጥዬ ቀን የኢትዮጵያ ጀግኖች፤ ጠላቶቻቸው፤ ታሪካቸውን እንደሚደልዙት ሳይሆን ዕውነተኛ 
ታሪካቸውን በቅርብ ከሚያውቋቸው የምንሰማበት፣ እነሱንም በማሰብ፤ አደራ በላዎች አለመሆናችንን
የምናረጋግጥበትና የምናመሰግናቸው ዕለት እንዲሆን እነሆ ዛሬ ለ፯ተኛ ጊዜ የቀይ ሽብር ሰማዕታትን ቀን
በአሲምባ የውይይት መድረክ ዘክረን እንውላለን።

በዚህ ዓመት የዚያን ትውልድ የሰማዕታት ቀን ስንዘክር፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያ ትውልድ ደሙን
አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ያስጨበጠውን ሳይለቅ፤ ለሕዝባዊ ፣ ለዴሞክራሲያዊና፣ ፍትኃዊ ሥርዓት
የሚያደርገውን መራራ ትግል ከመቼውም ጊዜ የበለጠ አምርሮ እንደቀጠለ ለመሆኑ እንደ እስልምና 
ኃይማኖት ተከታዮች ለመብታቸው እያደረጉ ያሉት ትንንቅ ከብዙው አንዱ ምልክት ነው። በአንፃሩ ደግሞ
ይህንን ትግል ለማኮላሸት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ በየአቅጣጫው የሚጎነጎኑት ሤራዎች፤ በተለያዩ አፍራሽ
እንቅሳቃሴዎች እየተከሰቱ እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው። የወያኔው ቁንጮ መለስ ዜናዊ እንኳ 
ቢሞትም ወያኔያዊነት ላለመሞት በመፍጨርጨር ላይ ለመሆኑ የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች የሟችን የአስከሬን 
ቋንጣ የሙጥኝ ብለው በዓለም ዙሪያ ባሉ የሥርዓቱ የጡት አባቶችና ደጋፊዎች አታሞ ታጅበው 
ዴሞክራሲያዊ በመምሰል የግፍ አገዛዛቸውን ለማስቀጠል የሚያደርጉትን መፍጨርጨር እየታዘብን ነው። 
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን በመታደግ ስም ኢትዮጵያውያን ነን የሚሉ ከሃዲ እበላ ባዮች ከጠባብ
ጎሠኛ ፖለቲከኞች ጋር በማበር የመለስን ውራጅ ጫማ ለማጥለቅ በዓለም ዙሪያ በሥልጣን ላይ 
የሚያስቀምጡአቸውን ፈረንጆች ደጅ በመጥናት እያደናቆሩን የሚገኙበት ወቅት ነው። ሁሉም አፍራሽ 
ኃይሎች የሚመሳሰሉበት በኢትዮጵያዊነት ላይ በድፍረት የሚያደርጉት መረባረብና የሀገር ታሪክ ብረዛ
ሲሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አምርሮ የሚታገላቸውን ኢትዮጵያዊነትን መሠረት ለማሳጣት የዚያን 
ትውልድ ታሪክ ለማጨቅየት ሲጥሩ እናያለን። እንደምሳሌም አምባገነኑና ዋናው የቀይ ሽብር አለቃ 
መንግሥቱ ኃይለማርያም ነጮቹ ባደባባይ ከደበቁበት ጉድጓድ ተቀምጦ ታሪክ ጻፍኩ ቢል አሳታሚዎቹና 
አረብራቢዎቹ ዘራፍ ያሉበትን የዘንድሮውን ዓመት እናስታውሰዋለን። ስለሆነም ነው አሲምባዎች
ከምሥረታችን ጅምሮ ያንን አኩሪ የታጋዮች የዚያን ትውልድ ታሪክ መከላከል ኃላፊነት የሁላችንም ነው
ብለን የምንወተውተው።አሲምባ ርዕሰ አንቀጽ 
ዘንድሮም እንዳምናውና ከዚያም በፊት ለሰባተኛ ዓመት ዛሬ ይህንን የሰማዕታት ቀን ስናከብር፤
የትውልዱን ታሪክ የተለያዩ ወገኖች መናገር መጀመራቸው፤ በተለም የትውልዱን አደራ ለመረከብ ታሪክን
መርምረው ራሳቸውን አደራጅተው እነሆ ጥሪአችሁን ተቀብለናል አስተምሩን ተመክሮአችሁን አካፍሉን
ብለው የተሰባሰቡትን የወጣቶችን ክንፍ ዕድገት በሥፋትና በተግባር ጥልቀት ራሳቸውን እያነጹ በአጭር 
ጊዜ በወዳጆቻቸውም ሆነ በጠላቶቻቸውም ክብርን እየተጎናጸፉ ያሉበትን ወቅት ስንመለከት የዚያ የኛ
ትውልድ ተተኪ ከዳዴ አልፎ ጎልምሶ አንገቱን ቀና ሲያደርግና የትግሉን ቀጣይነት ሲያረጋግጡልን
ሁላችንም የምንኮራበት መሆኑን እየገለጽን እስከ ዕልፈታችን ከጎናቸው ልንቆም የአመጽን ችቦ አብረን 
ልናቀጣጥል ያቅማችንን ያህል ያለፍንበትን የትግል ጎዳና ልናመላክት፤ ከተመክሮአችን ጠንካራውን ወገን
እንዲሰንቁ ደካማውን እንዳይደግሙ ልናስጠነቅቅ በዛሪው ዕለት ቃላችንን የምናድስበት ነው። ወጣት
ታጋዮችንም በርቱ አለንላችሁ! መንገዱንም እናሳያለን! አደራ ለመቀበል መዘጋጀታችሁንም በተግባር 
እያሳያችሁን ለመሆኑ አኩርቶናል እንላቸዋለን።
ታሪኩን ያላወቀና ትክክለኛውን መርምሮ ማገናዘብ ያልቻለ ሕዝብ ስህተትን መላልሶ ይደግማል ።
ስለሆነም ኢትዮጵያዊነት በትግላችን እንዲያቸንፍ ለማድረግና ለሚቀጥለውም ትውልድ አባቶቻችን
ያቆዩልንን ለማስተላለፍ በራሳችን ተማምነን፤ ያ ትውልድ ካባት ቅድም አያቶቹ የተማረውን ጨብጦ፤ 
ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል በምሳሌነት ያስተማረንን ከብረት የጠነከረ ዕምነት፤ ፅናትንና ቆራጥነትን፤
ከታሪኩ እንድንማር ታሪኩንም ከከላሾች መካላከል እንዳለብን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም። ዛሬ 
በአጭር ጊዜ ውስጥ በትግል ራሳቸውን እያነጹ ያሉትንም ወጣቶች የምናሳስባቸው በኢትዮጵያችን 
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊመሠረት የሚችለው በኢትዮጵያውያን መሥዋዕትነት ብቻ እንጂ እንደ ገና ስጦታ 
በሚያብረቀርቅ ወረቀት ተጠቅልሎ ከምዕራባውያን ሆነ ከማንም ኃይል የሚታደለን እንዳልሆነ ለመሆኑ 
እነሆ መለስ ዜናዊ ሲሞት ምዕራባውያን የጡት አባቶቹ ታሪኩን እንዴት እያሽሞነሞኑ ሊናገሩ እንደቃጡና 
የሚቀጥለውንም መለስ ሊመርጡልን እያመቻቹን እንደሆነ እያደረጉ ያሉት መፍጨርጨር ትልቅ በትግል 
የተገኛ ትምህርት መሆኑን ነው። እናንተም ይህ ትምህርት እንደገባችሁ በተግባር ያሳያችሁን የሰሞኑ 
የተቃውሞ ሰልፍ አኩርቶናል።
በሕዝቡ ላይ የሚካሄደው የክህደት ፖለቲካና የትግሉ እልህ አስጨራሽነት ናላቸውን ያዞረው
ወገኖች፤ ግራ ተጋብተውና ሁኔታው አናዷቸው በስሜት የሚጋልቡም ያንን የትግል ታሪክ
የሚመለከቱበት መነፅርም ላይተባበራቸው እንደሚችል ማወቁ ተገቢ ነው እንላለን። ስለሆነም ያንን
ትውልድ የሚወክሉት የአርበኞች፣ የወታደሮች፣ የነፍጠኞች፣ የአማራው፣ የኦሮሞው፣ የኤርትራዊው፣ 
የትግሬው፣ የወላሞው፣ የሶማሌው፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ልጆች በአንድ ድምፅ ተነስተው ሀገራችን
ለሁሉም እኩል እንድትሆን ማድረግ የሚያስችል አማራጭ አሳይተው በመስዋዕትነት ያስተማሩንን ታሪክ
ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ክፍ አድርን ማሰማት እንዳለብን አሲምባዎች አጥብቀን እናምናለን። ያ ትውልድ
ይነስም ይብዛ ባለው አቅሙና ጊዜው በሰጠው የመታገያ ስልትና ዘዴ የኢትዮጵያ ዜጎች በሙሉ ሴት
ወንድ፤ ሕፃን ሽማግሌ፣ ክርስቲያን ወይም እስላም፤ አማራ ወይም ጎምዝ ትግሬ ወይም ሲዳማ ታባብሎ
በጎጥ በዘር ሳይደራጅ በነበረው የጨቋኝ ሥርዓት ላይ እንዲነሳ ቅስቀሳ በማካሄድ የታገለና ያታገላ
ትውልድ ነው። ከነሱ በፊት ሊከተሉት የሚችሉ የትግል ምሳሌዎች ሀገራቸው ባታቆያቸውም ታሪክ
ሠርተው ያለፉ ወገኖች ራዕያቸው ለሀገር ለወገን ዕኩልነት ነበርና ጥንካሬአቸውንም ሆነ ድክመቶቻቸውን
ስንመረምር ከዚህ ተነስተን ካልሆነ እንሳሳታለን። የምንመረምርበት መነፅር በዘመኑ የዘር ወረርሽኝ
ከጎደፈም ትምህርትም ልንወስድ አንችልም
ምንም እንኳ የወያኔዎች ቁንጮ መለስ ዜናዊ ቢምትም ዛሬም ሀገር አፍራሽ የሆነው የጠባቦች
መንጋ ራሱን አጠናክሮ ሥርዓቱን ለማስቀጠል የማይገለብጠው ድንጋይ አለመኖሩን በድፍረት ሲበድለውና 
ሲንቀው የኖረውን ሕዝብ ለቅሶ አስወጥቶ ትዕይንት እያሳየን መክረሙ፤ ቀጥሎ ደግሞ ለሆዳሞችና እበላ 
ባዮች ፍርፋሪ በማቁለጭለጭ ተቃዋሚ ነን ብለው የሚያምሱንን አግቸልችሎ ብቅ ማለቱ አይቀሬ ለመሆኑ 
ለመገመት ጠንቋይ ቀላቢ መሆን አይጠይቅም። መለስ ዜናዊ ሞቷል ተብሎ ሲታማ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ 
ሞቶ ተቀበሮ እሰከ ዛሬዪቱ ቀን ድረስ የወያኔ ደመኛ ጠላቶች ነን ባዮችም የእንደራደር ዘፈንና ረገዳ 
ከመቼውም ጊዜ ሞቅ ብሎ መሰማቱ የሚጠብቀንን የትግል ሁናቴ አመላካች ነው። ለዚህም የጎሠኝነትን 
ሥርዓት ከሥረ-መሠሪቱ መንግሎ ለመጣል የአንድነት ኃይሎች በመካከላቸው ያለውን ልዩነቶች እያጠበቡ
ወደ አንድ አቅጣጫ በመሰባሰብ ኢትዮጵያዊነት ሚዘን እንዲደፉ ማድረግ የተገባ እንደሆነ እናምናለን።
ያም ሲሆን መታወስ ያለበት ትላንትና በሕዝብ ላይ የተፈጸመን በደል አልነበረም፤ አይኔን ግንባር
ያድርገው ብሎ በመካድ ሳይሆን ለፈጸሙት ግፍና ጥፋት ኃላፊነትን በመቀበል ወደፊት እንዳይደገም
ለሁሉም ወገን ተስፋ ሰጪ ሁኔታን በማመቻቸት ነው። ያለፈውን ታሪክ እንርሳው በማለት መጪውን
ብሩህ ቀን መናፈቅ አይቻልም። ለምን ቢሉ የትላንትናው ስህተት ወይም ጥፋት የማይደገምበት ሁናቴ 
ሊረጋገጥ አይቻልምና።  የትላንት ቀይ ሽብር አፋፋሚዎች ካለንሥሃ፤ በአንድ ወቅት የወያኔ ቁንጮዎች
የነበሩ ወይም ከሃዲዎች ካለፀፀት፤ የሕዝባችን ነፃ አውጪዎች ነን ያሉን ግንባሮች ወገናችንን አማራ ነው 
ብለው በገደል የወረወሩበት፤ ቆዳውን የገፈፉበትን ግፍ ትክክል አልነበርንም ብለው ከልብ ጸጸታቸውን 
ሳያሳዩ ዛሬም እንቀፋቸው ወይም የዛሬውን ትግል እንምራ ሲሉ እምቢ ማለት የእያንዳንዱ ዴሞክራሲያዊ 
ሥርዓት በሀገራችን እንዲመሠረት ምኞት ያለው ዜጋ ግዴታ ነው።
ለማጠቃለል፦
አሲምባዎች በየዓመቱ የቀይ ሽብር ሰማዕታት ቀንን የምንዘክርበት ዋና ምክንያት ሌላ ቀይ ሽብር 
በወገናችን ላይ እንዳይደገም ሕብረተሰባችን፣ ፖተሊከኞቻችን፣ ነጻ አውጪ ነን ባዮቻችን ወዘተ…ግንዛቤ
እንዲያደርጉ ቅስቀሳ ለማድረግ ነው። ከሁሉም በላይ ወደፊት ለምንመኘው ብሩሕ የዴሞክራሲያዊ 
ሥርዓት መሠረቱ ባለፍንበት ዘመን በሕዝባችን ላይ በደል ያደረሱ ሁሉ ዛሬም እንኳ ወያኔን ለመጣል 
የትግሉ አጋር ቢሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊጠይቃቸውና ሂሳብ ሊያወራርድ ከፈለገ ሙሉ መብቱ 
እንደሆነ አውቀን የምንገባበት ትግል እንደሆነ ጠንቅቆ ማወቅ እንደሚገባ ነው።  ለምን ቢባል ፍትሕን 
ለመጠየቅ የጊዜ ገደብ ማድረግ ወይም ዛሬ ታግዬልሃለሁና የትላንቱን አትጠይቁኝ ማለት እውነተኛ ፍትሃዊ 
ስርዓትን ሊያመጣ አይችልምና። ከሁሉም የበለጠ አሲምባዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደገዢዎቹ ጨካኝ 
ሳይሆን መሃሪም እንደሆነ የምንተማመንበት ሕዝብ ስለሆነ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ያለጥርጥር በትግላችን ያቸንፋል!

No comments:

Post a Comment