"Food is nothing without freedom! We Need Freedom

”Food is nothing without freedom! We Need Freedom!

Saturday, 26 May 2012

ፒተር ሃይንላይን ኢትዮጵያ ውስጥ ታሠረ


ፒተር ሃይንላይን ኢትዮጵያ ውስጥ ታሠረ
የአሜሪካ ድምፅ የአዲስ አበባ ዘጋቢ ፒተር ሃይንላይንን እና አስተርጓሚውን ስመኝሽ የቆየን ፖሊስ ይዞ አሥሯቸዋል፡፡
በ ስሎሞን አባተ | አዲስ አበባ / ዋሽንግተን ዲ.ሲ



More Sharing Services


ፎቶ፡ VOA
ፒተር ሃይንላይን፥ የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ
“ፒተር ሃይንላይን በሥራው ላይ የቆየ ዘጋቢ ነው፡፡ ልምድ ያካበተና በሙያው የተካነ የራዲዮ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በመሆኑም እኔ በግሌ እንደ ሃይንላይን ዓይነት ሰው ሙያዊ ባልሆነ መንገድ ይዘግባል ብዬ ለማመን ይከብደኛል፡፡” - ቶም ሮደስ፤ በሲፒጄ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ቃል አቀባይ፡፡
ሁለቱ የታሠሩት ለመንግሥት ያቀረብናቸው ሦስት ጥያቄዎች ይመለሱልን ብለው ዛሬ ስብሰባ የወጡ በርካታ ቁጥር አላቸው የተባሉ ሙስሊሞችን ስብሰባ ፒተር ሊዘግብ በሥፍራው ተገኝቶ በነበረበት ወቅት ነው፡፡
ቀደም ሲል ሾፌራቸው ሃብታሙም አብሮ ተይዞ የነበረ ሲሆን በኋላ ግን እርሱ መለቀቁ ተነግሯል፡፡
ፕሮግራማቸው እየተካሄደ ሳለ ለመዘገብ በሥፍራው የተገኘው ፒተር ሃይንላይን ሲወጣ ፖሊሶች እጁን መያዛቸውንና ካሜራውንም እንደነጠቁት ከሙስሊሙ ጥያቄ አስተባባሪዎች አንዱና ቃል አቀባይ የሆኑት ሙስታዝ አቡበከር አህመድ ሙሃመድ ገልፀውልናል።
በሥነ ሥርዓቱ ተገኝቶ የነበረው ተሰብሳቢም «ጋዜጠኛ ነው፥ መዘገብ ይችላል፥ መብቱ አለው፤ አትያዙት» እያለ ከአንድ ሰዓት ለበለጠ ጊዜ በሰዉና በፖሊስ መካከል ንትርክ እንደነበር አስተባባሪው ገልፀዋል።
ፒተር ሃይንላይን ሂደቱን ሲዘግብና ንግግሮችን ሲቀርፅ ከማየታቸው በላይ በአዳራሹ ውስጥ ሕገወጥ አድራጎት ሲፈፅም አለማየታቸውንም ሙስታዝ አቡበከር አህመድ ሙሃመድ አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በሥፍራው የነበረ አንድ ሌላ የውጭ ጋዜጠኛ የደንብ ልብስ ባልለበሱ የፀጥታ ኃይሎችና በከተማው ፖሊሶች ከአካባቢው እንዲርቅ ተደርጓል፡፡
ይህንኑ ጋዜጠኛ የፀጥታ ኃይሎቹና ፖሊሶቹ መታወቂያውን ወስደው ከተመለከቱ በኋላ ያለምንም ተጨማሪ ጥያቄና ማብራሪያ ከአካባቢው እንዲርቅ ያዘዙት መሆኑን አመልክቷል፡፡
በሥፍራው ላይ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊሶች እና አነስ ያለ ቁጥር ያላቸው ፌደራል ፖሊሶች እንደነበሩም ይኸው የውጭ ሚድያ ዘጋቢ ጠቁሟል፡፡
የንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሺመልስ ከማል ለዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ድርጅት - ሲፒጄ በሰጡት መግለጫ ፒተር የተያዘው “ዲፕሎማቲክ ተሽከርካሪ በሕገወጥና ሙያዊ ባልሆነ መንገድ ለሥራ በመጠቀም፤ የመገናኛ ብዙኃን መታወቂያ ለማሣየትም ፍቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ ነው” ብለዋል፡፡
ፒተር ክስ ይመሥረትበት ወይም ለጊዜው በቁጥጥር ሥር ይዋል የሚያውቁት ነገር እንደሌለ የመንግሥቱ ቃል አቀባይ አቶ ሺመልስ አክለው ገልፀዋል፡፡
እንደአውሮፓ አቆጣጠር ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ ለሃያ አራት ዓመታት ለቪኦኤ እየሠራ ካለውና ባለቤቱ በኢትዮጵያ የዴንማርክ ዲፕሎማት የሆኑት ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት ያለው ፒተር የተሰሙበት ክሦች ዝናው ጋር ጨርሶ የማይሄዱ ሆነው ያገኙት መሆኑን በሲፒጄ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ቶም ሮደስ አመልክቷል፡፡
“ፒተር ሃይንላይን በሥራው ላይ የቆየ ዘጋቢ ነው፡፡ ልምድ ያካበተና በሙያው የተካነ የራዲዮ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በመሆኑም እኔ በግሌ እንደ ሃይንላይን ዓይነት ሰው ሙያዊ ባልሆነ መንገድ ይዘግባል ብዬ ለማመን ይከብደኛል፡፡” ብሏል ሮደስ፡፡
ፒተርና ረዳቱ ስመኝሽ በመጀመሪያ የተወሰዱት ወደ ኮልፌ ፖሊስ ጣቢያ ሲሆን በኋላ ግን ማዕከላዊ ተብሎ ወደሚታወቀው ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱና እዚያው እንደሚገኝ ተሰምቷል፡፡
የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጣቢያም የጋዜጠኛው ፒተር ሃይንላይንን መታሠር በሚመለከት አሁን ማምሻውን መግለጫ አውጥቷል።
“የዘጋቢዎቻችንን ደህንነት መጠበቅ በብርቱ የሚያሳስበን ጉዳይ ነው - ሲል የሚጀምረው የቪኦኤ ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ኤንሶር መግለጫ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃዎች እየሰበሰብን ነው” ብሏል።
ቪኦኤ ከዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናትም ጋር እየተነጋገረ መሆኑንና ተጨማሪ መግለጫ ሲገኝ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቆ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሚስተር ሃይንላይን የጋዜጠኝነት ሥራውን ማከናወን እንዲችል ጣልቃ እንዳይገቡ ጠይቋል።
ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

No comments:

Post a Comment