"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Friday 11 January 2013

“በህወሓት ተወርረናል!” ደቡብ ሱዳኖች


“በህወሓት ተወርረናል!” ደቡብ ሱዳኖች

tplf and south sudan
ኃያልነታችን ብሔራዊ ይሁን

አዲሷ አገር ደቡብ ሱዳን እንደ መንግሥት ተመቻችታ አልቆመችም። የፋይናንስ ስርዓቱም የተረጋጋ አይደለም። የገቢና ወጪ ቁጥጥሩ ክፍተት ያለበት በመሆኑ ለሙስና የተጋለጠ ነው። የጁባ ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ የአገሪቱ ሃብት በግለሰቦች እጅ ነው። በተለያዩ መስኮችም የባለሙያና የአቅም ችግር አገሪቱ ምስጢርና የኔ የምትለው አስተዳደር እንዳይኖራት አድርጓታል የሚሉ በርከቶች ናቸው።
ይህንኑ ክፍተት ለመሙላት በሚል ኢህአዴግ ደቡብ ሱዳንን ከተወዳጀ ጀምሮ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። የመከላከያ መኮንኖችን አሰልጥኗል፤ የፖሊስ ኃይሉን አደራጅቷል። በአማካሪነት በተለያዩ ዘርፎች የራሱን ሰዎች ጠቅጥቆ አሁንም ይህንኑ ድጋፉን አጠናክሮ ቀጥሏል። የተመሰረተው ግንኙነት ወደፊትም እንዲሁ በቀላሉ ንፋስ የሚገባው አይመስልም። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው እንደሚሉት ኢህአዴግ በህወሃት አማካይነት ደቡብ ሱዳንን ጠፍንጎ የያዘበት ሰንሰለት በቀላሉ ሊበጠስና ሊሸረሸር የሚችል እንዳልሆነ ይናገራሉ።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ እነዚሁ በጁባ የሚኖሩ ክፍሎች በፋይናንስ፣ በፖሊስ፣ በመከላከያ፣ በደህንነት፣ በተለያዩ ከፍተኛ ግዢዎችና በገንዘብ ዝውውር በኩል የደቡብ ሱዳን ማናቸውም እንቅስቃሴ ከኢህአዴግ እይታና ክትትል ውጪ አይደለም። እንደ አገር ኢትዮጵያ በቀጠናው ኃያል መሆኗ ቢያስደስትም አሰራሩ “ህወሃት በኢትዮጵያ ስም፣ የህወሃት ልጆች በኢህአዴግ ስም” መከናወኑ ቅሬታ ፈጥሯል።
“ብሔራዊ ጥቅምን በብሔራዊ አጀንዳ ማስጠበቅና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ማስኬድ ኩራቱ የሁሉም ዜጎች እንዲሆን ያደርገዋል” የሚሉት ክፍሎች በተግባር የሚታየውና በብሔራዊ ስም የሚከናወነው ስራ “ህወሃትና የህወሃት ሰዎች በብቸኛነት እንዲጠቀሙበት የሚያደርግ ነው፤ ሕዝብ የወከለውና የራሱን አገር ጥቅም የሚያስከብር አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ እስከለሌለ ድረስ አካሄዱን ብሔራዊ ወይም የአገር ኩራት ለማለት አይቻልም” ብለዋል። አያይዘውም ኃያልነታችን በብሔራዊ ደረጃ እንጂ በድርጅትና በጎሣ ደረጃ መሆን የለበትም በማለት ይከራከራሉ፡፡ ሲያስረዱም በብሔራዊ ሽፋን ለመበልጸግ የሚደረግ ሩጫ ዓቅምን ካላገናዘበው የኤርትራ ፍላጎትና በውጤቱም ከጎረቤት ሁሉ ጋር ከጠብ እስከ ዓይነቁራኛ መተያየት ከመድረስ ጋር ልዩነት አይኖረውም ይላሉ፡፡
በአቅም ማጎልበት፣ በማማከርና በባለሙያ ድጋፍ ስም የሚካሄደው ምልመላና ምደባ በቀጥታ ተቀማጭነቱ ጁባ ከሆነው የመረጃና የደህንነት ቡድን ጋር የሚቆራኝ ነው። በምልመላው የሚካተቱት አብዛኞቹም ከህወሃት የሚወከሉ ናቸው። ከዚሁ የመረጃ ቡድን ጋር በመተሳሰር የሚሰሩ ነጋዴዎችና በግል ስራ የሚንቀሳቀሱ የትግራይ ተወላጆችም አሉበት።
በብሄራዊ ደረጃ በጥንቃቄ መያዝ ያለበት የጥቅም፣ የኢኮኖሚ ስትራቴጂና የደህንነት ጉዳይ በፓርላማውም ሆነ በአባል የኢህአዴግ ድርጅቶች በወጉ የማይታወቅ፣ በዚሁ ሰንሰለት ስር የሚገኘው ያገሪቱ ገቢ ቁጥጥር የማይደረግበት እንደሆነ የመረጃው ምንጮች ይናገራሉ። አያይዘውም ይህንኑ ብሔራዊ ሽፋን ያለውን ግንኙነት በመንተራስ የህወሃት ሰዎች አለአግባብ እየበለጸጉበት መሆኑን አመልክተዋል።

በደቡብ ሱዳን የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከሚሰጡት 5ኩባንያዎች አንዱ የሆነው Vivacell 30ኢትዮጵያውያንን በቴክኒክና ፋይናንስ መስክ ቀጥሯል:: (ፎቶ: አዲስ ፎርቹን)
የሚሰሩበትን አገርና ስማቸውን እንዳይገለጽ የጠየቁ በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የተማሩ የደቡብ ሱዳን መንግስት የመዋቅር ሰው “ህወሃት ወርሮናል” ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፤ “ከተራ የችርቻሮ ንግድ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የወጪና የገቢ ንግድ የህወሃት ሰዎች እየተቀራመቱን ነው” የሚሉት እኚሁ ሰው በከፍተኛ ደረጃ ባሉ አመራሮች ዘንድ የሚሰማው ቅሬታ እየጨመረ መሆኑንን ያስረዳሉ።
“አገራችን” አሉ “አገራችን ካንዱ ነጻ ከወጣች በኋላ ሌላ እጅ ላይ የወደቀች ያህል የሚሰማን ብዙዎች ነን” በማለት ቅሬታቸው የጨመረ ክፍሎች መበራከታቸውን የሚናገሩት የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ሰው፣ በትግሉ ዘመን ኢትዮጵያ ያደረገችው ድጋፍ የሚረሳ ባይሆንም አሁን እየተደረገ ያለው ድርጊት ከብሔራዊ ደረጃ የወረደ ስግብግብነት፣ ለመዝረፍ የመራወጥ፣ በከፍተኛ ደረጃ ደግሞ ሙሉ የአገሪቱን ንግድ እንቅስቃሴ የመቆጣጠር እንደሚመስላቸው አመልክተዋል።
“በበርካታ ባልደረቦቼ ዘንድ ያለው እምነት እንደገና የመወረር ዓይነት ነው” በማለት አስተያየታቸውን የሚያጠናክሩት ባለስልጣን፣ ውስጥ ውስጡን ያለው ቅሬታ ሳይባባስ ኢህአዴግ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለውን ግንኙነት “ክብር የተላበሰ፣ በአገርና በመሪዎች ደረጃ ስትራቴጂና የጋራ ጥቅም ላይ ብቻ ባተኮረ መንገድ ለማድረግ አካሄዱን መመርመር አለበት” ባይ ናቸው።
“ካለብን ተጽዕኖ የተነሳ ለባለውለታችን ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም ያሰራነውን ቪላ ለመሸለም እንኳን አልቻልንም” ሲሉ የተጠፈሩበትን የቁጥጥር ገመድ ጥብቅነት ባለስልጣኑ አመልክተዋል። አያይዘውም ይህ ስሜት እያደገ ሲመጣ ህወሓት አገር ውስጥ ከሚታማበት የንግድ የበላይነት ጋር ተዳምሮ አላስፈላጊ መተራመስ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል። ደቡብ ሱዳን ነጻ አገር መሆኗን ስታውጅ ባለስልጣናቱ በዕለቱ ለኮሎኔል መንግስቱ ቪላ ቤት ለመሸለም እቅድ መያዛቸውን ይፋ ማድረጋቸው፣ እቅዱ በተለያዩ ሚዲያዎች ይፋ እንደሆነ የኢህአዴግ የስለላ ሰዎች ባደረጉት ተጽዕኖ እቅዱ መሰረዙንና ቀደም ሲልም የተነገረው ስህተት መሆኑ ተጠቅሶ ማስተባቢያ መበተኑ የሚታወስ ነው።
ጄኔራል ጻድቃን በበላይነት የደቡብ ሱዳን የመከላከያና የደኅንነት አማካሪ እንደሆኑ በማስታወስ አስተያየት የሚሰጡት ክፍሎች፣ ህወሓት በኢትዮጵያ እንዳደረገው በደቡብ ሱዳንም ለወደፊቱ ታላቅ የንግድ ኢምፓየር ለመክፈት ዝግጅት እንዳለ ገልጸዋል። እነዚህ ክፍሎች እንደሚሉት ኢህአዴግ ብሔራዊ ክብሩን ጠብቆና ብሔራዊ ኃላፊነቱን በማስቀደም ካልተንቀሳቀሰ በውስጥም በውጪም ችግር ይገጥመዋል።
በደቡብ ሱዳን የሚፈጸሙ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ሙሉ በሙሉ ዝርዝሩን ለጊዜው ከመናገር መቆጠባቸውን የሚናገሩት ወገኖች “ኬንያን ጨምሮ በቀጣናው ኃያል አገር መሆናችን ያስደስተናል። ይህ የኃያልነት ሚናችን እንዲቀጥል በብሔራዊነት ስር ሃብት እያግበሰበሱ ያሉትን ወገኖች መለየትና፣ መንግሥትም እንደ መንግሥት ክብሩን ሊጠብቅ ይገባል” በማለት ማሳሰቢያቸውን ያስተላልፋሉ። ከሌሎቹ ከባድ ንግዶች ውጪ ህዝብ እየተራበ በኮንትሮባንድ እህል ወደ ሱዳንና ወደ ሌላም አገር የሚያጓጉዙት ክፍሎች፣ በሱዳን በባለሃብት ስም የሚንቀሳቀሱትንና በተራ የሱቅ በደረቴ ስራ ተሰማርተው ዶላር የሚሰበስቡት ክፍሎች ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባም አሳስበዋል።

No comments:

Post a Comment