"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Friday 28 December 2012

ጠቃሚ እና አስፈላጊ ሁሉም ሊተገብረው የሚገባ ምክር

Ashenafimekonen
ቊርባን እንዳይነጥብ ቀሳውስት እንደሚጠነቀቁ ምክርም እንዳያልፍህ ጆሮህ ነቅቶ ሊሰማ፣ ብዕርህ ሰልቶ ሊመዘግብ ይገባዋል፡፡ ምክር ባለበት የጠራ ውሳኔ ይኖራል፣ ድልም ይገኛል፡፡ ምክር ገንዘብ ሊገዛው የማይችል ትልቅ ሀብት ነው፡፡ ገንዘብ የሰጠህ ባለጠጋ ከኪሱ መዝዞ ነው፡፡ ምክር የሚሰጥህ አዋቂ ግን ከነፍሱ አውጥቶ ነው፡፡ ምክር የነፍስ ስጦታ መሆኑን አስተውል፣ ተጠንቅቀህም ያዘው፡፡ በትክክል የሚታዘዝ በትክክል የሰማ ነው፡፡ በደንብ ለመታዘዝ በደንብ መስማት እንደሚያስፈልግ እወቅ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
የተቋረጠውን ጥቅምህን ለማስቀጠል ብለህ ይቅርታ መጠየቅ አይገባህም፡፡ የምትፈልገውን ከወዳጅህ ከመጠየቅህ በፊት የወሰድክበትን ሰላም በይቅርታ መልስለት፡፡ ይቅርታ ሳይጠይቁ ንብረትን መጠየቅ አንተን አልፈልግህም ንብረትህን ግን እፈልጋለሁ እንደ ማለት ነው፡፡ ይቅርታ የበረከት ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ ያ ሰው ይቅር ካለህ ካሰብከው በላይ ይሆንልሃል፡፡ ቢሆንም ይቅርታን የጥቅም ማግኛ መንገድ አታድርገው፡፡ ካጣኸው ንብረት ያጣኸው ወንድምነት የበለጠ ኪሣራ መሆኑን እባክህ አስተውል፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ይቅር ያልከውን ስህተት መልሰህ አትናገረው፡፡ ይህ ግርሻት ያመጣል፡፡ ከዋናው በሽታ በድንገት የሚጥል ግርሻት ነው፡፡ ይቅር ያሉትን ስህተት ማሰላሰልም ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ ዛሬ የተሳሳተውን ወገንህን ካለፈው ስህተቱ ተነሥተህ አትውቀሰው፡፡ እርሱ ከስህተቱ እንዳልተመለሰ ሁሉ አንተም ከቂምህ አልተመለስክም ማለት ነው፡፡ የሰጡትን ስጦታ መልሶ መቀበል ውርደት ነው፡፡ ይቅርታም ስጦታ ነውና ከሰጠኸው በኋላ መንሣት ትልቅ ሐፍረት ነው፡፡ ውሻ የተነቀፈው የተፋውን በመላሱ ነው፡፡ የተፉትን ቂም መላስም ያስነቅፋል፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ረጅም ሰዓት ዝም ብለህ ስትናገር ንግግርህ ኃይል የተሞላ ይሆናልና ከዝምታ በኋላ ስትናገር አንደበትህን በስመ ሥላሴ አሟሸው፡፡ ዝምተኛ ሰው ሁሉ አስተዋይ ነው አትበል፡፡ የሚናገረው የሌለውም ዝም እንደሚል እወቅ፡፡ “የእንጦጦ መምህር ቢናገር ባመት፣ ያውም እሬት” እንዲሉ ዝም ብሎ የኖረ ሰውም ሲናገር ንግግሩ ከባድ ነው፡፡ ንግግር ልምምድ መሆኑን አስተውል፡፡ አንድ ጊዜ ለመናገር ሁለት ጊዜ ማሰብ ከፀፀት እንደሚጠብቅ ተረዳ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
አፍ ቢደፍኑት ይሸታል፣ ችግርም ይዘው ቢያሰላስሉት ይጐዳል፡፡ ለሁነኛ ሰው ማማከር ግን ይቀላል፡፡ ችግርህ ከሴት ጋር የተያያዘ ከሆነ ለሴት አማክረው፡፡ ችግርህ ከጭንቀት ጋር የተያያዘ ከሆነ ከእናቶች ጋር ተማከረው፡፡ ችግርህ ከኃጢአት ጋር የተያያዘ ከሆነ ከሃይማኖት አገልጋይ ጋር ተማከረው፡፡ ችግርህ የማይነገር መስሎ ከተሰማህ ከእግዚአብሔር ጋር ተማከረው፡፡ ከመጣው ችግር በላይ ዝምታ እንደሚጎዳ እወቅ፡፡ ደግሞም፡- “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፣ ለሃምሳ ሰው ግን ጌጡ ነው” የተባለውን አትርሳ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ሰው ቆሞ የሚጠብቅህ ሐውልት አይደለም፡፡ ሐውልት እንኳ ዘመን ሲረዝም ወድቆ ይሰበራል፡፡ ሰው ጠዋት ለማታ የማታገኘው ሕልም እልም ነው፡፡ ለመኖር ሲደላደል የሞት ጥሪ የሚደርስበት፣ በምድር አለ ስትለው በሰማይ የሚውል፣ ካመለጠህ የማታገኘው ነውና ፍቅርህን ለመግለጥ ሰዓቱ አሁን መሆኑን አስተውል፡፡ ሰው ለቀጠሮ የማይመች ፍጡር መሆኑን እወቅ፡፡ ትልቁ የፍቅር መግለጫም ክርስቶስን መስጠት መሆኑን አስተውል፡፡ ሰውን ለማፍቀር ጊዜው አሁን፣ ለመርዳትም ቀኑ ዛሬ፣ ይቅር ለማለትም ሆነ ይቅርታ ለመጠየቅ ዕድሉ ይህች ጀምበር፣ አብሮ ለመኖርም ከአሁን የተሻለ ምቹ ዘመን የለም፡፡ የተሰጠን ዕድሜም እንኳን ለጠብ ለፍቅርም እንደማይበቃ አስተውል፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ሰውን ከማሳቅ ሰውን ማስደሰት ይበልጣል፡፡ ሰውን የምታስቀው እውነትና ሐሰትን ቦታ በማለዋወጥ ነው፣ ወይም ውሸትን በማቆንጀት ነው፡፡ ሰውን የምታስደስተው ግን በቁምነገርህ ነው፡፡ ፌዝ የአንደበት፣ ቊምነገር የተግባር ጉዳይ መሆኑን እወቅ፡፡ ፌዘኛ የሚያረሳሳ፣ ቁምነገረኛ ግን የሚፈውስ መሆኑን ተረዳ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
የምስክር ወረቀት ያላቸው አዋቂዎች ዕውቀታቸውን ብዙ ጊዜ የሚወስዱት ያልተማሩ ከሚባሉት መሆኑን እወቅ፡፡ ኑሮ የተግባር ትምህርት ቤት ነውና በዕድሜ ከበረቱት ጠይቅ፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ከወጣት ሞት ይልቅ የሽማግሌ መታጣት አሳሳቢ ነው፡፡ ሽምግልና የዕድሜ ብቻ ሳይሆን የጸጋ ነው፡፡ በዕድሜ የሸመገሉ ሁሉ ጠቢባን አይደሉም እንደ ተባለ ጸጋ የለበሱ ሽማግሌዎችን እንዲሰጠን መጸለይ ያስፈልጋል፡፡ የአንድ ማኅበረሰብ ቀጣይነቱ የሚረጋገጠው የሚሰማቸው አባቶች ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡

ወዳጄ ሆይ!
ንግግርህ ዕውቀት ብቻ ሆኖ እንዳያሰለች፣ የምትናገረው ፍቅር የሌለው እውነት ሆኖ እንዳይሰብር፣ “ጌታ ሆይ በንግግሬ አንተ ተናገርበት፣ በዕውቀቴ ጥበብ ጨምርበት” ብለህ ጸልይ፡፡ እግዚአብሔር የቀደሰው አንደበት ቡሩክ ምንጭ ነውና፡፡





No comments:

Post a Comment