"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Friday 28 December 2012

ምክር ለሰሚው


ወዳጄ ሆይ!
እግዚአብሔር ለልብ ይናገራል፡፡ ከግርግር፣ ከትርምስ ወጣ ብለህ በጽሞና ስትቀመጥ የእግዚአብሔርን ድምፅ ትሰማለህ፡፡ እግዚአብሔርን የምትሰማ ነፍስ ከመከራ ስጋት ታርፋለችና እርሱን ስማ፡፡ እግዚአብሔርን በጆሮህ ብቻ ሳይሆን በዕዝነ ልቡናህም አድምጠው፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ከራስህ ጋር ሰላም ሆነህ ሰዎች ቢጠሉህ አያስደነግጥም፣ ከራስህ ጋር ተጣልተህ ሰዎች ቢወዱህ ግን አስደንጋጭ መሆኑን እወቅ፡፡ ሰዎች ሁሉ የሚከዱኝ እውነተኛ ስለሆንኩ፣ ሐቁን ስለምናገር ነው ብለህም ተማምነህ አትቀመጥ፡፡ ራስህን መርምር፣ ምክርንም ተቀበል፡፡

ወዳጄ ሆይ!
በሳቅ ብቻ ይህችን ዓለም ለመርሳት አትሞክር፣ በመደነቅ ብቻ ያለ ሥራ አትቀመጥ፡፡ ዕረፍት ያለበትን የእግዚአብሔር ጸጋ ፈልግ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
የምትወደውን ሰው ድምፅ በስልክ እየሰማህ ሞቷል እንደማትል፣ ድምፅ የህልውና መገለጫ እንደሆነ ሁሉ የማይታየው እግዚአብሔርም ህልውናው በመናገሩ እንደሚገልጥ ዕወቅ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
እግዚአብሔር በሕጻናት አንደበት በጽድቅ ይናገራል፣ በድሆች አፍም በጥበብ ይናገራል፣ በዳኞች አንደበትም በፍርድ ይናገራል፣ በነገሥታት ሥልጣንም በቅጣት ይናገራል፣ በወዳጆች ምክርም በፍቅር ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር የሚናገርበት መንገዱ ብዙ ነውና አስተውል፡፡


ወዳጄ ሆይ!
እግዚአብሔር ለባለጠጎች የፈለጉትን የሚያደርጉበት ገንዘብ፣ ለድሆች ዓለምን የሚያዩበት መነጽር እንደሰጣቸው ዕውቅ፡፡ ያለ ቦታው መቆፈር ወርቅን እንደማያወጣ ጥበብም ያለ ቦታዋ እንደምታደክም ተረዳ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
እግዚአብሔርን ደጃፍ ከፍተህ፣ ምንጣፍ ጠርገህ፣ ወንበር ዘርግተህ መቀበል ትፈልጋለህ? እግዚአብሔርን እንዲህ የምትቀበለው በጽሞና በመስማት መሆኑን አስተውል፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ከንግግር ይልቅ ዝምታ ትልቅ ንግግር መሆኑን የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ እየበደልከውና እየገፋኸው ዝም ያለህ ስላልገባህ እንጂ ብዙ ተናግሮሃል፡፡

ወዳጄ ሆይ!
አራስ ልጅ እንኳ የእናቱን ድምፅ በሚለይበት ዓለም አንተ የእግዚአብሔርን ድምፅ ልትለይ ይገባሃል፡፡ ብዙ ድምፆች አሉ፣ በመጨረሻው ዘመን በእግዚአብሔር ስም የሚነገሩ የእግዚአብሔር ያልሆኑ ነገሮች አሉና ድምፁን መለየትን ተለማመድ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
እንደፈለግኸው መኖር ባትችል እንደ ተፈቀደልህ እየኖርህ ነውና ደስ ይበልህ!

ወዳጄ ሆይ!
እግዚአብሔር በክፉ ሥራህ ዝም ሲልህ ለንስሐ እየጋበዘህ እንጂ ሥራህን እያጸደቀልህ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በብዙ ዝም የሚልህ ፍርዱ ይግባኝ ስለሌለው መሆኑን እወቅ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
የሚታየው አጥር የሚመልሰው የሚታየውን ባላጋራ ነው፡፡ የማይታየው አጥር እምነት ግን የሚመልሰው የሚታየውንና የማይታየውን ጠላት መሆኑን አውቀህ በእምነት ኑር፡፡ አማኝ ሁለት ዓለምን የገዛ ትርፋማ ነጋዴ መሆኑንም ዕወቅ፡፡ የሥጋ በረከት ለነፍስ አይተርፍም፣ የነፍስ በረከት ግን ለሥጋም ይተርፋል የተባለውን አስብ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ሰው ብዙ ቢፎክርብህ፣ ብዙ ቢዘምትብህ፣ ብዙ ቢዋጋህ፣ ብዙ ቢተኩስብህ ድሉ ግን የክርስቶስ መሆኑን በመገንዘብ ተማምነህ ኑር፡፡ የቀደሙት አባቶች፡- “ሰልፍ የጀግና ነው፣ ድል የጌታ ነው” ያሉትን አስታውስ፡፡ ሰው ሲሰለፍ ቢውል፣ እንደ ጀግናም ቢተኩስ ድል ግን ስጦታ ነው፡፡ ክርስትናም ድል ጨብጦ ውጊያ መሆኑን፣ ዓለሙ በክርስቶስ በጌታችን ድል እንደ ተነሣ ዕወቅ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
የሚገፋህ ያጎረስከው፣ አሳልፎ የሚሰጥህ ያቀረብከው ነው፡፡ ይህ ግን ዱብ ዕዳ ሳይሆን ከጥንት የነበረ የሰው መገለጫ ነው፡፡ ስለዚህ አትደንግጥ፤ ከሰዎች ክፋት በላይ ድንጋጤህ እንደሚጎዳህ አስተውል፡፡

ወዳጄ ሆይ!
የማታውቀው ድምፅ በውስጥህ ሲረብሽህ፣ ምክንያቱን የማታውቀው ጭንቀት ሲገጥምህ የሰይጣን ውጊያ ነውና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ገስጸው፡፡ የሰይጣን ሁከት የሚሻረው በክርስቶስ የሰላም ድምፅ ነውና፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ሰው ያመጣው በእግዚአብሔር ይከሽፋል፣ የእግዚአብሔር ቊጣ ግን በጋሻ አይጋረድምና ከሰው ክፋት በላይ እግዚአብሔር እንዳይቀጣህ ተጠንቀቅ፡፡ እግዚአብሔርን የከሰረ ሺህ ወዳጅ አያጽናናውም፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ጫካ የቀን ጨለማ እንደሆነ ድብቅ ሰውም እንዲሁ ነው፡፡ ድብቅና ሽምቅ ሰውን እግዚአብሔር አይወድም፡፡ የሰውነት ክብሩ አሳብን መግለጥ መቻል፣ የታላቅነት መለኪያውም የሚያስፈልጉበትን ቦታ መለየት መሆኑን ተረዳ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ብቸኝነት ፀጥ ያለ ድምፅ አልባ ሳይሆን ብቸኝነት አስከፊ ጩኸት ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ምድረ በዳውን በቃሉ ያናውጣል፡፡ ብቸኝነትህ እንዲገሰጽ ራስህን ሳይሆን ጌታን አዳምጥ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
እሳት በጥንቃቄ ከያዙት ኃይል፣ ካልተጠነቀቁት አጥፊ ነው፡፡ ችኩል ሰውም በጥንቃቄ ከተጠቀሙበት ፈጣን ረዳት ነው፡፡ ካልተጠነቀቁት ግን ጥፋትን ይዞ የሚመጣ ነው፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ጦር ይዞ ከሚመጣብህ ወሬ ይዞ የሚመጣብህን ተጠንቀቅ፡፡ የማይበርድ ጦርነት ምንጩ የወሬ ሱሰኛ መሆን ነውና፡፡ ወገኔ ሆይ ያልሰሙት አይቆጭምና ምን አሉኝ አትበል፡፡ የሰሙትም አንተነህን አይቀይረውምና ንቀህ እለፈው፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ሥራን በሙያ ብቻ ሳይሆን በባለ አደራነት መንፈስ ሥራው፡፡ ጠቃሚ ሰው የምትሆነው አደራ የሚሰማህ ሰው ስትሆን ብቻ ነው፡፡ ብዙ አቁሳይ ሰዎች ሙያ ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡

ወዳጄ ሆይ!
የምድረ በዳ አስተሳሰብ በምድረ በዳ እንደሚያስቀር ከእስራኤል ተማር፡፡ እስራኤል በረሃ የቀሩት በመልክአ ምድሩ አስከፊነት ሳይሆን በባሕርያቸው ነው፡፡ የምድረ በዳ ጠባይም ማጉረምረም፣ ስህተትን መቀበል አለመፈለግ፣ በመሪዎች ላይ እንከን ፈላጊ መሆን ነው፡፡ ይህ ጠባይ ካለህ እንደ በረሃ አዙሪት የተጓዝህ ይመስልሃል፣ ያለኸው ግን መነሻህ ላይ ነው፡፡ በትክክል እንድትጓዝ ከምድረ በዳ አስተሳሰብ ተላቀቅ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ባለጌ ሰው ትልቁን የሚያሳንስ፣ የከበረውንም የሚያዋርድ ነው፡፡ ነገር ግን ሰማይን አቆሽሻለሁ ብሎ ተንጋሎ የሚተፋ ራሱ እንደሚያቆሽሽ ባለጌም ራሱን ሲያረክስ ይኖራል፡፡ ደግሞም፡-
ማክበር መከበር ነው
መወደድ ነው መውደድ
ላዋርድ ካሉማ ይመጣል መዋረድ
የተባለውን አስብ፡፡ ሰው የሚያጭደው የዘራውን ነው፡፡ ፍቅርን የዘራ ፍቅርን፣ ክብርን የዘራ ክብርን ያጭዳል፡፡ ሰው የሆነም ሰውን ያከብራል፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ከለምለም እንጀራ በፊት ለምለም ፊትን አቅርብ፡፡ ገንዘብ ከመስጠት በፊትም ፍቅርን ስጥ፡፡ ገንዘብህንም ከሚበቅልበት እርሻ ላይ ዝራው እንጂ ቋጥኝ ላይ አትበትነው፡፡ እርሻውም የሙት ልጆች፣ ጧሪ ያጡ አረጋውያን፣ ስለ ክርስቶስ ስም የሚገፉ ወገኖች ናቸው፡፡ በቋጥኝ ላይ መጣልም በሀብት ለሚወዳደሩ ጉረኛ ባልንጀሮች መነስነስ ነው፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ሰደድ እሳትን የሚያቆመው ውሃ ብቻ ሳይሆን እሳቱን የሚቆርጥ ጉድጓድም ነው፡፡ ክፉ ቀን በመጣብህ ጊዜም የመገናኛ መስመሮችን ዘግተህ ጸሎት ያዝ፡፡ ከመጣብህ ነገር በላይ እንዳዘኑልህ የሚናገሩትን ማባበል ጉልበት ይጨርሳል፡፡ ለችግር ገድል ከሚጽፉ፣ መልክ ከሚደርሱ ሰዎች ራቅ፡፡ ኃይል የእግዚአብሔር መሆኑን ከሚያውጁ ጋር ተቀመጥ፡፡ እነዚህ ሰዎች አንድ የእምነት ቃል በተናገሩ ጊዜ ሁሉ ችግርህ መፍረስ ይጀምራል፡፡

ወዳጄ ሆይ!
አላልፍም ብሎ የቀረ ጉዳይ፣ ላያልፍም የመጣ ምንም ነገር የለምና ተጽናና፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ውሳኔ የማያውቅ ሰው ሰንሰለታማ ችግር ይገጥመዋል በመጨረሻ ወዳጅ አልባ ሆኖ ይቀራል፡፡ አንተ ግን የውሳኔ ሰው ሁን፡፡ የማይሆንን ነገር አይሆንም ማለትን ልመድ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ሰዎች ልክህን ሳያሳውቁህ ልክህን አውቀህ በትሕትና ኑር፡፡ ስላንተ ሰዎች ይመስክሩ እንጂ የራስህን ውዳሴ አትድገም፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ልብህ የነሆለለ ሆኖ እንዳይቀር ያየኸውን ሁሉ የእኔ ይሁን ብለህ አትመኝ፡፡ ለምኞትህ ልክ ካልሰጠኸው መቆሚያው መቃብር ብቻ መሆኑን እወቅ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
አሸንፍ እንጂ አትሸነፍ፡፡ ከተሸነፍህም እንደ ተሸነፍህ አትቅር፡፡

ወዳጄ ሆይ!
መምህር ዓርብ ማታ የቤት ሥራ ሰጥቶ ሰኞ ጠዋት ይጠይቃል፡፡ የዓርቡ ጌታ ስድስት የቤት ሥራ ሰጥቶ እንዳረገ ሁሉ ሊጠይቅህም ይመጣል፡፡ ታዲያ የተራበ አብልተሃልን? የተጠማ አጠጥተሃልን? የታረዘ አልብሰሃልን? የታመመና የታሠረ ጠይቀሃል? እንግዳንስ ተቀብለሃልን?

No comments:

Post a Comment